Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ለውጡ  በአገር ላይ  ብቻ ሳይሆን ወደ በግለሰቦችም  ወርዷል!  

0 294

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ለውጡ  በአገር ላይ  ብቻ ሳይሆን ወደ በግለሰቦችም  ወርዷል!  

ወንድይራድ ኃብተየስ

የኢኮኖሚ ዕድገትንና የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂን  ማስተሳሰር ከጀመሩ   አገራት መካከል  ኢትዮጵያ  አንዷና በግንባር ቀደምትነት የምትነሳ አገር ነች።  አካባቢን የማይበክሉ የሃይል አቅርቦቶችን ከማስፋፋት ባሻገር የደን ልማትን በማካሄድ ኢትዮጵያ   ለአካባቢ ጥበቃ ስራ ስኬት የምትጠቀስ አገር  ለመሆን በቅታለች።  የአየር ንብረት ለውጥ አደጋ ድንበር  የሚወስነው አይደለም። በአንዱ ጥፋት ሌላው ጭምር  የሚለበለብበት  ነው። እንደኢትዮጵያ ያሉ ታዳጊ አገራት ለአካባቢ ብከላ ወይም ለአየር መለወጥ ያላቸው አስተዋጽዖ አነስተኛ ቢሆንም  በዚህ ሳቢያ ለሚከሰተው አደጋ ተጋላጭነታቸው ግን እጅግ ከፍተኛ ነው። ለዚህ ነው ኢትዮጵያ የአየር ለውጥና የአካባቢ ብክለትን ለመከላከል ጠንክራ በመስራት ላይ የምትገኘው።

ባሳለፍነው ሳምንት የአውሮፓ ሕብረትና አባል አገራት አምባሳደሮችና ዲፕሎማቶች በቅርቡ “የአየር ንብረት ለውጥ የዲፕሎማሲ ሳምንትን”  በሚል  በጉለሌ ዕፅዋት ማዕከል ተገኝተው  ባከበሩበት ወቅት ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል የምታደርገው ጥረት ለሌሎች አገራት አርዓያነት ያለው እንደሆነም  ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል። እነዚህ የአውሮፓ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ  የአየር ንብረት ለውጥ የዲፕሎማሲ ሳምንትን ያከበሩት ችግኝ በመትከልና ድንበር አልባውን የአየር ብክለትና በረሀማነት መስፋፋት  አደጋ ለመግታት በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ  በመምከር ነው። የአየር ንብረት ለውጥ የሁሉም አገራት የጋራ ጉዳይ መሆን መቻል እንዳለበትም  በስነስርዓቱ ላይ ተገልጿል።

የአውሮፓ ሕብረት ተወካይ አምባሳደር ቻንታል ሀብርቸት እንዳሉት ኢትዮጵያ በካይ ጋዝን ወደ ከባቢ አየር የመልቀቅ እድሏ አናሳ  ቢሆንም   የችግሩ ገፋት ቀማሽ ከመሆን እንዳልዳነች ገልጸው የአየር ንብረት ለውጥ አደጋ  ድንበር ተሻጋሪነትንና ለመከላከልም የሁሉንም ርብርብ እንደሚጠይቅ  አስምረውበታል።    አምባሳደሯ  አያይዘው በዚህ ረገድ  ኢትዮጵያ እየተገበረች ያለችው የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂ  ተጨባጭ ለውጦችን ማስገኘት የቻለና  በመሆኑ  ለሌሎችም ትምህርት የሚሰጥ እንደሆነ ተናግረወል።  በስነስርዓቱ ላይ የአካባቢ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ሚኒስትሩ ዶክተር ገመዶ ዳሌ  እንዳሉት የአገሪቱ እድገት የአረንጓዴ ልማት ታሳቢ ያደረገ እንዲሆን መንግስት  ከመቼውም ጊዜ በላይ ለአካባቢ ጥበቃ ስራዎች  ትኩረት መስጠቱን  ተናግረዋል።

ጊዜው ክረምት በመሆኑ  በበርካታ የአገራችን ክፍሎች ዝናብ የሚጥልበትና የእርሻ ተግባር የሚከናወንበት በመሆኑ  አርሶና አርብቶ አደሩ  ቀን ከሌት የሚሰራበት ወቅት ነው።   የኢትዮጵያ በአካባቢ ጥበቃ ስራ ውጤታማ ለማድረግ ስትራቴጂ ነድፋ በዕቅድ የተመራ  ተግባራትን ማከናወን የቻለች አገር ናት። ባለፉት ጥቂት ዓመታት መንግስትና ህዝብ ተቀራርበው በሰሯቸው የአካባቢ ጥበቃ ስራዎች  የሚታዩና የሚዳሰሱ ስኬቶችን የግለሰብ ተጠቃሚነትን  ማስመዝገብ ተችሏል።

የአገራችን የደን ሽፋን ከ3 በመቶ አካባቢ  አሁን ላይ ከ15 በመቶ  በላይ ማድረስ ተችሏል።  በርካታ አካባቢዎች በማገገማቸው የአገራችን ስነምህዳራዊ ህይወት ወደተሻለ ደረጃ ተሸጋግሯል። በድርቅ ይመቱና በዕርዳታ ላይ የተንጠልጥለው የነበሩ የአካባቢ ጥበቃ ስራ  በመከናወኑ ትርፍ አምራች ወደመሆን ተሸጋግረዋል። የግብርናው  ክፍለ ኢኮኖሚ  ከአካባቢ ጥበቃ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያለው መስክ በመሆኑ ግብርናው በዘመነ ቁጥር  የአካበቢ ጥበቃ ስራውም ስኬታማ ይሆናል።  በኢትዮጵያ 83 በመቶ ህዝብ ነዋሪነቱ በገጠር  በመሆኑ  በአንድም ሆነ በሌላ ከግብርና ጋር የተሳሰረ እንደሆነ መገመት አያዳግትም።

ግብርና የኢትዮጵያ  ኢኮኖሚ  የጀርባ አጥንት ነው።  በመሆኑም በዚህ ዘርፍ ላይ የሚደረግ ርብርብ የአገሪቱን ኢኮኖሚ ላይ ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል መንግስት በመረዳቱ፤ በግብርናውን ለማዘመን  ከፍተኛ ርብርብ  በማድረግ ላይ ይገኛል። በዚህም ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት ችሏል።   በየዓመቱ  በግብርናው ዘርፍ  በአማካይ ስምንት በመቶ ዕድገት በማሳየት ባለፉት 15 ዓመታት ተከታታይ ለውጥ  ማስመዝገብ በመቻሉ  ባለፈው የመኸር ምርት ዘመን ብቻ በዋና ዋና ሰብሎች  ከ323 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት መሰብሰብ ተችሏል። በዘንድሮው መኸር ደግሞ ይህን አሃዝ ወደ 340 ሚሊዮን ኩንታል ለማሳደግ ጥረት እየተደረገ ነው።  ኢትዮጵያ የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂን መተግበር በመቻሏ  በርካታ አካባቢዎች ማገገም በመቻላቸው  ለግብርናው ምርት ዕድገት ትልቅ አስተዋጽ  በማበርከት ላይ ናቸው። ለስራ ዕድል  ማስገኛና የዜጎች ገቢ እንዲያድግም ምክንያት ሆነዋል።

የመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ማብቂያ ላይ የግብርናው ዘርፍ  ከአጠቃላይ ዓመታዊ የአገር ውስጥ ምርት ከ38 በመቶ  አካባቢ ድርሻ እንዳለው ጥናቶች አመላክተዋል። የግብርናው ዘርፍ የአገሪቱ ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት ወይም ሞተር ይሁን አንጂ  መንግስት በቀጣይ  የአገሪቱን ኢኮኖሚ  ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ ለማሸጋገር ተጨማሪ ስራዎችን በማከናወን  ላይ ይገኛል።  ይህ ሽግግር ከአካባቢ ጋር የተጣጣመ እንዲሆንም የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂን በመንደፍ  በመተግበር ላይ ይገኛል።  ግብርናውን ለማዘመን የሚያስችሉ ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎችም  ለአረንጓዴ ልማት መጠናከር  ድርሻ  እንዲኖራቸው ተደርገው  የተቀረጹ ናቸው።   

በተፈጥሮ ሃብት ላይ የተመሰረተ ዕድገት እያስመዘገቡ ያሉ አገራት  የኢኮኖሚ ዕድገታቸው  በአካባቢ ላይ  ከፍተኛ ብክነት  በመፍጠር ላይ ነው። ለዚህ ጥሩ ማሳያ የሚሆኑት ነዳጅ አምራች የሆኑ አገራት ለአካባቢ ብክለት ትልቅ ድርሻ በማበርከት ላይ ናቸው።  ይሁንና የኢትዮጵያ ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት  ከአካባቢ ብክለት የጸዳ ነው ማለት ይቻላል። በመሆኑም በቀጣይም  የኢትዮጵያ መንግስት የአገሪቱን  የኢኮኖሚ ዕድገት ከአረንጓዴ ልማት ጋር በማጣጣም በመጪዎቹ  አስር አመታት መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገሮች  ተርታ ለመቀላቀል  ጥረት በማድረግ ላይ  ይገኛል። መንግስት በሁለተኛው የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ ትኩረት የሰጠው ነገር አንዱ ዘላቂ ልማትን ከአካባቢ ደህንነት ጋር እንዲጣጣም ማድረግ ላይ ነው።  የአረንጓዴ ልማት ኢኮኖሚ ግንባታ ስትራቴጂ መሠረታዊ መነሻው የአከባቢ ሙቀት ሳቢ ጋዞች ልቀትን በመቀነስ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ነው።  የመንግስት ትኩረት ግብርናን በማዘመን  ማለትም  የሰብልና የእንስሳት ምርትን  በማሳደግ  የአርሶ እና  አርብቶ አደሩን  ገቢ  በቀላሉ  ማሻሻል ነው።

በሰብል ምርትና እና እንስሳት እርባታ የተሻሻሉ አሰራሮችን በመጠቀም  የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ  ሲባል  ለእርሻ የሚሆን ያለተጨማሪ መሬት ወይም ደን መጨፈጨፍ    ሳያስፈልግ የአርሶና አርብቶ አደሩን ገቢ ማሳደግ ማለት ነው። የግብርና መሬትን ከማስፋፋትና የከብትን ቁጥርን ከመጨመር ይልቅ፤  ባለው መሬት ላይ ግብዓትን  በአግባቡ በመጠቀም እንዲሁም  በውሱን የእንሰሳት ቁጥር  በዘመናዊ ቴክኖሎጂ  በመጠቀም አርሶና አርብቶ አደሩ ብዙ ሳይለፉ የተሻለ ተጠቃሚ የሚሆበትን አሰራር ማስፈን ይቻላል። ደኖችን እንዳይጨፈጨፉ መንግስት የተለያዩ ስትራቴጂዎችን በመተግበር ላይ ይገኛል። በዚህም ተጨባጭ ውጤት ማስመዝገብ ተችሏል።  

በበርካታ አገሮች ለአካባቢ ብክለት ዋንኛ ምንጭ ተደረጎ የሚወሰደው ሃይል ለማመንጨት የሚደረግ ጥረት ነው። በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ የሃይል ምንጮች  ሙሉ ለሙሉ በሚያስብል መልኩ ከውሃና ነፋስ መሆናቸው መንግስት ለአካባቢ ጥበቃ የሰጠውን ትኩረት ያሳያል። ኢትዮጵያ መንግስት  ከታዳሽ ሃይል በማመንጨት ለጎረቤት አገራት ጭምር በስፋት ለማቅረብ የሚያስችሉ ፕሮጀክቶችን በመተግበር ላይ ነው።  ከዚህ ጎን ለጎን መንግስት  ከዘመናዊ ኢነርጂ ቆጣቢ ቴክኖሎጂዎች በአገሪቱ በተለይ በገጠር አካባቢ በስፋት በማስተዋወቅ ላይ ይገኛል። ዛሬ በአገራችን ከተሞች  በኤሌክትሪክ ማብሰል  በስፋት እየተለመደ በመምጣቱ ለማገዶ ተብሎ የሚጨፈጨፈው ደን በከፍተኛ ሁኔታ በመቀነስ ላይ ነው።  በኢትዮጵያ እየተገነቡ ያሉ ዘመናዊ የባቡር አገልግሎቶችም  በኤሌክትሪክ ሃይል የሚሰሩ በመሆናቸው ለአካባቢ ተስማሚ  ናቸው።  

ኢትዮጵያ መንግስት በስፋት እየሰራው ያለውየአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂው አካል የሆነው  ሌላው ጉዳይ የተፋሰስ ልማት ስራዎች ናቸው።  ባለፉት ጥቂት ዓመታት ብቻ በሁሉም  አርሶና አርብቶ  አደር አካባቢዎች መንግስት ሰፊ የአካባቢ ጥበቃ ስራዎችን እንዲከናወኑ በማድረጉ ተጨባጭ ለውጦችን  በመላ አገሪቱ  ማስመዝገብ ችሏል። በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የገጠሩ ነዋሪ በአካባቢ ጥበቃ ስራዎች ላይ በፍቃደኝነት  በመሰማራታቸው በርካታ አካባቢዎች ማገገም ብቻ ሳይሆን ፍጹም መቀየር  ጀምረዋል። መንግስት እየተገበረ ያለው የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂ በአገሪቱ ላይ ብቻ ሳይሆን በግለሰብ ህይወት ላይ ለውጥ ማምጣት በመቻሉ ይህ ተጠናክሮ መቀጠል የኖርበታል።   

 

 

 

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy