Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

 ሕጻናት እና  ትምህርት በኢትዮ-ሶማሌ

0 368

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

              ሕጻናት እና  ትምህርት በኢትዮ-ሶማሌ

ትምህርት የአንድን ሰው ሁለንተናዊ ሕይወት ለመገንባት ከሚያስፈልጉ መሠረታዊ ነገሮች  አንዱ ነው፡፡ በመሆኑም ተተኪውን ትውልድ ቅርጽ ለማስያዝ፣ ጠንካራ እና ጤናማ ማኅበረሰብ ለመገንባት ዓይነተኛ ሚና አለው። ስለዚህ የትምህርት ዋጋ በምንም አይተመንም፡፡ አንዲት ሀገር የቱንም ያህል ሕዝብ ቢኖራት፤ በትምህርት አዕምሮው ያልተገራ፣ ባህሪው ያልተስተካከለ እንዲሁም አዎንታዊ አመለካከት የሌለው ዜጋ ካላት የትም ልትደርስ አትችልም፡፡

ሥኬታማ የሆኑ፣ በራሳቸው የሚተማመኑ፣ መልካም ስብዕና ያላቸው እና ችግር ፈጣሪ ሳይሆን፤ ችግር ፈቺ የሆኑ ዜጎችን ከመፍጠር አኳያ ትምህርት ከፍተኛ ሚና ይጫወታል፡፡ መልካም ዜጋን ለማፍራት እና ባላስፈላጊ ነገሮች ያልተበረዘ ትውልድን ለመፍጠር ከሚያስችሉ መንገዶች አንዱ ነው፡፡

ሀገሪቱ ከድህነት በመላቀቅ ያደጉ ሀገራት የደረሱበት ደረጃ ለመድረስ  እና ራዕይዋን ከግብ ለማድረስ የተማሩ፣ ሥራ ፈጣሪ እና ችግር ፈቺ የሆኑ ዜጎች ያስፈልጓታል ፡፡ ይህን ዕውን ለማድረግ ደግሞ ያሉትን ችግሮች ተቋቁሞ ትምህርት ቤቶችን በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች ማስፋፋት የግድ ይላል፡፡ ሕጻናት በሚኖሩበት አካባቢ በቅርበት የትምህርት ዕድል እንዲያገኙ እና ወላጆችም ያለሥጋት ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት እንዲልኩ ለማስቻል ትምህርት ቤቶች አስፈላጊ ናቸው፡፡

የኢትዮ-ሶማሌ ክልል ዋና ከተማ በሆነችው የጅግጅጋ ከተማ ከሕጻናት እና ትምህርት ጋር የተገኘውን ተሞክሮ ማሳየት የዚህ ጽሑፍ ዓላማ ነው። የከተማዌ ትምህርት ቢሮ በ2009ዓ.ም ሕጻናትን በተለይም ሴት ሕጻናትን ትምህርት ቤት ከማስገባት ጋር በተያያዘ ከፍተኛ ሥራ ተሠርቷል፡፡የሕዝብ ንቅናቄ ለመፍጠር በተደረገው እንቅስቃሴ የባለድርሻ አካላት መሳተፋቸው ለሥኬቱ ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል። በመሆኑም በትምህርት ተደራሽነት እና ጥራት ላይ የነበሩ የግንዛቤ እጥረቶችን በመቅረፍ አበረታች ውጤት እንዲመዘገብ አስችለዋል። ስለሆነም ትምህርትን የማስፋፋት ሥራም በሰፊው ተሠርቷል፡፡

በተያያዘም በ2009 ዓ.ም ዕድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ፣ በ2008 ዓ.ም ሲማሩ የነበሩ እና ከ2009 ዓ.ም በፊት ያቋረጡ ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ገበታ የመመለስ እና ዕድሜያቸው 4-6 ዓመት የሆናቸውን ሕጻናት መዋዕለ ሕጻናት ትምህርት ቤት በማምጣት ረገድ አበረታች ሥራዎች እንደተከናወኑ ከከተማው ትምህርት ቢሮ የተገኘው መረጃ ያስረዳል።  ከዚህ በተጨማሪ የልዩ ፍላጎት እና የተቀናጀ ተግባር ተኮር ትምህርትን ባካተተ መልኩ በክልሉ በሚገኙ በ11ዱ ዞኖች አሥራ አንድ ቡድኖችን በማደራጀት ወደ ሥራ ተገብቷል። ቡድኖቹ  ከሕዝብ ክንፍ፣ ከተወካዮች ምክር ቤት፣ ከመንግሥት እና ከድርጅት ክንፍ የተውጣጡ 55 አባላትን ያቀፉ ሲሆኑ፤ እነሱን በመጠቀምም እንደ ክልል ከፍተኛ የሕዝብ ንቅናቄ ተካሂዷል፡፡

በክልሉ የሚኖሩት አብዛኛዎቹ ነዋሪዎች አርብቶ አደር ስለሆኑ እና መተዳደሪያቸው ከእንስሳት ሕይወት ጋር በእጅጉ የተቆራኘ በመሆኑ፤ የግዴታ ዝናብ ፍለጋ ከቦታ ቦታ ይንቀሳቀሳሉ፡፡ በዚህ ምክንያት ሕጻናት ከቤተሰቦቻቸው ጋር ስለሚንቀሳቀሱ ወደ ትምህርት ቤት መሄድ ይከብዳቸዋል፡፡ ይህን የአኗኗር ሁኔታ ግምት ውስጥ በማስገባትም ክልሉ መንግሥት ሕፃናት በየሚንቀሳቀሱበት አካባቢ ሆነው አማራጭ መሠረታዊ ትምህርት እንዲያገኙ ለማድረግ ተንቀሳቃሽ መምህራንን (Mobile Teachers) በማሠማራት ላይ ይገኛል፡፡ በዚህም  የAP Schools እና IDP ምን ማለት ይሆን?? ጊዜያዊ መጠለያ እየሠራ ሕጻናቱ ባሉበት ቦታ ትምህርት እንዲያገኙ ያደርጋል፡፡

በተጨማሪም የአርብቶ አደሩን ልጆች የበለጠ ተጠቃሚ ለማድረግ በ8ኛ ክፍል የመልቀቂያ ፈተና ከፍተኛ ውጤት የሚያስመዘግቡ ተማሪዎችን ከየአካባቢያቸው በማሰባሰብ በጅግጅጋ ሞዴል ትምህርት ቤት (Model school) በማስገባት በተፈጥሮ ሣይንስ (Natural Science) የትምህርት መሥክ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርትቸውን እንዲከታተሉ ያደርጋል።

የክልሉ የሴቶች እና ሕጻናት ቢሮ የዓቅም ግንባታ ማጎልበት ኬዝ ቲም አባል/መሪ??? የሆኑት ወ/ሮ ዘሀራ አብዲ እንደገለጹት፤ ከተለያዩ አጋር ድርጅቶች ጋር በመቀናጀት ወላጅ አልባ የሆኑ ሕጻናትን በአንድ ተቋም በማሰባሰብ የትምህርት አገልግሎትን ከሌሎች አገልግሎቶች (ከምግብ፣ መጠጥ…) ጋር በማድረግ እስከ ዩኒቨርስቲ ደረጃ እንዲማሩ የማድረግ ሥራ እየተሠራ ይገኛል ብለዋል፡፡ የደሀ ደሀ የሆኑ ሕጻናትን ደግሞ ከሰኞ እስከ አርብ ባሉት ቀናት አጠቃላይ ወጪያቸውን በመሸፈን እና በመንከባከብ እና በማስተማር የዕረፍት ቀናትን ወደ ቤተሰብ ተመልሰው እንዲያሳልፉ ይደረጋል።

የክልሉን የትምህርት ሽፋን ለማሳደግ በተሠራው ሥራ፤ በቅድመ መደበኛ ትምህርት  59,198 (ሃምሳ ዘጠኝ ሺህ አንድ መቶ ዘጠና ሥምንት) ፣ በአንደኛ ደረጃ ትምህርት 1,028,552 (አንድ ሚሊዮን ሃያ ሥምንት ሺህ አምስት መቶ ሃምሳ ሁለት) ፣ በሁለተኛ ደረጃ (9-10ኛ)  35,206 (ሰላሳ አምስት ሺህ ሁለት መቶ ስድስት)  እንዲሁም በመሰናዶ (11-12ኛ) 18,739 (አሥራ ሥምንት ሺህ ሰባት መቶ ሰላሳ ዘጠኝ) የሚጠጉ  በአጠቃላይ በሁሉም የትምህርት ደረጃዎች 1,141,695 (አንድ ሚሊዮን አንድ መቶ አርባ አንድ ሺህ ስድስት መቶ ዘጠና አምስት) ተማሪዎች  በትምህርት ገበታ ላይ እንዲገኙ ማድረግ ተችሏል፡፡ ለዚህ ሥኬትም አርብቶ አደሮች ልጆቻቸውን እንዲያስተምሩ እና በተለይም ሴት ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ገበታ እንዲልኩ ለማበረታታት  እንደ ዘይት የመሳሰሉ እና የተለያዩ ድጎማዎች (Incentives) ለወላጆች የሚሰጡበት አሠራር ተፈጥሯል።  

በ2009 ዓ.ም በልዩ ፍላጎት ትምህርት ውስጥ (የአካል እና የጤና ጉዳት ያለባቸው፣ መስማት የተሳናቸው፣ ማየት የተሳናቸው፣ የአዕምሮ ዘገምተኝነት ያለባቸው) ከ1ኛ-12ኛ ክፍል ያሉ ተማሪዎችን በመለየት ወደ 3,041 (ሦስት ሺህ አርባ አንድ) የልዩ ፍላጎት ተማሪዎች ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ተደርጓል፡፡

በክልሉ 11 ዞኖች ውስጥ የሙያ እና የቴክኒክ ትምህርት እየሰጡ የሚገኙት አራት ትምህርት ቤቶች ብቻ ናቸው። ይህን ችግር ለመቅረፍም የክልሉ መንግሥት በ2009 በጀት ዓመት ወደ ስድስት የሚጠጉ የቴክኒክ እና የሙያ ትምህርት ቤቶች በመገንባት ላይ ይገኛሉ.፡፡ በዘርፉም ቀደም ካሉት ጊዜያት ጋር ሲነጻጸር ቁጥራቸው ከፍተኛ የሆኑ ሴት ተማሪዎች እየገቡ ይገኛሉ፡፡

በያዝነው በጀት ዓመት በክልሉ ተከስቶ የነበረውን ድርቅ ምክንያት በማድረግ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው እንዳይስተጓጎሉ በ217 (ሁለት መቶ አሥራ ሰባት) ትምህርት ቤቶች የተማሪ ምገባ ፕሮግራም ተካሂዷል፡፡ በዚህም በድርቁ ምክንያት ተዘግተው የነበሩ ትምህርት ቤቶች እንዲከፈቱ ተደርጓል። ይህ በመደረጉም በርካታ የአርብቶ አደር አካባቢ ትምህርት ቤቶች ተማሪዎቻቸውን በተገቢው ሁኔታ ማስተማር ችለዋል። የተገኘውን ተሞክሮ በመቀመርም የክልሉ መንግሥት የተማሪዎች የምገባ ፕሮግራምን በ2010ዓ.ም በመደበኛነት ለመያዝ ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡

ከትምህርት ጥራት ጋር በተያያዘ ቅድሚያ ሊሰጣቸው ይገባል ላላቸው መምህራን የደሞዝ ማስተካከያ ከማድረጉም በተጨማሪ ለ 23,000 (ሃያ ሦስት ሺህ) መምህራን በየሚኖሩበት አካባቢ ወደ 250 ካሬ የሚጠጋ የቤት መሥሪያ ቦታ እየሰጠ ይገኛል፡፡

በክልሉ ትምህርት ቢሮ የተጠቀሱት አበረታች ውጤቶች ቢመዘገቡም፤ ጥቂት የማይባሉ ተግዳሮቶችም አሉ።  ከእነዚህ መካከል ጥቂቶቹ በሶማሊኛ ቋንቋ የሚያስተምሩ መምህራን እጥረት፣ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ፣ ጄኔራል ቢዝነስ፣ የቴክኒካል ድሮዊንግ እና የኢኮኖሚክስ መምህራን በገበያ ያለመገኘት እንዲሁም ለደረጃው የሚመጥኑ እና ብቁ የሆኑ የትምህርት አመራሮች ውስንነት በዋናነት ይጠቀሳሉ።

ሕጻናት የነገ ሀገር ተረካቢ ትውልድ እንደመሆናቸው በተገቢው ተኮትኩተው ማደግ አለባቸው። ዛሬ በእነርሱ ላይ ያልዘራነውን ነገ አናጭድም፡፡ ስለዚህ ዛሬ በትምህርት እና በምግባር አንጸን ካላሳደግናቸው፤ ሀገር ወዳድ እና አልሚ በመሆን ፈንታ የሚያጠፉ ይሆናሉ፡፡ ከልጅነታቸው ጀምሮ በትምህርት እና በሥነ ምግባር የታነጹ እንዲሆኑ ትኩረት ሰጥቶ በመሥራት ጠንካራ እና ጤናማ ትውልድ ለመፍጠር የክልሉ መንግሥት የሚያደርገውን ጥረት የሚመለከተው ሁሉ መደገፍ አለበት። ይህ ሲሆን፤ ሕፃናቱ በተለያየ መስክ ሠልጥነው ሀገሪቱ ያለባትን ክፍተት የሚፈቱ ይሆናሉ፡፡ ስለዚህ እንደማኅበረሰብ ለልጆቻችን ደህንነትን የሚዋጉ፣ ዕውቀትን የሚሹ እንዲሁም መልካም እሴቶችን የሚከብሩ እንዲሆኑ ማስተማር እና ማሳወቅ ለነገ የሚባል አይደለም።  የትምህርትን ዋጋ በመረዳት ለአዕምሯዊ ዕድገት፣ ለመልካም ባህሪይ ቀረፃ ቸውን እና ለአመለካከታቸው መዳበር የሚበጇቸውን በማድረግ መልካም ዜጋ እንፍጠር በማለት መልዕክቴን አስተላልፋለሁ።

  

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy