Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

መቼምና የትም ዜጎቹን ችላ የማይል መንግስት

0 301

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

መቼምና የትም ዜጎቹን ችላ የማይል መንግስት

ብ. ነጋሽ

በሳኡዲ አረቢያ በህገወጥነት የሚኖሩ የተለያዩ ሃገራት ዜጎች ሃገሪቱን ለቀው እንዲወጡ  ተቀምጦ የነበረው የምህረት የጊዜ ገደብ ሰኔ 20፣ 2009 ዓ/ም ተጠናቋል። በሳኡዲ አረቢያ በህገወጥነት ከሚኖሩ የተለያዩ ሃገራት ዜጎች መሃከል ኢትዮጵያውያን ከፍተኛውን ቁጥር እንደሚይዙ መረጃዎች ያመለክታሉ። እነዚህ ኢትዮጵያውያን ሳኡዲ አረቢያ ውስጥ በህገወጥነት የሚኖሩ ከመሆናቸው ባሻገር፣ ቀደመውንም ከኢትዮጵያ የወጡት በህጋዊ መንገድ አልነበረም። ኢትዮጵያን ለቀው የወጡት በህገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች አማካኝነት የተሰወረ የጉዞ መስመር ተከትለው ነው።

በመሆኑም የኢትዮጵያ መንግስት እነዚህ ዜጎቹ እነማን እንደሆኑ፣ የትና በምን አይነት አኳኋን እንደሚኖሩ አያውቅም፤ ይህን የሚያመለክት ሰነድ ስለሌለው። በመሆኑም የኢፌዴሪ መንግስት፤ ዓለም አቀፍ ህጎች፣ ስምምነቶችና የሳኡዲ አረቢያ ህግ በሚፈቀዱትና በሚያዙት መሰረት መብታቸው መረጋገጡን መከታታልና መብታቸውን ማስከበር የሚችልበት ሁኔታ ጠባብ ሆኖ ቆይቷል። እነዚህ በህገወጥነት በሳኡዲ አረቢያ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ከህግ ተደብቀው ስለሚኖሩ፣ እንኳን ሩቅ ያለው የኢትዮጵያ መንግስት፣ ራሱ የሳኡዲ አረቢያ መንግስትም መበቶቻቸውን ለማስከበር የሚችልበት እድል ጠባብ ነው።

ያም ሆነ ይህ፤ ሳኡዲ አረቢያ አሁን የምትገኝበትን ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያ ሁኔታ መነሻ በማድረግ መንግሰቱ በሃገሩ በህገወጥነት የሚኖሩ የየትኛውም ሃገር ዜጎች ሃገሪቱን ለቀው እንዲወጡ ወስኗል። ህገወጥ ነዋሪዎቹ ላይ በቀጥታ ህግ የሚፈቅድለትን እርምጃ ወደመወሰድ መግባትን ግን አልመረጠም። ከዚህ ይልቅ አዋጁ ከወጣበት መጋቢት 20 እስከ ሰኔ 20፣ 2009 ዓ/ም ደረስ ባሉት 90 ቀናት የጊዜ ገደብ ውስጥ ሃገሪቱን ለቀው እንዲወጡ የምህረት አዋጅ ነበር ያወጣው። በዚህ የምህረት አዋጅ የጊዜ ገደብ ውስጥ ሃገሪቱን ለቀው ካለወጡ፣ ከለላ የሰጧቸውን ሰዎች ጨምሮ የቅጣት እርምጃ አንደሚወስድም አሳውቋል።

እንግዲህ፣ ሁሉም ኢትዮጵያዊ እንደሚያውቀው የኢትዮጵያ መንግስት በህገወጥ መንገድ ከሃገር ወጥተው፣ በሀገወጥነት በሳኡዲ አረቢያ የሚኖሩ ዜጎቹን ስራችሁ ያውጣችሁ ብሎ አልተዋቸውም። አዋጁ ተግባራዊ መደረግ ከተጀመረበት እለት አንስቶ፣ የምህረት ጊዜው አብቅቶ ለቅጣት ከመዳረጋቸው፣ ለስቃይና እንግልት ከመጋለጣቸው አስቀድሞ ወደሃገራቸው እንዲመለሱ ለማድረግ ከፍተኛ እንቅስቃሴ አድርጓል።

የኢትዮጵያ መንግስት በህገወጥ መንገድ በሳኡዲ አረቢያ የሚኖሩ ዜጎቹን በሰላም ወደሃገራቸው ለመመለስ እንቅስቃሴ የጀመረው አዋጁ ይፋ በተደረገ ማግስት ነበር። መንግስት  በህገ ወጥነት በሳኡዲ አረቢያ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ሳይጉላሉ ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ለማድረግ መጋቢት 21፣ 2009 ዓ/ም ከሳዑዲ ባለስልጣናት ጋር የሚመክርና አቅጠጫ የሚያስቀምጥ የልኡካን ቡድን ወደሳኡዲ አራቢያ ልኮ ስምምነት ላይ ደርሰዋል።

በዚህ መሰረት መንግስት ኢትዮጵያውያኑ ሳይጉላሉ ወደ ሃገራቸው በሰላም እንዲመለሱ ለማድረግ የሚያግዘውን ዝግጅት አድርጓል። በዚህ መሰረት በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል ኢትዮጵያውያኑን ወደሃገራቸው የሚመልስ አስተባባሪ ኮማንድ ፖስት እንዲደራጅ ተደርጓል።

በሀገር አቀፍ ደረጃም እንዲሁ ስራውን የሚመራ ኮማንድ ፖስት ተደራጀቷል። የፌዴራልና የክልል መንግስታትን ጨምሮ ሁሉም የባለድርሻ አካላትን ያካተተ በከፍተኛ የመንግስት ኃላፊዎች የሚመራ ብሔራዊ ግብረ ኃይልና በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የሚመራ አስመላሽ ኮማንድ ፖስት በሳዑዲ አረቢያ ዘጠኝ ማዕከላት አቋቁሞ ኢትዮጵያውያኑን ወደሃገራቸው ለመመለስ ከፍተኛ ጥረት ሲያደግ ቆይቷል።

በህገወጥነት በሳኡዲ አረቢያ የሚኖሩት ኢትዮጵያውያን ወደሃገራቸው እንዲመለሱ ለማድረግ መንግስት እያደረገ ያለውን እንቅሰቃሴ እንዲያውቁ፣ እንዲሁም በጊዜ ገደቡ ውስጥ መመለስ ካልቻሉ ምን አይነት ችግር እንደሚጠብቃቸው ግንዛቤ እንዲኖራቸው በተለያዩ የኢትዮጵያ ብሄሮችና ብሄረሰቦች ቋንቋዎች መልዕክቶች እንዲተላለፉ ተደርጓል።

የኢትዮጵያ መንግስት በህገወጥነት በሳኡዲ አረቢያ የሚኖሩ ዜጎቹን በየአካባቢው ባዘጋጀው ጣቢያ ቀርበው ወደሃገራቸው ለመመለስ የሚያስፈልጋቸውን የጉዞ ሰነድ ወስደው እንዲመዘገቡ ባደረገው ከፍተኛ ጥረት የ90 ቀናት ገደቡ እስከተጠናቀቀበት ጊዜ ደረስ 111 ሺህ ኢትዮጵያውያን እንዲመዘገቡ ማድረግ ችሏል። በሳኡዲ አረቢያ በህገወጥነት ይኖራሉ ተብሎ ከሚጠበቀው ከ150 ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን ቁጥር አንጻር ሲታይ ወደሃገራቸው ለመመለስ የተመዘገቡት 75 በመቶ ገደማ ይሆናሉ። ይህን ከአራት ዓመት በፊት ከነበረው ተመሳሳይ ሁኔታ ጋር ሲነጻጻር ስኬታማ ስራ ተከናውኗል ማለት ይቻላል።

ከእነዚህ ከተመዘገቡት 111 ሺህ ኢትዮጵያውያን መሃከል እስከአሁን ወደሃገራቸው የተመለሱት ከ46 ሺህ ብዙም አይበልጡም። ወደሃገራቸው ለመመለስ ከተመዘገቡት ውስጥ ወደሃገራቸው የተመለሱት 41 በመቶ ገደማ ብቻ ናቸው። ኢትዮጵያውያኑን ወደሃገራቸው ለመመለስ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የየእለት በረራውንና የመዳረሻ ቦታውን ወትሮ ከነበረው ጨምሯል። በገንዘብ ችግር ምክንያት የሚያመነቱ ኢትዮጵያውያን እንዳይኖሩ አየር መነገዱ የበረራ ክፍያ ላይ የ50 በመቶ ቅናሽ አድርጓል።

ይህም ሆኖ ለመመለስ ከተመዘገቡት ውስጥ 41 በመቶ የሚሆኑት ብቻ መመለስ መቻላቸው ችግር መኖሩን ያመለክታል። ይሁን እንጂ ችግሩ የተፈጠረው በመንግስት በኩል ሳይሆን፣ ኢትዮጵያውያኑ ወደሃገራቸው ለመመለስ ተመዝግበው ለጉዞ የተዘጋጁት ቀነ ገደቡ ሊያበቃ ትቂት ቀናት ሲቀሩት በመሆኑ በተፈጠረ የትራንስፖርት መጨናነቅ ነው። ኢትዮጵያውያኑ መንግስት ወደሃገራቸው እንዲመለሱ ቅስቀሳ ማድረግ ከጀመረበት ጊዜ ጀምረው ተመልሰው ቢሆን ኖሩ፣ ወደሃገራቸው ለመመለስ የተመዘገቡትን ሁሉንም ኢትዮጵያውያን ያለምንም መጨናነቅ ማጓጓዝ የሚቻልበት እድል ነበረ።

ያም ሆነ ይህ፣ የኢትዮጰያ መንግስት በጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም አማካኝነት ለሳኡዲ አረቢያው ንጉስ ሳልማን ቢን አብዱልአዚዝ የምህረት ቀኑ እንዲራዘም ጥያቄ አቅርቧል። ይህ የኢትዮጵያ መንግስት ጥያቄ በሳኡዲ አረቢያው ንጉስ ተቀባይነት አግኝቶ የምህረት ጊዜው ከሰኔ 18፣ 2009 ዓ/ም ጀምሮ በ30 ቀናት ተራዝሟል። የኢትዮጵያ መንግስት በዚህ በተራዘመ የጊዜ ገደብ ውስጥ እስካሁን ያልተመዘገቡትን ጨምሩ ከተመዘገቡት 111 ሺህ ውስጥ የቀሩትን በሙሉ በሰላም ወደሃገራቸው ለማጓጓዝ የጀመረውን ጥረት አጠናክሮ ቀጥሎበታል።

እንግዲህ በሳኡዲ አረቢያ በህገወጥነት የሚኖሩት ኢትዮጵያውያን ብቻ አይደሉም። የበርካታ የአፍሪካና የኢሲያ ሃገራት ዜጎች በህገወጥነት እንደሚኖሩ ይታወቃል። ሳኡዲ አረቢያን ለቀው እንዲወጡ መታወጁን ተከትሎ ዜጎቹን ከቅጣት፣ ከእንግልትና ስቃይ ለመታደግ በጀት መድቦ የተደራጀ እንቅስቃሴ ያደረገው ግን የኢትዮጵያ መንግስት ብቻ ነው። ይህ የኢፌዴሪ መንግስት በማንኛውም ሁኔታ፣ መቼምና የትም አቅሙ በፈቀደው ልክ የዜጎቹን ሰብአዊ መብትና ክብር ለማስጠበቅ የሚሰራ መሆኑን የሚያሳይ ተጨባጭ አስረጂ ነው።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy