Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

መንገላታትና ክብር መነካት እንዳይኖር…

0 315

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

መንገላታትና ክብር መነካት እንዳይኖር…

                                                       ቶሎሳ ኡርጌሳ

የኢትዮጵያ መንግስት በሳዑዲ አረቢያ በህገ ወጥነት የተፈረጁ ዜጎችን ህይወት እንዳይንገላቱና ክብራቸውም እንዳይነካ ለማድረግ እጅግ ብርቱ ጥረት አድርጓል። ይህ ተግባሩ የትኛውም ሀገር ባላደረገው መልኩ በመንግስት ደረጃ የተከናወነ ነው። መንግስት በዚህ ተግባሩ ከ50 ሺህ በላይ ዜጎች በሰላም ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ በዚያች ሀገር ውስጥ ሊደርስባቸው የሚችለውን ችግር እያቃለለ ነው።

በተለያዩ ወቅቶች የመንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናትን ጨምሮ ዲፕሎማቶችን በመላክ ብርቱ ጥረት አድርጓል። በሳዑዲ ውስጥ ዜጎቻችን በሚገኙበት ቦታዎች ሁሉ የጉዞ ሰነዶችን በማዘጋጀት፣ የትራንስፖርት መጓጓዣ ወጪዎችን በመቀነስና በርካታ እቃዎቻቸውን ከቀረጥ ነፃ እንዲያስገቡ በመፍቀድ እንዲሁም በሳዑዲ መንግስት የተወሰነውን የምህረት ጊዜ ገደብ አዋጅ በአንድ ወር እንዲራዘም ከሪያድ መንግስት ጋር ተደራድሮ በማስፈቀድ በህገ ወጥነት የተፈረጁ ዜጎቻችን ከስቃይና ከእንግልት ለመታደግ ካደረጋቸው በርካታ ጥረቶቹ ውስጥ ጥቂቶቹ ናቸው።

ይህ ሁሉ ጥረት ተደርጎም ቢሆን እስካሁን ድረስ በአጥጋቢ ሁኔታ ዜጎቻችን ወደ ሀገራቸው ተመልሰዋል ማለት አይቻልም። በመንግስት ጥረት የተጨመረው አንድ ወር እያለቀ ነው- በጣት የሚቆጠሩ ቀናት ብቻ ናቸው የቀሩት። እናም ቀሪው አንድም ቀን ቢሆን እንኳን ዜጎቻችን መጠቀም ይኖርባቸዋል። በእኔ እምነት ዜጎች ይህን በማድረጋቸው የመንግስትን ጥረት መደገፍ ይኖርባቸዋል።

አሁንም ቢሆን ሳዑዲ ውስጥ ቁጥራቸው እጅግ የበዛ ኢትዮጵያዊያን እንዳሉ ይታወቃል። ታዲያ ይህን ዕውነታ በሚገባ የተገነዘበው የኢፌዴሪ መንግስት ካለው ህዝባዊ ወገንተኝነት በመነሳት ዜጎቹ በተሰጠው ምህረት ተጠቅመው ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ሰፊ ጥረት ተደርጓል።

በተለይም በሪያድ መንግስት በህገ ወጥነት የተፈረጁት ስደተኞች በዚያች ሀገር ቆይታቸው ያፈሩትን ንብረት ይዘው በህጋዊ መንገድ እንዲገቡ እንዲሁም አሻራ መስጠት ሳያስፈልጋቸው ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ የማድረግ ጥረት ሁሉ ተደርጓል። ይህም ስደተኞቹ ሀገር ቤት ውስጥ ከመጡ በኋላ ፍላጎት ካላቸው ተመልሰው እንዲሄዱ የሚያደርግ ነው።

ይህ መንግስታዊ ተግባር መነሻው ለዜጎች ከማሰብና ወገኖቻችን እንግልት እንዳይደርስባቸው ከማሰብ የመነጨ ነው። ርግጥ ከዛሬ ሶስት ዓመት በፊት በሳዑዲ ውስጥ የሚኖሩ ዜጎቻችን ለደረሰባቸው ሞት፣ እንግልትና ስቃይና በባዶእጅ ንብረትን ጥሎ የመመለስ እውነታን መንግስት ዝም ብሎ አልተቀበለም። ለዜጎቹ እጅግ ተከራክሯል። ተገቢውንም ድጋፍ አድርጓል። ዛሬም እያከናወነ ያለው ጥረቱ ያ ጉዳይ ዳግም እንዳይከሰት ካለው ህዝባዊ መንፈስ የመነጨ ነው።

በዚያን ወቅት በህገ ወጥ መንገድ በሳዑዲ ይኖሩ በነበሩ ዜጎች ላይ የደረሰው ሞት፣ እንግልትና በባዶ እጅ መመለስ የሚያሳየው ነገር ቢኖር፤ ዛሬም በምህረት አዋጁ እንዲሁም መንገስት ተደራድሮ ባስጨመረው የአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ያልተጠቀሙ ስደተኞች የዚያን ጊዜው አደጋ ሊያጋጥማቸው እንደማይችል ምንም ዓይነት ዋስትና የለም።

ያም ሆኖ በርግጥ በህገ ወጥ መንገድ ባህር ተሻግረው በሳዑዲ አረቢያ የሚገኙ ዜጎቻችን ቁጥር በርካታ እንደሆነ የሚታወቅ ቢሆንም ህገ ወጥንም በህግ መጠየቅ እንጂ ህይወት ማጥፋት ወንጀል እንደሆነ የሚያስገነዝብ አቋሙን የኢትዮጵያ መንግስት ገልፆ እንደነበር እናስታውሳለን። በወቅቱ በዚህ የመንግስት አቋም የአያሌ ዜጎቻችንን ህይወት ከአደጋ መታደግ መቻሉን የተገነዘበ ኢትዮጵያዊ ምን ያህል እንደተደሰተና በኢትዮጵያዊነቱም ምን ያህል እንደኮራ መገመቱ አዳጋች አይመስለኝም።

በእኔ እምነት መንግስት በሳዑዲ አረቢያ ፀጥታ ኃይሎች እየተዋከበ የሚገኘው ዜጋችንን ለመታደግ የወሰደው የያኔው ርምጃ ውጤታማነቱን ማስመስከር የቻለበትን ሁኔታ መፍጠር ችሏል—በወቅቱ የዜጎችን መብት ለማስከበር በቅቷልና።

ሆኖም አሁንም ዜጎቻችን በሚፈለገው መንገድ ወደ ሀገር ቤት እንዳይመለሱ ህገ ወጥ ደላሎች ውሸት በማውራት እንቅፋት እየፈጠሩ መሆኑ ይታወቃል። ያም ቢሆን ስደተኞቹ ይህንን የለየት የህገ ወጥ ደላላዎችን ቅጥፈት ባለመስማት አንድም የሳዑዲ መንግስት ለሁለተኛ ጊዜ ያራዘመውን የጊዜ ገደብ መጠቀም፣ ሁለትም የኢትዮጵያ መንግስት የዜጎቹን ደህንነት አስቀድሞ ለመጠበቅ ከወዲሁ የሚያደርገውን ጥረት ማገዝ ይኖርባቸዋል። በመሆኑም ስደተኞቹ ዕውነታውን ሚዛናዊ በሆነ መንገድ ተገንዝበው ለራሳቸው ዘላቂ ህይወትም ይሁን ለመንግስት ህዝባዊ ወገንተኝነት ጥረት ዋጋ መስጠት አለባቸው።

የኢፌዴሪ መንግስት እንኳንስ የራሱን ዜጋ ቀርቶ የሌሎች ሀገራትን ስደተኞች ተቀብሎ የሚያስተናግድ የህዝብ ወገንተኝነትን የተላበሰ ነው። ይህ ምስጉን ተግባሩም በተለያዩ ሀገራት የተመሰገነ ነው። መንግስት በዜጎቹ ላይ ወደፊት ሊደርስ የሚችለውን ችግር ከወዲሁ በመገንዘብ የስጋት ትንተና በማካሄድ ከወዲሁ ችግሩን ለመፍታት ያደረገው ጥረትም የዚህ ህዝባዊ ወገንተኝነቱና ሃላፊነቱ መገለጫ ነው ማለት ይቻላል።

የኢፌዴሪ መንግስት ህዝባዊ በመሆኑ ከሁሉም በላይ ለዜጎቹ ችግር ፈጥኖ ደራሽ መሆኑን የዛሬ ሶስት ዓመትና በአሁኑ ወቅት እስከ መጨረሻዋ ሰዓት ድረስ እያከናወናቸው ያሉት ተግባራት እያው ምስክሮች ናቸው።

ይህ ሁኔታም በዜጎች ላይ ችግር በተፈጠረ ቁጥር በሀገር ውሰጥም ይሁን በባህር ማዶ እየተገኘ ፈጣን ምላሽ በመስጠትና ተገቢውን ርምጃ መውሰዱ ለህዝቡ የሚሰጠው ከፍተኛ ክብር ምን ያህል እንደሆነ ያሳያል።

መንግስት ሁሌም እንዲህ ዓይነቱን ተግባር የሚያከናውነው መነሻውም ይሁን መድረሻው ከሚከተለው ህዝባዊ ወገንተኝነት የመነጨ ነው። ዜጎቹ ሳዑዲ ዓረቢያ ውስጥ በህገ ወጥነት በመገኘታቸው ምንም ዓይነት ተፅዕኖ ስር ሳይወድቁ ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ያደረጋቸው ጥረቶች የዚህ እውነታ አስረጅ ናቸው። ግና ሁሌም ለማደግ የመጣር መፍትሔን ከመንግስትና ከሀገር መሻት ተገቢ ይመስለኛል።

ርግጥ ማንም ሰው የትኛውም ቦታ ተንቀሳቅሶ የመስራት ህገ መንግስታዊ መብት አለው። እንዲሁም በላቡ ጥሮና ግሮ ህይወቱን ለማሻሻል የማይሻ ሰው አለ ብሎ ለመናገር አይቻልም። ለዚህ አባባሌ መላው ህዝባችንና መንግስት ከድህነትና ኋላቀርነት ለመውጣት ከፍተኛ ትግል በማካሄድ ላይ የሚገኙበት ዋነኛው ምክንያታቸው ለዜጎች ብልፅግናና ኑሮ መሻሻል መሆኑን በአስረጅነት ማጣቀስ የሚቻል ይመስለኛል።

ታዲያ ዜጎች ድህነትን ለመቅረፍ የሚያደርጉት ተነሳሽነት ትክክል አይደለም ሊባል የማይችል ቢሆንም፤ በህገ ወጥ ደላሎችና አፈ ቅቤዎች ተታልለው የእነርሱ ሲሳይ መሆናቸው ግን እጅጉን የሚያስቆጭ ነው። ከዚህም ባሻገር ሁሉም ነገር ህግን የተከተለ አካሄድ ተጠቅሞ መበልጸግ ሲቻል ህገ ወጥ አካሄድን መርጦ ለአደጋ መጋለጡ ተገቢ አይደለም።

እንደሚታወቀው በአሁኑ ወቅት ሀገራችን በትክክለኛ የልማት ጎዳና ላይ ትገኛለች። በዚህም ከፍተኛ የሥራ ዕድል በመፈጠሩ ዜጎች የልማቱ ተጠቃሚ መሆን ችለዋል። በተለይም ወጣቶች በግንባታ ሥራዎች ላይ በቋሚነትና በጊዜያዊነት ተቀጥረው በመሥራታቸው የቤተሰብ እጅን ከመጠበቅ ከመዳናቸውም ባሻገር፤ ራሳቸውን የሚችሉበት ዕድል ተፈጥሯል። ይህ ዕድል በውጭም ላሉት ዜጎቻችን ጭምር ነው።

ለሳዑዲ ተመላሾች አቅም በፈቀደ መጠን ሁሉም ነገር ይመቻቻል። ዜጋ በመሆናቸው ለሌላው ህዝብ የሚደረገው ለእነርሱ ሊነፈግ አይችልም። በሀገራቸው በፈለጉት የስራ መስኮች ውስጥ ተሰማርተው ራሳቸውንና ወገናቸውን መጥቀም የማይችሉበት ምክንያት የለም። እነዚህ ሀገር ውስጥ እየተሳለጠ ያለው የምጣኔ ሃብት እድገት ዜጎች በሀገራቸው ውስጥ መስራት እንዲችሉ እንዲሁም በባዕድ ሀገር ውስጥ ለስራ ፍለጋ ሄደው እንዳይንገላቱና ክብራቸው እንዳይነካ ጭምር የሚያደርግ ነው። እናም ሽርፍራፊ ሰዓትም ቢሆን መጠቀም ያስፈልጋል።

መንግስት እጅግ ረጅም የሚባል ርቀት ተጉዞ የዜጎቹን እንግልትና ክብር መነካት እንዲሁም ያፈሩትን ጥሪት እንዳይቀሙ አስመስጋኝ ጥረት አድርጓል። በህዝባዊ ወገንተኝነቱ የቻለውን ሁሉ አድርጓል። አሁን ባለው ሁኔታ እኔ እስከሚገባኝ ድረስ የሳዑዲ አረቢያን መንግስት ለሁለተኛ ጊዜ የምህረት አዋጁን እንዲያራዝም የመጠየቅ ህጋዊ መንገድ ይኖረዋል ብዬ አላስብም። እናም ስደተኞቹ ይህን ሊገነዘቡ የሚገባ ይመስለኛል። ግና ሁሌም ቢሆን መንግስት ከእነርሱ ጋር መሆኑን መሀንዘብ አለባቸው—በየትኛውም ቦታና ሁኔታ ለዜጎቹ ቀድሞ ደራሽ ነውና።    

 

  

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy