CURRENT

መንግስት ለኢትዮጵያ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላደረጉ የውጭ አገር ዜጎች መታወቂያ ሊሰጥ ነው

By Admin

July 28, 2017

መንግስት ለኢትዮጵያ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላደረጉ የውጭ አገር ዜጎች፣ቤተ እስራኤላውያንና የራስ ተፈሪያኖች የኢትዮጵያዊነት መታወቂያ ሊሰጥ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

በሚኒስቴር የቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ጉዳዩን አስመልክቶ  ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ መለስ አለም በመግለጫው እንዳሉት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከብሔራዊ  መረጃና ደህንነት አገልግሎት ጋር በመሆን ጉዳዩ ተፈጻሚ የሚሆንበትን መመሪያ አዘጋጅቷል፡፡

መመሪያው የተዘጋጀውም በኢትዮጵያ ተወላጅ የሆኑ የውጭ ሃገር ዜጎች በትውልድ አገራቸው የተለያዩ መብቶችን ተጠቃሚ ለማድረግ የወጣውን አዋጅ ቁጥር 270/1994 መሰረት በማድረግ መሆኑ ተገልጿል፡፡

መታወቂያውን እንዲያገኙ የተዘረዘሩ አካላት ከኢትዮጵያ ጋር ካላቸው ስር የሰደደ ትስስር አንጻር ህጋዊ እውቅና መስጠት አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱን ቃል አቀባዩ አብራርተዋል፡፡

በሌላ በኩል አብዛኛው ቤተ እስራኤላዊያን ህጋዊ ሰነድ ሳያሟሉ ከኢትዮጵያ መውጣታቸውን  የጠቆሙት አቶ መለስ፤  “የመመሪያው መዘጋጀት በእነዚህ አካላት በተደጋጋሚ ሲነሳ የነበረን የትውልደ ኢትዮጵያዊነት መብት ጥያቄን ይመልሳል” ብለዋል::

የመመሪያው መጽደቅ መታወቂያውን የሚያገኙ አካላት ለኢትዮጵያ ልማት የሚኖራቸውን አስተዋጽኦ የበለጠ እንደሚያጠናክረውም ጨምረው አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ የባህል አምባሳደር በመሆን በአገር ገጽታ ግንባታና ኢትዮጵያን  በማስተዋወቅ ረገድ ትልቅ ሚና ይጫወታሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም ጠቁመዋል።

በመመሪያው መሰረት መታወቂያ ያገኙ የውጭ አገር ዜጎች ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ  ቪዛና የመኖሪያ ፈቃድ አይጠየቁም፡፡

በተጨማሪም በመመሪያው መሰረት ለአገር ውስጥ ባለሃብቶች በተፈቀዱ የኢንቨስትመንት መስኮች ላይ እንዲሰማሩ ሲፈቅድ ፣የመምረጥና የመመረጥ መብት፣በመከላከያ፣የአገር ደህንነትና ውጭ ጉዳይ መስኮች ላይ ግን መሳተፍ አይችሉም፡፡

አገልግሎቱን በኢሚግሬሽንና ዜግነት ጉዳዮች አማካኝነት ለመስጠት ቅድመ ዝግጅቱ መጠናቀቁም  ተገልጿል።