Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

መንግስት ለኦሮሞ ህዝብ የገባውን ቃል አክብሯል!

0 407

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

መንግስት ለኦሮሞ ህዝብ የገባውን ቃል አክብሯል!

ሰለሞን ሽፈራው

የኢትዮጵያ ፌደራላዊ መንግስት፤ የአፍሪካ ህብረትና እንዲሁም ደግሞ፣ የሌሎች ዓለም አቀፋዊ ተቋማት መቀመጫ የሆነችው መዲናችን አዲስ አበባ በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልል ውስጥ እንደ ምትገኝ ይታወቃል፡፡ ከዚሁ የማይካድ ነባራዊ ሀቅ የተነሳም የኢፌድሪ ሕገ መንግስት ገና ሲረቀቅና ሲጸድቅ ጀምሮ የኦሮሚያ ክልል ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ላይ ልዩ ጥቅም እንዲያገኝ የሚያደርገው መብት ታሳቢ ተደርጎ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ስምምነቱ ወደ መሬት ወርዶ ተግባራዊ ሳይደረግ በመቆየቱ ምክንያት፤ ጉዳዩ ለየራሳቸው ድብቅ አጀንዳ ማስፈጸሚያነት ሊጠቀሙበት የሚፈልጉ ተቃዋሚ የፖለቲካ ቡድኖች፤ ለሚቀሰቅሱት ሁከትና ብጥብጥ ምቹ ሁኔታ ሲፈጠር መስተዋሉ የሚካድ አይደለም፡፡

ከዚህ አኳያ “የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ያዘጋጀው አዲስ መሪ እቅድ (ማስተር ፕላን) ከመዲናዋ ጋር በሚዋሰኑት የኦሮሚያ ዞኖች ነዋሪ ህብረተሰብ ላይ ፈርጀ ብዙ ጉዳት ስለሚያደርስ ተግባራዊ ሊደረግ አይገባም” የሚል መነሻ የነበረውን ቅሬታ በማራገብ ሕገ ወጥ የተቃውሞ ሰልፍ እየጠሩ ክልሉን ለማተራመስ የሞከሩት ቡድኖች ከ2006 ዓ.ም ጀምሮ እንደ ሀገር የማይናቅ ዋጋ ያስከፈለንን የነውጠኝነት እንቅስቃሴያቸውን አጧጡፈውት መቆየታቸው አይዘነጋም፡፡ በተለይም ደግሞ የቡድኖቹ አፍራሽ እንቅስቃሴ ግንባር ቀደም ሰለባ የመሆን ዕጣ የገጠመው የኦሮሚያ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች ነዋሪ ህዝብ ላልተፈለገ የህይወትና የንብረት ኪሳራ መዳረጉ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው ፡፡

በአዲስ አበባ ፊንፊኔ ዙሪያ የሚያጠነጥን የአንድ ሰሞን ተቃውሞ አቀነባብረው የኦሮሚያ ክልል ወጣቶችን በፌደራል ስርዓቱ ላይ ለማሳመጽ የተንቀሳቀሱት የኦ.ነ.ግ. እና መሰሎቹ ጉዳይ አስፈፃሚ ቡድኖች ያደረሱት ፈርጀ ብዙ ጥፋት ግንባር ቀደም ሰለባ የመሆን ዕጣ የገጠመውም ራሱ የኦሮሞ ህዝብ ስለነበር መንግስት በወቅቱ ይቅርታ ሲጠይቅ መደመጡን ማስታወስ ይቻላል፡፡ የያኔው የፀጥታ መደፍረስ ችግር እንዲከሰት ላደረጉት የጥፋት ኃይሎች የአመጽ ተግባር መቀስቀሻ አጀንዳ የሆናቸውን የአዲስ አበባው ማስተር ፕላን ጉዳይ፤ በተቻለ ፍጥነት ሕገ መንግስታዊ እልባት እንዲበጅለት ለማድረግ ያለመ ጥረት እንደሚጀመር የኢፌድሪ ጠቅላይ ሚኒስቴር ክቡር አቶ ኃ/ማርያም ደሳለኝ በህዝብ ተዋካዮች ምክር ቤት መድረክ ተገኝተው ሲናገሩ መደመጣቸውም ይታወሳል፡፡

    አሁን ላይ ቀዳሚ የመነጋገሪያ አጀንዳ ሆኖ የሚገኘው የኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ውስጥ ስለሚኖረው ኢኮኖሚያዊ፤ ፖለቲካዊና ማህበራዊ መብት የተደነገገ ረቂቅ ሕግ ተዘጋጅቶ የወጣውም መንግስት ያኔ የገባውን ቃል ወደ ተግባር ለመለወጥ ሲል ባሳየው ጥረት ነው ብሎ ማጠቃለል የሚቻል ይመስለኛል፡፡ ስለዚህ እርምጃውን ሊበረታታ እንደሚገባው መልካም ጅምር ወስጄ ወደተጫባጭ ተግባር ተተርጉሞ እናይ ዘንድ መሰራት በሚኖርባቸው ቀሪ የቤት ስራዎች ዙሪያ አንዳንድ ተጨማሪ ነጥቦችን ለማንሳት እሞክራለሁ፡፡

በዚህ መሰረትም፤ የሚኒስቴሮች ምክር ቤት ተወያይቶበት ወደ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲላክ የተደረገው ረቂቅ አዋጅ፤ ሐሙስ ሰኔ 22 ቀን 2009 ዓ.ም በዋለው የፓርላማ መድረክ ለውይይት ቀርቦ እንደነበርና የምክር ቤቱ አባላት የተለያየ አስተያየት እንደሰጡበት ጋዜጦች ላይ ተጽፎ አንብቤያለሁ፡፡  ስለሆነም፤ እኔ  ህዝቦች ተፈቃቅዶ ተፈቃቅሮና ተከባብሮ መኖር ጽኑ መሰረት የጣለውን ፌደራላዊ ስርዓት የሚደግፍ ዜጋ፤ የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልል ከአዲስ አበባ ከተማ መስተዳደር ላይ ሊያገኝ ስለሚገባው ልዩ ጥቅም፤ ሕገ መንግስታችን ሲረቀቅ ጀምሮ፤ የታመነበትን መብት ለማረጋገጥ የሚያስችል ዝርዝር መመሪያ ተዘጋጅቶ በዚህ መልኩ ይፋ መደረጉን ስሰማ ደስ ብሎኛል፡፡

በአዲሱ ረቂቅ ሕግ አማካኝነት ተደንግገው የወጡትን የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልል ህዝብ ከአዲስ አበባ ከተማ መስተዳደር ላይ ማግኘት ስለሚኖርበት ጥቅሞች የሚያትቱ ዝርዝር ነጥቦች ተገቢነታቸው የሚያጠያይቅ እንዳልሆነ ለመገንዘብ ያህን ያህልም ምርምር የሚያሻው ጉዳይ አይደለም ማለቴ ነው፡፡ ምክንያቱም፤ ይህን ማድረግ አስፈላጊ ሊሆን የሚችለው፤ ለኦሮሞ ህዝብ ጥያቄ ምላሽ መስጠት ስለሚጠበቅብን ብቻ አይደለምና ነው፡፡ ይልቁንም መላው የሀገራችን ብሔሮች፤ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዘመናት ትግላቸው የተቀዳጁትን ሕገ መንግስታዊ ድል ተከትሎ በተፈጠረው የጋራ መግባባት መሰረት የማያሻማ ምላሽ እንዳገኘ ከሚታመንበት የብሔራዊ ማንነት ጥያቄ አኳያ ሲታይ ጉዳዩ ለማንም ቢሆን ሊነፈገው የማይገባ የመብት ጥያቄ የተነሳበትና ተገቢ ምላሽ የሚያሻው መሆኑ ስለማያከራክር እንጂ፡፡

 መዲናችን አዲስ አበባ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ የምትገኝ የፌደራሉ መንግስት መቀመጫ ከተማ ናት ካልን፤ የታሪክ አጋጣሚው ባስከተለው ምክንያት ከመላው የሀገራችን ክፍል እየመጡ እዚህ መኖርን የመረጡት የኢትዮጵያ ብሔሮች፤ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ከኦሮምኛ ተናጋሪ ወገናቸው ጋር ይበልጥ ለመቀራረብ የሚችሉበትን አግባብ ማመቻቸት ለሁላችን የሚጠቅም እንጂ ማንንም የሚጎዳ የጎንዮሽ ችግር ያስከትላል ተብሎ አይታመንም፡፡ ስለዚህ እንደኔ ፤ የኢፌድሪ ሕገ መንግስት ላይ፤ የኦሮሚያ ክልል ከአዲስ አበባው የከተማ አስተዳደር ማግኘት ስለሚገባው ልዩ ጥቅም ታሳቢ ተደርጎ የተቀመጠውን ሀገራዊ የጋራ መግባባት ወደ ተግባር ለመቀየር ሲባል ሰሞኑን ይፋ የሆነው ረቂቅ አዋጅ የደነገጋቸው ዝርዝር ሕጎች ቅር ሊያሰኙት የሚችሉ ወገን ይኖራል የሚል እምነት የለኝም፡፡

ምክንያቱም ደግሞ፤ የከተማዋ ነዋሪ የብሔር ብሄረሰብ ህዝብ ላይ ምንም ዓይነት አሉታዊ ተጽዕኖ የሚያሳድር ካለመሆኑም ባሻገር፤ ይህ የሚደረገው የኦሮምኛ ቋንቋ ተናጋሪ ኢትዮጵያውያን ዜጎችን የመብት ጥያቄ ለመመለስ ሲባል ብቻ አይደለምና ነው፡፡ ይልቁንስ “ባንተ ላይ እንዲደረግብህ የማትሻውን ነገር ሁሉ በሌሎች ላይ አታድርግ” እንዲል ቅዱስ መጽሐፍ፤ ለማንኛውም የሀገራችን የብሔር ብሔረሰብ ህዝብ ቢሆን ከብሔራዊ ማንነቱ ጋር በተያያዘ መልኩ ለሚያነሳው የመብት ጥያቄ የማያሻማ ምላሽ መስጠት መቻል ጥቅሙ ሁሉንም ወገን በዕኩል መጠን የሚመለከት ትርፍ እንደሚያስገኝ ስለሚታመንበት ነው፡፡

ስለዚህም፤ የኢፌድሪ ሕገ መንግስት ላይ አስቀድሞ የተመለከተውን ስምምነት መሰረት ባደረገ መልኩ አሁን ይፋ የሆነው ረቂቅ አዋጅ ውስጥ የተካተቱትን ዝርዝር የሕግ ድንጋጌዎች ወደ መሬት አውርዶ ተግባራዊ በማድረግ ረገድ የበርካታ ባለድርሻ አካላትን የተቀናጀ ጥረት የሚጠይቅ ርብርብ ሊደረግበት የሚገባ ወሳኝ የቤት ስራ የመኖሩ ጉዳይ በስፋት እያነጋገረ ይገኛል፡፡ ይልቁንም ደግሞ የረቂቅ አዋጁ ዝርዝር ድንጋጌ ሕግ ሆኖ ከመጽደቁ በፊት፤ ለመላው የመዲናችን ነዋሪ ህብረተሰብ ስለሚያስገኘው ዘለቄታዊ ጥቅምና የትኛውንም ወገን የሚጎዳ ውጤት የማያስከትል ስለመሆኑም ጭምር የጋራ ግንዛቤ ላይ ለመድረስ የሚረዳ ውይይት ማካሄድ እንደሚያስፈልግ ያመላክታል፡፡

ይህን ጉዳይ የማስፈጸሙ ተግባርና ኃላፊነት በቀጥታ የሚመለከታቸውን የፌደራሉ መንግስት ባለድርሻ አካላት ጨምሮ፤ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና እንዲሁም ደግሞ የኦሮሚያ ክልል ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ረቂቅ አዋጁ ላይ በተደነገጉት የልዩ ጥቅም ማስጠበቂያ ሕጎች ዙሪያ ህዝቡን ለማወያየት ስለመታሰቡ ተመሳሳይ አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ ስለሆነም፤ የተባለውን የውይይት መድረክ ቶሎ ማካሄድና ከዚያም ረቂቅ አዋጁን ሕግ ሆኖ እንዲጸድቅ በማድረግ ለህዝቡ የቆየ ጥያቄ የተሟላ ምላሽ የሚሰጥ ተግባራዊ የአፈፃፀም ጥረት ማሳየት ግድ ይላል የሚለውን ቁልፍ ነጥብ ደጋግሜ አሰምርበታለሁ፡፡  

ስለዚህ ክልሉ ከአዲስ አበባ ከተማ መስተዳደር ላይ ማግኘት የሚገባውን ኢኮኖሚያዊ ጥቅማ-ጥቅሞች እንዲያገኝ ማድረግን ጨምሮ፤ በመዲናዋ ውስጥ ኦሮምኛን ሁለተኛ የስራ ቋንቋ እንዲሆን የማደረግና እንዲሁም ደግሞ የብሔሩ ተወላጅ የሆኑ ነዋሪዎች ህጻናት ልጆቻቸውን በአፋን ኦሮሞ ፊደል የማስቆጠር ፍላጎት እስካላቸው የከተማዋ አስተዳደር ፍላጎታቸውን የሚያሟላ ትምህርት ቤት መገንባት ይጠበቅበታል የሚለውን የረቂቅ አዋጁ ድንጋጌ ወደ መሬት ወርዶ አንድናይ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ተግባራዊ እርምጃ መውሰድ ይጀምሩ፡፡ በተለይም ደግሞ፤ የሀገራችን መዲና ከሆነችው አዲስ አበባ ከተማ ጋር በሚዋሰኑት የፊንፊኔ ዙሪያ ዞኖችና ወረዳዎች ውስጥ፤ ከሚኖሩ የኦሮሚያ ክልል አርሶአደሮች ላይ ለልማት ተግባር ተፈልጎ በሚወሰደው መሬት ምትክ ትርጉም ያለው የካሳ ክፍያ የመፈጸም-አለመፈጸም ጉዳይ እጅግ አንገብጋቢ መፍትሄ የሚያሻው ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡

ምክንያቱም፤ አዲስ አበባ ከተማ በርካታ ዓለም አቀፋዊ የፖለቲካ፤ የኢኮኖሚና እንዲሁም የማህበራዊ ጉዳዮችን የምታስተናግድ የአፍሪካ መዲና ከመሆኗ አኳያ፤ ለዚህ የላቀ ክብር በሚመጥን መልኩ ማደግ አለባት የሚለው ነጥብ ተገቢነቱ የማያጠያይቅ የመሆኑን ያህል፤ የፊንፊኔ ዙሪያ ነዋሪ አርሶአደሮችን ዘላቂ እጣ ፈንታ ታሳቢ ያደረገ የመሰረተ ልማት ተግባር መከወንም በዚያው ልክ ትኩረት ሊሰጠው ይገባልና ነው፡፡ ጉዳዩ፤ ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን መሰረት ላደረገ የመብት ጥያቄ ህገ መንግስታዊ ምላሽ የመስጠት አለመስጠት ጉዳይ እንጂ አብሮ መልማትንና ማደግን የማይፈልግ ህዝብ ስላለ የሚነሳ ቅሬታ እንዳልሆነም የተሟላ የጋራ ግንዛቤ መጨበጥ ይጠበቅብናል ባይ ነኝ ፡፡ አለበለዚያ ግን፤ ከኦህዴድ ይልቅ ለኦሮሞ ህዝብ መብትና ጥቅም የሚቆረቆሩ መስለው ለመታየት ከመሞከር ቦዝነው የማያውቁት ጠባብ ብሔርተኛ ቡድኖች በአንድ በኩል፤ በሌላ በኩል ደግሞ የፌደራሊዝም ሥርዓታችንን በጸረ የሀገር አንድነት ለመፈረጅ የሚቃጣቸው የትምክህት ኃይሎች፤ ዛሬም እንደተለመደው ሁሉ ረቂቅ አዋጁ ላይ አቃቂር ለማውጣት መንቀሳቀሳቸው እንደማይቀር ከወዲሁ መገመት አያዳግትም፡፡

በተረፈ ግን ይሄን ረቂቅ አዋጅ ሳይውል ሳያድር ወደ ተግባር እንዲቀየር በማድረጉ ረገድ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስትና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሥራ ኃላፊዎች፤ ከየትኛውም ባለድርሻ አካል ይልቅ፤ በተለየ የፖለቲካ ቁርጠኝነት መንቀሳቀስ ይኖርባቸዋል ተብሎ ይታመናል፡፡ ምናልባት ከአንድ በላይ የስራ ቋንቋ እንዴት ሊኖር ይችላል? የሚል ጥያቄ የሚያስነሱ ወገኖች ቢያጋጥሙም ደግሞ፤ ወደ ሌላው ክፍለ ዓለም ሄደን ምሳሌ ማፈላለግ ሳይጠበቅብን፤ እዚሁ አህጉራችን ውስጥ የምትገኘው ደቡብ አፍሪካ 11 የሥራ ቋንቋዎችን ጎን ለጎን የምትጠቀምበት አግባብ እንዳለ ማስታወስ ብቻ ይበቃል፡፡ ስለዚህ እኛም ብንሆን የኢኮኖሚያዊ አቅማችን ውስንነት አይፈቅድልን እንደሁ እንጂ፤ ከሁለትም በላይ ቋንቋዎችን ለፌደራሉ መንግስት የሥራ ቋንቋነት እንዳንጠቀም የሚያግደን ሌላ ምክንያት የሚኖር አይመስለኝም፡፡ በተረፈ ግን እኔ እዚህ ላይ አበቃሁ፡፡

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy