NEWS

መንግስት የሰብዓዊ መብት ቀውስን የሚያባብሱ ጉዳዮችን ለመፍታት ጥረት እያደረገ ነው-ኮሚሽኑ

By Admin

July 24, 2017

የሰብዓዊ መብት ቀውስን የሚያባብሱ የስራ አጥነትና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት መንግስት ጥረት እያደረገ መሆኑን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን አስታወቀ፡፡

በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት አያያዝ ላይ ያተኮረ የውይይት መድረክ በአሜሪካ ተካሂዷል፡፡

በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር አቶ ግርማ ብሩ የመድረኩ ዓላማ በአንዳንድ የኮንግረስ አባላት እና በሰብዓዊ መብት ተከራካሪ ቡድኖች፥ በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት አያያዝ ላይ ለሚቀርበው ጥያቄና ስጋት ትክክለኛውን ግንዛቤ ማስጨበጥ ነው ብለዋል፡፡

በውይይቱ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽነር ዶክተር አዲሱ ገብረእግዚአብሔር፥ በአሜሪካ ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ለተውጣጡ አካላት ስለ ኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት አያያዝ ገለፃ አድርገዋል፡፡

ዶክተር አዲሱ ኮሚሽኑ ገለልተኛ መሆኑን ገልጸው፥ ከጥቂት ወራት በፊት በሀገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች በነበረው ሁከትና ብጥብጥ የጠፋውን የሰው ህይወት በራሱ ተነሳሽነት ያደረገውን ምርመራ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማቅረቡን አስታውሰዋል፡፡

ኮሚሽነሩ መንግስት ተጠያቂ እንዲሆን መደረጉንም ተናግረዋል፡፡

በኢትዮጵያ ከጥቂት አስርት ዓመታት በፊት የባለሃብቶች እና የባለስልጣናት ሰብዓዊ መብት ብቻ ተከብሮ የብዙሃኑ መብት ግን ሲጣስ እንደነበር ነው የጠቀሱት፡፡

አሁን ላይ ግን የዜጎችን ሰብዓዊ መብት ማስከበር ከፖለቲካዊ እና ከኢኮኖሚያዊ ልማት ቅድሚያ ተሰጥቶት እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

በሀገሪቱ ዜጎች በጾታቸው፣ በእድሜያቸው፣ በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ደረጃቸው ልዩነት ምክንያት ሰብዓዊ መብታቸው የማይጣስበት ደረጃ ላይ መደረሱንም ጠቁመዋል፡፡

በሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች መካከል ሰላማዊ ግንኙነት እንዲኖር በሚሰራው ስራም የሰብዓዊ መብቶችን ማክበር ጉልህ ሚና እንዳለው መግባባት ላይ ተደርሷል ብለዋል፡፡

ተሳታፊዎች በበኩላቸው፥ በኢትዮጵያ ያሉ ለውጦች እና በሰብዓዊ መብት አያያዝ ዙሪያ የሚታዩ ችግሮች በመድረኩ ላይ መነሳታቸውን ገልፀዋል፡፡

በመድረኩ ላይ በመቶዎቹ የሚቆጠሩ የአሜሪካ ኮንግረስ አባላት፣ የህግ አማካሪዎች፣ አምባሳደሮች፣ የኢትዮ አሜሪካ ማህበረሰብ ተወካዮች እና ሌሎችም የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል፡፡

ምንጭ፡-ኢብኮ