Artcles

ሰላምና መረጋጋት—ለዘላቂ እድገት

By Admin

July 28, 2017

ሰላምና መረጋጋት—ለዘላቂ እድገት

                                                        ታዬ ከበደ

የሰላምና መረጋጋት ጠቀሜታ ዘርፈ ብዙ ነው። በተለይም እንደ ኢትዮጵያ ባሉ በማደግ ላይ ለሚገኙ አገራትሰላምና መረጋጋት ወሳኝ ጉዳይ ነው። በሰላምና መረጋጋት አገራዊ ምጣኔ ሃብትን ማሳደግ ይቻላል። በሌላ በኩልም የሰላምና መረጋጋት እጦት ዕድገትን ያቀጭጫል። በመሆኑም ህብረተሰቡ ለሰላምና መረጋጋት በቂ ትኩረት መስጠት ብቻ ሳይሆን ሰላምና መረጋጋትን ሊያሳጡን ከሚችሉ ጽንፈኛ ሃይሎች ራሱን መጠበቅም ይኖርበታል።

ፅንፈኛ ሃይሎቹ ዋነኛው ግባቸው በሀገሪቱ ሰላምና መረጋጋት እንዳይኖር፤ ማንኛውም መንግስታዊ ስራ በመደበኛ መልኩ እንዳይሰራ፤ የመማር ማስተማሩ ሂደት እንዲስተጓጎል፤ የንግድ ልውውጥና ግብይት እንዳይኖር፤ ህብረተሰቡ በሰላም ከቦታ ቦታ እንዳይዘዋወር፤ የትራንስፖርት አገልግሎት እንዲቋረጥ ወዘተ ለማድረግ እጅግ ከፍተኛ ጥረት ያደርጋሉ፡፡  

ከዚህ በተጨማሪም ብዙ ሺህ ዜጎች ሰርተው የሚያድሩበትን ፋብሪካዎች፣ የእርሻ ልማቶች፣ የመንግስት ቢሮዎች፣ የግለሰብ ድርጅቶች፣ በብዙ ሚሊዮን ብር የተገዙ ከባድና ቀላል ተሸከርካሪዎች፣ የህዝብ መገልገያ አምቡላንሶች እንዲወድሙ ሲሰሩ ተመልክተናል፡፡

የእነዚህ ሃይሎች እቅዳቸው ያተኮረው ሀገሪቱ ከድህነት ለመውጣት የጀመረችውን የመሰረተ ልማት ግንባታ ማሰናከል፣ ማጥፋት በተለይም የታላቁን ህዳሴ ግድብ ግንባታና ሌሎችንም ማስቆም ላይ ያተኮሩ እንደነበሩ የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው፡፡

ለዚህ ድርጊታቸው በግንባር የተሰለፉ ሃይሎችን በፋይናንስ፣ በስልጠና፣ በስምሪትና በአማካሪነት በቅርብ የሚረዷቸው እንደ ኤርትራ ዓይነት የሀገራችንን ሰላም ለማወክ ሁሌም የሚሰሩ ሀገሮች መሆናቸውንም እናስታውሳለን፡፡ ያ ሁሉ ተግባራቸውም አልፎ ዛሬ ለዘላቂ ሰላም በሚያበቃን ሰላምና መረጋጋት ውስጥ እንገኛለን፡፡

እንደሚታወቀው የኢትዮጵያ መንግስት መርሁ ሰላም ነው። በዚህም ኢንቨስትመንትንና ቱሪዝምን መሳብ ችላለች፡፡ በአንድ ሀገር ውስጥ ቱሪዝምም ሆነ ኢንቨስትመንት ሊስፋፉና ሊያድጉ የሚችሉት አስተማማኝ ሰላምና ለዘርፎቹ ምቹ የሆነ የፖሊሲ አቅጣጫ ሲኖር ነው። ከዚህ አኳያ ባባፉት 26 ዓመታት መንግስትና ህዝቡ የሀገሪቱን ሰላም በአስተማማኝ የሰላም መሰረት ላይ ለማቆም ባረደጉት ጥረት እንዲሁም መንግስት ለቱሪዝምም ሆነ ለኢንቨስትመንት ምቹ የሆነ የፖሊሲ አቅጣጫን በመከተሉ፤ ሁለቱም ዘርፎች ከፍተኛ የሆነ እመርታ አሳይተዋል።

በእነዚህ ዓመታት ውስጥ ሀገራችን የሰላም ተምሳሌት ተብላ ስትጠቀስ ኖራለች። ፈጣንና ተከታታይ ዕድገት በማስመዝገቧና የነገ ራዕይዋ ከወዲሁ እየታየ በመሆኑም የተለያዩ የውጭ ኩባንያዎች መዋዕለ ነዋያቸውን ሀገራችን ውስጥ በማፍሰስ አብረውን እየተረባረቡ ነው።

የኢትዮጵያ ሰላም ላለፉት 26 ዓመታት በጥሩ መሰረት ላይ የተገነባ በመሆኑ እንደ ደንቡሽት ቤት በጥቂት ጊዜ ውስጥ የሚፈራርስ አይደለም። ምንም እንኳን በየትኛውም ማህበረሰብ ውሰጥ ሰላም ያለው እሴታዊ ዋጋ የሚታወቅ ቢሆንም፤ የተረጋጋና አስተማማኝ ሰላም ያላቸው ሀገራት ሰላማቸው በጥቂት ጊዜ ውስጥ ሲደፈርስ ብሎም በትርምስና ሁከት ውስጥ ሲቆዩ የተመለከትናቸው አጋጣሚዎች ጥቂት አይደሉም።

ከእኛ ሀገር አንፃር ግን ሰላማችን ሲጀመር የተገነባው በህዝቦች ፅኑ ፍላጎት በመሆኑ በቀላሉ ሊናጋ የሚችል አይመስለኝም። ሆኖም ልክ እንደ አለፈው አንድ ዓመት ሰላማችን የመሸራረፍ ሁኔታ ሲያጋጥመው የሰላሙ ባለቤቶች የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በመሆናቸው በቀላሉ ከህዝቡ ጋር በመሆን የተለያዩ ድንጋጌዎችን በማውጣት መጠገን ይቻላል፤ እየተቻለም ነው። ይህም ወደ ሀገራችን መምጣት ለሚፈልጉ ቱሪስቶች አስተማማኝ ዋስትናን ይሰጣል።

ኢንቬስተሮችም በአዋጁ ዋስትናቸው በአስተማማኝ ሁኔታ የሚረጋገጥ ይመስለኛል። በስራቸው ላይ የሚፈጥረውም ተፅዕኖም ሊኖር አይችልም—ሰላምን ይበልጥ አስተማማኝ በማድረግ መዋዕለ ነዋያቸውን ይበልጥ እንዲያፈሱ ያነሳሳቸዋል እንጂ።

አገራችን ለወደፊቱ ብሩህ ተስፋ ካላቸው የአፍሪካ ሀገራት አንዷ እየሆነች ነው። ለዚህም በተለያዩ ወቅቶች ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋሞች ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ የኢኮኖሚ መሪ አገር እንደምትሆን ሲተነብዩ መጥተዋል። ይህም ኢትዮጵያ ውስጥ የዛሬ ሁለት ዓመት ገደማ በተወሰኑ አካባቢዎች የነበረው ሁከትና ብጥብጥ በሀገራችን የልማት ግስጋሴ ውስጥ ትርጉም የሌለው ተፅዕኖ አለመፍጠሩን የሚያሳይ ነው።

እርግጥ ሁከትና ብጥብጥ በነበረባቸው አንዳንድ አካባቢዎች የተፈጠረው የንብረት ውድመት ምንም ዓይነት አሉታዊ ተፅዕኖ አልፈጠረም ሊባል አይቻልም። ይሁንና ችግሩ ከመንግስትና ከህዝብ አቅም በላይ የሚሆን አይደለም።

በቀላሉ በመንግስትና በህዝቡ ጥረት ሊስተካከል የሚችልና በመስተካካል ላይ ያለ ጉዳይ ነው። የሰላም ማጣት ትንሽ ባይኖረውም፤ ከጠቅላላው የሀገሪቱ የልማት እንቅስቃሴ አኳያ ሲታይ፣ ችግሩ ያስከተለው የልማት መስተጓጎል እዚህ ግባ ሊባል የሚችል አይመስለኝም።

በመሆኑም በተለያዩ አካባቢዎች ተፈጥሮ የነበረው የሰላም እጦት በመንግስትና በህዝብ ቅንጅታዊ ስራ በቀላሉ በቁጥጥር ስር እየዋለ በመሆኑ እንዲሁም ዓለም አቀፉን የገንዘብ ተቋማት የመሳሰሉ ድርጅቶች ሀገራችን የምስራቅ አፍሪካ ቀዳሚ የኢኮኖሚ ባለቤት እንደምትሆን መተንበያቸው ኢንቬስተሮችን የሚያረጋጋ ይመስለኛል። እስካሁንም ድረስ የኢንቨስትመንት ፍሰቱ ተጠናክሮ መቀጠሉና ኢትዮጵያም በዘርፉ ቀዳሚ እንደምትሆን መተንበዩ የዚህ አባባል አስረጅ ነው ብዬ አስባለሁ።

እርግጥሰላም ከሌለ የህግ የበላይነት ብሎ ነገር የለም። መብት አይከበርም። መብት ሰጪና ነሺዎች ጥቂቶች ይሆናሉ። ጉልበት ያለው የህግ አስፈፃሚ ይሆናል። በሰላም ወጥቶ የመግባት ጉዳይም በህግና በስርዓት ሳይሆን በጉልበተኞች የሚወሰን ይሆናል።

ጉልበተኞቹ ከሚፈልጉት ጊዜና ዕውቅና ውጭ ማንም ሰው መነቃነቅ አይችልም። ህግ የበላይነቱን ስለሚነጠቅም በእነዚህ ሃይሎች እጅ ይወድቅና ሁሉም ነገር ምስቅልቅሉ ይወጣል። ሃይል ያለው ሁሉ በህገ ወጥ መንገድ ሰላምን አስጠባቂ ነኝ ሊል ይችላል።

ለነገሩ የሰላም እጦት ፈተናን የየትኛውም ሀገር ህዝብ ይገነዘበዋል። ያለ ሰላም አንዳችም ነገር መፈፀም እንደማይቻል የሁሉም ሀገር ህዝብ በሚገባ ያውቃል። አንድ ሀገር ሰላምን ለማስፈን ሰላምን ሊያረጋግጡ የሚችሉ አዋጆችን ሊያወጣ ይችላል። አዋጁ ግን በህዝቡ ይሁንታ ሊደገፍ ካልቻለ ተፈፃሚነቱ አጠራጣሪ ይሆናል።

እርግጥም ህዝቡ ያልደገፈው አዋጅ የታለመለትን ግብ ሊመታ አይችልም። ይህም የሰላም ዋነኛው ምሶሶና ማገር የዚያች ሀገር ህዝብ እንጂ አዋጅ ሊሆን እንደማይችል የሚያሳይ ነው። ለዚህም በሀገራችን ተከስቶ የነበረውን የሰላምና መረጋጋት እጦት በህዝቡ ፍላጎት ። ከሀገራችን ህዝብ በላይ የሰላምን ጥቅም በሚገባ የሚያውቅ ያለ አይመስለኝም። ላለፉት 26 ዓመታት በተፈጠረው አስተማማኝ ሰላም ውስጥ ያገኘውን የልማትና የዴሞክራሲ ትሩፋቶችን ጠንቅቆ የሚገነዘብ ነው። የእነዚያ ዓመታት ሰላምና መረጋጋቱ ለዘላቂ እድገቱ ያስገኙለትን ጥቅም ስለሚያውቅ ዛሬም ይሁን ነገ በሰላምና መረጋጋቱ ላይ አይደራደርም።