Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ስደተኞችን በመያዝ የተመሰገነች ሀገር

0 722

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ስደተኞችን በመያዝ የተመሰገነች ሀገር

                                                      ቶሎሳ ኡርጌሳ

የኢፌዴሪ መንግስት በባህሪው ህዝባዊ ነው። ለህዝብ ወገንተኛ ነው። ይህ መንግስት በህዝብ ውስጥ ተወልዶ በህዝብ ውስጥ ያደገ በመሆኑ የሚያከናውናቸው ማናቸውም ተግባራቱ የህዝብን ጥቅም ያማከለ ነው። ይህ ተፈጥሮአዊ ባህሪው በሀገር ውስጥ ብቻ የተገደበ አይደለም። የየትኛውንም ሀገር ህዝብ እንደ ህዝብ የሚያከብር ነው። ለህዝቦች ባላው አክብሮትም የቀጣናው ሀገራት ህዝቦች በጦርነትም ይሁን በሌላ አደጋ በሀገራቸው መኖር ሲያቅታቸው ወደ ኢትዮጵያ ሲሰደዱ የሚያደርገው ድጋፍ ከፍተኛ ነው። በዚህም ዓለም አቀፍ ከበሬታን መጎናፀፍ ችሏል።

ታዲያ ይህን ህዝባዊ ባህሪ ተመርኩዞ በሚከተለው የስደተኞች ፖሊሲ በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ውስጥ ከ850 ሺህ በላይ ስደተኞችን አቅፎ መያዝ ችሏል። በተለይም እንደ ኤርትራ ያሉና ህዝቦቻቸው በአምባገነናዊ ስርዓት ለስደት የሚዳረጉ ሀገሮች ስደተኞች እስከ ሁለተኛ ዲግሪ ድረስ እንዲማሩ በማድረግ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱ እንዲሰፋ እያደረገ ነው።

እንደሚታወቀው የኢትዮጵያና የኤርትራ ህዝቦች በአንድ ላይ ሲኖሩ የነበሩ ናቸው። ተጋብተዋል፤ ተዋልደዋል። በታሪክና በባህልም ጠንካራ ትስስር ያላቸው ናቸው። ከዛሬ 26 ዓመት በፊት በተካሄደው ውሳኔ-ህዝብ ሁለቱ ሀገራት ቢለያዩም፤ የህዝቦቹ ትስስር ግን የላላ አይደለም።

ኤርትራዊያን ህዝቦች ኢትዮጵያን እንደ ሀገራቸው ይቆጥሯታል። ኢትዮጵያዊያንም የኤርትራን ህዝቦች እንደ ሌላው ሀገር ህዝቦች አይመለከቷቸውም። ወንድሞቻቸውና እህቶቻቸው መሆናቸውን በሚገባ ይገነዘባሉ። መንግስትም ሆነ የኢትዮጵያ ህዝቦች እነዚህ ወንድምና እህት ህዝቦች በገዛ መንግስታቸው ስቃይ ደርሶባቸው ሀገራችንን በመጠለያነት በመቁመር፣ እኛን አምነው ሲመጡ ልንቀበላቸው የግድ ነው።

እኔ እስከሚገባኝ ድረስ መንግስት የጎረበቤት ሀገር ስደተኞች ወደ ሀገራችን ሲመጡ ተገቢውን ትብብር የሚያደርገው አንድም፣ ቀደም ሲል እንደጠቀስኩት ካለው ህዝባዊ ባህሪ በመነጨ፤ ሁለትም፣ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን እንደ መንግስት የማጠናከር ሃላፊነት ስላለበት ነው። ሆኖም አንዳንድ ወገኖች ይህን የመንግስት ጥረት በተሳሳተ መንገድ ሲመለከቱት ይስተዋላል—በተለይም ኤርትራዊያን የኢትዮጵያዊያንን ስራ እየተሻሙ ነው የሚል ትክክል ያልሆነን ምልከታ በማራመድ።

እኔ እስከማውቀው ድረስ መንግስት የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን የማጠናከር ተግባር ከመወጣት በስተቀር ከኢትዮጵያዊያን ተወስዶ ለኤርትራዊያን የተሰጠ ስራ የለም። ሊኖርም አይችልም። ምክንያቱም ኤርትራዊያን ኢትዮጵያዊያን ስላልሆኑ ነው። እዚህ ሀገር ውስጥ በአንዳንድ የተለዩ ጉዳዩች ካልሆኑ በስተቀር ኤርትራዊያን ከሌሎች ስደተኞች የተለየ መብት ሊኖራቸው የሚኖራቸው አይመስለኝም።

ያም ሆኖ በእኔ እምነት ኤርትራዊያኑ በቀለምና በቋንቋ ጭምር ከእኛ ጋር ስለሚመሳሰሉ ምናልባትም ብዥታው ከዚህ አኳያ የመነጨ ሊሆን ይችላል። ከዚህ ውጭ በህዝባዊ አስተሳሰብ የሚመራው መንግስት የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን ከማጠናከር ውጭ የኢትዮጵያዊያንን ስራ ለኤርትራዊያን የሚሰጥበት አንዳችም ምክንያት የለውም። ሊኖረውም አይችልም።

እንደ እውነቱ ከሆነ ህዝባዊ ባህሪን የተላበሰ ማንኛውም መንግስት የየትኛውም ሀገር ህዝብ ቢሆን ለህዝብ ሰላምና ደህንነት ውጭ የሚያስበው ነገር የለውም። ይህ በመሆኑም የሌሎች ሀገራትን ህዝቦች የራሱ ህዝቦች የሚያገኙትን ጥቅማ ጥቅሞች ሳይቀር እንዲያገኙ እያደረገ ነው።

የኤርትራ ህዝብ አምባገነኑ የኤርትራ መንግስት በሚያደርስበት ከፍተኛ ጫና እንዲሁም በገዛ ሀገሩ ውስጥ የመኖር ዋስትና በማጣቱ በየቀኑ ወደ ኢትዮጵያ ይጎርፋል። ከእነዚህ ውስጥ ወጣቶች፣ ሽማግሌዎች፣ አሮጊቶች፣ ህፃናትና ወታደሮች ተጠቃሽ ናቸው። የኢትዮጵያ መንግስትና ህዝብ ጠባቸው በገዛ ህዝቡ ላይ “ተኩሰህ ግደል” የሚል ፖሊሲን የሚከተለውና የቀጣናውን ሀገራት የሚያሸብሩ ኃይሎችን በጉያው ውስጥ አቅፎ አካባቢውን ከሚያተራምሰው ከአስመራው አስተዳደር ጋር እንጂ፤  ወንድም ከሆነው የኤርትራ ህዝብ ጋር ምንም ዓይነት ጠብ የለውም።

ይህ በመሆኑም ወንድም የሆነው የዚያች ሀገር ህዝብ እንደ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ እስከ ሶስተኛ ዲግሪ ድረስ እንዲማር እየተደረገ ነው። በእኔ እምነት ይህ የኢትዮጵያ መንግስትና ህዝብ አቋም፤ ምን ያህል የህዝቦችን መከራና ስቃይ እንደሚገነዘቡ፣ ምን ያህል የጎረቤታቸው ህዝቦች የሰላም እጦት የራሳቸው ጭምር መሆኑን እንደሚያምኑ፣ ምን ያህል ለጎረቤቶቻቸው መድህን ሆነውና የቀጣናው ህዝቦች ሀገራቸው ውስጥ ያላገኙትን ኢትዮጵያ ውስጥ ቢያገኙ በጋራ እናድጋለን ብለው በቁርጠኝነት እንደሚያምኑ የሚያሳይ ነው። ይህ ሁኔታ ደግሞ በየትኛውም ዓይነት መስፈርት የኢትዮጰያዊያንን ስራ መስጠት አይደለም—ህዝብ ለህዝብን የማቀራረብ ስራ እንጂ።

ታዲያ እዚህ ላይ የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት የጎረቤት ሀገራት ህዝቦችን ችግር የሚካፈሉት ድጋፍ እንዲደረግላቸው አስበው አለመሆኑን መገንዘብ ተገቢ ነው—ለህዝቦች ካላቸው ፅኑ ፍቅርና የአገራቱ ዜጎች በየአገራቸው የተፈጠረው ችግር እስኪረጋጋ ድረስ ኢትዮጵያን እንደ ሁለተኛ ሀገራቸው በመቁጠር ቢኖሩ ቀጣናውን የማረጋጋት አካል ሊሆን ይችላል ብለው ስለሚያስቡ እንጂ። በመሆኑም ሀገራችን ለውስጧ ችግሮች ቅድሚያ በመስጠት የቀጣናውን ሀገራት ህዝቦች የሰላም እጦትን ለማገዝ የምታደርገው ጥረት ከዚህ አኳያ መታየት ያለበት ይመስለኛል።

እንደሚታወቀው የኢፌዴሪ መንግስት በጥቂት ዓመታት ውስጥ ብቻ በቀጣናው ሀገራት መካከል ሰላም ሰፍኖ ልማታዊ ትስስር እንዲጎለብት ፈርጀ ብዙ ተግባራትን እያከናወነ ነው። ውጤትም እያገኘበት ነው። በኤሌክትሪክ ሃይል፣ በየብስ፣ በባቡርና በሌሎች የመሰረተ-ልማት አውታሮች ቀጣናውን ለማስተሳሰር የሚያደርጋቸው ጥረቶች ተጠቃሽ ናቸው። እናም መንግስት የቀጣናው ህዝቦች መቸገር አገራችን እንዲኖር የምትሻው ቀጣናዊ የልማት ትስስር እንዳይኖር ያግዳል ብሎ ስለሚያምንም  ጭምር ይመስለኛል።

ታዲያ ይህን የትስስር ሁኔታ ሲከውን በውጭ ጉዳይ ፖሊሲው ላይ በግልፅ እንዳስቀመጠው ሁለት መሰረታዊ ሁነቶችን ተከትሎ ነው—ውሰጣዊና ውጫዊ ሁኔታዎችን። መንግስት ሀገራዊ ህልውናን የማስጠበቁ ጉዳይ ሊሳካ የሚችለው ውስጣዊና ውጫዊ ሁኔታዎች ላይ መሰረት በማድረግ ብቻ እንደሆነ በማመን ለተግባራዊነቱ ሲንቀሳቀስ መቆየቱ ይታወቃል።  

በከፍተኛ ኋላ ቀርነትና የድህነት አዘቅት ተዘፍቃ ለቆየችው ሀገራችን ፈጣን የኢኮኖሚ ልማት፣ የዴሞክራሲያዊ ግንባታና ሰላምን የማረጋገጥ የህልውና ጉዳይ መሆኑን በመገንዘብ አቅጣጫዎች በማስቀመጥ ወደ ተግባር ተሸጋግሮ ላለፉት 26 ዓመታት ተጉዟል። በተለይም ባለፉት 15 ዓመታት በመላ ሀገሪቱ አስተማማኝ ሰላም የማስገን፣ ፈጣንና ተከታታይ ልማትን እውን የማድረግ እንዲሁም የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ባህል ግንባታ ስር እንዲሰድ ምቹ ምህዳርን የመፍጠር ተግባሮችን ከውኗል።

መንግስት ለአገራችን ሰላምና ልማት እውን መሆን ከፍተኛ ጥረት እንደሚያደርግ ሁሉ፤ የጎረቤት ሃገሮች ሰላምና ልማትም እንዲፋጠን ካለው ፅኑ እምነት በመነጨ በጋራ ማደግ ቀዳሚ ነው ብሎ ያምናል። ምክንያቱ ደግሞ የአገራችን ሰላምና ልማት ለአካባቢያችን ዕድገት ድርሻ እንዳለው ሁሉ፤ የአካባቢያችን ሰላምና ልማትም ለሀገራችን ዕድገት መፋጠን የሚያበረክተው አዎንታዊ አስተዋጽኦ የላቀ እንደሚሆን በፅናት ስለሚያምን ነው።

ታዲያ ይህ እንዲሆን መንግስት ከራሱ አገር ህዝቦች አልፎ ለአጎራባች አገራት ህዝቦች ማሰብ ይኖርበታል። በተለይም የሀገሪቱን የውጭ ግንኙነትና በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላትን ስፍራ ለማጎልበት ሰፊ ጥረት አድርጓል።

በዚህም ኢትዮጵያ ለሀገሪቱም ሆነ ለአካባቢው የተረጋጋ የፖለቲካ ሂደት እንዲኖር ግጭቶችና ውዝግቦች በሰላማዊ ጥረት እንዲፈቱ ብቻ ሳይሆን፤ የቀጣናውን ዜጎች በስደተኝነት ተቀብላ በማስተናገድ ጊዜያዊ እፎይታን እንዲያገኙ ትብብር በማድረግ ላይ ትገኛለች። በዚህ ውጤታማ ጥረቷም የዓለም ህዝቦች አመኔታን አግኝታለች።

ይህ ስደተኞችን የመያዝ ተግባሯም አይቋረጥም። መንግስታችን ህዝባዊ፣ ህዝባችንም ቢሆን እንግዳ ተቀባይ በመሆኑ ወደፊትም ተጠናክሮ ይቀጥላል። ምንም እንኳን የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት ምስጋና ለማግኘት ሲሉ ስደተኞችን የሚቀበሉ ባይሆኑም፤ እስካሁን ባደረጉት ወደር የሌለው ስደተኞችን የመቀበል ተግባራቸው ምስጋና የተቸራቸው በሚከተሉት ህዝብን የሚደገፍ የስደተኞች ፖሊሲ መሆኑን ግንዘቤ መያዝ ይገባል።     

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy