Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

በማምረቻ ኢንዱስትሪው የአፍሪካ ማዕከል እንድንሆን የተያዘው ዕቅድ

0 314

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

በማምረቻ ኢንዱስትሪው የአፍሪካ ማዕከል እንድንሆን የተያዘው ዕቅድ

                                                       ዘአማን በላይ

የኢፌዴሪ መንግስት ሀገራችንን ከግብርና መር ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ለማሸጋገር ከፍትኛ ርብርብ እያደረገ ነው። በተለይም ሀገራችን በማምረቻ ኢንዱስትሪው ዘርፍ የአፍሪካ ማዕከል ለመሆን በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ የጣለውን ግብ ለማሳካት በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች የኢንዱስትሪ ፓርኮችን እየገነባ ነው። በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ላይ እንደተገለፀው ሀገራችን የመጀመሪያ ደረጃ መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገራት ተርታ እንድትሰለፍ የኢኮኖሚያዊ መዋቅራዊ ለውጥ መመዝገብ አለበት። ለዚህም የማምረቻ ኢንዱስትሪው ዘርፍ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶታል።

ኢኮኖሚያዊ መዋቅራዊ ለውጡን ለማስጀመር የማምረቻ ኢንዱስትሪው በየዓመቱ ቢያንስ የ24 በመቶ ዓመታዊ አማካይ ዕድገት ማስመዝገብ ይኖርበታል። በዚህም በ2012 ዓ.ም የማምረቻ ኢንዱስትሪው በአጠቃላይ ኢኮኖሚው ያለውን ድርሻ ወደ ስምንት በመቶ ከፍ ለማድረግ ዕቅድ ተይዟል። ይህም የማምረቻ ኢንዱስትሪው ድርሻ አሁን ካለበት በአራት እጥፍ በማሳደግ በ2ዐ17 ዓ.ም ወደ 18 በመቶ እንዲደርስ ምቹ መደላድል ይፈጥራል።

የማምረቻ ኢንዱስትሪው የኤክስፖርት ሚና ከፍተኛ ነው። እንደሚታወቀው በአሁኑ ወቅት የዘርፉ ምርቶች ጠቅላላ የኤክስፖርት ገቢ ያላቸው ድርሻ ከጠቅላላው የኤክስፖርት ገቢ ውስጥ ከ1ዐ በመቶ የማይበልጥ ነው። ሆኖም በዕቅዱ መሰረት በ2012 ላይ ወደ አምስት ቢልዮን ዶላር ገቢ እንዲያስገኝ ለማድረግ ታስቧል። ይህ ድርሻም ወደ 25 በመቶ ከፍ ለማድረግና በ2017 ዓ.ም 40 በመቶ ለማድረስ ግዙፍ ዕቅድ ተቀምጧል።

ሌላው የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ለውጡ አመላካች የሚሆነው በሚቀጥሉት ዓመታት ወደ ማምረቻ ኢንዱስትሪ የሚደረገው የሰው ሃይል ሽግሽግ ነው። ይህም በአሁኑ ወቅት በመካከለኛና በከፍተኛ የማምረቻ ኢንዱስትሪዎች የተሰማራውና ከ350 ሺህ የማይበልጠውን የሰው ሃይል በቀጣዩቹ አስር ዓመታት በአራት እጥፍ እንዲጨምር ለማድረግ ታስቧል። ይህም አንድ ነጥብ አምስት ሚሊዩን ዜጎች የስራ ዕድል እንዲያገኙ እድል የሚፈጥር ነው። እነዚህን የማምረቻ ኢንዱስትሪውን ልማታዊ ፋይዳዎች ከግምት ውስጥ በማስገባት መንግስት ብርቱ ርብርብ እያደረገ ነው።

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ማንኛውም ሀገር በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊና በፖለቲካ መስኮች ሁለንተናዊ በሆነ መልኩ ተጠቃሚ ያደርጋል። ልማቱ እንደ ጨርቃጨርቅ በመሳሰሉ ቀላል የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ በርካታ የስራ ዕድል የሚፈጠር እና የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትንም በስፋት መሳብ የሚችል ነው።

ይህም የህዝቦችን ተጠቃሚነት ከፍ የሚያደርግ ከመሆኑም በላይ፤ የውጭ ምንዛሬ በማስገኘት ረገድም የራሱን ሚና ይጫወታል። ከዚህ ጎን ለጎንም የቀላል ማኑፋክቸሪንግ ልማቱን ያፋጥናል፤ ከተሞችን ወደ ላቀ የዕድገት ደረጃ የማሸጋገር ብሎም አዳዲስ ከተሞች እንዲፈጠሩና በዚያኑ ልክም የመልካም አስተዳደር ችግሮች እንዲቀረፉ የራሱን አዎንታዊ ሚና ይጫወታል።

በሀገራችን የተተለመው የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ፕሮግራም መሬትን ውጤታማ በሆነ መልኩ ለልማት ስራ ብቻ እንዲውል የሚያደርግና የኪራይ ሰብሳቢነት በር የሚዘጋ መሆኑን መገንዘብ ተገቢ ይመስለኛል። እርግጥም ልማቱ ለመሰረተ ልማት ግንባታ የሚወጣውን ወጪ በተቀናጀ መልኩ መጠቀም የሚያስችልና ለአካባቢ ጥበቃ ሥራ ትኩረት የሚሰጥ በመሆኑ ኢንዱስትሪዎችን በእሴት ሰንሰለት እርስ በርስ ስለሚያስተሳስር ብክነትን የሚቀንስና የኪራይ ሰብሳቢነትን በመዋጋት ረገድ ሚናው የጎላ ነው።

ከዚህ በተጨማሪ በውጭ ሀገር ባለሙያዎች የሚከናወኑ ስራዎችን በሂደት በሀገር ውስጥ የሙያው ባለቤቶችና በሀገር በቀል ተቋማት አማካኝነት እንዲከናወኑ መሰረት ይጥላል። ይህም የዕውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲረጋገጥ ሰፊ ዕድልን ይፈጥራል።

በመላ ሀገሪቱ የሚገነቡ የኢንዱስትሪ ፓርኮች የተለያዩ መሠረተ ልማቶችን ማሟላት የግድ ይላቸዋል። በዘመናዊ አሰራር ውስጥ የሚታወቀውን የአንድ መስኮት አገልግሎት አሰጣጥ አሰራርንም ይከተላል።

በማንኛውም የኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ የሚገነቡት ኢንዱስትሪዎች የሚጠቀሙባቸው የጋራ መገልገያዎች፣ መጋዘን፣ የብክለት ማጣሪያና ማስወገጃ፣ የጥናትና ምርምር ማዕከል፣ መኖሪያ ቤቶች፣ የቢሮ መገልገያ ህንፃዎች፣ የሕክምና ማዕከል፣ ትምህርት ቤት፣ ማህበረሰብ አቀፍ የፖሊስ አገልግሎት፣ መዝናኛዎች፣ አረንጓዴ ቦታዎችና ለኢንዱስትሪዎቹ የሚያገለግሉ መሰል ተቋማትን የሚያካትቱ አገልግሎት መስጫዎች ይኖራቸዋል። ይህ በመሆኑም ፓርኩ በውስጡ የተገነቡት ኢንዱስትሪዎች ደህንነታቸው ተጠብቆ በጤናማ ሁኔታ የእርስ በእርስ ውድድር የሚያደርጉበት አካባቢ ነው ማለት ይቻላል።

በዚህ መሰረትም መንግስት በአሁኑ ወቅት በመላ ሀገሪቱ በራሱ ወጪ እየገነባቸው የሚገኙት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ኢትዮጵያ በማምረቻ ኢንዱስትሪው ዘርፍ የአፍሪካ ማዕከል እንድትሆን የነደፈውን ዕቅድ ለመሳካት ጥረት እያደረገ ነው።

በዚህም የልማት ዕቅዱን ግብ ለማሳካት በግል ባለሃብቱ ከሚገነቡ የኢንዱስትሪዎች ባሻገር በመንግስት ሙሉ ወጪ አስፈላጊ መሰረተ ልማቶች የተሟሉላቸው 13 የኢንዱስትሪ ፓርኮች እና 17 የግብርና ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎች  በመላ አገሪቱ  በመገንባት ላይ  ይገኛሉ።

ታዲያ ይህን የመንግስት ጥረት ለማብራራት የሃዋሳ የኢንዱስትሪ ፓርክ ሁነኛ ማሳያ የሚሆን ይመስለኛል። በሃዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ 18 ዓለም ዓቀፍ ኩባንያዎች በፓርኩ ከትመው ስራ ጀምረዋል። ምርትም እየላኩ ነው። ከዚህ የኢንዱስትሪ ፓርክ ብቻ ሀገራችን በዓመት እስከ አንድ ቢሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሬ ታገኛለች።

የሃዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ በልማቱ የተነሱ 186 አባዎራዎች ከክልሉ መንግስትና ሃዋሳ ከተማ መስተዳድር ጋር በመሆን ምትክ የመስጠት ስራ ተከናውኗል። በልማቱ ለተነሱ የህብረተሰብ ክፍሎች ከተማ አስተዳደሩ ወደ 200 የሚጠጉ ቤቶችን ገንብቶ ሰጥቷል። በሃዋሳ ከተማ የሚገኙ ሰፊ ቦታ ያላቸውና ቤት የሚያከራዩ ግለሰቦችም መንግስት ባቀረበው የብድር አቅርቦት ተጠቃሚ ሆነው ቤት የመገንባት ስራውን እንዲጀምሩ ተደርጓል።

እነዚህ ተግባራት የሚያመላክቱት ነገር ቢኖር ለልማት የሚነሱ ዜጎች ተመጣጣኝና ተጠቃሚ በሚያደርጋቸው ሁኔታ ተገቢው ምትክና ካሳ በመንግስት በኩል ተፈፃሚ እየሆነላቸው መሆኑን ነው። ይህ ሁኔታም ዜጎች ለልማት ተነሺ ቢሆኑም፣ ከሚካሄደው ልማት በየደረጃው ተጠቃሚ መሆን እንደሚችሉ የሚያሳይ ይመስለኛል።

ርግጥ ስራዎቹ በሀገራችን ጅምር በመሆናቸውና የሚጠይቁትም በጀት ግዙፍ በመሆኑ የተወሰኑ ተግዳሮቶች ሊያጋጥሟቸው ይችላል። በተለይም ቀደም ሲል ዘላቂ የፋይናንስ ምንጭ በበቂ ሁኔታ አለመኖር፣ የመሰረተ ልማት አቅርቦት ችግርና ሁነኛ የግል ባለሃብቶችን በስፋት መሳብ አለመቻል ችግሮች ይስተዋሉ ነበር ነበር።

ሆኖም እነዚህን ችግሮች ከሞላ ጎደል የተሻለ አቅም በመፍጠር፣ የገንዘብ ምንጮችን በማፈላለግና ሁሉም ዜጋ የበኩሉን እገዛ በማድረጉ መፍታት እየተቻለ ነው። ይህም በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ቀዳሚዋ የኢንቨስትመንት መዳረሻ እንድትሆን እያደረጋት ይገኛል። እመርታውም በቀጣዮቹ ዓመታት ሀገራችን በማምረቻ ኢንዱስትሪው ዘርፍ የአፍሪካ ማዕከል እንድትሆን ለማድረግ የተያዘውን ዕቅድ እንደምታሳካ ጠቋሚ ይመስለኛል።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy