CURRENT

“በር የሌለው ቁልፍ “

By Admin

July 28, 2017

ሚሰባህ አወል

የሐምሌ ክረምት በተለይ ጠዋት ጠዋት እኝኝ.. እያለ ከሞቀው እንቅልፋችሁ አትነሱ እስከማለት ደርሷል፡፡ ሁሌም ዝናብ የማያጣውና ሌላው አካባቢ ሲዳምን ዶፍ የመጣል አባዜ ያተጠናወተው አስኮ እና አካባቢው ዛሬም ሰማዩን አጨፍግጎ እንደልማዱ አኩሩፏል፡፡

አንድ ወዳጄ አስር ዘጠና የጋራ መኖሪያ ቤት ደርሶት እባክህን መጥተህ እይልኝ ካለኝ ዓመት ሊሞላው ጥቂት ቀናት ቀርተውታል፡፡

ከዚህኛው የእረፍት ቀኔ ልዘለው አልፈለኩም፡፡ በፈረንጅኛ ይሁን በአራዳ አጠራሬ ለይቼ ባላውቀውም “ሼም” የሚለው ቃል አስገድዶኝ በጭጋጋማው ጠዋት ወደ ወዳጄ ቤት ለማዝገም ተነሳሳሁ፡፡

ሀምሌም እያለቀሰ እኔም እየተነጫነጭኩ ከሰፈሬ ወጣሁ፡፡ ጉዞ “ከአስኮ አወሊያ” አካባቢ ወደ “ኮየፈጬ ኮንዶሚኒየም” ርቀቱ ሲታሰብ ተስፋ የመቁረጥ ስሜት ያጭራል፡፡

“ሼሙ” አሁንም ብልጭ አለ፡፡ ለወዳጄ ደውዬ ለመምጣት ጉዞ መጀመሬን ሳወጋው ደስታው ከፍ ያለ ነበር!! የፒያሳን ታክሲ አስቆምኩና በረርኩ፡፡ ከሰላሳ ደቂቃ በሁዋላም ፒያሳ ላይ ተገኘሁ፡፡ ኮዬ አማራጩ መገናኛ መሆኑን የጠቆመኝ የወዳጄን አቅጣጫ ተከትዬ 10 ቁጥር አንበሳ አውቶቢስ ላይ ተሰቀልኩ፡፡

የወቅቱ የቀን ገቢ ግብር አጀንዳ በሰፊው የሚነገርበት አውቶብሱ ሌሎችንም መሰረታዊ የማህበራዊ ህይወት ገጠመኞችን እየሰማን ጉዟችንን አገባደን መገናኛ ደረስን ፤ አሁንም ጉዞው አልተጠናቀቀም፡፡

በከተማዋ በተለያዩ አካባቢዎች እግረኞች ቅድሚያ የማግኘት መብታቸው በአሽከርካሪዎች እየተነፈጉ አደጋም ሲገጥም ይስተዋላል፤በመገናኛ ግን እግረኞች በአሽከርካሪዎች ሲለመኑ ይታያል ቅድሚያ ለማግኘት!!፡፡

በቅርቡ በከተማዋ የትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት ከተሰማሩት የብዙሀን ትራንስፖት አገልግሎት ከሚሰጡት አውቶቢሶች መካከል ቢጫው አልያንስ “ቱሉ ዲምቱ” “ኮዬ” ሲል ዘው አልኩ፡፡ አውቶቢሱ ለደቂቃዎች ቆሞ የየኔ ቢጤዎችን ዜማዊ መልእክትና የማስቲካና ሶፍት ሻጮችን ጥሪ ተቀብሎ ረጅሙን ጉዞ ተያያዘው፡፡

ከመገናኛ ጥቂት ተጉዞ በቀለበት የፍጥነት መንገድ ላይ የገባው አልያንስ በሚያስፈራ ፍጥነቱ ገርጂን ጎሮንና የመሳሰሉ ቆየት ያሉና አዳዲስ ሰፈሮችን አቆራርጦ ኮዬ አደባባይ ደረሰ፡፡

አንድ ባልተት  ኮዬ ፈጨን ሲገልጹ  “ኮዬ ራሱ ብቻውን ድሬዳዋን ያክላል እኮ!” ነበር ያሉት፡፡ ኮዬ እስከምደርስ እቺ ! ግነት; ነበር ያልኩት ፤ እውነታው ግን ድሬን በመጠኑ እንጂ በጥልቅ ባላውቃትም “ኮዬ ፈጬ” ራሷን የቻለች አንድ ከተማ ሆና አገኘኋት፡፡

ለዓይኔ እስኪታክተኝ ወደ ኮንዶሚኒየሞቹ አስተዋልኩ በተዘረጋው ሰፊ መስክ ላይ በርካታ የአስር ዘጠና ፣የሀያ ሰማንያ እና አርባ ስልሳ ኮንዶሚኒየም ቤቶች በሚያምር ሁኔታ ተደርድረው ይስተዋላሉ፤ ርቀቱ ፣ ስፋቱ ፣ ዓየሩ በጣም ይማርካል ኮዬፈጨ፡፡

ትልቅ የለውጥ ጉዞ ጅማሬ መሆኑ ማሳያ ነው፡፡ በፍጥነት መንገድ ላይ ሆነው ሲመለከቱት በቅርብ ርቀት የደመቀ ምርጥ ከተማ እንደሚሆን በእዝነ ልቦናዎ ይታይዎታል!!

ቀደም ብለው ተገንብተው ለአገልግሎት የበቁት እነጀሞ አንድ እና ሁለት እንዲሁም ሌሎች የኮንዶሚኒየም ሳይቶች  ሁኔታን “ያየ የነኮዬ ፈጬም” ሆነ “ቱሉ ዲምቱ” ኮንዶሚኒየሞች ብሩህ ተስፋ ያጓጓል፡፡

ከኮዬ አደባባይ ንፋስ ስልክ ወደተባለው አካባቢ በሶስት ብር ባጃጅ በርሬ ደረስኩ፡፡ ወዳጄ በጉጉት ሲጠብቀኝ አገኘሁትና በስተግራ ወዳሉት የ10/90 ኮንዶሚኒየም ቤቶች አቀናን፡፡

ወደ ወዳጄ ቤት ከመሄዳችን በፊት ብሎ በጥቁሩ ጭቃ ሜዳ ላይ ወደ ተቀመጠው የመሰረት ድንጋይ አመራኝ፡፡ በከተማዋ ከንቲባ በ2008 ዓመተ ምህረት መመረቁን የሚገልፅ ጹሁፍ ነበር፡፡

ስለአካባቢው ንጹህ አየር እያወጋን ወደ ወዳጄ ቤት አቀናን ባሻ ወልዴ ችሎት የነበረባትን ያቺን ጠባብ ክፍል እያስታወስን እያወጋን የፎቅ ደረጃ መውጣት ጀመርን፡፡

በፊት የነበረበት ጠባብ የጭቃ ቤት ዋጋዋ ሰባት መቶ ብር ብትሆንም አሁን ያገኘውን ኮንዶሚኒየም የውስጥ ክፍል ታክላለች፡፡

ወዳጄ ለኔ አቀባበል የገዛውን ምሳና ለስላሳ አቅርቦ እየተገባበዝን ወጋችንን ቀጠልን፡፡

መንግስት የህብረተሰቡን ኑሮ ለማሻሻል በሀገሪቷ ፍትሃዊ የሀብት አጠቃቀም እንዲሰፍንና ለሀገሪቷ እድገት በማሰብ ይህን ፕሮጀክት ተግባራዊ ማድረጉ ጥሩ ጅማሮ ቢሆንም ፕሮጀክቶቹን ዘለቅ ብለህ ስታያቸው “ውስጡን ለቄስ” ይሉት ይትበሀል በተግባርና በስፋት ይታይበታል፡፡

ከወዳጄ በታች አንደኛው ፎቅ ላይ የደረሳቸው አንዲት ባልቴት ባይገቡበትም ሁሌም እየመጡ ያጸዳዱታል፤ ታድያ እንዴት ነው! ለሚላቸው ሁሉ “ተመስጌን ላይ ላዩን ጥሩ ነው ውስጥ ውስጡን ቁስል ነው” እያሉ ማንጎራጎር ይቀናቸዋል ሲል ነበር ያወጋኝ፡፡

ወዳጄ እንደነገረኝ ቤቱ ተመርቆ ቁልፍ ከተረከበ በኋላ ለቤቱ የውስጥ ግንባታ ብቻ ከ20 ሺህ ብር በላይ ለማውጣት መገደዱን ነበር ያጫወተኝ፡፡ ለኔ ሻይ ቡና ለመጋበዝ እንኳ የመብራት አገልግሎት ተጠቃሚ አለመሆኑን ወዳጄ የነገረኝ ሲሆን እኔም ተዘዋውሬ እንዳየሁት ምንም አይነት ቆጣሪ የገባለት ቤት አላየሁም፡፡

የተሟላ ሆኖ እንደተመረቀ ሚዲያዎች ሲያራግቡት እገረም ነበር የሚለው ወዳጄ አንድም የአስር ዘጠና ቤት የውሃም ሆነ የመብራት ቆጣሪ አላገኘም ነው ያለኝ፡፡ የፎቁ መጨረሻ ወለል ላይ ያለው ወዳጄ የኮርኒስ ፣ የውስጥ በሮች ፣ የዋናው በር በአግባቡ አለመገጠምና የውስጥ ቀለምን ጨምሮ የፊኒሺንግ ስራ ናላውን አዙሮት እንዳጠናቀቀው ነው ያወሳኝ፡፡

ገና ስመጣ በብሩህ አዕምሮዬ ያየሁት አግራሞት በእነዚህ ጥቃቅን ችግሮች ድባብ ተሸፍኖ በውስጤ ጥላሸት  ማጥላቱ “አይጥ ወልዳ ወልዳ …” የምትለዋን  አባባል  አስታወሰኝ፡፡  ሀምሌ አሁንም ማካፋቱን ቀጥሎአል በወዳጄ ጨዋታ ተመስጬ ጊዜው መንጎዱን አላወኩም ነበር ፤ የረጅም ርቀት ተጓዥ መሆኔን በመገንዘብ በጊዜ ወደ ከተማ ለመመለስ ተነሳሁ፡፡

ጓደኛዬም እስከመሳፈሪያው ሊሸኘኝ ተያይዘን ወጣን ካፊያው ያን ጥቁር አፈር አጨቅይቶት በየት እንለፍ!! ለነገሩ በየቦታው የተደፉ ጠጠሮች የወደፊቱን ተስፋ ከማሳየት ውጭ  ምንም ጥቅም እንደሌላቸው ለመረዳት ጊዜ አልወሰደብኝም፤እየዘለልንና በጭቃ እየተጨማለቅን ጉዞአችንን ቀጠልን፡፡

በወዳጄ ብርታት ቦታ እየመረጥን አስፋልቱ ላይ እንደምንም ደርሰን ተሰነባበትን፡፡ ወዳጄ ወደዛ ጥቁር ጭቃ ሲያዘግም ባለ ሶስት ብርዋ ባጃጅ እኔን ይዛ ወደ ኮዬ አደባባይ ፈረጠጠች፡፡

በአንድ ፋብሪካ ተቀጥሮ የሚሰራ ወዳጄን እያሰብኩ በመሰረተ ልማት አለመሟላት የአካባቢው ህብረተሰብን ስቃይ በእዝነ ህሊናዬ እያየሁና ነገም ሌላ ቀን ነው የሚለውን የተለመደ ማጽናኛ ለራሴ እየመገብኩ ጉዞዬን ቀጠልኩ፡፡

ወዳጄ በአንድ ፋብሪካ በባለሙያነት ሲሰራ ለረጅም ጊዜያት ያጠራቀማትንና የተበዳደረውን አውጥቶ  ውስጡን የማስተካከል (የፊኒሺንግ) ስራውን  ማከናወኑንም አውቃለሁ፡፡ አስር ዘጠና የጋራ መኖሪያ ቤት  በአነስተኛ ገቢ የሚተዳዳሩ ዜጎች የሚገቡበት መሆኑ እየታወቀ ያላለቀና ያልተስተካከለ ቤት ማስረከቡ ምን የሚሉት ፈሊጥ ይሆን? እያልኩ ጉዞዬን ቀጠልኩ፡፡

“ያለ ውሃ ፣ያለ መብራት” እንዴት ገባችሁ ብዬ የጠየቅኩት ወዳጄ “ ያለበርም ቁልፍ የተረከበ አለ”ሲል ነበር የመለሰልኝ  “ያለ በር ቁልፍ” እስኪ አስቡት ምኑን ሊቆልፉበት ይሆን የተረከቡት? እያልኩ ጥያቄውን ለሚመለከተው አቅርቤ ፅሑፌን ቋጨሁ።  ቸር እንሰንብት!