Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

በተቀጣሪ ዜጎች ጫንቃ ላይ የመኖር ፍላጎት

0 1,004

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

በተቀጣሪ ዜጎች ጫንቃ ላይ የመኖር ፍላጎት

ኢብሳ ነመራ

ሰሞኑን የኤርትራ ሚዲያዎችና ከኤርትራ መንግስት በሚሰጣቸው ኢትዮጵያን የማተራመስ የፕሮፓጋንዳ አቅጣጫ የሚሰሩ ሚዲያዎች ላንቃቸው ተከፍቷል። ተዘግቶ የከረመውን ላንቃቸውን እንዲከፍቱ ያነቃቸው በቅርቡ ከነጋዴዎች የእለት ገቢ ትመና ጋር በተያያዘ የተፈጠረው ቅሬታና መደናገር ነው። ይህን አጋጣሚ ኢትዮጵያን ለማተራመስ ዓላማ ለማዋል ተዘግቶ የዛገ ላንቃቸውን እንደምንም አላቀው ውዥንብር እየተፉ ነው። ህዝባዊ እምቢተኝነቱ ቀጥሏል፣ ጀግናው የምንትስ ከተማ ህዝብ የመከላከያ ሰራዊት ተሽከርካሪን አቃጠለ፣ የመንግስት ታማኞች በተኮሱት ጥይት ሁለት ሰዎች ተገደሉ . . . ማለቱን ተያይዘውታል። በባለቤትነትና በቀጥታ አቅጣጫን በመቀበል በኤርትራ መንግስት ቁጥጥር ስር የሌሉ፣ ግን የኤርትራ ተላላኪዎችን ስሜት የሚጋሩ አንዳንድ “ጋዜጠኞች” የሚሰሩባቸው ሚዲያዎችም አድማው ቀጥሏል፣ ምንትሴ ቀን አስቆጠረ . . . በማለት ሁኔታውን ያለወጉ በማራገብ ለኤርትራ የትርምስ ስትራቴጂ አስፈጻሚዎች ያላቸውን አጋርነት ለማሳየት ያህል ሲንጣጡ ሰንብተዋል።

ከነጋዴዎች የእለት ገቢ ትመና ጋር ተያይዞ ከተፈጠረው ቅሬታና መደናገር ጋር የተያያዙ ጉዳዮች በሚዲያ መዘገብ የለባቸውም የሚል አቋም የለኝም። የህዝብ ጉዳዮች በመሆናቸው ሊዘገቡ ይገባል። የዘገባዎቹ ዓላማ ግን፣ ህዝብ በተለይ የጉዳዩ ዋነኛ ባለቤት የሆነው ነጋዴው ግልጽ መረጃና ግንዛቤ እንዲኖረው ማድረግና የተዛነፈ ፍትህ ካለ እንዲቃና ማድረግ መሆን ይገባዋል። የጋዜጠኝነት ሞያ፣ የሞያው ስነምግባርም የሚያዘው ይህንኑ ነው። በተጨባጭ እየታየ ያለው ግን ከዚህ የተለየ ነው።

እርግጥ የኤርትራ መንግስት በቀጥታ አቅጣጫ እየሰጠ የሚያሰማራቸው “ጋዜጠኞች” ሞያና ስነምግባር ይከተላሉ ተብሎ አይጠበቅም። “የጋዜጠኞቹ” ባህሪም፣ ጌታቸው የኤርትራ መንግስትም አይፈቅድላቸውም። መድረሻቸውም ኢትዮጵያን ማፈራረስ በመሆኑ። የኤርትራ መንግስት በቀጥታ የማይመራቸው ሚዲያዎች ግን፣ ይህን ሊያደርጉ ይገባ ነበር። የኤርትራ መንግስት ተላላኪዎችን ዓላማ የሚጋሩ “ጋዜጠኞች” ውስጣቸው ቢኖሩም በሚዲያው ኤዲቶረያል ፖሊሲ እንዲከረከሙ ማድረግ በተገባ ነበር።

ያም ሆነ ይህ በኢትዮጵያ የሚያጋጥም ማንኛውንም ጉዳይ ያለወጉ በመጠምዘዝ ውዥንብር በመፍጠር ሃገሪቱን ለማተራመስ ዓላማ የማዋል ሩጫ አዲስ አይደለም። በዚህ ሁኔታ በተፈጠረ ውዥንብር ሁከቶች ተቀስቅሰው ያውቃሉ። ዋናውን የሃገሪቱን የእድገትና ልማት ጉዞ መቀልበስ ባይችሉም ጉዳት አድርሰዋል። ይህ ሰላምን የማወክ ጥረት ለወደፊትም ይቀጥላል። የሻአቢያ ታላላኪ ሚዲያዎችና ስውር አጋሮቻቸው የሰሞኑ ርብርብ የዚህ ውጤት ነው።

ወደዋናው ጉዳይ ልመለስ። በዚህ ዓመት የተካሄደው የነጋዴዎች የቀን ገቢ ግምት በነጋዴዎች ዘንድ ቅሬታና መደናገር መፍጠሩ ገሃድ እውነት ነው። ይህ ቅሬታና መደናገር የተፈጠረው የሂሳብ መዝገብ በማይዙ የደረጃ ‘ሐ’ ግብር ከፋይ ነጋዴዎች ዘንድ ነው። በዚህ የግብር ከፋዮች ደረጃ የእለት ገቢን ለማወቅ የሚያስችል ተጨባጭ አስረጂ ባለመኖሩ፣ የተወሰኑ መነሻዎች ላይ በመመርኮዝ በግምት ነው የሚቀመጠው። ይህ ግምት፣ ለግምት መነሻነት እንደተወሰዱት ማስረጃዎች ጥራትና እንደገማቹ አተያይ ከትክክለኛው መጠን በመብዛት ወይም በማነሰ ልዩነት ሊያሳይ ይችላል።

በመሆኑም ከእለት ገቢ ግምት ጋር በተያያዘ ቅሬታ ያላቸው ነጋዴዎች ሊኖሩ መቻላቸው የሚጠበቅ ነው። የዚህ አይነት ቅሬታ ሲኖር የሚፈታበት የአቤቱታና የይግባኝ ስርአትም አለ፤ በህግ የተቀመጠ ስርአት። በመሆኑም ቅሬታ ያላቸው ነጋዴዎች በዚህ ስርአት መሰረት ቅሬታቸውን የማቅረብ የማይገሰስ መብት አላቸው። በሃገሪቱ ካለው ስር የሰደደ የመልካም አስተዳደር መጓደልና አልፎ አልፎም ሆን ተብሎ ህዝቡን ለማማረር በሚከናወን ሃላፊነትን በአግባቡ ከመወጣት ማፈግፈግ ሳቢያ አቤቱታዎቹ በአግባቡ የማይሰሙበት ሁኔታ ማጋጠሙም የተለመደ ነው። ይህ ችግር በተጨባጭ ታይቷል።

በአንድ የአዲስ አበባ ወረዳ ያጋጠመኝን ለዚህ አስረጂነት ላንሳ። የአዲስ አበባ ከተማ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ በከተማዋ በገቢ ግምቱ ቅሬታ ያላቸው በርካታ ነጋዴዎች መኖራቸውን መነሻ በማድረግ የአቤቱታ ማቅረቢያ ጊዜው እንዲራዘም ወስኖ ነበር። በዚህ መሰረት፣ ሃምሌ 1 ያበቃ የነበረው የደረጃ ‘ሐ’ ግብር ከፋዮች አቤቱታ ማቅረቢያ ጊዜ እስከ ሃምሌ 15 እንዲራዘም ምክር ቤቱ ወስኗል። ሃምሌ 4 የተላለፈውን የምክር ቤቱን ወሳኔ ተከትሎ፣ ነጋዴዎች ሃምሌ 5 እና 6 ለአቤቱታ ሲቀርቡ፤ የግብር ይግባኝ አቤቱታ ማሰሚያችሁ ጊዜ አልፏል እየተባሉ እንዲመለሱ የተደረገበት ሁኔታ ተመልክቻለሁ።

ይህ ብቻ አይደለም። የቅሬታ አቤቱታ ከተቀበሉም በኋላ፣ የአቤቱታ አቅራቢዎቹን ጉዳይ በተጨባጭ ማሰረጃ ከመመርመር ይልቅ፣ ከዚህ በታኝ ግምት የለም፣ ከዚህ በታች የተገመተው ለጉሊት ነጋዴዎች ብቻ ነው የሚል ድፍን ምላሽ በመስጠት ነጋዴውን ግራ ሲያጋቡ የነበሩም አጋጥመውኛል።

እነዚህና መሰል ከመልካም አስተዳደር መጓደልና ከፈጻሚዎች ዳተኝነት የመነጩ ችግሮች ቅሬታ ያለውን ነጋዴ አበሳጭተውታል። በመንግስት በኩል እነዚህና መሰል በየደረጃው በሚገኙ ፈጻሚዎች ዘንድ የሚታዩ ችግሮች ጊዜ ሳይሰጣቸው ሊፈቱ ይገባል። እነዚህ ችግሮች እስካሉ ድረስ፣ በህግ የተደነገገው እስከጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የተዘረጋ የይግባኝ አቤቱታ መስሚያ ስርአት ምንም የሚፈይደው ነገር አይኖርም። እርግጥ በትክክል የነጋዴውን አቤቱታ ተቀብለው፣ ቅሬታው የተፈጠረበትን ምክንያት ለይተው፣ ከግንዛቤ ክፍፈት የተፈጠረ ከሆነ ግንዛቤ አስጨብጠው የሚመልሱ ፈጻሚዎች አጋጥመውኛል። እነዚህ ከአጥፊዎቹና ከዳተኞቹ ይበዛሉ።

በአዲስ አበባ ከተማ ከአጠቃለይ የዕለት ገቢ ግምት ከተካሄደባቸው ነጋዴዎች መሃከል 32 በመቶዎቹ አቤቱታ አቅርበዋል። ከእነዚህ አቤቱታ ካቀረቡ ነጋዴዎች መሃከል የ38 በመቶ አቤቱታ መፍትሄ አግኝቷል። ለአቤቱታ ሲሄዱ፣ ሱቄን ከመዝጋት ውጭ አማራጭ የለኝም ሲሉ የነበሩ ነጋዴዎች፣ በጉዳዩ ላይ ግንዛቤ ሲኖራቸው እዚያው ግብራቸውን ከፍለው ደስ ብሏቸው የተመለሱም አጋጥመውኛል።

እኔ እንደታዘብኩት፣ አብዛኞቹ ነጋዴዎች  ላይ ቅሬታ የተፈጠረው ከግንዛቤ እጥረት ነው። የቀን ሽያጭ 600 ብር፣ የዓመት 180 ሺህ ብር እንደሆነ የሚያመለክት የገቢ ግምት ደብዳቤ የደረሳቸው ነጋዴዎች፣ በመጀመሪያ 180 ሺህ ብር ዓመታዊ ግብር እንዲከፍሉ የተጠየቁ አድርገው ነበር የወሰዱት። በርካታ ነጋዴዎች የዚህ አይነት ግንዛቤ ነበራቸው። ይህ አጠቃላይ ዓመታዊ ሽያጭ መሆኑን፣ የገቢ ግብር የሚከፍሉት ሁሉም ወጪዎቻቸው ተቀንሰው ከሚቀራቸው ትርፍ ላይ መሆኑን ሲገነዘቡ ግን ብዙዎቹ የግብር መጠናቸውን ወደማስገመት ተሸጋግረዋል። ለምሳሌ በቀን 600 ብር በዓመት 180 ሺህ ብር ሽያጭ የተገመተባቸው ነጋዴዎች እንዲከፍሉ የተጠየቁት ዓመታዊ የገቢ ግብር 3170 ብር ብቻ ነው። የቀን ገቢያቸው 800 ብር፣ የዓመት 240 ሺህ ብር የተገመተባቸው ነጋዴዎች የከፈሉት ዓመታዊ የገቢ ግብር 4500 ብር ብቻ ነው። በቀን 1500 ብር በዓመት 450 ሺህ ብር ሽያጭ የተገመተባቸው ነጋዴዎች የከፈሉት ዓመታዊ ግብር 5170 ብር ብቻ ነው።

በርካታ ነጋዴዎች በእለትና ዓመት ገቢ ትመናና ዓመታዊ የግብር ክፍያ መጠን ላይ ግንዛቤ ሲኖራቸው ቅሬታቸውን አንስተው ግብራቸውን ከፍለዋል፤ አሁንም እየከፈሉ ይገኛሉ። በዚህ ጉዳይ ዙሪያ ቀድሞውኑ የተሟላ ግንዛቤ አለመፈጠሩ የአብዛኛው ነጋዴ ቅሬታ መንስኤ መሆኑ መታወቅ አለበት። ይህ እንደመንግስት ችግር ሊወሰድም ይችላል።

እንግዲህ የኤርትራ መንግስት ተላላኪዎችና የዓላማ አጋሮቻቸው የሆኑ “ጋዜጠኞች” ይህን በተሳሳተ ግንዛቤ ላይ የተያዘ የነጋዴዎች ቅሬታ ያለወጉ በማራገብ ነው ሁከት በመቀስቀስ ሃገሪቱን ለማተራመስ ላንቃቸውን የከፈቱት። እነዚህ ኢትዮጵያ የምትተራመስበት ቀን ናፍቆት ያንገበገባቸው ሚዲያዎችና አጋሮቻቻው፣ ቀድሞውኑ የግንዛቤ ጉድለት የነበረበትን ነጋዴ ውዥንብር ውስጥ ከተው በሁለት የኦሮሚያ ከተሞች አድማና ይህን መነሻ ያደረጉ ሁከት ቢጤ ሙከራወች ቀስቅሰዋል።

እነዚህ የንግድ መደብርን በመዝጋት በአድማ ቅሬታ የተገለጸባቸው አካባቢዎች በጣም ጥቂት ናቸው። በተለይ ኦሮሚያ፣ ከኦሮሚያም አምቦ፣ ወሊሶና የአካባቢው ከተሞች ናቸው። ወሊሶና አምቦ በ30 ኪሎ ሜትር ርቀት ውስጥ ያሉ ከተሞች ናቸው፤ አምቦ ከወሊሶ የሚርቀው 30 ኪሎ ሜትር ያህል ነው። እናም በአንድ አካባቢ እንደተከናወነ አድማ መውሰድ ይቻላል። ይህ አካባቢ ባለፈው ዓመት የሚንተከተክ የሁከት ፖለቲካ ግለት የነበረበትና  ይህ ሰክኖ ያላበቃበት አካባቢ ነው። በመሆኑም አድማው በነጋዴው ቅሬታ ብቻ ሳይሆን በሌላ ያደረ የሁከት አመለካከት የተገፋ መሆኑን መገመት አያዳግትም። በአምቦና በወሊሶ ከተሞች መደብራቸውን ከዘጉ ነጋዴዎች መሃከል አብዛኞቹ ለአድማ የሚያስነሳ ቅሬታ ያላቸው አይደሉም። ከዚህ ይልቅ በስውር የሚንቀሳቀሱ የተቃውሞ እጆችን የፈሩ ናቸው። እናም አድማውን ሙሉ በሙሉ ከዕለት ገቢ ትመና ጋር ማያያዝ ስህተትነቱ ያይላል። በዚህ ላይ በአጠቃላይ በኦሮሚያ የዕለት ገቢ ግምት ከተሰራላቸው ነጋዴዎች ውስጥ 80 በመቶ የሚሆኑት ግምቱንና የተወሰነባቸውን ግብር የተቀበሉ መሆናቸው መታወስ አለበት።

ከዚህ በተጨማሪ፣ ግብር ሳይከፍሉ አየር ባየር ንግድ መበልጸግ የለመዱ አንዳንድ ነጋዴዎች፣ በዕለታዊ የገቢ ትመናው የግብር መረብ ውስጥ መግባታቸውና ከገቢያቸው ጋር የሚመጣጠን ግብር እንዲከፍሉ መጠያቃቸው አስደንግጧቸዋል። በኦሮሚያ ውስጥ ከዚህ ቀደም ግብር ሳይከፍሉ ይሰሩ የነበሩ 46 ሺህ ነጋዴዎች መገኘታቸውን ልብ ይሏል። እነዚህ ኪራይ ሰብሳቢ ጥገኛ ነጋዴዎች በህጋዊ ንግድ መረብ እንዲጠለፉ ያደረጋቸውን ሁኔታ ለመቀልበስ በስውር ከሚንቀሳቀሱ ህገወጥ የፖለቲካ አጀንዳ ካላቸው ቡድኖች ጋር ተመሳጥረው የመንግስትን ውሳኔ በሃይል ለማስቀየር አድማና ሁከት እንዲፈጠር ለማድረግ የሞከሩበት ሁኔታ አለ። እነዚህ ግብር ሳይከፍሉ ወይም መክፈል ከሚገባቸው በታች እየከፈሉ ያለአግባብ የከበሩ ጥገኛ ነጋዴዎችን፣ ከህጋዊ ነጋዴዎች መነጠል ያስፈልጋል። ይህ በኦሮሚያ ያለ ሁኔታ በሌሎችም ክልሎች ያለ መሆኑ መታወቅ አለበት።

ህገወጥ አድማና ሁከት በመቀስቀስ የግብር አለመክፈል ዝንባሌ ያሳዩ ነጋዴዎች አካሄድ፣ ግብር በሚከፍለው ተቀጣሪ ሰራተኛና አርሶ አደር ጫንቃ ለመኖር ካለ ፍላጎት ተለይቶ አይታይም። ሰሞኑን ከኦሮሚያ ክልል የተገኙ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት የኦሮሚያ ክልል ከግብርና ሌሎች ገቢዎች የሚሰበስበው ዓመታዊ ገቢ 10 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር ብቻ ነው። በስፋት፣ በህዝብ ብዛት፣ በኢኮኖሚ አቅም፣ በገበያ እንቅስቃሴ ከሃገሪቱ ቀዳሚ ከሆነው የኦሮሚያ ክልል የሚሰበስበው ገቢ፣ በአዲስ አበባ ከተማ ከሚሰበሰበው ጋር ተመጣጣኝ ነው። የፌደራል መንግስት ድጎማ ባይኖር የክልሉ ህዝብ የሚያነሳውን ሰፊ የመሰረተ ልማት፣ የማህበራዊ ልማት፣ የስራ አጥነት ችግር ጥያቄዎች በክልሉ አቅም ለመፍታት መሞከር የማይታሰብ ነው። ትልቁ የኦሮሚያ ክልል በፌደራል መንግስት ላይ ጥገኛ ነው። ይህ የክልሉ የግብር አሰባሰብ ምን ያህል ደካማ እንደሆነ ያሳያል።

ይህ ብቻ አይደለም። ከልሉ በግብር ከሚያገኘው ገቢ 47 ነጥብ 5 በመቶ ከተቀጣሪ ሰራተኞች የሚሰበሰብ ነው። ከተቀጣሪ ሰራተኞች ጋር ተቀራራቢ ከሆነው 360 ሺህ ነጋዴ የሚሰበሰበው ግብር 15 ነጥብ 7 በመቶ ብቻ ነው። በገቢ መጠንና በኑሮ ደረጃ ነጋዴውንና ተቀጣሪ ሰራተኛውን ስናነጻጸር ደግሞ የሰማይና የምድር ያህል የተራራቁ ሆነው እናገኛቸዋለን። በክለሉ ውስጥ ያሉት የግል መኪናዎች፣ ቪላ ቤቶች፣ . . . ሙሉ በሙሉ የነጋዴዎች ናቸው። ዘመናዊ ቪላ ቤት የገነባ፣ የቤት መኪና ያለው አንድም ተቀጣሪ ሰራተኛ የለም።  ይህ ሁኔታ ነጋዴው ምን ያህል ከፍተኛ ገቢ እንደሚያገኝ፣ በሌላ በኩል ምን ያህል ግብር እንደማይከፍል ያረጋግጣል።

እናም፣ ግብር ሳይከፍልና መክፈል ከሚገባው በታች እየከፈለ ተገቢ ባልሆነ መንገድ የከበረው ጥገኛ ነጋዴ አሁን በግብር መረብ ውስጥ ገብቶ ከገቢው ጋር የሚመጣጠን ግብር እንዲከፍል ሲጠየቅ ከህገወጥ ፖለቲከኞች ጋር ተጋብቶ የመንግስትን ግብር የመሰብሰብ ውሳኔ በሁከት ለመቀልበስ እያደረገ ያለው ሙከራ፣ በግብር ከፋይ ተቀጣሪ ሰራተኛና በዙሃን አርሶ አደር ዜጎች ጫንቃ ላይ ለመኖር ከመፈለግ የተለየ አይደለም።   

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy