Artcles

በአዲሲቷ ኢትዮጵያ ውስጥ የትጥቅ ትግል አያዋጣም!

By Admin

July 20, 2017

በአዲሲቷ ኢትዮጵያ ውስጥ የትጥቅ ትግል አያዋጣም!

                                                                  ደስታ ኃይሉ

በቅርቡ 95 የሚሆኑና ራሳቸውን የቤኒሻንጉል ነፃነት ንቅናቄ (ቤነን) እያሉ የሚጠሩ ኃይሎች ከኤርትራ ወደ ኢትዮጵያ በመግባት ለመንግስት በሰላም እጃቸውን የሰጡበትን ሰጥተዋል። እነዚህ ኃይሎች ቀጠናውን በሚያውከው የኤርትራ መንግስት ጋር የነበራቸውን ግንኙነት አቋርጠው ወደ አገራቸው በሰላም የተመለሱት በአዲሲቷ ኢትዮጵያ ውስጥ ለትጥቅ ትግል የሚሆን ምህዳር የሌለ መሆኑን በመገንዘባቸው ነው።

እርግጥ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ነባራዊ ሁኔታ ሰላምን፣ ልማትንና ዴሞክራሲን የሚያበረታታ እንጂ ነፍጥ አንግቦ የተገኘውን ሁለንተናዊ አገራዊ ለውጥ የሚቀለብስ እሳቤን የማያስተናግድ አይደለም። አዲሲቷ ኢትዮጵያ ዛሬ ለተጎናጸፈችው የሠላም፣ የፈጣን ልማትና የዴሞክራሲ ባህል ግንባታ ድሎች መሰረት ለሆነው የኢፌዴሪ ህገ መንግስት ነው።

ህገ መንግስቱ የህዝቦችን የዘመናት ጥያቄዎች በተገቢው መንገድ ምላሽ የሰጠ ነው። ምንም እንኳን ኢትዮጵያ የበርካታ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች መኖሪያ ብትሆንም፤ እነዚህ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ለዘመናት በአፈናና በጭቆና ሥርዓት ቀንበር ስር ወድቀው ከመማቀቅ ያዳናቸው ይኸው ህገ መንግስት ነው። የአገራችን የዘመናት ጥያቄዎች በተመለሱበት አገር ውስጥ የትጥቅ ትግል ቦታ ሊኖረው አይችልም።

ህገ መንግስቱ በስራ ላይ ከዋለ ወዲህ ሀገራችን ትክክለኛ የዕድገት አቅጣጫ ይዛ በአዲስ የታሪክ ምዕራፍ ላይ በድል ለመረማመድ በቅታለች፡፡ የብሔሮችና ብሔረሰቦች እስር ቤት እስከመባል ደርሳ የነበረችው ሀገራችን፤ የህዝቦቿ መብት የተረጋገጠባት፣ የዕድገትና ልማት ብሩህ ተስፋን የሰነቀች፣ የእኩልነትና የፍትህ አምባ ለመሆን ችላለች። ይህ የህገ መንግስቱ ችግር ፈቺነት አንዱ ማሳያ ይመስለኛል።

በመሆኑም የአፈና አገዛዝ፣ የግፍ ቀንበር ተጭኖት የኋላቀርነትና የበታችነት ተምሳሌት ተደርጎ ይታይ የነበረው የብሔር ብሔረሰቦቿ ባህል፣ ታሪክና ቋንቋ የህዝቦቿ መኩሪያና መከበሪያ፣ የሀገራችን መድመቂያ ጌጥና የመልካም ገጽታዋ መገለጫ ወደ መሆን ተሸጋግሯል።

የተለያየ እምነትና የአኗኗር ዘይቤን የሚከተሉ የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች በመግባባትና በመረዳዳት መንፈስ አብሮ በመኖር በዓለም የሚታወቁበት የመቻቻል ባህልም ከመቼውም በላቀ ሁኔታ ዳብሯል። እነዚህ ታሪካዊ፣ ባህላዊና መንፈሳዊ የጋራ እሴቶቻችን ለሀገራችን ተጨማሪ ክብርና ሞገስ ከማላበስ አልፎ ለፈጣን ዕድገት ስራዎች የበኩላቸውን ድርሻ ማበርከት ወደ ሚችሉበት ደረጃ ላይ የደረሱ ይመስለኛል።

ከዚህ በተጨማሪ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ከሀገራቸው ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ህይወት ተገልለውና ተረስተው በባይተዋርነት ለመኖር የተገደዱበት አድሎአዊና ፍትህ አልባ ሁኔታ ሊቀየር ችሏል። በዚህም ዜጎች በማንኛውም አገራዊ ጉዳይ ውስጥ እኩል ተሳታፊ የመሆን ዕድል አግኝተዋል። ታዲያ በዚህ የህዝቦች ተጠቃሚነት ላይ የትጥቅ ትግልን ማሰብ ምን ማለት ይሆን?…

ህገ መንግስታዊ ስርዓቱ የሀገራችንና የህዝባችን የማደግና የመበልጸግ ተስፋን በእጅጉ ለማለምለም ያስቻለ ሁኔታ ነው። መላው ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች በመብቶቻቸው እየተገለገሉና ዘላቂ ጥቅሞቻቸውን እያስከበሩ በፈጣን ልማትና በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ አቅጣጫ ላይ የተያያዙት ፈጣን የዕድገት ጉዞም የዚሁ ህገ መንግስት ሌላኛው ችግር ፈቺነት ማሳያ ይመስለኛል። እናም ችግርን በህገ መንግስቱ እንጂ በትጥቅ ትግል ለመፍታት መሞከር ተገቢነት ሊኖረው አይችልም።

በአገራችን እውን በመሆን ላይ የሚገኘው ፌዴራላዊ የመንግስት ሥርዓት ለሀገራችንና ለህዝባችን አንድነት፣ ሠላምና ዕድገት መጠናከር ወሳኝ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው፡፡ የዚህ አዲስ ሥርዓት ግንባታ ሂደት በተጨባጭ ተፈትኖ ፍቱንነቱ የተረጋገጠ ነው፡፡ በመገንባት ላይ የሚገኘው ፌዴራላዊ ሥርዓት በሀገራችን ላይ አንዣቦ የነበረውን የመበታተን አደጋ ያስወገደና በእኩልነትና በመፈቃቀድ  ላይ ለተመሰረተ የህዝቦች አንድነት ዘላቂ ዋስትናን ማስገኘት ችሏል።

የአዲሲቷ ኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ረጅሙንና አስቸጋሪውን የፀረ-ደርግ የትግል ምዕራፍን በድል አድራጊነት በቋጩ ማግስት በጋራ ተወያይተውና አምነው ዕውን እንዲሆን ያደረጉት ህገ- መንግስት የዘመናት ጥያቄዎቻቸውን ሙሉ ለሙሉ የመለሰ ከመሆኑም ባሻገር፤ በቀጣይ ለሚያካሄዷቸው የጋራ አጀንዳዎች ዘላቂነትና ውጤታማነት ዋስትና የሰጠ ነው።

የሀገራችን ህዝብና ህገ መንግስቱ በብዙ መልኮች እጅግ የጠበቀ ቁርኝት ያላቸው በመሆናቸው፤ የሚያጋጥማቸውን ጊዜያዊ ችግሮች የሚፈቱትም በእርሱው አግባብ ነው። ለዚህ በዋነኝነት የሚጠቀሰው ጉዳይ የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የህገ- መንግስቱ ባለቤቶች መሆናቸው ነው፡፡ ህዝቡ ህገ መንግስቱን ያቋቋመ፣ የመንግስትን አወቃቀር የነደፈ ነው። ይህ ሁኔታ ባለበት ሀጔ ውስጥ የትጥቅ ትግል ምንም ዓይነት ቦታ የለውም።

ህገ መንግስቱ ምርጥ የሚባሉ ዓለም አቀፍ ድንጋጌዎችን የያዘና ማናቸውንም ችግር ስልጡን በሆነ መንገድ መፍታት የሚችል ተራማጅ ሰነድ ስለሆነ ነው። ላለፉት 22 ህገ መንግስታዊ ዓመታት አገራችን ውስጥ የታዩት እመርታዎችም የህገ መንግስቱን ችግር ፈቺነት የሚያሳዩ ናቸው። እናም ችግር ፈቺነት ባለበት ምህዳር ውስጥ የትጥቅ ትግልን ማሰብ የዋህነት ነው።

ለነገሩ ህገ መንግስቱ ፀድቆ በስራ ላይ ከዋለ ጀምሮ ሀገራችንና ህዝቦቿ በፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ መስኮች እጅግ ውጤታማ ተግባር ማከናወን ችለዋል። በህገ መንግስቱ መርሆዎች ሀገራችንና ህዝቦቿ ከራሳቸው አልፈው የአፍሪካ ፖለቲካዊ ድምፅ እስከ መሆን ድረስ ደርሰዋል።

በመርሆዎቹ የሀገራችን የድህነትና ኋላቀርነት ገፅታ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሊለወጥ ችሏል። የህዝብን ተጠቃሚነት በየደረጃው ማረጋገጥ የቻለ የልማት ተምሳሌት ሆነንም ለአፍሪካውያን ልምዳችንን እስከማካፈል ድረስ ደርሰናል። በመርሆዎቹ የህዝቡ ተቻችሎና ተከባብሮ በጋራ የመኖር እሴቶች እየተገነቡ ዛሬ ላይ ደርሰዋል።

እነዚህ ሁሉ ተግባራት የተከናወኑት በህገ መንግስቱ ቁልፍ መፍትሔ ሰጪነት ነው። ነገም ችግሮችን በህገ-መንግስቱ ማዕቀፍ ውስጥ መፍታት ይቻላል። በዚህ ላይ መወላወል ሊኖር አይገባም—የህገ-መንግሰቱ የትናንት የችግር አፈታት መንገዶች ነገንም የሚያሳዩ ናቸውና። እናም ይህን በመሰለ አገራዊ ምህዳር ውስጥ የትጥቅ ትግልን ማሰብ የዋህነት ነው።

በእኔ እምነት ራሳቸውን “ቤነን” እያሉ የሚጠሩ ኃይሎች በቅርቡ እጃቸውን ሰጥተው ወደ አገራችን መግባታቸው ይህን ዕውነታ በመገንዘባቸው በመሆኑ የውሳኔያቸው ትክክለኛነት አያጠያይቅም። ምንም እንኳን ባለማወቅ ሁሌም ለአገራችን ቀና በማያስበው የኤርትራ መንግስት እየታገዙ በገዛ አገራቸው ላይ ለጥፋት በመነሳታቸው ስህተት ነበር። ይህንንም ተገንዝበው እዚህ ሀገር ውሰጥ መጥተው በሰላም እጃቸውን ለህዝብና ለመንግስት መስጠታቸው ወደፊት ብሩህ ነገር ይጠብቃቸዋል። በዚህ ብሩህ ተስፋቸውም ለመበደል ያሰቡን ህዝብ ለመካስ ያግዛቸዋል። መጪው ጊዜ ከህዝባቸው ጋር ብሩህ መሆኑ አያጠያይቅም።