Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

በኦሮሚያ ክልል በቀን ገቢ ትመናው ላይ ያለውን የተሳሳተ ግንዛቤ ለመፍታት ከንግዱ ማኅበረሰብ ጋር እየተሰራ ነው

0 323

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

በኦሮሚያ ክልል ከቀን ገቢ ትመና ጋር ያለውን የተሳሳተ ግንዛቤ ለመፍታት ከንግዱ ማኅበረሰብ ጋር በቅርበት እየሰራ መሆኑ ተገለፀ።

በክልሉ ከግምቱ ጋር የሚነሱ ቅሬታዎችን ለማስተናገድ የደረጃ ‘ሐ’ ግብር ከፋዮች የመክፈያ ቀን ለ15 ቀናት ተራዝሟል።

የክልሉ ፕሬዚዳንት አቶ ለማ መገርሳ በቀን ገቢ ግምቱ ላይ ከምዕራብ ሸዋ ዞንና አጎራባች ከተሞች ከተውጣጡ የንግዱ ማኅበረሰብ አባላትና ከኅብረተሰቡ ጋር በወሊሶ ከተማ እየተወያዩ ነው።

የክልሉ የበጀት ፍላጎት በአዲሱ ዓመት 56 ቢሊዮን ብር የደረሰ ሲሆን ገቢ የመሰብሰበ አቅሙ ግን ባለፈው በጀት ዓመት ብቻ እንኳን 10 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ነበር።

ከተሰበሰበው ገቢ 45 ነጥብ 7 በመቶ የሚሆነው ከመንግሥት ሰራተኛው ሲሆን ከንግዱ ማኅበረሰብ የሚሰበሰበው ደግሞ 15 ነጥብ 7 በመቶ እንደሆነ ነው መረጃዎች የሚያሳዩት።

ችግሩን ለመቅረፍ በተደረገው የማጣራት ዘመቻ ከ16 ሺህ በላይ ነጋዴዎች ሕጋዊ ፈቃድ ሳይኖራቸው በንግድ ሥራ መሰማራታቸው ተደርሶባቸዋል።

ድርጊቱ በሕጋዊ ነጋዴዎች ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር ከግምት በማስገባት የገቢ አሰባሰብ ሥርዓቱን ህግን የተከተለ ለማድረግ ጥረት መደረጉን ፕሬዚዳንቱ መናገራቸውን የክልሉ የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አዲሱ አረጋ  ገልጸዋል።

በዚህም ሕገ-ወጦቹ ነጋዴዎች ፍቃድ እንዲያወጡና የግብር አሰባሰብ ሂደቱን ለማጠናከርም ግብር መክፈያ መለያ እንዲያወጡ የማድረግ ሥራዎችም ተሰርተዋል።

በመቀጠልም መተማመን ለመፍጠር ከንግዱ ማኅበረሰብ ጋር በመሆን ለነጋዴዎቹ የደረጃ አመዳደብና የዕለት ገቢ ትመና ሕጉን ተከትሎ መውጣቱን ገልጸዋል።

ይሁን እንጂ ነጋዴዎች “ግምቱ የተጋነነ ነው፣ አድሎአዊ አሰራር አለው” በማለት ቅሬታዎችን እንዳነሱና አሰራሩ ላይም የግንዛቤ ክፍተት መስተዋሉን ተናግረዋል።

በዚህም የተነሳ በአምቦና በወሊሶ እንዲሁም በምዕራብ ሸዋ እንደ ጀልዱ፣ ግንደ በረትና ጊንጪ አካባቢዎች የንግድ ተቋማትን እስከ መዝጋት የደረሰ ቅሬታ መፈጠሩን ጠቁመዋል።

በመሆኑም ክልሉ ከንግዱ ማኅበረሰብ ጋር በቅርበት ሆኖ ችግሮቹን ነቅሶ በማውጣትና በመወያየቱ በአሁኑ ወቅት እነዚህ ችግሮች በከተሞቹ ላይ አለመኖራቸውን ገልጸዋል።

የደረጃ ‘ሐ’ ግብር ከፋዮችን ቅሬታ ተቀብሎ ለማስተናገድም ክፍያው ይጠናቀቅበት የነበረው ሐምሌ 30 ወደ ነሐሴ 15 እንዲዘዋወር መደረጉን ተናግረዋል።

በተመሳሳይ ለሌሎቹም ነጋዴዎች የቅሬታ ማቅረቢያ ሥርዓት መዘጋጀቱን በመጠቆም።

ጎን ለጎንም በትናንሽ የንግድ ሥራዎች ላይ የተሰማሩ በሚወጣው የገቢ ግምት ተጎጂ እንዳይሆኑ አቅጣጫ መቀመጡን አስረድተዋል።

በገቢ ግብሩ ላይ ያለውን ብዥታ ለማጥራት አሁንም ከመገናኛ ብዙኃንና ከነጋዴው ጋር ጭምር ገጽ ለገጽ በመገናኘት እየተሰራ መሆኑን ነው ያብራሩት።

በሌላ በኩል ፕሬዚዳንቱ በክልሉ በሚካሄዱ የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች እንዲሁም በሌሎች ጉዳዮች ላይ ከነጋዴውና ከኅብረተሰቡ ለሚነሱ ጥያቄዎች ማብራሪያና ምላሽ ሰጥተዋል።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy