Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ተመልካችና አድማጭ ያጣው የጽንፈኞች ጩኸት   

1 345

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ተመልካችና አድማጭ ያጣው የጽንፈኞች ጩኸት   

አባ መላኩ

ጽንፈኞች አሁን ላይ ተገለዋል። አድማጭና ተመልካች አጥተዋል።  በየፌስ ቡኩ የሚረጩት መርዛማ ፖለቲካቸው  መክኖባቸዋል። ለዚህ ጥሩ ማሳያ የሚሆነው ሰሞኑን በአዲስ አበባ  የኦሮሚያ ልዩ ጥቅም የሚያስጠብቀውን ረቂቅ አዋጅ ላይ ሁለቱን ጽንፈኛ ፖለቲከኞች (የኦነግንና የግንቦት ሰባትን ደጋፊዎች) እርስ በርስ ሲበላሉ ማየት እጅግ ያስገርማል። ባለፈው ጊዜ  እነዚህ ሁለት አካላት ለጥፋትና ለውድመት ግንባር ገጥመው ተመለከትናቸው እንጂ  ጥንትም ፍቅራቸው የሰመረ አልነበረም። እነዚህ አካላት ምንም አይነት የጋራ ነገር የላቸውም። ተጠፋፊ፣ ተበያዪ ናቸው። እነዚህ አከላት ኢትዮጵያን ለአንድ ቀን እንኳን ሊያስተዳድሯት አይችሉም።

እነዚህ ጽንፈኛ ቡድኖች ባለፈው ጊዜ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን እንደሽፋን በመጠቀም  የወጣቶችን ስሜት በመኮርኮር አመጻና ረብሻ በማስነሳት በርካታ ህይወትና ንብረት እንዲወድም ምክንያት ሆነው ነበር። “እንደዚያ ያለ ቅጥ ያጣ አካሄድ በአገራችን መቼም የትም አይደገምም”። መንግስትና ህዝብ  የህግ የበላይነት እንዲከበር ተቀራርበው በመስራታቸው አገራችን ወደቀድሞዋ መረጋጋቷ በአጭር ጊዜ በመመለሷ የህዝቦች አብሮነት፣ ኢንቨስትመንትና የቱሪስቶች  ፍሰት ወደ ቀድሞው ሁኔታ ተመልሷል።  በጥልቅ ተሃድሶ ወቅት የተነሱ የመልካም አስተዳደር ችግሮች ተብለው  የተለዩ ጥያቄዎች  ምላሽ እያገኙ ያሉት ገዥው ፓርቲ  በተከተለው የሰከነ አካሄድ ነው።  

አሁን ላይ አገራችን  ወደቀድሞዋ የሰላም ተምሳሌትነቷ፣ የኢንቨስትመንት የስበት ማዕከልነቷ እንዲሁም ፈጣንና ቀጣይነት ያለው የኢኮኖሚ ዕድገቷ ተመልሳለች።  አገራችን በውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ፍሰት በአፍሪካ በቀዳሚነት ከተቀመጡት አገራት ተርታ መሰለፍ ችላለች። በቅርቡ የዓለም ባንክ ባወጣው ሪፖርት አገራችን በድርቅ ተመታች በተባለበት በአሁኑ ወቅት እንኳን  በኢኮኖሚ ዕድገት በአፍሪካ በቀዳሚነት መቀመጥ ችላለች። በዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ረገድም  ቢሆን አገራችን ጀማሪ ትሁን እንጂ  ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት  ማንም ሊክደው የማይቻል በርካታ ስኬቶችን ማስመዝገብ ችላለች። በዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ረገድ አገራራችን ካስመዘገበቻቸው ስኬቶች መካከል አንዱ  ዜጎች የሃሳብ ልዩነታቸውን በሰላማዊ መንገድ ማራመድ የሚችሉበትን ሁኔታ መመቻቸቱ ተጠቃሽ ነው።

ጽንፈኛ የዳያስፖራ ፖለቲከኞች በተንደላቀቀው የምዕራብ አገራት እየኖሩ፣ ትንንሽ ጉዳዮችን መልካቸውን እንዲቀይሩ ወይም ተጭባጭነት የሌላቸውን የተሳሳቱ የፈጠራ መረጃዎችን  በማሰራጨት  ህዝቦች ወደብጥብጥና ሁከት እንዲገቡ ምክንያት ሆኗል።  እነዚህ ሃይሎች አሜሪካና አውሮፓ ተቀምጠው በለኮሱት እሳት   የተለበለብነው እኛው ነን። የወደመው ንብረትም የንጹሃን ግለሰቦችና  ከእያንዳንዳችን ኪስ  በተሰበሰበ  የተገነቡ   የጋራ መሃበራዊ  መገልገያዎቻችን ናቸው። አሁንም እነዚህን የጋራ  መገልገያዎችን ለመጠገን እየወጣ ያለው ገንዘብ  ከእያንዳንዳችን ኪስ  የተሰበሰበ የእኛው ሃብት ነው።

እውነቱን እንነጋገር ከተባለ መንግስት ከሰላም ወዳዱ የህብረተሰብ ክፍል ጋር ተቀራርቦ  በመስራት ህግና ስርዓትን ማስከበር ባይችል ኖሮ ምን እንደሚፈጠር መገመት የሚያስቸግር አይደለም። የጸጥታ ሃይሎችን ማጥቃት፣ ሰላማዊ ሰዎችን መገድልና አካል ማጉደል፣ የመንግስትና የግለሰቦችን ንብረት ማውደም  የኢትዮጵያዊያን  ባህል አይደለም። ጽንፈኛው የዳያሰፖራ ፖለቲከኞች  በመርዘኛ  ሚዲያዎቻችው  እንደኢሳት፣ ኦ ኤም ኤንና አንዳንድ ማህበራዊ ሚዲያዎችን  በመጠቀም  አገራችንን ወደብጥብጥ እንድታመራ ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት አድርገው ነበር።

በየትኛውም አገር መንግስት መንግስት ሊባል የሚችለው የህግ የበላይነትን ማረጋገገጥ ሲችል ብቻ ነው። መንግስት ጸጥታ ማስጠበቅና የህግ የበላይነትን ማረጋገጥ ካልቻለ የአገር  ህልውና ሊኖር አይችልም።  ማንም በሰላም ወጥቶ በሰላም መግባት የማይችልበት ሁኔታ ይፈጠራል። ከላይ ለማንሳት እንደሞከርኩት ህይወት የሚያጠፋና ንብረት የሚያወድም ሃይል የህግ የበላይነትን አያውቅም። ዘራፊና ቀሚ ሃይል ሰላምን አይፈልግም። ይህን  ሃይል መንግስትና ህዝብ በመተባበር ሃይ ባይሉት ኖሮ አገርን ይበትኑት ነበር።

በአግባብ ከተያዘ ወጣት ለአንድ  አገር ልማት ትልቅ አቅም ነው። በአግባብ መያዝ ካልተቻለም ይህ ሃይል  ለጥፋትም ቅርብ ነው። እኛ ወጣቶች ነገሮችን በትኩረት ተመልክተን መልካሙን ከመጥፎው መለየት ካልቻልን በቀላሉ ለጥፋት ሃይሎች መገልገያ እንሆንና  አገርና ህዝብን በሚጎዳ  ነገሮች ላይ ተሰማርተን ወገንን ልንጎዳ እንችላለን።

በስሜታዊነት  የሚቀሰቀስ አመጻና ነውጥ  መነሻውም መድረሻውም አይታወቅም።  በሊቢያና በሶሪያ ያመጣውን ቀውስ መለስ ብለን መመልከቱ ጠቃሚ ይሆናል። ወጣቶች የሃሰት መረጃዎችን ከእውነታ እንለያቸው።  በቅድሚያ የእነዚህን የጥፋት ሃይሎች ድብቅ አጀንዳ እኛ ወጣቶች ቀድመን ልንነቃባቸው ይገባል። እውነት እነዚህ ሃይሎች ለወጣቱ ስራ ፈጣሪዎች፣ የህዝቦችን አብሮነት  የሚያጠናክሩ ነበሩን? የህግ የበላይነት የሚከበረው በመንግስት ጥረት ብቻ ሳይሆን በሁሉም ሰላም ወዳድ ህብረተሰብ በመሆኑ፣ መንግስትና ህዝብ በቅርበት መስራት በመቻላቸው በአጭር ጊዜ  አጥፊዎችን ወደ ህግ  ማቅረብ ተችሏል።  

አሁን በየአካባቢው በተግባር እየታየ ያለው  ልማት የተገኘው በወጣቶች ግንባር ቀደም ተሳትፎም መሆኑ መታወቅ መቻል አለበት።  ወጣቶች  ከልማቱም ተጠቃሚ የሚሆኑበትን  ሁኔታ መንግስት በማመቻቸት ላይ ነው።  የሁሉም ነገር መሰረት ሰላም ነው። በአገራችን የተጀመረውን ልማት ቀጣይነትና ፍተሃዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የአገራችን ሰላም ማስጠበቅ የሁላችንም ግዴታ ነው።  እስካሁን ያስመዘገብናቸውን ድሎችን በመጠበቅ የቀሩንን ለማሳካት ጠንክረን በመስራት የአገራችንን ህዳሴ እናረጋግጣለን። ይህ ካልሆነ ግን “ዉሃ ቅዳ ዉሃ መልስ ”  እንደሚባለው ነው። ያለንን እያጠፋን ለውጥ መጠበቅ የሚታሰብ ነገር አይደለም።

በአገራችን  ማንኛውንም ነገር በመነጋገር መፍታት የሚቻልበት ሁኔታ ተመቻችቶ ሳለ ሃሳብን በሃይል ለማራመድ መሞከር ህገመንግስታዊ አካሄድ አይደለም። ወጥቶ ለመግባትም ሆነ ሰርቶ ለመበልጸግ ሰላም ዋነኛ ምሰሶ በመሆኑ ህብረተሰቡ የአካባቢውን ሰላም ማስጠበቅ ይኖርበታል። ልማት የሚኖረው፣ ሰርተን መብላት፣ ወጥተን መግባት የምንችለው የህግ የበላይነት ሲረጋገጥ ብቻ ነው።

መንግስት በህዝብ ይሁንታ የተቋቋመ ሆኖ ሳለ በአመጻና በሁካታ ለማፍረስ መሞከር ተጠያቂነትን ያስከትላል። ከእንግዲህ በአገራችን ስልጣን የሚመነጨው ከምርጫ ኮሮጆ ብቻ እንደሆነ ህገመንግስታችን ደንግጓል። መንግስት ይሄዳል፤ በተመሳሳይ መንግስት ይመጣል፤ ነገር ግን አገርና ህዝብ ሁሌም ይኖራሉ። ለስልጣን ተብሎ አገርን የሚያፈርስ ህዝብን እርስ በርስ እንዲበላላ የሚያደርግ አካሄድ መከተል እጅግ አሳፋሪ ነው።  የህግ የበላይነት ማስጠበቅ በዋነኝነት የመንግስት ስራ ይሁን እንጂ ለመንግስት ብቻ የምንተወው ጉዳይ አይደለም። መንግስትና ህዝብ ተቀራርበው መስራት በመቻላቸው በአገራችን ሰላምና ልማት ዘላቂ ሆነዋል። ዴሞክራሲ ማለት የህግ የበላይነት ማለት ነው። ከእያንዳንዱ መብቶች ጎን ለጎን ግዴታዎችንም መታሰብ ይኖርበታል። መቼም ቢሆን በሁከትና በአመጽ የተሳተፈ  መጠየቁ አይቀርም። ማንም ለሰራው ጥፋት ተጠያቂነትን ማስፈን ካልተቻለ የህግ የበላይነት ከጥያቄ ላይ የሚወድቅ ይሆናል።

የአገራችንን  የዴሞክራሲ ስርዓት ለማጎልበትና የኢኮኖሚ ዕድገት ለማስቀጠል ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል የጥፋት ሃይሎችን አካሄድ ማጋለጥ ይኖርበታል። የመልካም አስተዳደር ችግሮች ሊፈቱ የሚችሉት በሁከትና በብጥብጥ ሳይሆን መንግስትና ህዝብ በቅርበት በመነጋገር ነው። በጥልቅ ተሃድሶ ወቅት   የመልካም አስተዳደር ችግሮች ናቸው ተየብለው ተለዩ  ነገሮች  አሁን ላይ መንግስት  መፍትሄ ናቸው ያላቸውን ነገሮች በመተግበር ላይ ነው። ለውጦችም እየታዩ ናቸው። አዎ  የመልካም አስተዳደር ችግር ሊፈቱ የሚችሉት ኢህአዴግ በሚከተለው የሰከነ መስመር እንጂ ኢሳትና ኦ ኤም ኤን  በሚያራግቡት አሉባልታ እንዳልሆነ  ተመልክተናል።

 

  1. Aba says

    Please share ESAT lies secret by Abebe Belew: https://www.youtube.com/watch?v=0ECJ0nUm9n8&t=4s

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy