Artcles

አንድ ቤት የሚሰሩ ሣር አይሻሙም

By Admin

July 04, 2017

አንድ ቤት የሚሰሩ ሣር አይሻሙም

ኢብሳ ነመራ

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሰኔ 22፣ 2009 ዓ/ም በሚኒስትሮች ምክር ቤት የተመራለትን የኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ ከተማ ላይ ያለውን ህገመንግሥታዊ ልዩ ጥቅም ለማስጠበቅ የተዘጋጀ ረቂቅ አዋጅ ተመልክቶ ለዝርዝር ጥናት ለህግ፣ ለፍትህና አስተዳዳር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መርቷል።

5ኛው ዙር የመንግስት የስራ ዘመን 2ኛው ዓመት መጀመሪያ ላይ የህዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች ባካሄዱት የጋራ ስብሰባ ላይ የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ ባደረጉት ንግግር፣ ይህ በህገመንግስቱ አንቀጽ 49 ንኡስ አንቀጽ 5 ላይ የሰፈረ አዋጅ እንደሚወጣ ገልጸው እንደነበረ ይታወሳል። ፕሬዝዳንት ሙላቱ በንግግራቸው በዘንድሮ ዓመት የኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ ላይ ያለውን ልዩ ጥቅም ለመደንገግ የሚወጣውን አዋጅ ጨምሮ ሌሎች በርካታ አዋጆች የሚወጡ ይሆናል ብለው ነበረ።

በዚህ መሰረት አዋጁ በያዝነው ዓመት እንዲወጣ ነበር የታቀደው። ይሁን እንጂ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ረቂቅ አዋጁን ወደህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመራው፣ ምክር ቤቱ ለእረፍት ሊዘጋ አንድ ሳምንት በቀረው ጊዜ ማለትም ሰኔ 20፣ 2009 ዓ/ም ነው። ይህ አዋጅ በባህሪው የህዝብን ጥልቅ ግንዛቤና ይሁንታ የሚፈልግ ነው።

በመሆኑም በህዝብ ተወካዮች ብቻ ውይይት ተደርጎበት ከመጽደቅ ይልቅ ህዝብና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተወያይተውበት ቢያዳብሩት ተመራጭ ነው። የሚኒስትሮች ምክር ቤትም ረቂቁን ወደ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሲመራ በአዋጁ የመጽደቅ ሂደት በርካታ የህብረተሰብ ክፍሎች የሚሣተፉበት ይሆናል የሚል አስተያየት ሰጥቷል።

እርግጥ እንዲጸድቁ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚላኩ ረቂቅ አዋጆችን ወደህዝብ የመምራት አካሄድ ህገመንግስታዊ አይደለም። ዴሞክራሲ የውክልና ስርአት በመሆኑ እያንዳንዱን ረቂቅ አዋጅ መልሶ ለወካዩ መምራት ተገቢ ነው የሚል እምነትም የለኝም። ይሁን እንጂ አንዳንድ አዋጆች ህዝብ ላይ ውዠንብር ለመፍጠር ዓላማ የሚውሉበት ሁኔታ ስላለ ህዝብን ከውዥንብር ለመከላከል፣ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከጸደቁ በኋላ አፈጻጸም ላይ የሚከተለውን ችግር አስቀድሞ ለመከላከል ህዝብ ረቂቅ አዋጁን እንዲመለከተው መደረጉ  ተገቢ የሚሆነበት አግባብ አለ።

ረቂቅ አዋጁ ወደመጽደቅ ደረጃ ከመሸጋገሩ አስቀድሞ ህዝብ እንዲወያይበት ለማደረግ ሰፋ ያለ ጊዜ ይፈልጋል። ይህን ጉዳይ ምክር ቤቱ ለእረፍት ለመዘጋት ከቀሩት አምስትና ስድስት ቀናት አኳያ ተመልክተው፣ ብዙዎች ህዝብ ሳይወያይበት እንዳይጸድቅ ያላቸውን ስጋት ገልጸዋል። የምክር ቤቱ አባላትም ይህን የህዝብ ስጋት ተጋርተውታል። አባላቱ የምክር ቤቱ የዚህ አመት የስራ ዘመን ሊጠናቀቅ በተቃረበበት ወቅት ረቂቁ መቅረቡ አግባብ አይደለም ብለዋል። አንድ ሳምንት በቀረው የምክር ቤቱ የስራ ዘመን ማብቂያ ላይ የቀረበው ረቂቅ ከህዝብ ጋር ለመወያየት እንዴት ያስችላል? ሲሉም ጠይቀዋል።

ከአባላቱ ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ የሰጡት የኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አባዱላ ገመዳ፣ በረቂቁ ላይ በፍጥነትና በአጭር ጊዜ ውስጥ የመወሰን አካሄድ እንደማይኖር አስታውቀዋል። አንድ ሳምንት በቀረው የምክር ቤቱ የስራ ዘመን ረቂቅ አዋጁ ይፀድቃል ተብሎ እንደማይጠበቅም ገልጸዋል። በ25 አንቀጾች እና በአራት ክፍሎች በቀረበው ረቂቅ ላይ በሚነሱ ጥያቄዎች ዙሪያ ሰፊ ህዝባዊ ውይይቶች እንደሚካሄዱም አንስተዋል።

ይህ የኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ ላይ ያለውን ልዩ ጥቅም ለማሰጠበቅ የተዘጋጀ ረቂቅ አዋጅ ለውዥንብር የተጋለጠ ነው። በተለያየ ጽንፍ ላይ በቆሙ ጎራዎች – በጠባብ ብሄረተኞችም በትምክህተኞችም ያልሆነ ትርጉም እየተሰጠው የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት ዓላማ መዋሉ አይቀሬ ነው። አዋጁን ለፖለቲካ ትርፍ ለማዋል ውዠንብር የመፍጠሩ እንቅስቃሴ ካሁኑ ተጀምሯል።

ህዝብን የሚያደናግር መረጃ አነፍንፈው በማራገብ የሚታወቁ የአሜሪካ ድምጽ የአማርኛ ፕሮግራምን የመሳሰሉ አንዳንድ ጨዋ መሰል ሚዲያዎችም፣ ጉዳዩን ከእነማን ጋር ቢያራግቡት ለውዥንብር እንደሚጠቅም እያሰቡ መሆኑን የሚጠቁሙ ምልክቶች አሉ። አናም ህዝብ አዋጁን በማይደናገርበት አኳኋን እንዲገነዘበውና የእኔ ነው ብሎ እንዲቀበለው ለውይይት ማቀረብ አስፈላጊ ነው።

በመሆኑም በዚህ ዓመት ይጸድቃል በሚል ቃል መገባቱን ብቻ መነሻ በማድረግ በለብ ለብ እንዲጸድቅ የማይደረግ መሆኑ መገለጹ ለህዝቡ እፎይታ ሰጥቷል።  

ወደዋናው ጉዳይ እንመለስ። የኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ ላይ ያለውን ጥቅም የሚደነግገውን አዋጅ እንዲወጣ ያደረገው መሰረታዊ መነሻ የኢፌዴሪ ህገመንግስት ነው። አንዳንዶች ባለፈው ዓመት በኦሮሚያ ውስጥ ተቀስቅሶ የነበረውን ተቃውሞ አዋጁን ለማውጣት እንዳስገደደ ሁኔታ ሲያቀርቡ ይሰማል። የባለፈው ዓመት ተቃውሞ ኮርኳሪ ሆኖ ይሆናል እንጂ አዋጁን ለማውጣት መሰረታዊ መነሻ አይደለም። የኢፌዴሪ ህገመንግስት በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስትና በክልሉ መሃከል በምትገኘው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መካከል ያለውን ግንኙነት የሚዳኝ ድንጋጌ ባይኖረው ኖሮ አዋጁን ማውጣት ቀላል አይሆንም ነበር፣ ምናልባት አይቻልም ነበር።

የኢፌዴሪ ህገመንግስት አንቀጽ 49 ንኡስ አንቀጽ 5፤ በኦሮሚያ ክልል የአገልግሎት አቅርቦት ወይም የተፈጥሮ ሃብት አጠቃቀምንና የመሳሰሉትን ጉዳዮች በተመለከተ፣ እንዲሁም አዲስ አበባ በኦሮሚያ ክልል መሃከል የሚገኝ በመሆኑ የሚነሱ ሁለቱን የሚያስተሳስሩ አስተዳደራዊ ጉዳዮች በተመለከተ ያለው ልዩ ጥቅም ይጠበቅለታል። ዝርዝሩ በህግ ይወሰናል  ይላል።

ስለረቂቅ አዋጁ አጠቃላይ ሁኔታ ይህን ያህል ካልን፣ በቀጣይ በአዋጁ የተካተቱ በህዝብ ዘንድ ግልጽ እይታ ሊያዝባቸው ይገባል ያልኳቸውን የተወሰኑ ጉዳዮች ወደመመለከት እንሻገር። በዚህ ጽሁፍ አዲስ አበባ ውስጥ ስለሚደራጁ በኦሮሚኛ ቋንቋ የሚያስተምሩ ትምህርት ቤቶች፣ ኦሮሚኛ በአዲስ አበባ ውስጥ የስራ ቋንቋ ሆኖ ስለሚያገለግልበትና በአዲሰ አበባ ውስጥ ለሚኖሩ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት የመንግስት ሰራተኞች የኮንዶሚኒየም ቤት እጣ ኮታ በሚመለከት በረቂቅ አዋጁ ላይ የተደነገጉ ጉዳዮችን ለማንሳት ወድጃለሁ።

አዲስ አበባ ውስጥ በሚደራጁት በኦሮሚኛ ቋንቋ የሚያስተምሩ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እንጀምር። ረቂቅ አዋጁ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በከተማዋ ውስጥ በኦሮሚኛ ቋንቋ የሚያስተምሩ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶን ያደራጃል ይላል። እንግዲህ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ውስጥ በርካታ ነባር የኦሮሞ አርሶ አደሮች ይኖራሉ። እንዲሁም አዲስ አበባ ወይም ፊንፊኔ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ዋና ከተማ በመሆኗ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ የክልሉ የመንግስት ሰራተኞች ይኖራሉ። እነዚህ የኦሮሞ ተወላጆች ልጆቻቸውን በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ወይም በኦሮሚኛ ቋንቋ የማስተማር መብት አላቸው። በኦሮሚኛ ቋንቋ የሚያስተምሩ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ማደራጀት ያስፈለገው በክልላቸው መሃከል በምትገኘውና የክልሉ ርዕሰ መዲናም በሆችው አዲስ አበባ ወይም ፊንፊኔ የሚኖሮ ኦሮሞዎች ልጆቻቸውን በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው የማስተማር ህገመንግስታዊ መብታቸው መከበሩን ለማረጋገጥ ነው።

ልብ በሉ፤ ልጆች በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው የመማር ሀገመንግስታዊ መብት አላቸው። በዚህ መሰረት የኦሮሚያ ክልል የትምህርት መስጫ ቋንቋ ኦሮሚኛ ነው። ኦሮሚያ ውስጥ በተለይ የአዲስ አበባ ከተማ በቅርቡ የተስፋፋበቸው አካባቢዎች ነባር ነዋሪዎች ኦሮሞዎች ናቸው። እነዚህ ኦሮሞ የከተማዋ ነዋሪዎች የሚጠቀሙበት ቋንቋ ኦሮሚኛ ነው። ለጆቻቸውም አፍ የፈቱት በኦሮሚኛ ነው። እነዚህ ልጆች በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው የመማር ህገመንግስታዊ መብታቸው ሊረጋገጥላቸው ይገባል።

ከዚህ በተጨማሪ አዲስ አበባ ወይም ፊንፊኔ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት መቀመጫ ከተማ በመሆኗ በክልላዊ መንስቱ መስሪያ ቤቶች ውስጥ የሚሰሩ በረካታ ኦሮሞዎች አሉ። ከእነዚህ የክልሉ መንግስት ሰራተኞች መሃከል ልጆቻቸውን በኦሮሚኛ ቋንቋ ማስተማር የሚፈልጉ መኖራቸውም እርግጥ ነው።

የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት መቀመጣው ፊንፊኔ ወይም አዲሰ አበባ ቢሆንም ከተማዋን አያስተዳድርም። በዚህ ሳቢያ በከተማዋ ውስጥ በኦሮሚኛ ቋንቋ የሚያስተምሩ ትምህርት ቤቶችን ማቋቋም ወይም ማደራጀት የሚችለበት አግባብ የለም። ረቂቅ አዋጁ ላይ ትምህርት ቤቶቹን የአዲስ አበባ ከተማ እንዲያደራጅ የተደነገገው ለዚህ ነው።

በረቂቅ አዋጁ ላይ የተካተተው ሌላው ጉዳይ የኦሮሚኛ ቋንቋን ከአማርኛ በተጓዳኝ የአዲስ አበባ አስተዳደር የስራ ቋንቋ ሆኖ እንዲያገለግል ይደረጋል የሚለው ነው። እንግዲህ የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች በቋንቋቸው የመንግስት አገልግሎት የማግኘት መብታቸው በኢፌዴሪ ህገመንግስት ተረጋግጧል። በዚህ መሰረት በኦሮሚያ ክልል መሃከል በምትገኘው አዲስ አበባ ወይም ፊንፊኔ የሚኖሩና የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎት ተጠቃሚ የሆኑ የኦሮሞ ተወላጆች በቋንቋቸው አገልግሎት የማግኘት ህገመንግስታዊ መብት አላቸው። በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መስሪያ ቤቶች ኦሮሚኛ ከአማርኛ በተጓዳኝ የሥራ ቋንቋ ሆኖ እንዲያገለግል የተደነገገው ለዚህ ነው።

ይህ ማለት፣ ኦሮሚኛ አማርኛን ተክቶ የከተማ አስተዳደሩ የስራ ቋንቋ ሆኖ ያገለግላል ማለት አይደለም። በከተማዋ የሚገኙ ነባር የኦሮሞ ብሄር አባላትና ከተማዋ በክልሉ ውስጥ የምትገኝ በመሆኗ በብዛት በከተማዋ የሚገኙ ሌሎች ኦሮሞ ነዋሪዎች እንዲሁም የክልላዊ መንግስቱ የመንግስት ሰራተኞች በከተማ አስተዳደሩ መስሪያ ቤቶች፣ ፍርድ ቤቶችን ጨምሮ በኦሮሚኛ ቋንቋ መስተናገድ ይችላሉ ማለት ነው።

ይህም ማመልከቻቸውን በኦሮሚኛ የማቅረብ፣ ጉዳያቸውን በኦሮሚኛ ቋንቋ የማስረዳት፣ ፍርድ ቤት በኦሮሚኛ ቋንቋ የመሟገት መብትን ያጠቃልላል። ይህ ማለት የከተማ አስተዳደሩ ሰራተኞችና ዳኞች ኦሮሚኛ ቋንቋ መቻል አለባቸው ማለት አይደለም። ከዚህ ይልቅ መስሪያ ቤቶቹ አስተርጓሚ የማቆም ግዴታ ያለባቸው መሆኑን የሚያመለክት ነው። ልብ በሉ፤ በርካታ አማርኛ ተናጋሪዎች በሚኖሩባቸው የሰሜን አሜሪካ ግዛቶች አማርኛ የስራ ቋንቋ ሆኗል።

ይህ ማለት ግን የአሜሪካ መንግስት አማርኛ የሚችል የመንግስት ሰራተኛና ዳኛ ለመቅቀጠርና ለመሾም ይገደዳል ማለት ሳይሆን፣ አማርኛ ተናጋሪዎቹ በቋንቋቸው የመደመጥ መብት አላቸው፣ መንግስት ደግሞ ይህን ለማድረግ አስተርጓሚ ያቆማል ማለት ነው። የአዲሰ አበባው የኦሮሚኛ የስራ ቋንቋነትም ከዚህ የተለየ አይደለም።

በመጨረሻ የምመለከተው ብዙ ሰዎች የተደናገሩበት ሆኖ ያገኘሁትን ከኮንዶሚኒየም ቤቶች እጣ ካር ተያይዞ ያለውን ጉዳይ ነው። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር በመተባበር የኮንዶሚኒየም መኖሪያ ቤቶች አስገንብቶ በየወቅቱ በእጣ ሲያድል መቆየቱ ይታወቃል። በዚህ የእጣ አሰጣጥ ሴቶቸ 30 በመቶ፣ በከተማው የሚገኙ የከተማ አስተዳደሩና የፌደራል መንግስት መስሪያ ቤቶች የመንግሥት ሠራተኞት ደግሞ 20 በመቶ ልዩ ኮታ ተይዞላቸው እጣ ውስጥ እንዲገቡ ተደርጓል።

አሁን በተዘጋጀው የኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ ከተማ ላይ የሚኖረውን ህገመንግሥታዊ ልዩ ጥቅም አስመልክቶ የተዘጋጀው ረቂቅ አዋጅ፣ በከተማዋ ውስጥ የሚኖሩ የኦሮሚያ ክልል የመንግሥት ሠራተኞች ለፌደራል መንግስትናና ለአዲስ አበባ አስተዳደር ሰራተኞች የተሰጠውን ኮነዶሚኒየም ቤት የማግኘት መብት እንዲጠቀሙ የሚጠይቅ ነው። በአጠቃላይ የመንግስት ሰራተኞች የዚህ እድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ የተደረገበት የራሱ ምክንያት አለው። ከዚህ ጽሁፍ አጀንዳ ውጭ ስላልሆነ ይህን ጉዳይ ማንሳት አልፈልግም።

በአጠቃላይ ከላይ የተመለከትናቸውና ሌሎቹም ምናልባት በቀጣይ ጽሁፎች የማነሳቸው በቅርቡ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ተዘጋጅቶ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ ከተማ ላይ ያለውን ህገመንግሥታዊ ልዩ ጥቅም የሚመለከት ረቂቅ አዋጅ ላይ የሰፈሩ ድንጋጌዎች ኦሮሞዎች እና/ወይም በአዲስ አበባ ከተማ የሚኖሩ ኦሮሞዎች በሌሎች ብሄሮች መስዋእትነት እንዲጠቀሙ የሚያደርግ አንዳችም ነገር የለውም። ከዚህ ይልቅ የአዲስ አበባ ከተማና የኦሮሚያ ክልል ባላቸው ትስስር የተነሳ የተፈጠሩ ግንኙነቶች የሁሉንም ህገመንግስታዊ መብትና ነጻነት እንዲሁም ፍትሃዊ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት በሚያረጋግጥ ሁኔታ እንዲዳኙ ማድረግ የሚያስችል አዋጅ ነው።

የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስትና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ራስገዞች ቢሆኑም ፍጹም የተነጣጠሉ አካላት አይደሉም። ከዚህ ይልቅ በህገመንግስት የተሰጣቸው የራስገዝ ስልጣን እንደተጠበቀ አንድ ጠንካራ የጋራ የፖለቲካና ኢኮኖሚ ማህበረሰብ ወይም ሃገር ለመገንባት የሚሰሩ አካላት ናቸው። ይህን የጋራ የፖለቲካና ኢኮኖሚ ማህበረሰብ የመገንባት ዓላማ እንዲሳካ የአንዱ ጥቅም ከሌላው ጋር የሚጣረስ፣ የአንዱ ጥቅም በሌላው መስዋእትነት የሚገኝ መሆን የለበትም። እናም ከላይ የጠቀስነው ረቂቅ አዋጅ ዓላማ የጥቅም ሽሚያ አይደለም፣ ሁሉም ባለድርሻ ፍትሃዊ ተጠቃሚ እንዲሆን በማደረግ የጋራ ሃገር መገንባት እንጂ። ኦሮሞዎች namoonnii mana tokko ijaaran citaa walhinsaaman/ አንድ ቤት የሚሰሩ ሰዎች ሳር አይሻሙም” እንዲሉ።