አገር የሚያብበውም ሆነ የሚከስመው በወጣቶቹ ነው!
ውብሸት ሰንደቁ
በአጭርና ረጅም ልቦለዶቹ የሚታወቀው ደረሲ ስብሓት ገብረእግዚአብሔር ከልቦለዶቹ አንዱ በሆነው “ትኩሳት” በሚባለው የረጅም ልቦለድ መፅሐፉ ስለወጣትነት እንዲህ ይላል፡፡ “ጥሩ ነው ወጣት መሆን፡፡ ገንዘብ ባይኖርህም ጤና ይኖርሃል፣ አንጎል ባይኖርህም መልክ ይኖርሃል፣ ፍቅር ባይኖርህም ተስፋ ይኖርሃል፣ …. መጨቆን ቢበዛብህ ሪቮሉሽን ታነሳለህ….” እያለ በማተት ወጣትነት ከውበቱ ባሻገር የብዙ ተፈጥሯዊና ማህበራዊ ፈተናዎች አይቀሬነትን አሳይቶ ይፈቴነትንም አመላክቶ አልፏል፡፡
በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ያገኘሁዋቸው ወጣቶች ይህንኑ ከላይ የገለፅኩትን አባባል በብዙ መንገድ መገለጫቸው አድርገው አገኝቻቸዋለሁ፡፡ የኢትዮጵያ ሱማሌ ክልል ርዕሰ መዲና የሆነችው የጅግጅጋ በርካታ በተለያዩ መንግስታዊና መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች እንዲሁም በግል ስራ ላይ ተጠምደው ነጋቸውን ብሩህ ለማድረግ የሚታትሩ እልፍ ወጣቶች ባለቤት የሆነች ከተማ ናት፡፡ ከተማዋ እንኳን ለምትገኝበት የሱማሌ ክልል ይቅርና በሀገር ደረጃም በፈጣን እድገቷና የመሰረተ ልማት ዝርጋታዋ ተምሳሌት ልትሆን የምትችል ከተማ ነች፡፡ አዎ በቅን አይን ለተመለከተው ከተማዋ ተጨባጭ ለውጦችን በማሳየት ላይ ነች።
የዚች ከተማ ብሎም የክልሉ እድገት ታዲያ በቁስ ላይ ብቻ የተንጠለጠለ እንዳይደለና በሰው ሃብት ልማት ላይም እየተሰራ መሆኑን የሚያሳዩ በርካታ መገለጫዎችን ማንሳት ይቻላል፡፡ በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል በ2009 ዓ.ም በተከሰተው ድርቅ በአርብቶ አደሩ አካባቢዎች የሚገኙ 267 ትምህርት ቤቶች ተማሪዎች ትምህርታቸው እንዳይደናቀፍ የክልሉ መንግስት ከፌዴራል መንግስት ጋር በመተባበር ለተማሪዎች የምገባ ፕሮግራም በማካሄድ ላይ ይገኛል፡፡ በዚህም ተማሪዎች ትምህርታቸውን እንዳያቋርጡ በጎ ተፅእኖ ተፈጥሯል፡፡ ይህ የተማሪዎች የምገባ መርሐግብር ቀጣይነት እንዲኖው ለማድረግ የክልሉ መንግስት ከህብረተሰቡና ከፌዴራል መንግስቱ ጋር በቅርበት እየሰራ ይገኛል።
በክልሉ 161 የመሰናዶና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ያሉ ሲሆን በሚቀጥለው ዓመት ደግሞ የተለያዩ ደረጃዎች ያላቸው 20 አዳዲስ ትምህርት ቤቶችን ለመገንባት እቅድ መያዙን የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ መሐመድ አህመድ ኑር ገልፀውልኛል፡፡ ከዚህም ባለፈ በጅግጅጋ ከሚገኘው ጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ በተጨማሪ የቀብሪደሃር ዩኒቨርሲቲም በ2010 ዓ.ም ስራ እንደሚጀምር ተገልጾልኛል፡፡ ከዚህ ቀደም ባሉት መንግስታት የአርብቶ አደር አካባቢዎች እንኳን የከፍተኛ የትምህርት ተቋም ሊያገኙ ይቅርና በክልሉ የነበሩትየ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ቁጥር ሁለት ብቻ ነበሩ። በክልሉ በርካታ የሙያ ማሰልጠኛ ተቋማት ተገንብተዋል። በ2009 ዓ.ም በጎንደር ከተማ በተካሄደው 7ኛው የኢትዮጵያ ከተሞች ፎረም ላይ ጅግጅጋ “የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ተቋማት የላቀ አፈፃፀም” ተሸላሚ ለመሆን በቅቷል፡፡ ይህ ለክልሉ ትልቅ ስኬት ነው።
በቴክኒክና ሙያ ስልጠና፣ በወጣቶችና ስፖርት ቢሮ እንዲሁም የአነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎች ቢሮ ከከተሞች የምግብ ዋስትናና የስራ ፈጠራ ጋር በመተባበር ለወጣቱ በርካታ የስራ እድሎችን በመፍጠር ላይ ናቸው። እነዚህ ተቋማት በመቀናጀት የወጣቱን አቅም በማጎልበት የክህሎት ክፍተቱን በመሙላት ረገድ እየተሰራ ያለው ስራ ይበል የሚያሰኝ ነው፡፡ ተዘዋውሬ ካየኋቸውና የሰዎችን የኢኮኖሚ ደረጃ ብቻ ሳይሆን የሰዎችን አስተሳሰብ ጭምር ከጎፈር ወደ ዘውድ፣ ከጫካና በረሃ ወደ ቤት፣ ከጎዳና ተዳዳሪነት ወደ ሙያ ባለቤትነት በመለወጥ በአስደማሚ መልኩ፤ ካገኘኋቸው ውስጥ ጥቂቶቹን ማካፈል ወደድኩኝ፡፡
በጅግጅጋ 50 ወጣቶች ተደራጅተው ካቋቋሙት ኅልገን የቤትና የቢሮ እቃዎች ማምረቻ ድርጅት አንዳንዶቹ ወጣቶች ከጥቂት ዓመታት በፊት ነፍጥ አንስተው ከሽብርና ፀረ ሰላም ሃይሎች ጋር ወግነው የተሰለፉና አንዳንዶቹ ከባድ ሌሎቹ ደግሞ ቀላል የሚባል የአካል ጉዳት የደረሰባቸው ናቸው፡፡ ወጣቶቹ እንደነገሩኝ የነበሩበትን መንገድ ሲያጤኑና ውሎ አድሮ ጉዳዩ ሲገባቸው እየተዋጉ ያሉት ከዋናው ጠላታቸው ጋር ሳይሆን ከወገናቸው ጋር መሆኑን እንደተገለጠላቸው ይናገራሉ፡፡ ዘግይተውም ቢሆን እውነታው ሲገለጥላቸው የሰላምን ዋጋ ተረዱ፣ ለመንግስትም እጃቸውን ሰጥተው መፀፀታቸውን አስረዱ፡፡ መንግስትም መጸጸታቸውን ተገንዝቦ ይቅር በማለት ወደ ልማት የሚገቡበትን ሁኔታ አመቻቸላቸው።
አነኝህ ወጣቶች ዛሬ እጃቸው የሚያገላብጠው ክላሽንኮቭ፣ መትረየስ ወይም ቦምብ አይደለም፡፡ አሁን ላይ የእነዚህ ወጣት እጆች ጨብጠው የሚውሉት ዋናው ጠላታቸው የሆነውን ድህነት መዋጋት የሚያስችሉ ሞርሳ፣ መላጊያ፣ መጋዝና እስኳድራ እና ሌሎች ዘመኑ ያፈራቸውን የቤትና ቢሮ እቃዎች ማምረቻ የሆኑትን መሳሪያዎች ነው፡፡ ዛሬ ወገናቸውን ከመግደል፣ አካል ከማጉደልና ከማሳቀቅ ተላቀው ለማህበረሰባቸው ተጨማሪ የገበያ አማራጭና ምቾት፤ ለለራሳቸውም አለኝ የሚሉት ሀብትና ንብረት በማፍራት ላይ ናቸው፡፡
በአሁኑ ጊዜ ከነዚሁ ወጣቶች ጋር ተቀላቅሎ የሚሰራውና ከዚህ ቀደም ጊዜውን ባልባሌ ቦታ ያሳልፍ የነበረ መሆኑን የነገረኝ ወጣት አህመድ መሐመድ አብዱ በጅግጅጋ ቀበሌ 12 ነዋሪ ነው፡፡ ወጣቱ እዚህ ድርጅት ውስጥ በመስራቱ ብዙ ነገሮችን እንዳፈራ ይናገራል፡፡ በራሱ የሚኮራበት የሙያ ባለቤት ከመሆኑም በተጨማሪ በህይወቱ እና በቤተሰቡ ላይ ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት እንደቻለ ይናገራል። ወጣት አህመድ እንደሚለው ዛሬ ራሱን ችሎ ከመኖር ባለፈ ለሌሎችም መትረፍ ችሏል።
ወጣት አህመድ የሚሰራበት ኅልገን የቤትና የቢሮ እቃዎች ማምረቻ ከመቋቋሙ በፊት መንግስት ወጣቶቹ አስፈላጊውን ስልጠና እንዲያገኙ በማድረግ 1 ሚሊዮን ብር በማበደር የተጀመረው ተቋም በ6 ወር ውስጥ ካፒሉ ከእጥፍ በላይ አድጓል፡፡ በወጣት አህመድ ድርጅት ውስጥ ወንበሮች፣ ጠረጴዛዎች፣ አልጋዎች፣ በሮችና የመሳሰሉትን የቤትና የቢሮ እቃዎች በማምረት የክልሉ መንግስት በፈጠረላቸው የገበያ ትስስር ለተጠቃሚዎች እንደሚያቀርቡ አጫውቶኛል፡፡ በተመሳሳይ ሌሎች ያነጋገርኳቸው ሰራተኞችም እንዳሉኝ ይህ ድርጅት በመቃቋሙ ህይወታቸው መለወጥ መጀመሩንና አሁን ላይ ቁጠባ እንደጀመሩም ነግረውኛል።
የክልሉ መንግስት በሚያደርገው ድጋፍና ክትትል በድርጅታቸው የነበረውን የመብራትና የመሳሪያ እጥረት በእጅጉ እንደቀረፈላቸው ሰራተኞች በአንደበታቸው ይመሰክራሉ። ከዚህ ቀደም መንግስት እንዳደረገላቸውና እያደረገም እንዳለው ለአዳዲስና ለዘመናዊ ማሽኖች አጠቃቀም የሙያ ስልጠና በመሰጠት ላይ እንደሆነም መረዳት ችያለሁ፡፡ ይህ የመንግስት ክትትልና ድጋፍ ይበል የሚያሰኝ ነው።
በወጣቶችና ስፖርት ቢሮ በ15/10/09ዓ.ም በድንገት በደረስኩት ጊዜም በርከት ያሉ ወጣቶች በቢሮው ቅጥር ውስጥ ተሰብስበው አገኘኋቸው፡፡ ቢሮው ከፌዴራል መንግስት በተለቀቀው የወጣቶች ፈንድና ክልሉ በራሱ አቅም በመደበው ገንዘብ ለ781,389 ለሚሆኑ ወጣቶች የስራ እድል ለመፍጠር አቅዶ እየተንቀሳቀሰ እንደሆነ መረዳት ችያለሁ። እስካሁን ባለው ለ1,116 የሚሆኑ የጅግጅጋ ወጣቶች ስልጠና መሰጠታቸውንና ወደስራ ለመግባት ዝግጅታቸውን ማጠናቀቃቸውን ከነዚህም ውስጥ ደግሞ 491 ወጣቶች ለስራ ማስኬጃ የሚሆናቸውን ገንዘብ ለመቀበል በቢሮው ቅጥር ውስጥ ተሰብስበው እንደሚገኙ ተመልክቻለሁ፡፡
ከእነዚህ ወጣቶች መካከል መሀመድ ሐሰን አሊ አንዱ ነበር፡፡ በጅግጅጋ ከተማ 09 ቀበሌ ነዋሪ ነው፡፡ በአካባቢው ከሚኖሩ ሌሎች 5 ወንዶችና 4 ሴቶች ጋር ተደራጅቷል፡፡ ወጣቱ በተሰማራበት የእንስሳት እርባታ ስለ እንስሳት አያያዝ፣ ስለመኖ አዘገጃጀትና አቀራረብ እንዲሁም ስለእንስሳት ጤና አጠባበቅ በተመለከተ ስልጠና ማግኘቱን ነገረኝ፡፡ ወጣት መሐመድ እና ከሱ ጋር የተደራጁት ሌሎች ዘጠኝ ወጣቶች ሰፊ ቅድመ ዝግጅት ማድረጋቸውን እና ለነሱም ሆነ ለሀገር የሚጠቅም ስራ እንደሚሰሩ ተስፋ አንግበው በመንቀሳቀስ ላይ ናቸው፡፡ ወጣትነት ተስፋን በተግባር ለመተርጎም ትልቅ አቅም እንዳለው በመረዳቴ በውስጤ ለወጣቶቹ መልካም ነገር ተመኘሁላቸው።
ከዚሁ ቅጥር ሳልወጣ እንስት ወጣት ሃዊያ አብዲ ሁሴንን አገኘኋት፡፡ በጅግጅጋ ቀበሌ 19 ነዋሪ ነች፡፡ እንደሌሎች ወጣቶች ሁሉ የዚህች እንስት ቡድንም አራት ሴትና አራት ወንዶችን አካቶ በመደራጀት ስልጠና ወስደው ቢዝነስ ፕሮፖዛል በመቅረጽ ቅድመ ዝግጅታቸውን አጠናቀዋል፡፡ የእነሃዊያ አብዲ ቡድን ለመስራት የመረጡት በግብርናው ዘርፍ መሆኑን አጫወተችኝ፡፡ ሰፊ ሀገር፣ ሰፊ ክልል አለን። ይህን ተጠቅመን ጎንበስ ብለን በመስራት ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ እራሳችንንም ሀገራችንንም እንጠቅማለን ስትል ሃዊያ በዕርግጠኝነት ትናገራለች፡፡ ከመንግስት ቢደረግልን የምትለው ድጋፍ እንዳለ በጠየኳት ጊዜም ከዚህ በፊት ለተደረገላቸው ሁሉ ምስጋናዋን በማቅረብ ወደፊትም ወደስራ ሲገቡ የመሬት አቅርቦት እጥረት ሊገጥማቸው ስለሚችል መንግስት ተጨማሪ መሬት ቢያዘጋጅላቸው እንደምትወድ ገለጸችልኝ፡፡
እስካሁን በክልል ደረጃ የስራ እድል የተፈጠረላቸው ወጣቶች ወደ 28,365 (ሃያ ስምንት ሺህ ሦስት መቶ ስድሳ አምስት) የሚጠጉ ሲሆን ይህንን ተግባራዊ ለማድረግም 114,454,000 ብር ወጪ ተደርጓል፡፡ አሁንም በክልሉ ከሚገኙ ወረዳዎች ከእያንዳንዳቸው 40 ወጣቶች እንዲመለመሉ ተደርጎ ስልጠና እየተሰጣቸው ነው፡፡ ከነዚህ ውስጥ ደግሞ 70 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች ናቸው፡፡ ሁሉም ሰልጣኞች ቢዝነስ ፕላን እያዘጋጁ ወደስራ እንዲገቡ እድሎች ተመቻችቶላቸዋል፡፡ አንድ ክልል ብሎም ሀገር ሊያድግ የሚችለው ያለውን ሃብትና የሰው ሃይል በተደራጀና በተቀናጀ መልኩ ሲጠቀም ነው፡፡ መንግስት ለወጣቶች የስራ እድል ፈጠራ እያደረገ ያለው ጥረት ተጠናከሮ መቀጠል ይኖርበታል። ክልሎች አብበው የሚያፈሩት ወጣቶቻቸውን እንደሀብት ቆጥረው ጉልበታቸውንና አእምሯቸውን ባግባቡ ሲጠቀሙት ነው። ይህ ካልሆነ ውጤቱ በተቃራኒው ይሆንና አደጋው የከፋ ይሆናል። በመሆኑም የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ ለወጣቶች ተገቢውን ድጋፍና ክትትል ማድረግ ይኖርባቸዋል።