ኢህአዴግ እና ተቃዋሚ ፓርቲዎች ከትናንት እስከ ዛሬ (ክፍል 1)
ሰለሞን ሽፈራው
ሀገራችን ኢትዮጵያ ስር ከሰደደ ድህነትና ኋላ ቀርነት ለመላቀቅ የሚያስችላት ትክክለኛ የልማት አቅጣጫ ላይ የምትገኝ ስለመሆኗ መላው የዓለም ማህበረሰብም ጭምር ይስማማበታል፡፡ ለዚህ ደግሞ በርካታ የምዕራባውያን ባለፀጋ ሀገራት መሪዎች ሳይቀሩ ወደ አዲስ አበባ ለይፋዊ ጉብኝት እየመጡ ከኢትዮጵያ ፌደራላዊ መንግስት ጋር ያላቸውን የሁለትዮሽ ግንኙነት ይበልጥ ስለማጠናከር ጉዳይ ሲመክሩ ማየት የዘወትር ተግባር ከሆነ መሰነባበቱን እንደ አብነት ማንሳት በቂ ይመስለኛል፡፡ ይሁን እንጂ የዛሬዋ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ዘንድ አድናቆትንና ከበሬታን ኢያገኘትበት ያለውን ፈርጀ ብዙ በጎ ገጽታዋን ላልታሰበ የቅልበሳ አደጋ ሊያጋልጡ ከሚችሉ ውስጣዊ ችግሮች የጸዳች ሀገር እንዳልሆነችም ደፍሮ መናገር ይቻላል፡፡
በተለይም ደግሞ፤ የዓለም አቀፉን ማህበረሰብ ቀልብ እየሳበ ስለመምጣቱም ጭምር ለሚታመንበት የፌደራሊዝም ስርዓታችንና እንዲሁም ለፈርጀ ብዙ ትሩፋቶቹ በጎ አመለካከት የሌላቸው ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች፤ ከትናንት አስከ ዛሬ የሚታወቁበት ጽንፈኛ አቋም በስርነቀል የለውጥ ሂደቱ ላይ የተጋረጠ አሳሳቢ አደጋ ተደርጎ ይወስዳል፡፡ በድህረ-ደርግ ኢትዮጵያ ውስጥ ለተከፈተው አዲስ የታሪክ ምዕራፍ አንድም ቀን እንኳን ተገቢ እውቅና ሲሰጡ ተደምጠው የሚያውቁት የሀገራችን ጽንፈኛ ተቃዋሚ የፖለቲካ ኃይሎች፤ ሕገ መንግስታዊ ስርዓቱን ለመደርመስና በአቋራጭ ስልጣን ላይ ለመውጣት ያለመ የአመጽ ሴራቸውን ከማውጠንጠን የታቀቡበት አጋጣሚ እንዳልነበረም ደፍሮ መናገር ይቻላል፡፡
ከዚህም የተነሳም፤ በኢህአዴግ የሚመራው የኢፌድሪ መንግስት፤ የጉዳዩን አሳሳቢነት ተገንዝቦ፤ ከተቃዋሚዎቹ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በመቀራረብና በመደማመጥ የተሻለ የጋራ መግባባትን መፍጠር ስለሚቻልበት ሁኔታ ይበጃል ያለውን የመፍትሄ ፍለጋ ጥረት ከማድረግ የተቆጠበበት አጋጣሚ የለም፡፡ ለዚህ አስተያየቴ ተጨባጭ ማሳያ ይሆናሉ የምላቸው አብነቶችም ደግሞ፤ ኢህአዴግ ገና ከሽግግሩ መንግስት ዘመን ጀምሮ በሀገራችን የተከፈተው አዲስ የታሪክ ምዕራፍ፤ የኢትዮጵያ ጉዳይ ይመለከተናል የሚሉ የፖለቲካ ኃይሎችን በሙሉ የሚያካትት ሆኖ እንዲመቻች በማድረግ ረገድ ያሳየው ጥረትና ከዚያን ጊዜው ሰፊ የዴሞክራሲያዊ ስርዓት መገለጫ ምህዳር ወዲህም በተለያዩ መድረኮች ላይ ለተቃዋሚ ፓርቲዎች እንቅስቃሴ ተገቢ ስፍራ እየሰጠ ለማስተናገድ ሲሞክር የተስረተዋለበትን ሆድ ማስፋት ነው፡፡
ምንም አንኳን የደርግ ኢ.ስ.ፓ ወታደራዊ አገዛዝ ይጠቀምበት የነበረውን መጠነ ግዙፍ የአፈና መዋቅር ለማፈራረስ ሲባል በተካሄደው እጅጉን ፈታኝ የትጥቅ ትግል ጉዞ የአንበሳውን ድርሻ የሚወስድ ሚና የተጨወተው ኢህአዴግ መሆኑ ቢታወቅም፤ ግን ደግሞ ከግንቦት 20ው ድል ማግስት እንደ አሸን መፍላት ለጀሀመሩት ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ያሳየው ሆደ ሰፊነት የሚስተባበል አይደለም፡፡ ግንባሩ ያን ዓይነት አቋም ያሳየው ደግሞ፤ የትግሉ አልፋና ኦሜጋ የሀገራችንን ፖለቲካዊ ችግሮች በማያዳግም መልኩ ለመፍታት የሚያስችል ዴሞክራሲያዊ የጋራ መድረክ እንዲፈጠር ማድረግ እንደመሆኑ መጠን፤ የሰማዕታቱን አደራ አክብሮ ለመገኘት ሲል እንጂ በሌላ ምክንያት አልነበረም፡፡
እናም ኢህአዴግ እንደ አብዛኛዎቹ በትጥቅ ትግል ሂደት አልፈው ወደስልጣን እንደመጡ የአፍሪካ ሀገራት ገዢ ፓርቲዎች ማን አለብኝነትን ከማሳየት ይልቅ፤ ኢትዮጵያ በቀደመው ታሪኳ የምትታወቅበትን መሰረታዊ የፖለቲካ ችግር ለመፍታት የሚያስችል ዴሞክራሲያዊ ምህዳር የመፍጠርን አስፈላጊነት አበክሮ ከመገንዘብ በመነጨ ሆደ ሰፊነት ተቃዋሚዎችን አይቶ እንዳላየ ሲያልፍ ስለመቆየቱ ራሳቸውም ጭምር የሚክዱት ጉዳይ አይመስለኝም፡፡ ለምሳሌ ያህል የኤርትራውን ሻዕቢያ ጨምሮ፤ በኦጋንዳና በዚምባዌ እንዲሁም ደግሞ በደቡብ ሱዳን ተመሳሳይ ይዘት እንደነበረው የሚነገርለትን ጸረ ጭቆና የትጥቅ ትግል ጉዞ አልፈው ስልጣን ለመጨበጥ የበቁት የፖለቲካ ፓርቲዎች፤ የኢህአዴግን ያህል ለየሀገሮቻቸው ችግር ዘላቂ መፍትሄ ከመሻት የመነጨ ሆደ ሰፊነት ሲያሳዩ የተስተዋሉበት አንድም ትርጉም ያለው ጥረት አለመኖሩን ነው መረጃዎች የሚያመለክቱት፡፡
እንዲያውም በተጠቀሱት የአፍሪካ ሀገራት ጸረ ጭቆና የትጥቅ ትግል አካሂደው ወደ ስልጣን የመጡ የፖለቲካ ፓርቲዎች የኋላ ኋላ እነርሱ ራሳቸው የለየለትን የማን አለብኝነት አቋም የሙጥኝ ሲሉ ከተስተዋሉበት አሳዛኝ እውነታ አኳያ ሲታይ በኛ አገር ውስጥ የሆነው ኢህአዴግ የትግሉ ሰማዕታት ለወደቁለት መሰረታዊ ዓላማ ታምኖ በመገኘት ረገድ ከሁሉም የተሻለ ተደርጎ ሊወሰድ እንደሚችል ነው የምንረዳው ጉዳይ፡፡ እንዳለመታደል ሆኖ ግን፤ ይህንን የገዢው ፓርቲ ጠንካራ ጎን አምኖ በመቀበልና ተገቢ እውቅና በመስጠት ዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ ምህዳሩን ይበልጥ ለማስፋት የሚያስችል የየራሳቸውን ተጨማሪ ገንቢ አስተዋጽኦ ከማበርከት ይልቅ፤ ጭራሽ የተስፋ ጭላንጭል እንዳልፈነጠቀ አድርገው የሚቆጠሩ ጨለምተኛ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ናቸው እኛ አገር ውስጥ የሚመሰረቱት፡፡ሁሉንም ማለቴ ግን እነዳልሆነ ይታወቅልኝ፡፡
ይህ የሆነበትን ምክንያት በተመለከተ የተለያየ ሃሳብ ሲዘነዝሩ የሚደመጡ ወገኖች ቢኖሩም፤ በይበልጥ ሚዛን የሚደፋው አስተያየት ግን፤ አብዛኛዎቹ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ኢህአዴግ መራሹን የኢትዮጵያ ህዝቦች ትግል የሚመለከቱበት መነጽር ከደርግ ኢ.ስ.ፓ የ“ገንጣይ አስገንጣይ” ውንጀላ የተወረሰ ስለሆነና ስር ነቀል የስርዓት ለውጡን በፀረ የሀገር አንድነት ለመፈረጅ ስለሚቃጣቸውም ጭምር ነው የሚል ሆኖ አግኝቸዋለሁ፡፡ ሌላው ከዚሁ ነጥብ ጋር በተያያዘ መልኩ ምክንያት የሚነሳ ጉዳይ ደግሞ፤ በተለይም እንደነ ኢ.ህ.አ.ፓ.መ.ኢ.ሰ.ን እና ኦ.ነ.ግ ዓይነቶቹ ነባር የፖለቲካ ደርጅቶች ኢህአዴግ መራሹ ፀረ ጭቆና የትጥቅ ትግል ደርግን አስወግዶ ወደ ስልጣን በመምጣቱ ቅናት ስሜት አድሮባቸው ስለነበር የለውጥ ሂደቱን ገና ከመነሻው ጥላሸት ለመቀባት ሲሞክሩ የተስተዋሉበት አግባብ የማይናቅ አሉታዊ ተጽዕኖ ፈጥሯል የሚል ነው፡፡
በእርግጥም ደግሞ አሁንም ድረስ የፌደራል ስርዓቱን ላልተጠበቀ የቅልበሳ አደጋ የሚያጋልጥ የአመጽ ተግባር ለመቀስቀስና ሕገ መንግስታዊ ስርዓቱን በመናድ ስልጣን ለመቆናጠጥ ያለመ የተቃውሞ ፖለቲካ እንቅስቃሴ የሚያደርጉት ቡድኖች ከላይ የተጠቀሱት የ1960ዎቹ ፓርቲዎች የሚታወቁበትን ህቡዕ የመግባት አባዜ በተከተለ ድብብቆሽ ነው እቺን ሀገር ሊያተራምሷት ሲሞክሩ የሚስተዋሉት፡፡ ስለዚህም ገና ከትጥቅ ትግሉ ዘመን ጀምሮ በኢህአዴግ ጥርስ የነከሱበትን ተሸናፊ ኃይሎች ወክለው አዲሱን የታሪክ ምዕራፍ ሲወቅሱና ሲከሱ የምናውቃቸው የ1960ዎቹ ፓርቲዎች አባላት፤ በድህረ ደርግ ኢትዮጵያ ውስጥ የተጀመረውን ሰላማዊ የተቃውሞ ፖለቲካ እንቅስቃሴ ወደለየለት ጭፍን ጥላቻ እንዲያመራ ያደረገ አሉታዊ ተጽእኖ ማሳደራቸው የሚካድ ጉዳይ አይደለም፡፡
ከዚህ የተነሳም፤ ኢህአዴግ እንደ አንድ በትጥቅ ትግል ሂደት ውስጥ አልፎ ወደ ስልጣን የመጣ ገዢ የፖለቲካ ፓርቲ፤ እጅግ በርካታ የትግሉ ሰማእታት የወደቁለትን፤ መላ የብሔር ብሔረሰብ ህዝቦቿ ዕርስ በርስ ተፈቃቅደውና ተፈቃቅረው በእኩልነት የሚኖሩባት ዴክሞራሲያዊት ኢትዮጵያን የመመስረት ዓላማ አንግቦ፤ ከትናንት እስከ ዛሬ ዓላመውን ለማሳካት ሲል ያደረገው ያላሰለሰ ጥረት ሁሉ፤ ከላይ የተጠቀሱት ተቃዋሚ የፖለቲካ ኃይሎች በሚፈጥሩት ውስብስብ ችግር ምክንያት ሲፈተን ቆይቷል፡፡ ለዚህ ደግሞ ኢህአዴግ መራሹ የኢፌድሪ መንግስት አዲሱ የታሪክ ምዕራፍ ከተከፈተበት የሽግግር ዘመን ጀምሮ፤ አስከ ሰሞነኛው የፓርቲዎች ውይይትና ድርድር መድረክ ድረስ በዘለቀ የስር ነቀል ለውጡ ሂደት ውስጥ ለዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ያሳየውን የፖለቲካ ቁርጠኝነት ማስታወስ ይቻላል፡፡
ሌላውን ትተን የምርጫ 97ቱን አስገራሚ የህዝብ ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ የመነሳሳት መንፈስ የፈጠረውን ምቹ ቅድመ ሁኔታ በማሟላት ረገድ የኢፌድሪ መንግስት ያሳየውን የፖለቲካ ቁርጠኝነት ብቻ እንኳን ከጭፍን ተቃውሞ በፀዳ ስሜት አስታውሰን ብንመረምረው፤ የኔ አስተያየት በእርግጥም ከሚዛናዊ የህሊና ፍርድ የመነጨ እንጂ፤ ተራ ውዳሴ ከንቱ እንዳልሆነ መረዳት የሚቻል ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ፤ ሀገራችን ኢትዮጵያ ግንቦት ሰባት ቀን 1997 ዓ.ም ባካሄደችው ጠቅላላ ምርጫ ላይ የተስተዋለውን መጠነ ሰፊ የህዝብ ተሳትፎ ያስከተለው መሰረታዊ ጉዳይ፤ ገዢው ፓርቲና መንግስት “ዲሞክራሲ ለኛ የህልውና ጥያቄ እንጂ አማራጭ አይደለም” ከሚለው የኢህአዴግ ጽኑ አቋም በመነጨ የፖለቲካ ቁርጠኝነት ተነሳስተው የፈጠሩት ምቹ ቅድመ ሁኔታ ከመሆኑም ባሻገር፤ ተቃዋሚዎች ያን ያህል ያልተጠበቀ የህዝብ ድምጽ አግኝተው በአንዳንድ አካባቢዎች እንዳሻነፉ የተረጋገጠበት የብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ውጤት ይፋ መደረጉን ተከትሎ ኢህአዴግ ውጤቱን ያለ ምንም ማቅማማት እንደሚቀበለው ማሳወቁ ይታወሳልና ነው፡፡
በቀድሞው የኢፌድሪ ጠቅላይ ሚኒስቴር በክቡር አቶ መለስ ዜናዊ አማካኝነት የቀረበው የኢህአዴግ መግለጫ ይዘት “የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባወጣው ሪፖርት ላይ የተገለፀውን ውጤት ተቀብለን፤ አዲስ አበባን ጨምሮ በሌሎችም የሀገራችን አንዳንድ ከተሞች ህዝቡ ድምጹን ከሰጣቸው ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር አብረን ለመስራት ዝግጁ ነን” የሚል እንደነበርም ማስታወስ ይቻላል፡፡ ይሁን እንጂ፤ ከመ.ኢ.ሶ.ኑ ነገደ ጎበዜ፤ እሰከ የኢ.ህ.አ.ፓው ክፍሉ ታደሰ የሚደርሱ ዲያስፖራ ፖለቲከኞች እንዳቀነባበሩት ተደጋግሞ የተነገረለትን “ቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ” የተሰኘ የአንድ ሰሞን ስብስብ ወክለው በ1997ቱ ጠቅላላ ምርጫ የተሳተፉት ተቃዋሚ ፖለቲከኞች “ከኢህአዴግ ያነሰ ድምጽ ተቀብለን ወደ ፓርላማ መግባትማ ውርደት ነው!” የሚል ግትር አቋም ይዘው ሕገ መንግስቱን በጎዳና ላይ ነውጥ ለመናድ ያለመ የአመፃ ተግባር ለመቀስቀስ ተጣደፉ፡፡
እናም ኢህአዴግን ሙሉ በሙሉ አስወግደው ሀገር የመምራቱን ስልጣን በብቸኝነት የመቆጣጠር ምኞት ያናወዛቸው የቀድሞው ቅንጅት ነውጠኛ አመራር አካላት፤ የአዲስ አበባን ድሀ ህዝብ ወጣት ልጆች ለአመጽ ተግባር አነሳስተው ወደ አራት ኪሎው ቤተ መንግስት ያዘመቱበት ሁኔታ እንደነበር አይዘነጋም፡፡ በዚሁ ከንቱ ሙከራቸው ምክንያት ለደረሰው የህይወትና የንብረት ኪሳራ ሕግ ፊት ቀርበው ይጠየቁ ዘንድ ግድ ስለነበረም አብዛኞዎቹ የስብስቡ አመራር አካላት ላይ ክስ ተመስርቶባቸው ጥፋተኛነታቸው ሲረጋገጥ በዕድሜ ልክ ጽኑ እስራት እንዲቀጡ ጉዳዩን ያየው የፌደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ብይን ሰጠ፡፡ ይሁን እንጂ ብዙም ሳይቆዩ ሕገ መንግስታችን ላይ በተደነገገው ይቅርታ የመጠየቂያ አግባብ እያንዳንዳቸው በፈፀሙት ስህተት እንደተፀፀቱና ዳግመኛ በመሰል ተግባር እንደማይሳተፉም ጭምር ገልጸው የምህረት ይደረግልን ጥያቄያቸውን ለሪፐብሊኳ ፕሬዚዳንት ስላቀረቡ በነፃ መለቀቃቸው ተሰማ፡፡
ጉዳዩ ሀገራችን ኢትዮጵያ የጀመረችውን የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ሂደት ይበልጥ በተጠናከረ መልኩ ለማስቀጠል የሚረዳ ብሔራዊ የጋራ መግባባት እንዲሰፍን የሚጋብዝና የኢህአዴግ መራሹን መንግስት የተለመደ ሆደ ሰፊነት የሚያመለክት ሆኖ ስላገኘነውም፤ እንብዛም ቅር አልተሰኘንም ነበር፡፡ ምክንያቱም ደግሞ የይቅርታ ይደረግልን ደብዳቤ ለቀድሞው የኢፌድሪ ፕሬዚዳንት ለክቡር አቶ ግርማ ወ/ጊዮርጊስ ጽፈው ምህረት እንደተሰጣቸው ስንሰማ፤ ቢያንስ እነርሱ ወደ አዕምሯቸው እንደተመለሱና ለሕገ መንግስታዊ ስርዓቱ ተገቢ ክብር ከመስጠት ውጪ አማራጭ የፖለቲካዊ ትግል መንገድ ሊኖር እንደማይችል የተገነዘቡ አድርገን ከመገመታችን የተነሳ ነበር፡፡
ዳሩ ምን ዋጋ አለው? የኛ ግምት ከተራ ቅንነት የመነጨ የስሌት ስህተት መሆኑን በተግባር ሲያረጋግጡልን ጊዜ አልፈጀባቸውም ጽንፈኞቹ ተቃዋሚ ፖለቲከኞች፡፡ ለአብነት ያህልም ከቀድሞ የኢ.ህ.አ.ፓ አባላት መካከል አንዱ ተደርጎ የሚወሰደውና በምርጫ 97ቱ ክስተት ምክንያት እድሜ ልክ ተፈርዶባቸው ከነበሩት የቅንጅት መሪዎች ጋር ምህረት ጠይቆ የተፈታው ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ፤ በምን ያህል ፍጥነት ወደ ሁለተኛ አገሩ (አሜሪካ) ተመልሶ “ግንቦት ሰባት” የተሰኘውን የሽብር ቡድን ሰለመሰረቱ ሲናገር እንደተደመጠ ማስታወስ ይበቃል፡፡ ለነገሩ እዚሁ አገር ውስጥ የሚገኙት የቀድሞው ቅንጅት አመራር አካላትና እንዲሁም አባላት ጭምር በሕገ መንግስቱ አስፈላጊነት ላይ ምን ከዚያን ጊዜው አቋማቸው የተለየ አዝማሚያ አሳይተውን ያውቃሉ? እንዲያውም እውነቱን አንነጋገር ከተባለማ መንግስት በቀድሞው ቅንጅት ነውጠኛ አመራር ላይ ፍረድ ቤት የሰጠው የዕድሜ ይፍታህ እስር ውሳኔ የሻረበት ይቅርታ የመጣው ውጤት ምናልባትም ሰከተጠበቀው በተቃራኒ ሳይሆን እንዳልቀረ ነው ጥሬ ሀቁ የሚያረጋግጥልን፡፡
ይህን ስልም ደግሞ፤ በተለይ ትምክህትና ጠባብ ብሔርተኝነት ተብለው የሚፈረጁት ጽንፈኛ አመለካከቶች ከመቸውም ጊዜ ይልቅ እየተባባሰ የመጣ አሳሳቢ ጥላቻ ፖለቲካን ወደሚያስከትል ደረጃ ደርሰው የተገኙት ከምርጫ 97ቱ ክስተት ወዲህ ነው የሚል እምነት እንዳለኝ ለመግለጽ ነው፡፡ ስለዚህ ከ2008 ዓ.ም አጋማሽ ጀምሮ አስካለፈው መስከረም 2009 ዓ.ም ድረስ በአንዳንድ የአማራና የኦሮሚያ ክልሎች የተስተዋለው የነውጠኝነት እንቅስቃሴም፤ ከዓመታት በፊት መንግስትን ይቅርታ ጠይቀው ከእስር የተለቀቁትን ጨምሮ፤ ሌሎች ጽንፈተኛ ተቃዋሚ ፖለቲከኞች ከዲያስፖራ መሰሎቻቸው ጋር እየተመሳጠሩ የሚያውጠነጥኑትን የቀለም አብዮት ሴራ ለማሳካት የሞከሩበት እንደነበር ምንም ጥርጥር የለውም፡፡
እንግዲያውስ ይህን ዓይነቱን ስር ከሰደደ የተቃውሞው ጎራ ተሸናፊ ኃይሎች ጭፍን ጥላቻ የሚመነጭ፤ በከረረና በመረረ ተቃርኖ የመጠላለፍ አዝማሚያ ከመጋፈጥ ቦዝኖ የማያውቀው የኢፌድሪ መንግስት፤ ይሄው ዛሬም ድረስ ችግሩን ለማርገብ የሚያስችል ሰላማዊ የመፍትሔ አቅጣጫ ከመቀየስ እንዳልተቆጠበ ነው መረጃዎች የሚያሳዩት፡፡ ስለሆነም፤ ሀገሪቷ ውስጥ ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ እንደሚገኙ የሚነገርላቸው ተቃዋሚ ፓርቲዎችና ኢህአዴግ ተነጋግረው የሚቀራረቡበትን መላ ይመቱ ዘንድ ታስቦ መንግስት በነደፈው የውይይትና የድርድር መርሀ ግብር መሰረት፤ የጋራ መድረኩ ከተጀመረ ወራት ተቆጥረዋል፡፡
ሆኖም ግን፤ ፓርቲዎቹ የአሁኑን የውይይትና የድርድር መርሐ ግብር ከጀመሩበት ጊዜ አንስተው ከአስር በላይ ተደጋጋሚ ስብሰባዎችን እንዳካሄዱ ቢታወቅም፤ ወደ የተሻለ የጋራ መግባባት የሚያደርስ አዝማሚያ እየተስተዋለበት አይመስልም- መድረኩ፡፡ ለዚህ እንደዋነኛ ምክንያት ሊወሰድ የሚችለው ደግሞ፤ ያው ከላይ ለማውሳት ከተሞከረው የአብዛኛዎቹ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጀርባ ታሪክ ጋር በተያያዘ መልኩ የሚገለጽ አሉታዊ ተጽዕኖ መኖሩ ነው፡፡ ለማንኛውም ግን፤ ኢህአዴግና 16 ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሰኞ ሰኔ 12 ቀን 2009 ዓ.ም ባካሄዱት ሰሞነኛ ስብሰባ ስለደረሱበት አጠቃላይ ሁኔታ (የየራሳቸውን የመደራደሪያ አቋም ይፋ ስለማድረጋቸው) የሚመለከት ዝርዝር ሐተታ በክፍል ሁለት ጽሑፌ ይዤ እንደምመለስ እየገልጽኩኝ ለዛሬው እዚህ ላይ አበቃለሁ፡፡