Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ኢህአዴግ እና ተቃዋሚ ፓርቲዎች ከትናንት እስከ ዛሬ (ክፍል 2)

0 430

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ኢህአዴግ እና ተቃዋሚ ፓርቲዎች ከትናንት እስከ ዛሬ (ክፍል 2)

ሰለሞን ሽፈራው

በዚሁ ርዕስ ስር የቀረበውን ክፍል አንድ መጣጥፌን ሳጠቃልል በገባሁት ቃል መሰረት፤ እነሆ ሁለተኛውን ክፍል ይዤ መጥቻለሁ፡፡ ስለዚህም የጽሑፌ ማጠንጠኛ ርዕሰ ጉዳይ በኢህአዴግና በተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል አሁን ላይ እየተካሄደ ስላለው ውይይት፤ ወይም ደግሞ ድርድር እንደሆነ ልብ ትሉልኝ ዘንድ እየጠየቅኩኝ በቀጥታ ወደ ዋናው ነጥብ አልፋለሁ፡፡

እንግዲያውስ በክፍል አንዱ ጽሑፌ ላይ የችግሩን መንስኤ ወይም ደግሞ ምንጭ ለማመልከት ስል ያነሳሁዋቸው ነጥቦች እንደ ተጠበቁ ሆነው፤ አሁንም ድረስ በኢህአዴግና በተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል እየተካሄደ የሚገኘው የውይይት መድረክ ምን እንደሚመስል ለማተት እሞክራለሁ፡፡ ስለ ሆነም ወራትን ባስቆጠረው የውይይትና የድርድር መድረክ ላይ እየተሳተፉ ያሉት የፖለቲካ ፓርቲዎች እስከዛሬ ድረስ በተደጋጋሚ ሲያካሂዱ የቆዩትን የጋራ ስብሰባ ጨምሮ ሰኞ ሰኔ 12 ቀን 2009 ዓ.ም ተገናኝተው የየራሳቸውን የመደራደሪያ አቋም ይፋ ያደረጉበት አግባብ ሲገመገም ምንን ያመለክታል? ለሚል ጥያቄ ምላሽ ይሰጣሉ የምላቸውን አንዳንድ ነጥቦች አንስቼ ለማብራራት እሞክራለሁ፡፡

እናም ከዚህ መሰረተ ሃሳብ አኳያ ሲታይ በቅድሚያ መነሳት ያለበት ቁልፍ ነጥብ ቢኖር፤ በተለይም አሁን እየተካሄደ ያለው የፓርቲዎች ውይይትና ድርድር መድረክ ላይ ኢህአዴግ ያሳየው ሆድ ማስፋት ከመቸውም ጊዜ ይልቅ ሊደነቅ የሚገባው ሆኖ የመገኘቱ ጉዳይ ነው፡፡ ይህን የምለውም ደግሞ፤ የውይይትና የድርድር ሂደቱን መጀመር ከሰማንበት ከታህሳስ ወር የመጨረሻ ሳምንት ጀምሮ፤ ፓርቲዎቹ ለተደጋጋሚ ጊዜ አንድ መድረክ ላይ ተገኝተው እየተሰበሰቡ ቅድመ ሁኔታዎችን ስለማሟላት ጉዳይ ብቻ እልህ አስጨራሽ ሊባል የሚችል ዓይነት ክርክር ሲያካሄዱ መቆየታቸውን ስለማስታወስና ኢህአዴግ ያኔ ለተቃዋሚዎቹ ምርጫ ቅድሚያ ሰጥቶ እነርሱው በፈለጉት መንገድ ለመነጋገር ዝግጁነቱን መግለጹም ጭምር ስለሚታወቅ ነው፡፡

ከዚሁ የተነሳም፤ የውይይትና ድርድሩ አጠቃላይ ሂደት ምን መምሰል አለበት? መድረኩን እነማን ይምሩት? በውይይትና ድርድሩ መድረክ ላይ የሚሳተፉት የፖለቲካ ፓርቲዎችስ በስንት ያህል አባላት ተወክለው ነው ኢህአዴግን መሞገት የሚኖርባቸው? እያንዳንዱ የፓርቲ ተወካይ በውይይትና በድርድሩ መድረክ ላይ ለሚያቀርበው ሃሳብ ምን ያህል ደቂቃ እንዲናገር ሊፈቀድለት ይገባል?…. ወዘተ የሚሉትን ጥያቄዎች በሚመለከት መክረው ዘክረው እንዲወስኑ ለተቃዋሚዎቹ ፓርቲዎች አባላት የአመራር አካላት ትቶላቸው ነበር ኢህአዴግ፡፡

እናም እነርሱ ራሳቸው ባቀረቡት የመግባቢያ ሃሳብ መሰረት፤ ከላይ ለተነሱት ቅድመ ሁኔታዎች የ“ፕሮሴጀር” ጥያቄዎች ምላሽ የሚሰጡ አምስት ሰዎች እንዲመረጡ ተደርጎ በኮሚቴ መልክ መክረው ዘክረው ሲያበቁ የወሰኑትን የመፍትሔ አቅጣጫ ለሁሉም የውይይት መድረክ ተሳታፊ ፓርቲዎች ያሳወቁትን ውጤት ተቀብሎ ነው ኢህአዴግ ወደ ድርድሩ ሂደት የገባው፡፡ ምክንያቱም ደግሞ፤ አብዛኛዎቹ የኛ አገር ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ኢህአዴግን ለውይይት በሩን የማይከፍት “የብሔራዊ መግባባት ፀር” እንደሆነ አድርገው በመፈረጅ የሚታወቁ እንደመሆናቸው መጠን፤ እስቲ እነርሱ በፈለጉት መልኩ ጭምር ፈቃደኛነቴን ላሳያቸው ያለ ይመስላል ገዢው ፓርቲ፡፡ስለዚህ ወራትን ባስቆጠረ ተደጋጋሚ ስብሰባ ላይ እየተገናኙ ተቀራርቦ ስለመስራት አስፈላጊነት ሲመክሩ የሰነበቱት የውይይት መድረኩ ተሳታፊ የፖለቲካ ፓርቲዎቻችን፤ ባለፈው ሰኞ ሰኔ 12 ቀን 2009 ዓ፣ም በተገናኙበት ሌላ ቀጠሮ፤ የመደራደሪያ አጀንዳቸውን ይፋ ማድረጋቸው ታውቋል፡፡

እንግዲያውስ፤ የሰኔ 12 ቀኑን የፖለቲካ ፓርቲዎች የውይይት መድረክ ውሎ አስመልክተው የዘገቡ መገናኛ ብዙሃን እንዳደረሱን መረጃ ከሆነ፤ አሁንም ከተለመደው የተለየ አዲስ ነገር ያነሳ ተቃዋሚ ድርጅት አልተገኘም፡፡ በዚህ መሰረትም አብዛኛዎቹ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከኢህአዴግ ጋር ልንደራደርባቸው ይገባል ሲሉ ያቀረቧቸውን ነጥቦች እየጠቀሱ የዘገቡት የሀገር ውስጥ ሚዲያዎች ጥቂት አይደሉም፡፡ ለአብነት ያህልም ረቡዕ ሰኔ 14 ቀን 2009 ዓ.ም የታተመው ሪፖርተር ጋዜጣ ዜናውን በፊት ለፊት ገፁ ይዞ መውጣቱ ይታወሳል፡፡ የብሮድካስቲንግ መገናኛ ብዙሃንም እንዲሁ፤ ዜናውን በተመሳሳይ ቅኝት አስደምጠውናል፡፡

ከዚህ አኳያ “ኢህአዴግ በሕገ መንግስቱ፤ በድንበር ማካለል ጉዳይና በህግ ጥላ ስር ያሉ እስረኞችን በሚመለከቱ ነጥቦች ዙሪያ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር እንደማይደራደር አስታወቀ” ሲል ዜናውን በፊት ገፁ የፃፈው ሪፖርተር ጋዜጣ ላይ ያገኘሁትን ዝርዝር መረጃ በምንጭነት ልጠቀምበት ወድጃለሁ፡፡ ስለሆነም፤ አስራ ስድስት ያህል ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከኢህአዴግ ጋር እየተወያዩ በሚገኙበት መድረክ ላይ ልንደራደርበት ይገባል ብለው ያቀረቡትን አጀንዳ በዝርዝር የጠቀሰው ሪፖርተር ጋዜጣ፤ ገዢው ፓርቲ የሰጠውን ምላሽ ጭምር አብራርቷል፡፡

ወጣም ወረደ ግን፤ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች አሁን አቀረቡ የተባለው የመደራደሪያ ጥያቄም ሆነ ኢህአዴግ ለጥያቄያቸው የሠጠው ምላሽ አዲስ ነገር ሆኖ አላገኘሁትም፡፡ እነዴት? ቢባልም ደግሞ እነሆ ምክንያቱን እንደሚከተለው አቀርባለሁ፡፡ ስለዚህም ከኢህአዴግ ጋር በአንድ መድረክ ላይ ተገናኝተው መወያየት ከጀመሩ 6ኛ ወራቸውን የያዙት ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለመደራደሪያነት ያቀረቧቸው ነጥቦች ዛሬ የተነሱ ሳይሆኑ ከደርግ ውድቀት ማግስት ጀምሮ የምናውቃቸው የተቃውሞው ጎራ ፖለቲከኞች በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ሲያንፀባርቁት የቆየው መሰረተ ሃሳብ ተቀጽላ ናቸው የሚያሰኘኝን ምክንያት ለማስረዳት እንዲያመቸኝ ትንሽ ወደኋላ ሄጄ አንዳንድ ነገሮችን ለማስታወስ ልሞክር፡፡

ስለዚህ እነርሱ “የህሊና እስረኞች” እያሉ ለሚጠሯቸው ወገኖች ጥብቅና ሲቆሙ የሚስተዋሉበትን አግባብና እንዲሁም ደግሞ የወደብ ጥያቄን ጨምሮ በድንበር ማካለል ዙሪያ የሚያሰሙት ቅሬታ በይዘቱ እጅግ ተመሳሳይ ባህሪ እንዳለው ማጤን አይከብድም ባይ ነኝ እኔ፡፡ ምክንያም ሀገራችን የምትመራበትን ፌደራላዊ ሕገ መንግስት መሰረት ባደረገ መልኩ የወጡ አንደ የፀረ ሽብር ሕጉን፤ የመረጃ ነፃነት አዋጅን፤ እንዲሁም ማህበራትንና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን በሚመለከት የተደነገጉ መሰል የቁጥጥር ህጎችን ለድርድር ስለማቅረብ ተቃዋሚዎቹ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚያሳዩት አቋም ከትናንት አስከ ዛሬ የምናውቀውን የትምክህትና የጠባብ ብሔርተኝነት ጽንፈኛ አስተሳሰብ የሚያንፀባርቅ እበንጂ አዲስ ክስተት እንዳልሆነም ደፍሮ መናገር ይቻላል፡፡

ጉዳዩ አዲስ ሆነም አልሆነም ግን፤ አሁን ላይ ፓርቲዎቹ ለድርድር እንዲቀርብ የጠየቁበት አግባብና ኢህአዴግ ጥያቄያቸውን የተቃወመበት አቋም ስለሚኖረው ፖለቲካዊ አንድምታ መገምገም የሚቻል መስሎ ይሰማኛል፡፡ ይልቁንም ደግሞ፤ ተቃዋሚዎቹ የፖለቲካ ፓርቲዎች “ኢህአዴግ ኢትዮጵያን ወደብ አልባ ሀገር አድርጓታል” የሚለውን የደርግ ኢ.ስ.ፓን ካድሬዎች የከሰረ ፕሮፓጋንዳ አሁንም ድረስ የሙጥኝ እንዳሉ መሆናቸውን ያረጋገጡበት ሰሞነኛው አቋማቸው በርካታ ዜጎችን ሳያስገርም እንዳልቀረ ነው ከአንዳንድ የመረጃ ምንጮች ላይ ለመገንዘብ የቻልኩት፡፡

ምክንያቱም፤ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ዛሬም እንደተለመደው ኢህአዴግን “ኤርትራን አስገንጥሎ ኢትዮጵያን ያለ አንዳች የባህር በር እንድትቀር ስላደረገ የሀገር ፍቅር ስሜት ሊኖረው አይችልምና ከስልጣኑ መውረድ አለበት” ብለው የሚወቅሱበትን ያረጀ ያፈጀ አቋም ለመደራደሪያነት እንዳቀረቡ ስንሰማ፤ አሁን ባለው ተጨባጭ እውነታ ውስጥ ዓለም አቀፉን ማህበረሰብ ቀልብ እየሳበ በመጣ የፈጣን እድገትና ብልጽግና ግስጋሴ ላይ የምትገኘው የአፍሪካ ቀንድ ሀገር ባለ ወደቧ ኤርትራ ናት? ወይስ ወደብ አልባዋ ኢትዮጵያ? ደግሞስ በድህረ ነፃነት ኤርትራ ውስጥ ከጊዜ ወደ ጊዜ እጅጉን እየከፋ ሲመጣ የሚስተዋለው ድህነትና ማህበራዊ ቀውስ ወደብ በራሱ የሥልጣኔ ምንጭ ሊሆን እንደማይችል የሚያሳይ ጥሬ ሀቅ አይደለምን? የሚል ጥያቄ ለማንሳት ተገደናልና ነው፡፡

ደግነቱ ግን፤ የኢህአዴግ ተወካዩ አቶ ሽፈራ ሽጉጤ “እንግዲያው የእናንተን ጥያቄ ላለመቃወምና የበለጠ ሆድ ለማስፋት ያህል እሺ እንደራደር ብንል እንኳን ወደብ ለኢትዮጵ ከየትና እንዴት ልታመጡላት ነው? ኢህአዴግ ራሱስ ከየትም ሊያመጣው እንደማይችል እያወቀ በወደብ ጉዳይ ለመደራደር ለምን ይሰማማል?” ሲሉ መልሰው ተቃዋሚዎቹን ፓርቲዎች እንደጠየቁ ነው ሪፖርተር ጋዜጣ የፃፈው፡፡ እንዲሁም ደግሞ 16 ሀገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎችን እንዳቀፈ በሚነገርለት የተቃዋሚ ስብሰብ ቀረበ ከተባለው ከኢህአዴግ ጋር የመደራደር ጥያቄ መካከል ጭራሽ ግንባሩን የማይመለከትና ጠያቂዎቹን አካላት ለተጨማሪ ትችት የሚያጋልጥ ሆኖ ያገኘሁት እንዳለም ማስታወስ አይከብድም፡፡

ለምሳሌ ያህልም፤ ሕገ መንግስታዊ ማሻሻያ ሊደረግባቸው ይገባል የሚሏቸውን ጉዳዮች በሚመለከት ከኢህአዴግ ጋር ስለመደራደር ያቀረቡት ጥያቄ ከግንዛቤ እጥረት የሚመነጭ ስህተት እንዳለበት ደፍሮ መናገር ይቻላል፡፡ ማለትም፤ ሕገ መንግስቱ የኢትዮጵያ ብሔሮች፤ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ልዑዋላዊ ስልጣን መገለጫ እንደመሆኑ መጠን፤ ኢህአዴግ አሊያም ደግሞ ሌላ ገዢ የፖለቲካ ፓርቲ ከተቃዋሚዎቹ ጋር ተደራድሮ የማሻሻል መብት የለውም ሲሉ የሕግ ሙያ ምሁራን ያስረዳሉና ነው ጥያቄውን ስህተት የሚያሰኘው ምክንያት፡፡ ስለሆነም፤ ምናልባት ከየወቅቱ ተጨባጭ ሁኔታ ጋር እየተገናዘበ መሻሻል ያለበት የሕገ መንግስቱ አንቀጽ፤ ወይም ንዑስ አንቀጽ ቢኖር እንኳን፤ ጉዳዩ የሚወሰነው በባለቤቶቹ የኢትዮጵያ ብሄሮች፤ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ተመክሮ ተዘክሮበት የጋራ መግባባት ላይ ሲደረስ ነው እንጂ በፖለቲካ ፓርቲዎች ድርድር ሊሆን አይችልም የሚለውን ገዢ ሃሳብ አለመዘንጋት ጠቃሚ ይመስለኛል፡፡  

ከዚህ አኳያ ኢህአዴግ “በህዝብ የተመረጥኩት ሕገ መንግስቱንና ሕገ መንግስታዊ ስርዓቱን አክብሬ እንስዳከብር ነው እንጂ ከተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር  እንድደራደርበት አይደለም” የሚል ምላሽ መስጠቱ የሚጠበቅ ሆኖ አግኝቸዋለሁ፡፡ ሌላው ከዚሁ ሕገ መንግስታዊ ጉዳዮችን ከገዢው ፓርቲ ፖለቲካዊ አቋም ለይቶ ያለመረዳት ችግር ጋር አብሮ መነሳት ያለበት ነጥብ ደግሞ፤ በተለይም ሀገራችን ከሱዳን ጋር የምትዋሰንበትን ድንበር የማካለል ጉዳይ ለድርድር ይቅረብ ሲሉ መጠየቃቸው ነው ተቃዋሚዎች፡፡

ይህን ነጥብ በተመለከተ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎቹ አነሱት የተባለው የእንደራደርበት ጥያቄ ምንኛ ቅንነት የጎደለው እንደሆነ ለመረዳት ጉዳዩ ሀገራችን ከሱዳን ጋር የምትዋሰንበትን ድንበር ብቻ ስለማካለል አስፈላጊነት የሚያወሳ ሆኖ መገኘቱን ብቻ ማጤን ይበቃል፡፡ በግልጽ አነጋገር፤ ጥያቄው ሀገራችን በዓባይ ወንዝ ላይ የምትገነባውን ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብ ለማስቆም ያለመ የፖለቲካ ሴራ በማውጠንጠን የተጠመዱ ጽንፈኛ ዲያስፖራ ተቃዋሚዎች ከሚያሰሙት ውንጀላ የመነጨ እንጂ ህዝቡን የሚመለከት ጉዳይ አይደለም ማለት ይቻላል፡፡

ምክንያቱ ደግሞ፤ እንደዚህ ዓይነቱ ዓለም አቀፋዊ ይዘት ባለው የተጎራባች ሀገራት መንግስታት የሁለትዮሽ ግኙነት ሊወሰን ይገባል ተብሎ የሚታመንበት የድንበር መካለልን የሚመለከት ጉዳይ፤ በገዢውና በተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል የሚካሄድ የድርድር መድረክ ላይ ይቅረብ ብሎ መጠየቅ ያልተለመደም ጭምር ተደርጎ ሊወሰድ የሚችል እንደሆነ ይታመናልና ነው፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎች “የፖለቲካ እስረኞች” የሚሏቸውን ወገኖች መንግስት እንዲፈታላቸው ለማድረግ ፈልገው ያቀረቡት የድርድር ጥያቄም፤ ያው ከዚህ ቀደም ተደጋግሞ እንደተነገረው ለሕገመንግስታዊ ስርዓቱ መከበር ከሚሰጡት አናሳ ግምት የሚመነጭ ቅንነት ማጣት ተደርጎ የሚወሰድ ግትር አቋም ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡

ፓርቲዎቹ በሽብርተኝነት ወንጀል ተከሰው የተፈረደባቸውን ሰዎች “የፖለቲካ እስረኞች” ወይም ደግሞ “የህሊና እስረኞች” እንደሆኑ አድርገው የሚቆጥሯቸውም፤ እነርሱ ራሳቸው ሕገ መንግስቱን በአመጽ ተግባር ለመደርመስ ያለመ መሰል ድርጊት ላይ ከመሳተፍ ተቆጥበው ስለማያውቁና ወደፊትም የመቆጠብ ፍላጎት ስለሌላቸው ነው፡፡ እንጂማ እቺን አገር እንደነሶሪያ፤ እንደነየመንና እንደነሊቢያ የእርስ በርስ ትርምስ አውድማ የሚያደርጋትን የቀለም አብዮት ለመቀስቀስ ያለመ የሽብር ተግባር ሲፈጽም የተገኘ ዜጋ በሕግ ፊት ቀርቦ ጥፋተኛነቱ ሲረጋገጥ ፍርድ ቤት የበየነበትን የእስር ቅጣት አምኖ መቀበል እንደምን ከበዳቸው ተቃዋሚ ፓርቲዎቹ? እኔ ለዚህ ጥያቄ የምሰጠው ምላሽ ከላይ ከቀረበው የመከራከሪያ ሃሳብ የተለየ አይሆንም፡፡

በግልጽ አማረኛ ለመናገር፤ ጉዳዩ ኢህአዴግ እንደ አንድ ጊዢ የፖለቲካ ፓርቲ በድህረ ደርግ ኢትዮጵያ የተከፈተውን አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ከሚቃጣበት ተደጋጋሚ የቅልበሳ አደጋ የመታደግ ህገ መንግስታዊ ግዴታውን (ኃላፊነቱን) በአግባቡ መወጣት ባችል ኖሮ ምን ዓይነት ሀገራዊ ትርምስ ይከሰት ነበር? ብሎ የመጠየቅንና ለጥያቄው ተራ ስሜታዊነት ከተጠናወተው ጭፍን ተቃውሞ የጸዳ ምላሽ መስጠትን ግድ የሚል ፈቃደኛነት ስለሚያስፈልገው እንጂ፤ እነርሱ ራሳቸውም እውነቱን ሳይረዱት ቀርተው አይደለም ማለቴ ነው፡፡ ስለዚህም፤ የዛሬዋ ኢትዮጵያ ውስጥ መላውን ዓለም አቀፋዊ ማህበረሰብም ጭምር ያሳመነ የዕድገትና የብልጽግና ተስፋ ሰፍኖ ለማየት የበቃነው፤ የኢፌድሪ መንግስት አበክሮ በነደፈው የጸረ ሽብርተኝነት ትግል ስትራቴጂ አማካኝነት፤ የሀገራችንን አስተማማኝ ሰላምና መረጋጋት ከሚቃጣበት ተደጋጋሚ የቅልበሳ አደጋ መታደግ ስለተቻለ ነው የሚለውን ቁልፍ ነጥብ ልናሰምርበት ይገባል፡፡

በተረፈ ግን ሀገር አቀፍ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ሰኞ ሰኔ 12 ቀን 2009 ዓ.ም በዋለው ስብሰባ ላይ ይፋ አደረጓቸው ከተባለው 13 የመደራደሪያ ረቂቅ ነጥቦች መካከል ኢህአዴግ ሊቀበለው የሚገባ ነጥብ የለም ማለቴ እንዳልሆነ ግንዛቤ ይወሰድልኝ፡፡ የኢትዮጵያ ብሔሮች፤ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ልዑዋላዊ ስልጣን መገለጫ በሆነው ሕገ መንግስታችን ላይ የተቀመጡ መሰረታዊ ጉዳዮችን በማይጋፋ መልኩ፤ ኢህአዴግና ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተወያይተው ከእስከዛሬው የተሻለ መቀራረብ ይፈጥሩ ዘንድ መላው የሀገራችን ህብረተሰብ የሚመኘው ጉዳይ ስለመሆኑ ይሰማኛል፡፡ ስለዚህ እኔ ራሴም እንደ አንድ የህብረተሰቡ አካል የፓርቲዎቹ ፖለቲካዊ ውይይትና ድርድር ለመላው የሀገራችን ህዝቦች ዘላቂ ዕጣ ፈንታ መቃናት በሚበጅ ሕገ መንግስታዊ ቅኝት ስር ተጠናክሮ እንዲቀጥል እየተመኘሁ፤ እነሆ ሐተታዬን እዚህ ላይ አበቃሁ፡፡ መዓሰላማት!

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy