Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ኢትዮጵያና የወቅቱ የአለም አቀፍ ማህበረሰብ እይታ

0 368

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ኢትዮጵያና የወቅቱ የአለም አቀፍ ማህበረሰብ እይታ

                                                                                    ይነበብ ይግለጡ

 

በግብርና ላይ ከተመሰረተ ኋላቀር ኢኮኖሚ በመነሳት፣ በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለው ስርነቀል የኢኮኖሚና የመሰረተ ልማት አብዮት ሂደቱን በመጠበቅ፤ ተመጋጋቢነትን በመፍጠር ወደ ኢንዱስትሪ ለመሸጋገር በርካታ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን በመገንባት የኢንዱስትሪ አብዮት ዘመንን ጀምሯል፡፡

 

የሀዋሳው ኢንዱስትሪ ፓርክ በቀዳሚ ምሳሌነት የሚጠቀስ ሁኖ 18 የሚደርሱ በርካታ አለም አቀፍ ታዋቂ ካምፓኒዎች በኢንዱስትሪ ፓርኩ ውስጥ ይገኛሉ፡፡ የሀዋሳውን የኢንዱስትሪ ፓርክ ተከትሎ የኮምቦልቻና የመቀሌ ኢንዱስትሪ ፓርኮችም ተመርቀው ስራ ጀምረዋል፡፡ ሌሎቹም ይቀጥላሉ፡፡

 

ኢንዱስትሪ ፓርኮቹ በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በትግራይ ክልሎች መገንባትና ስራ መጀመር ሀገሪቱ በታላቅ የኢኮኖሚ እድገት ሽግግር ውስጥ ለመሆንዋ ማረጋገጫ ነው፡፡

 

የኢንዱስትሪ ፓርኮቹ ለአየር ንብረት ተስማሚ የሚጠቀሙበትን ፈሳሽ መልሰው በማጣራት ለአገልግሎት ለማዋል የሚችሉ ምንም አይነት ችግር የማይፈጥሩ ለአካባቢ የአየር ነብረት ተስማሚ የሆኑ ሲሆን፤ ሰፊ የሆነ የስራ መስክ ለዜጎች የሚፈጥሩ ናቸው፡፡ የመቀሌው ብቻ ከ20ሺህ በላይ ኢትጵያውያንን በስራ ያሰማራል፡፡

 

አንዱ ፓርክ ይሄን ያህል ማሰማራት ከቻለ ሌሎቹ ደግም እንደ ስፋትና ይዞታቸው የበለጠ የሰው ኃይል ሊያሰማሩ እንደሚችሉ መገመት ይቻላል፡፡ መንግስት 13 የኢንዱስትሪ ፓርኮችንና 17 የግብርና ማቀነባበሪያዎችን በተያዘው እቅድ መሰረት ገንብቶ በስራ ላይ ያውላል፡፡ ከእነዚህ ሶስቱ የመጀመሪያ የአንዱስትሪ ፓርኮች የሀዋሳው፣ የኮምቦልቻው እና የመቀሌው ወደስራ ገብተዋል፡፡ ሌሎቹም በቅርብ ግዜያት ስራቸው ተጠናቆ ወደስራ ይገባሉ፡፡ ይህ ሀገራችን በላቀ የኢኮኖሚ እደገት ውስጥ በመረማመድ ላይ ለመሆንዋ ማረጋጋጫ ነው፡፡

 

በኢንዱስትሪ ፓርኮቹ ውስት ለመስራት ከተሰማሩት አለም አቀፍ ካምፓኒዎች የሚገነው የእውቀትና የልምድ ሽግግር ለሀገራችን ጠቀሜታው የጎላ ነው፡፡ የሚመረቱት ምርቶች በአለም አቀፍ ገበያ ላይ የሚውሉና ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ የሚያስገኙ ናቸው፡፡ ቀደም ሲል ከውጭ በውጭ ምንዛሪ ወደሀገር ውስጥ የምናስገባውን የተለያዩ ምርቶች በሀገራችን ውስጥ ለማምረት መብቃትና መቻላችን የውጭ ወጪያችንን በከፍተኛ ደረጃ እንዲቀንስ የሚያደርግ ሲሆን ይሄው ወጪ ለሀገር ልማትና ግንባታ እንዲውል ያስችለናል፡፡

 

ራስን መቻልና ለራስ መብቃት የሚገኘው እነዚህን የመሳሰሉ ጠንካራ ስራዎችን በመስራት ነው፡፡ በአሁኑ ሰአት የተለያዩ አለም አቀፍ መገናኛ ብዙህን ትኩረታቸውን በኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ ላይ በማድረግ ሀገሪቱ የጠያያዘችውን ፈጣን የኢኮኖሚ አድገት እየመዘገቡ ይገኛሉ፡፡ ፈጣን የሆነውን የኢኮኖሚ እድገት ከእኛም የመገናኛ ብዙሀን በበለጠ ለአለም አጉልተው በማሳየት ላይ ናቸው፡፡

 

የቻይናው ዜና ወኪል ቺንዋ የኢትዮጵያ የማዕድን፣ ነዳጅ እና የተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስቴር ሕገ ወጥ የወርቅ ንግድን ለመቆጣጠር በተለያዩ የሀገሪቷ አካባቢዎች አምስት የወርቅ ንግድ ማእከላትን እንደሚያቋቁም ማስታወቁን ዘግቧል። አዳዲሶቹ ማዕከላት በባሕላዊ የማዕድን ሥራ ላይ የተሰማሩ ሰዎች ወርቅ ለመሸጥ የሚጓዙትን ረጅም ጉዞ እንደሚያስቀር እና የወርቅ ሽያጭንም ሕጋዊ እንደሚያደርግ በሚኒስቴሩ የባሕል ማእድናት ምርት ማስተባበሪያ ድጋፍ ተጠሪ ዳይሬክተር ጅግሳ ኪዳኔ መናገራቸውን፤ አምስቱ የወርቅ ንግድ ማእከላት በትግራይ፣ ደቡብ፣ ጋምቤላ፣ ኦሮሚያ እና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች እንደሚገነቡ ገልጾአል፡፡

 

ኢትዮጵያና ሩሲያ ረዥም ዘመን ያስቆጠረ ጥንታዊ ግንኙነት ያላቸው ሀገራት መሆናቸው ይታወቃል፡፡ ሩሲያ በኢጣሊያን ወረራ ወቅት ከኢትዮጵያ ጎን በጽናት የቆመች የመጀመሪያውን የባልቻ ሆስፒታል በኢትዮጰያ ያቋቋመች፤ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንን በተለያዩ የሙያ መስኮች አስተምራ ተመልሰው ሀገራቸውን እንዲያገለግሉ ያደረገች ለሀገራችን ታላቅ ባለውለታ የሆነች ሀገር ነች፡፡ በቅርቡ የኢትዮጵያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ ወርቅነህ ገበየሁ በሞስኮ ከሩስያ አቻቸው ሴርጌይ ላቭሮቭ ጋር መወያየታቸውን በርካታ የሩሲያ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።

 

ኢትዮጵያ እና ሩሲያ በመካከላቸው ያለውን የረዥም ዘመን ግንኙነት ወደላቀ ደረጃ ለማሳደግ እና ለማጠናከር ፍላጎት እንዳላቸው የኢትዮጵያ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ ወርቅነህ ገበየሁ ከሩሲያው አቻቸው ሰርጌ ላቭሮቭ ጋር ባደረጉት ውይይት መናገራቸውን ኔፍትጋዝ ሩ ድረገጽና ስፑትኒክ ኢንተርናሽናል ሬድዮ ዘግቧል፡፡

 

ዶ/ ወርቅነህ ገበየሁ የሩሲያ ባለሀብቶች እና ኩባንያዎች ኢትዮጵያ ውስጥ በማእድን ዘርፍ ላይ የተመቻቸ ሁኔታ በመፈጠሩ መዋዕለ ንዋያቸውን ወደ ኢትዮጵያ በማሰገባት በዘርፉ ቢሰማሩ እንደሚያዋጣቸው በመጥቀስ ለባለሀብቶቹ ጥሪ ማቅረባቸውን ዘገባዎቹ ገልጸዋል፡፡ ይህንን ተከትሎም ኢንተር ራኦ ኤክስፖርት የተባለ ኩባንያ ኢትዮጵያ ውስጥ በኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግንባታ ዘርፍ ለመሰማራት ፍላጎት እንዳለው መግለጹን ኔፍቴጋዝ አስታውቋል።

የሩሲያ የነዳጅ እና ጋዝ ኩባንያ ጂፒቢ ግሎባል ሪሶርስ በምሥራቅ ኢትዮጵያ በኃይድሮ ካርቦን ፍለጋ ሥራ ላይ መሰማራቱም በድረገጹ ከተገለፁት ኢትዮጵያን የተመለከቱ ዜናዎች መካከል አንዱ ነው።

 

የዓለም ባንክ የሥራ አስፈጻሚ ዳይሬክተሮች ቦርድ የኢትዮጵያን የልማት ፍላጎትን ለመደገፍ የአምስት ዓመቱን የዓለም አቀፍ አጋርነት ማዕቀፍ (CPF) ማጽደቁን በድረ-ገጹ ይፋ አድርጓል። በርካታ ባለድርሻ አካላት በማእቀፉ ላይ ሰፊ ምክክር ማካሄዳቸውን ያስታወቀው የባንኩ ድረ-ገጽ ማእቀፉ በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ትኩረት ከተሰጣቸው ጉዳዮች ጋር አብሮ ሊሄድ እንደሚችል፤ ኢትዮጵያ እየተከተለች ያለውን ሁሉን አቀፍ እና ዘላቂ የልማት አቅጣጫ የሚደግፍ መሆኑን አስታውቆአል፡፡ማእቀፉ መሠረታዊ ትምህርት ላይ በማተኮር፣ የገበያ ተደራሽነትን በማሳደግ እና ለወጣቶች የሥራ እድልን በመፍጠር እንዲሁም በከተማም ሆነ በገጠር ምርትና ምርታማነትን በከፍተኛ ደረጃ በማስፋፋት መዋቅራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ሽግግርን ለማበረታታት እንደሚረዳ አመላክቷል።

 

ኢትዮጵያ ባለፉት ሁለት አሥርት ዓመታት በኢኮኖሚ፣ ማኅበራዊ እና ሰብአዊ ልማት ላይ አስደናቂ እድገት አስመዝግባለች ሲል የገለጸው ድረ-ገጹ የሀገሪቷ ጠቅላላ ሀገራዊ ምርትም በነዚሁ ዓመታት በአማካኝ በ10.5 በመቶ ማደጉን አወድሷል፡፡

 

ጆርናልዲካሜሩን ድረ-ገጽ በበኩሉ ኢትዮጵያ እና የአውሮፓ ኢንቨስትመንት ባንክ የ70ሚሊዮን ዩሮ የብድር ስምምነት መፈራረማቸውን የዘገበ ሲሆን፤ ብድሩ በማምረቻ እና አግሮኢንዱስትሪ ዘርፎች የተሰማሩ አነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች የገንዘብ አቅርቦት እንዲያገኙ የሚረዳ  መሆኑን፤ እንዲሁም የአውሮፓ ኢንቨስትመንት ባንክ ከሁለት ዓመት በፊት በአዲስ አበባ ጽ/ቤት ከከፈተ ጀምሮ ከባንኩ ጋር ያለው ግንኙነት ማደጉን፤ ይህ ግንኙነት ወደፊትም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፕሬዚዳንት ጌታሁን ናና ማስታወቃቸውን ዘገባው ይገልጻል፡፡

 

ግሎባል ታየምስ  የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአዲስ አበባ ኤርፖርት እያካሄደ ያለው የማስፋፊያ ፕሮጀክት በመጪው ዓመት ጥር ወር ላይ እንደሚጠናቀቅ መገለጹን፤ ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ አየር መንገዱ መንገደኞችን የመያዝ አቅሙ አሁን ካለው ሰባት ሚሊዮን ወደ 22 ሚሊዮን ያድጋል ተብሎ እንደሚጠበቅ፤ የማስፋፊያ ፕሮጀክቱ ሙሉ በሙሉ የገንዘብ ድጋፍ የተደረገለት በቻይና ኤግዚም ባንክ መሆኑን የአዲስ አበባ ኤርፖርት መንገደኞች ማስተናገጃ ሕንፃ ማስፋፊያ ፕሮጀክት ዋና መሐንዲስ አቶ ኃይሉ ለሙ መግለጻቸውን ግሎባል ታየምስ ገልጾአል፡፡

ዘ-ሲቲዝን  የተባለው የታንዛኒያ ዋና ጋዜጣ የታንዛኒያ ፕሬዚዳንት ማጉፉሊ ከኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል ልማት እና ግድብ ግንባታ የተወጣጣና በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ የተላከ የልዑካን ቡድን አባላትን ተቀብለው ማነጋገራቸውን አስነብቧል። ልዑካን ቡድኑን የመሩት የኢትዮጵያ ውኃ፣ መስኖ እና የኤሌክትሪክ ኃይል ሚኒስትር ዶ/ ስለሺ በቀለ መሆናቸውን የጠቆመው ጋዜጣው ቡድኑ ለታንዛኒያ አቻው በኤሌክትሪክ ኃይል ግንባታ ዙሪያ ልምድ እንደሚያካፍል ጠቁሟል። ታንዛኒያ በስቲግለር ሸለቆ 2ሺ ሜጋ ዋት የሚያመነጭ ታላቅ ግድብ ለመገንባት እንቅስቃሴ ላይ መሆኗንም ዘገባው አስታውቋል።

 

የጀርመኑ ዜና ምንጭ ዶቼ ቬሌ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በፍጥነት በማደግ ላይ እንደሚገኝ እና በቀጠናው ትልቁ ምጣኔ ሀብታዊ ኃይል እንደሚሆን ሰፊ ትንታኔ ሰጥቷል፡፡ እንደዶቼ ቬሌ ትንታኔ ኢትዮጵያ ኬንያን የበለጠችበት ምክንያት መንግሥት ትልልቅ ኢንቨስትመንቶችን እያካሄደ በመሆኑ እና ሸቀጦች በሀገር ውስጥ መመረት በመጀመራቸው ነው፡፡

 

የሐዋሳ ኢንደስትሪ ፓርክን ጨምሮ በርካታ ታላላቅ ፕሮጀክቶች በኢትዮጵያ በመከናወን ላይ መሆናቸውን፤ መንግሥት የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ለማሳደግ ባለው ፍላጎት ምክንያት ትላልቅ የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶችን በከፍተኛ ሁኔታ በመገንባት ላይ እንደሚገኝ፤ ባለፉት አሥርት ዓመታት የሀገሪቷ ኢኮኖሚ በአማካይ በ10.8 በመቶ ማደጉን ጣቢያው ገልጾ፤ ይህ የሀገሪቷ እድገት ምን ያህል ዘላቂ ሆኖ ይቀጥላል? የሚለው ነው ሲልም ጠይቋል፡፡ መልሳችንም ይቀጥላል ነው።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy