ኢትዮጵያ ለአፍሪካውያን
ይነበብ ይግለጡ
ኢትዮጵያ በመላው አለም የተከበረችና የነጻነት ቀንዲል ተደርጋ የምትወሰድ ሀገር ነች፡፡ በተለይም አፍሪካውያን በቅኝ ግዛት በሚማቅቁበት ዘመን ለነጻነታችው በሚያደርጉት ትግል በግንባር ሁና በተገኘው መድረክ ሁሉ ድምጻቸውን ስታሰማና ስትታገል የኖረች ከቀድሞ ግዜ ጀምሮ የአፍሪካውያን ተሟጋችና ተከራካሪ ሁና የዘለቀች ታላቅ ሀገር ነች፡፡
ለአፍሪካውያን ነጻነትና የጋራ ጥቅም መከበር፣ ከቅኝ ግዛት መውጣት፣ ለባርነት ቀንበር መሰበር ወዘተ ኢትዮጵያ ያደረገችው ትግል እጅግ ከፍተኛ ነው፡፡ ይህ ዘመንና ግዜ የማይሽረው ምስክርነት ዛሬም በ20ኛው የአፍሪካ የመሪዎች ጉባኤ ላይ ቀርቦ ታላቅ እውቅናን ተጎናፅፏል፡፡ በዚህም መሰረት የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት የነበሩት ቀዳማዊ ኃይለ ስላሴና የቀድሞው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ክቡር አቶ መለስ ዜናዊ በአፍሪካ ሕብረት ዋና ጽሕፈት ቤት ቅጥር ግቢ ውስጥ የመታሰቢያ ኃውልት እንዲቆምላቸው ተወስኖአል፡፡ ይህ የሚያሳየው ኢትዮጵያ እንደ ሀገር ለአፍሪካ ሕዝቦች ክብርና ነጻነት፤ ከቅኝ ግዛትና ከባርነት መላቀቅ ለከፈለችው ታላቅ መስዋእትነት እውቅና የሰጠ ታሪካዊ ክዋኔ ነው፡፡ ይገባናል!!!!
የቀድሞውን የአፍሪካ አንድነት ድርጅት፤ የዛሬውን የአፍሪካ ሕብረት ዋና ጽሕፈት ቤት ከኢትዮጵያ እንዲነሳ ለማድረግ አረባውያንና ወኪሎቻቸው፤ በተለይም የቀድሞው የሊቢያ ፕሬዚደንት መሐመድ ጋዳፊ ከፍተኛ ትግል ማድረጋቸው አይዘነጋም፡፡ ዋና አላማቸው የአፍሪካ ሕብረት ጽህፈት ቤት ከኢትዮጵያ ተነቅሎ ወጥቶ ሊቢያ እንዲገባ፤ መቀማጫውም ሲርጥ የተባለች የሊቢያ ከተማ ላይ እንዲሆን ነበር፡፡ ጸረ-ኢትዮጵያ ኃይሎች በተደጋጋሚና በተለየዩ ግዜያት ይህንኑ አይነት ሴራ ሲያሴሩ ኖረዋል፡፡
ከጀርባ ሁነው በኢትዮጵያ ውስጥ ሰላምና መረጋጋት እንዳይኖር በማድረግ፤ ኢትዮጵያ ሰላምና መረጋጋት የሌላት ሀገር ስለሆነች የአፍሪካ ሕብረት ዋና መቀመጫውን አዲስ አበባ ማድረግ የለበትም የሚል መከራከሪያ ሲያነሱ ቆይተዋል፡፡ ይህንን የተገመደ ሴራ ኢትዮጵያ ስትበጣጥሰው ኖራለች፡፡
ይሄው ጥያቄ በኢሕአዴግ ዘመንም ተነስቶ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ባሉበት ሰፊ ክርክር ተደርጎበታል፡፡ መለስ የተናገሩት ገዢ ኃሳብ የትኛውንም የአፍሪካ መሪ ዳግም በጉዳዩ ዙሪያ ተነስቶ እንዲናገር እድል የሰጠ አልነበረም፡፡
በአስተዳደራቸው ለሀገራቸው ሕዝብ ባይመቹና አምባገነን ቢሆኑም የትኞቹም የቀድሞ የኢትዮጵያ መሪዎች በአፍሪካና በአፍሪካውያን ጉዳይ፤ በአፍሪካ ነጻነት መከበር ላይ የነበራቸው አቋም የማያወላዳና የጸና ነበረ። ሲሉ ተከራክረው ማሸነፍ ብቻ ሳይሆን ጠያቂ ነኝ ባዮችን ሁሉ ፀጥ፤ እረጭ ማድረግ ችለዋል፡፡ እውነትም ነው፤ ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ያልሆነችው የለምና፡፡
መላ አፍሪካ በቅኝ ግዛት ቀንበር ስር ሲሰቃይ ብቸኞቹ ነጻ ሀገራት የነበሩት ኢትዮጵያና ላይቤሪያ ብቻ ነበሩ፡፡ በነዚህ ክፉ ግዜያት ኢትዮጵያ በተለያዩ መድረኮች ለአፍሪካውያን ከባርነትና ከቅኝ ተገዢነት ነጻ መውጣት ከፍተኛ ተጋድሎን አድርጋለች፡፡ ዛሬም ያንኑ የቀድሞ ለአፍሪካ ሀገራት ጥቅም መከበር የምታደርገውን ትግል አጠናክሮ የቀጠለው የኢፊድሪ መንግስት ለአፍሪካ ሰላምና ጥቅም መከበር በሁለንተናዊ መልኩ እየሰራ ይገኛል፡፡
ኢትዮጵያ በአፍሪካ የሰላም አስከባሪ ሠራዊት በማሰማራት ከአሸባሪዎችና ከእስላም አክራሪዎች ጋር በመታገል፤ መስዋእትነትም በመክፈል ሰፊ አስተዋጽኦ እያደረገች ያለች ሀገር ነች፡፡ ለአፍሪካ ጥቅም መከበር በተለይ በአየር ንብረት አለም አቀፍ ጉባኤ ላይ አቶ መለስ ዜናዊ አፍሪካን ወክለው በመቆምና በመከራከር የበለጸጉ ሀገራት በከባድ ኢንዱስትሪዎቻቸው አማካኝነት የሚለቁት በካይ ጋዝ ጉዳት በማድረሱ ለአፍሪካ ካሳ እንዲከፈል መጠየቃቸው መላ አፍሪካውያንን ያስደመመና ያኮራ ተግባር ሁኖ አልፎአል፡፡
በቀድሞው ንጉስ ኃይለስላሴ ዘመን ኢትዮጵያ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት እንዲመሰረት፤ ዋና ጽህፈቱ ቤቱ መቀመጫም በኢትዮጵያ ዋና ከተማ አዲስ አበባ እንዲሆን ማድረግ ችለዋል፡፡ ኢትዮጵያ የፀረ-አፓርታይድ ትግሉን በፅኑ በመደገፍ፤ ለደቡብ አፍሪካ የነጻነት ተዋጊዎች መጠለያ ከመሆንም አልፋ ወታደራዊ ስልጠና የሰጠችም ሀገር ነች፡፡
የዚምባዌ ታጋዮች ሀገራቸውን ነጻ ለማውጣት ባደረጉት ትግል ኢትዮጵያ ሁነኛ አጋራቸውና ወዳጃቸው ነበረች፡፡ የኮንጎ ብራዛቪል ሰላም በደፈረሰበት ወቅት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ኢትዮጵያ የሰላም አስከባሪ ሠራዊት እንድትልክ በጠየቀው መሰረት በ1955 ኢትዮጵያ የጠቅል ብርጌድን በሰላም አስከባሪነት ኮንጎ እንዲዘምቱ አረጋግታለች፡፡
የደቡብ ሱዳን ነጻ አውጪ ሠራዊት ለነጻነቱ ሲያደርግ በነበረው ትግል የዛሬውን ፕሬዚደንት ጨምሮ፤ መሪዎቹ እነኮሎኔል ጆን ጋራንግና ሬክ ማቻር ከነሠራዊታቸው ስልጠናና ድጋፍ ያገኙ የነበሩት እዚህ ኢትዮጵያ ውስጥ ነበር፡፡ ዛሬም በዘመነ ኢሕአዴግ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ባቀረበው የሰላም ማስከበር ጥሪ መሰረት ኢትዮጵያ በደቡብ ሱዳን/ዳርፉር፤ በሩዋንዳ፤ በብሩንዲ፤ በሶማሊያ ሠራዊትዋን በማሰማራት ኃላፊነቷን በመወጣት ላይ ትገኛለች፡፡ በተለይም በሶማሊያ ከአካባቢውና አለም አቀፍ አሸባሪዎች ጋር በተደረገው ትግል አልቃይዳን ያለበት ቦታ ድረስ በመዝለቅ መምታትና መደምሰስ የቻለች ሀገር ነች፡፡
በዚህ ትግል ውስጥ ከጎረቤት ሶማሊያ አክራሪ አሸባሪዎችን ለማጥፋት በተደረገው እልህ አስጨራሽ ጦርነት ውስጥ የኢትዮጵያ ድርሻ የላቀ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ይህ ኢትዮጵያ
የምታራምደው የሰላም አቋም በአፍሪካውያን ዘንድ ከፍተኛ ከበሬታና እውቅናን አስገኝቶላታል፡፡
20ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ ለንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለሥላሴና ለጠቅላይ ሚኒስትር ክቡር አቶ መለስ ዜናዊ በሕብረቱ ግቢ ውስጥ የመታሰቢያ ሐውልት እንዲቆምላቸው የሰጠው ውሳኔ ኢትዮጵያ ከቀድሞ መንግስታት ጀምሮ እስከዛሬ ድረስ ለአፍሪካ ክብርና ጥቅም የማይታጠፍ ትግል ለማድረግዋ ማረጋገጫ መሆኑ እርግጥ ነው፡፡
አሁን የተሰራውና እጅግ ዘመናዊ የሆነው የአፍሪካ ሕብረት ሕንጻ የተገነባው በኢሕአዴግ ዘመን ነው፡፡ ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰላም ማስከበር ግዳጅ ቀድሞ በኮርያና ኮንጎ፤ ዛሬ ደግሞ በሶማሊያ፣ በሩዋንዳ፣ በብሩንዲ እና በዳርፉር የተሰማራችው በኢሕአዴግ መራሹ ኢፊድሪ ዘመነ መንግስት ነው፡፡ ይህ የኢፊድሪ መንግስት የአፍሪካ አገራትን ጥቅም ከማስከበር አኳያ የሚከተለው ዲፕሎማሲ ውጤታማና ስኬታማ ለመሆኑ ተጨባጭ ማሳያ ሲሆን እውቅና የተሰጠውም ለኢትዮጵያ ሕዝብና መንግስት ነው፡፡
ኢትዮጵያውያን በማንኛውም ሥርአትና ጊዜ ለአፍሪካውያን ታማኝ ወዳጆችና አጋር ሆነው ኖረዋል፡፡ እየኖሩም ነው፡፡ ይሄ ድንቅ ተግባርም ከትውልድ ወደትውልድ ተጠብቆ ወደፊትም ይዘልቃል፡፡
ኢትዮጵያ ዛሬ ከ850ሺህ በላይ አፍሪካውያን ስደተኞችን ተቀብላ በማስተናገድ ላይ ያለች ሀገር ነች፡፡ መጠለያ፣ መሸሻ፣ የችግርና የክፉ ቀን ቤታቸው በመሆኗ ያለምንም ስጋት እየኖሩባት ይገኛሉ፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ እንግዳ ተቀባይ፤ ያለውን የሚያካፍል፤ ጨዋና ታላቅ ሕዝብ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ሕብረት ውሳኔዎች ሁሌም በቀዳሚነት ተገዥና ፈጻሚ ሀገር ነች፡፡
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን፤ አገሮች በኢኮኖሚ እንዲተሳሰሩ ለማድረግ የሚያስችሉ የመሰረተ ልማት አወታሮችን ማለትም በመንገድ ግንባታ፤ በባቡር መስመር ዝርጋታ፤ በአውሮፕላን በረራ ማስፋፋት፡ በኃይል (ኤሌክትሪክ) አቅርቦትን በማስፋፋት ረገድ እያደረገች ያለችው ጥረት እጅግ የላቀና ከፍተኛ ነው፡፡
ዛሬ ኢትዮጵያ በፈጣን የኢኮኖሚ እድገትዋ በአፍሪካና በአለም ደረጃ በቀዳሚነት ተጠቃሽ በመሆኗም በአርአያነት እየተከተሏተ ያሉ አገራት በርካቶች ናቸው።
ኢትዮጵያ ለአፍሪካውያን ኩራት፣ ክብርና አለኝታም ነች፡፡ ለተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት ተማሪዎች በተለያዩ የሙያ መስኮች ማለትም በአየር መንገድ፣ በመከላከያ፣ በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎችዋ ወዘተ ነፃ የትምህርት እድል (ስኮላርሽፕ) በመስጠትና በማስተማር ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ብቁ ሙያተኛ እንዲኖራቸው የበኩሏን የማይተካ አስተዋጽኦ እያደረገች ትገኛለች፡፡
የኢትዮጵያ ሕዝብ እንግዳ ተቀባይ በመሆኑ ለበርካታ ዓመታት የአፍሪካ መሪዎች አዲስ አበባ በሚሰበሰቡበት ወቅት ጉባዔው በሰላም እንዲጠናቀቅ፣ የሰላምና የጸጥታ ችግር እንዳይፈጠር፣ እንግዶች በሰላም መጥተው በሰላም እንዲመለሱ በማድረግ ረገድ ለአፍሪካውያን ወንድሞቹ ያለውን ታላቅ ከበሬታ ሲያሳይ ኖሮአል፡፡ ይሄው ዘመናትን ያስቆጠረ የእንግዳ ተቀባይነት አኩሪ ባሕል ወደፊትም የበለጠ ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡ ኢትዮጵያ በአፍሪካውያን ዘንድ ያላት ተቀባይነትም እየደመቀ ይሄዳል፡፡ ይህ ሁሉ የአኩሪ ባህላችን፣ ለአፍሪካና አፍሪካውያ ካለን ፍቅርና ክብር፤ እንዲሁም የዲፕሎማሲያችን ስኬት ውጤት መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል፡፡