Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

እውን ለአፍሪካዊያን እንደ ኢትዮጵያ የታገለ ማነው?

0 363

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

እውን ለአፍሪካዊያን እንደ ኢትዮጵያ የታገለ ማነው?

                                              ቶሎሳ ኡርጌሳ

ለዛሬው የፓን የአፍሪካ ህብረት እውን መሆን መነሻው የ“ፓን አፍሪካኒዝንም” እንቅስቃሴ ነው። ከአስከፊው የቅኝ አገዛዝ መንጋጋ ለመጀመሪያ ጊዜ የተላቀቀችው ምዕራብ አፍሪካዊቷ ሀገር ጋና ነፃነቷን ከተቀዳጀች እንዲሁም አብዛኛዎቹ ሀገራት ከቅኝ ግዛት ሲላቀቁ፤ ይህ እንቅስቃሴ በአፍሪካ የሚኖሩ ህዝቦች እንዲሁም የአህጉሪቱ ሀገራትና መንግስታት ጭምር ሆነ። ታዲያ የአፍሪካ አንድነትና ህብረት ጥያቄ የሀገራቱና የመንግስታቱ ዋነኛ ጥያቄ ሆኖ የመነጋገሪያ አጀንዳ ሲሆን፤ ሁለት የተለያዩ አመለካከቶች በይፋ መውጣት መጀመራቸውን ታሪክ ያስረዳናል።  

አንደኛውና ግንባር ቀደሙ አመለካከት ከቅኝ ግዛት ነፃ ያልወጡ የአፍሪካ ሀገራት ነፃነታቸውን እንዲቀዳጁ ሀገራቱ በጋራ ፖለቲካዊ፣ ዲፕሎማሲያዊና ወታደራዊ ድጋፍ ማድረግ እንዳለባቸው የሚያሳስብ ሲሆን፤ ሁለተኛው አመለካከት ደግሞ አፍሪካ በአለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት እንዲኖራት ተባብሮ የመስራት መርህን ያነገበ ነበር።

በሌላም በኩልም በያኔው የጋና ፕሬዚዳት ክዋሜ ንክሩማ የሚመራው ቡድን “በአፍሪካ ደረጃ አንድ የጋራ መንግስትና ኢኮኖሚ መፍጠር አለብን፣ ይህንንም አሁኑኑ ማከናወን ይኖርብናል” የሚል አቋም ሲያራምዱ፤ አፄ ኃይለስላሴ የሚገኙበት የአብዛኛው ሀገራት ስብስብ ደግሞ፤ አስተሳሰቡ ዕውን ሊሆን እንደማይችል በመግለፅ፤ “ከቅኝ አገዛዝ የወረስነውን ድንበር ይዘን እንደ ነፃ ሀገሮች በመደራጀት በአፍሪካዊነታችንና በነፃ መንግስታት መካከል በሚኖር ትብብር ነው መመስረት የምንችለው” የሚል አቋምን አራመዱ።

ታዲያ የኋላ ኋላ ነገሩ መፅሐፉ “ብዙሃን ይመውዑ” (ብዙሃን ያሸንፋሉ) እንዲል ሆኖ ነው መሰል፤ ውህዳኑ የእነ ንኩርማ ቡድን በብዙሃኑ ሃሳብ በመዋጡ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት (OAU) እ.ኤ.አ. በወርሃ ግንቦት 1963 ዓ.ም ነፃ የአፍሪካ ሀገሮች የመሰረቱት በይነ መንግስታዊ ድርጅት በመሆን አዲስ አበባ ላይ ሊመሰረት ችሏል። ድርጅቱ ቀደም ሲል የጠቀስኳቸውን ሁለት ሃሳቦችን አንግቦ የተጣለበትን ኃላፊነት ለ39 ዓመታት ያህል ሲወጣ ቆይቶ በ40ኛው ዓመት ዋዜማ ላይ በደቡብ አፍሪካ- ደርባን በተካሄደ የድርጅቱ ጉባኤ በይፋ ወደ አፍሪካ ህብረትነት (AU) እንዲለወጥ ተደርጓል። ርግጥ በዚህ የአ.አ.ድና የህብረቱ የዕድገት ጉዞ ውስጥ ኢትዮጵያ ሁሌም ከድርጅቱ ጎን ነበረች፤ አሁንም አልተለየችም። በአንፃሩ ዛሬ በአፍሪካ ህብረት ውስጥ የአፍሪካዊያን ተቆርቋሪ መስለው የሚታዩት ግብፆች በእነዚያ አፍሪካዊያን በግፍ በሚሰቃዩባቸው ዓመታት ምንም ዓይነት ነገር አልሰሩም። እንዲያውም ግብፃውያኑ በተጨባጭ የሀገራቸው የካርታ አቀማመጥ በአፍሪካ ስር ሆኖ እያለ፤ በተግባር ግን ወደ አረባዊ ስሜታቸው አድልተውና አፍሪካን ገሸሽ አድርገው ግንኙነታቸውን ከዓረቡ ዓለም ጋር ሲያጧጥፉት እንደነበር እዚህ ላይ ሳልጠቅሰው ባልፍ ታሪክን የመካድ ያህል ይቆጠርብኛል።

ያም ሆኖ ኢትዮጵያ ከትናንት እስከ ዛሬ ድርጅቱን በመመስረት፣ ችግሮቹን እንደ ችግሯ በመካፈል፣ ስኬቶቹን የራሷ እመርታ አድርጋ በመቁጠርና ለአፍሪካዊያን መስዋዕትነትን በመክፈል ከ50 ዓመታት በላይ ከድርጅቱ ጋር ስትወድቅና ስትነሳ ነበር። ዛሬም በሁሉም መስኮች የህብረቱ ውሳኔዎች ተገዥ በመሆን የአፍሪካዊያንን ፍላጎት በየዓለም አቀፍ መድረኩ እንዲንፀባረቅ እያደረገች ነው—ለአህጉሪቱ ሰላም በምትሰጠው ዋጋ መስዕዋትነት እየከፈለችም ጭምር።

ታዲያ እነዚህና ሌሎች ኋላ ላይ የማነሳቸው የሀገራችን ተግባሮች፤ በርዕሴ ላይ “እውን ለአፍሪካዊያን እንደ ኢትዮጵያ የታገለ ማነው?” የሚል ጥያቄ እንዳነሳ አድርገዋል። በእኔ እምነት እንደ ኢትዮጵያ ለአፍሪካዊያን ህዝቦች ነፃነት የታገለና ያታገለ እንዲሁም ለድርጅቱም መጎልበት የበኩሉን ሚና የተጫወተ ሀገር የለም። በዚህም ምክንያት ይመስለኛል— ኢትዮጵያ የህብረቱ መቀመጫ መሆኗና በህብረቱ 29ኛ ጉባኤ ላይ ለሁለት የሀገራችን የቀድሞ መሪዎች መታሰቢያ ሃውልት እንዲቆም የተወሰነው።  

አዎ! ‘እንደ ኢትዮጵያ ለአፍሪካዊያን የታገለ የለም’ የምለው እንዲያው ኢትዮጵያዊ ማንነቴ ነሽጦኝ አይደለም—ሀገራችን ለአፍሪካዊያን ያደገችው ተጋድሎ ህብረቱ የሚያውቀውና እውቅና የሰጠው ‘ነጭና ጥቁር’ (‘Black and White’) እውነታ ስለሆነ እንጂ። ርግጥም ኢትዮጵያ የአፍሪካዊያንን አህጉራዊ ድርጅት ከማዋለድ ጀምሮ በማሳደግና ወደ ህብረትነት እንዲቀየር በማድረግ ታሪካዊ ድርሻዋን መወጣቷ የትናንት ታሪካችን፣ የዛሬ ተግባራችን ነው። ኢትዮጵያ እንደ መስራችና እንደ ድርጅቱ ዋና መቀመጫነቷ በየትኛውም የፖለቲካ ሥርዓት ወቅት በአፍሪካዊ ወንድማማችነትና መንፈስ ተቀብሎ በማስተናገድ፣ ጭቆናና በደልን፣ ግፍና ብዝበዛን በመቃወም አቅሟ የፈቀደውን ሁሉ አድርጋለች። ዛሬም እያደረገች ነው። በተለያዩ ወቅቶች በአህጉሪቱ አለመግባባቶችና ግጭቶች ሲከሰቱም በማብረድ ረገድ ተሳትፎዋ ቀላል አልነበረም፤ አይደለምም። ይህ ተሳትፎዋ ዛሬ አፍሪካን ተሻግሮ በተባበሩት መንገስታት ደርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ተለዋጭ አባል እስከ መሆን አድርሷታል።  

በአህጉሪቱ የሚፈጠር አለመረጋጋትን በመረጋጋት በመተካት፣ የተጎዱትን በማቋቋምና የተቸገሩትን በመርዳት የማይናወጥ አቋሟን ስታንጸባርቅ የኖረች ሀገር ናት። ኢትዮጵያ አህጉሪቱን ከቅኝ አገዛዝ ሙሉ በሙሉ በማውጣትና የአፍሪካውያንን ነፃነትና ክብራቸውን ለመመለስ እንዲሁም አፍሪካን ወደ ኢኮኖሚ ዕድገት ለመምራት በተደረገው ትግል የማይነጥፍ አስተዋጽኦ ስታደርግም ቆይታለች። አሁንም በማድረግ ላይ ትገኛለች።

ከድርጅቱ ምስረታ በፊት አፍሪካን ለሁለት ከፍሏት በነበረው በክዋሜ ንኩርማና በብዘሁኑ ቡድኖች መካከል የነበረው የአካሄድና የአስተሳሰብ ልዩነት እንዲፈታ በማድረግ ታላቅ አስተዋጽኦ አበርክታለች። ሀገራችን ወራሪውን የጣሊያን ኃይል ታግላ ነፃነቷን በማስመለስ ያስመዘገበችው ድል በአህጉሪቱ ለነፃነት ሲደረግ የነበረውን ትግል በማቀጣጠል በርካታ ሀገሮች ነፃነታቸውን እንዲጎናፀፉ ያደረገች ሀገር ናት።

እ.ኤ.አ በ1960ዎቹ አፍሪካውያን በቅኝ አገዛዝ ሲሰቃዩ በዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት እየቀረበች በሕግ ትሟገትላቸውና ትከራከርላቸው የነበረችውም ሀገራችን ናት። በቅኝ አገዛዝና በአፓርታይድ ሥርዓት ሲሰቃዩ የነበሩ አፍሪካውያን የሞራል፣ የዲፕሎማሲና የቁሳቁስ ድጋፍ በማድረግ ሚናዋንም በሚገባ ተወጥታለች።

በንጉሱ ዘመን ሀገራችን ለመጀመሪያ ጊዜ የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን ጥሪ በመቀበል የሰላም አስከባሪ ሃይሏን ለሁለት ዓመታት በኮሪያ ልሳነ ምድር አዝምታለች። በአሁኗ ኮንጎ ዴሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ የነበረውን ችግር ለመፍታትም የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ኃይል እ.ኤ.አ ከ1960 እስከ 1964 በነበረው ጊዜ ውስጥ ግዳጁን ሥነ ምግባር በተሞላበት ሁኔታ ፈፅሟል። ለደቡብ አፍሪካ፣ ለናሚቢያና ለዚምባቡዌ የነፃነት ትግል ወታደራዊ ስልጠና በመስጠት ያደረገችው አስተዋፅኦም በታሪክ ድርሳናት ተከትቦ የሚቀመጥ አኩሪ ተግባር ነው።

አምባገነኑ የደርግ ስርዓት ከወደቀ በኋላም፤ ሰላም መርሁ የሆነው የኢፌደሪ መንግስት አፍሪካዊ አስተዋፅኦውንና ኃላፊነቱን ከምንጊዜውም በላቀ ሁኔታ ተወጥቷል፤ ዛሬም ድረስ እየተወጣ ነው። በዚህ መሰረትም በሩዋንዳ እ.ኤ.አ በ1990ዎቹ በተከሰተውና የዓለምን ሕዝብ ባስደነገጠው የዘር ማጥፋት እንቅስቃሴ ሠላም እንዲያስከብሩ ከተደረጉት ሀገሮች አንዷ ኢትዮጵያ እንድትሆን አስችሏል።

እንደሚታወቀው የፈረንጆቹ አዲሱ ሚሌኒየም ሲጀመር በቡሩንዲ ሁቱና ቱትሲ የተባሉ ጎሳዎቿ ግጭት ውስጥ ነበሩ። ዘር ለይቶ የተፈጠረውን ዘግናኝ ድርጊት ለማስቆም በአፋጣኝ ሰላም አስከባሪ ኃይላቸውን እንዲልኩ ከተደረጉት ሀገሮች መካከል ኢትዮጵያ ቀዳሚዋ ናት። በዚህም ታሪካዊ አስተዋፅኦዋን አበርክታለች።

በላይቤሪያም የነበራት አስተዋጽኦ ተመሳሳይ ነው። እንደሚታወቀው ላይቤሪያ ባለፉት የአውሮፓውያን አስርት መጨረሻ ዓመታት ላይ በከፍተኛ የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ነበረች። ሀገሪቱን ወደ ሠላምና መረጋጋት ጎዳና ለመመለስ በተደረገው ሂደት የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ኃይል ተሳትፎ ወደር አልነበረውም። በሀገሪቱ ሰላምና ዴሞክራሲ እንዲሰፍን በማድረግም የላቀ ሚናውን ተወጥቷል። ለዚህ ውለታውም የክብር ሜዳሊያ ተሸላሚ ሆኗል።  

ኢትዮጵያ በሱዳን-ዳርፉር ግዛት ከሌሎች ሀገሮች ጋር በመሆን ባሰማራችው ሰላም አስከባሪ ሃይልም የእርስ በርስ ግጭት እንዳይከሰት በማድረግ ላይ መሆኗም ይታወቃል። ሱዳንና ደቡብ ሱዳን በይገባኛል በሚከራከሩበት የአብዬ ግዛት ከዓለም ብቻውን የተሰማራ ሰላም አስከባሪ ኃይል በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጥላ ስር በማሰማራት በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነቷን ያሳደገ ተግባር እያከናወነች ነው። ይህ ተግባሯም ኢትዮጵያ በሁለቱም ሀገሮች መንግሥታትና ህዝቦች አክብሮት እንዲኖራት አድርጓል።

በጎረቤት ሶማሊያም አቆጥቁጦ የነበረውን የፅንፈኝነትና የአክራሪነት ተግባሮችን በመዋጋት ዛሬ በዚያች ሀገር ፌዴራላዊ መንግስት እንዲመሰረት የበኩሏን እገዛ አድርጋለች። በአሁኑ ወቅትም በአፍሪካ ህብረት የሶማሊያ ሰላም አስከባሪ ኃይል ጥላ ስር በመሆን አልሸባብ የተሰኘውን የሽብር ቡድን ከሌሎች አፍሪካዊያንና ሰላም ወዳድ ዓለም አቀፍ ኃይሎች ጋር በመሆን እያዳከመችው ነው። ከአሚሶም ውጭም ባለው ሰራዊቷ አማካኝነት በሶማሊያ ህዝብ ይሁንታ የተመረጠውን አዲሱን የሀገሪቱን መንግስት እየደገፈች ትገኛለች።    

ኢትዮጵያ በምሥራቅ አፍሪካ ሀገሮች ሰላም፣ ፀጥታና መረጋጋት ከፍተኛ ሚና እየተጫወተች ባለችው ሚና በሶማሊያ የነበረውን መንግሥት አልባነትና አክራሪነት በመታገልም ውጤታማ መሆን ችላለች። እርግጥ ሰላማቸው የተረጋገጠ፣ በኢኮኖሚያቸው የበለፀገና ዴሞክራሲ ያበበባቸው ጎረቤቶች የጋራ ጥቅም መሠረት መሆናቸው የማይታበይ ቢሆንም፤ ሀገራችን ከዚህ ባለፈ ለጎረቤቶቿ ህዝቦች ሰላም ያለማሰለስ በመስራት ላይ ትገኛለች። ባለፉት ዓመታት በሞሮኮ፣ በአልጄሪያና በናይጄሪያ ውስጥ የቢያፍራ የመገንጠል እንቅስቃሴን እንዲሁም በሱዳን የቤኛ እንቅስቃሴ ከማዕከላዊ መንግስቶቻቸው  ጋር የነበራቸውን ግጭት በመፍታት የማይዘነጋ ታሪካዊ አስተዋፅኦ አበርክታለች።

ሀገራችን በኢኮኖሚው መስክ ያላት አህጉራዊ ትብብር ኮሜሳ በሚሰኘው በምሥራቅና ማዕከላዊ አፍሪካ የጋራ ገበያ የተጠናከረ ውህደት ለመፍጠር ያላት ሚናም ከፍተኛ ነው። በዚህም በመሠረተ ልማት ግንባታና በንግድ በርካታ አስተዋፅኦዎችን አድርጋለች። ዛሬ ላይም በኢንቨስትመንት ቀዳሚም መሆን ችላለች።

በቀጣናው ሀገራት ውስጥ የጋራ የኢኮኖሚ ዕድገት ለማምጣትም እየሰራች ነው። ከጅቡቲ፣ ከሱዳንና ከደቡብ ሱዳን ጋር የመንገድ ግንኙነት በመፍጠር ለጋራ ተጠቃሚነት በመትጋት ላይ ተገኛለች። በዚህም ከጅቡቲ ጋር የሚያገናኝ የባቡር መስመር ዘርግታለች። ከኬንያ ጋር የሚያገናኘው የመንገድ ግንባታ መስመርንም እያሳለጠች ነው። ለጅቡቲ የኤሌክትሪክ ኃይል በማቅረብ ተጠቃሚ እንድትሆን ከማድረጓም በላይ፤ ኬንያንም 400 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል እንድትጠቀም ለማድረግ እየጣረች ነው። ለሌሎች የቀጣናው ሀገራትም እንዲሁ።

የአባይን ውሃ ፍትሃዊ በሆነ ሁኔታ መጠቀም አስፈላጊነቱን አምናም እየሰራች ነው። ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በመገንባት 6ሺህ 450 ሜጋ ዋት የማመንጨት ዓላማዋ ከሀገር ውስጥ ፍጆታ አልፎ ጎረቤት ሀገሮችንም እንደሚጠቅም አምና እየሰራች ነው። በአህጉሪቱ መልካም አስተዳደርና ዴሞክራሲን ለማስፈን የተያዘውን ጥረትም በአፍሪካ እርስ በርስ መገማገሚያ ስልትም እየተገበረች ነው።

ሀገራችን በድርጅቱ ፈቃድና በቀደምት መሪዎቿ ብርታት የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን/የአፍሪካ ህብረት ፅህፈት ቤትን በአዲስ አበባ ከተማ እንዲሆን ማድረጓ፤ ከሁሉም በፊት በኢትዮጵያና በሌሎች የአፍሪካ አገሮች መካከል ያለው ግንኙነት እንዲሻሻል ማድረግ ችላለች። ከዚህ በተጨማሪ ከተማዋ የዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲ መናኸሪያ እንድትሆን በማድረግ ዛሬ ከኒውዮርክና ከጄኔቫ ቀጥሎ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ መሰብሰቢያ እንድትሆን አድርጋለች። ይህም ለሀገራችን ከሚሰጠው ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ባሻገር፤ ለአፍሪካዊያን ገፅታ ግንባታ የበኩሉን አስተዋፅኦ የሚያበረክት ነው—የአፍሪካ ህብረት መዲና የዓለም መናኸሪያም እየሆነች ነውና።

በጥቅሉ እነዚህ በጥቂቱ ያነሷኋቸውና ኢትዮጵያ ለአፍሪካዊያን ያበረከተቻቸው ተግባሮች፤ ርግጥም ለአፍሪካዊያን እንደ ኢትዮጵያ የሰራ ሀገር አለመኖሩን አፍ አውጥተው የሚናገሩ ናቸው። ዛሬም ቢሆን የሀገራችን አፍሪካዊ ተግባሮች አልተቋረጡም። አይቋረጡምም። አፍሪካዊያን የፖለቲካና የኢኮኖሚ ውህደት እስከሚያደርጉበት እ.ኤ.አ እስከ 2063 ዓ.ም ድረስ ይቀጥላሉ።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy