Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ከለጋሽ ተለጋሽ ወደ ትብብር ያደገ ግንኙነት

0 828

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ከለጋሽ ተለጋሽ ወደ ትብብር ያደገ ግንኙነት

ብ. ነጋሽ  

ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ትስስር ውስጥ ትታወቅ የነበረው በተወሰኑ የግብርና ጥሬ ምርቶች የወጪ ንግድና በዚህ ልክ በተገደበ የውጭ ምንዛሪ ገቢ ነበር። የመንግስት የልማት ኢንቨስትመኖቶች እጅግ ውስን በመሆናቸው ሃገሪቱ ታገኝ የነበረው ዓለም አቀፍ ብድርም ጥቂት ነበር። የመንግስት የልማት እቅድ ትልቅ ቢሆን እንኳን ብድር ማግኘት የሚያስችል መተማመኛ አልነበረም። አብዛኛው ገንዘብ ወይም ምርት ነክ የኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ግንኙነት በእርዳታ ተቀባይነት ላይ የተመሰረተ ነበር።

ኢትዮጵያ በድርቅ ሳቢያ የምግብ እጥረት ባልተፈጠረበትም ጊዜ ቢሆን በእጅጉ እርዳታ ጠባቂ ነበረች። ይህ  የኢትዮጵያ ድጋፍ ጠባቂነት አሁንም መኖሩ ባይካድም፣ በድጋፍ ላይ ያለው ጥገኝነት ግን በጉልህ ቀንሷል። ኢትዮጵያ አሁንም 30 በመቶ ገደማ የሚሆነው ዓመታዊ በጀቷ በብድርና እርዳታ ነው የሚሸፈነው። ይሁን እንጂ ባለፈው ዓመትና ዘንድሮም እንዳየነው በሃገሪቱ በተከሰተው ድርቅ ሳቢያ በሚሊየን የሚቆጠሩ ዜጎች ለአስቸኳይ ጊዜ የምግብ እርዳታ ጠባቂነት ቢጋለጡም፣ ይህን እርዳታ በማቅረብ ውስጥ የኢትዮጵያ መንግስት የአንበሳውን ድርሻ ይዟል። ድሮ ድርቅ የሚያስከትለው የምግብ እጥረት ሙሉ በሙሉ በእርዳታ በሚገኝ ሃብት የሚሸፈን ነበር። ይህ እውነታ ሃገሪቱ አሁንም ድጋፍ ጠባቂ ብትሆንም፣  በእርዳታ ላይ ያላት ጥገኝነት በምን ያህል ከፍተኛ መጠን እንደቀነሰ ያሳያል።

ኢትዮጵያ ባለፉ ሁለት ተኩል አስርት ዓመታት በመላ ሃገሪቱ ዋስትና ያለው ሰላም ማስፈን ችላለች። ይህ ሰላምና መረጋጋት ከሁለት ተኩል አስርት ዓመታት በፊት አንቀላፍቶ የነበረውን ኢኮኖሚ አነቃቅቶታል። ሰላምና መረጋጋት የፈጠረው የኢኮኖሚ መነቃቃት መንግስት ከሚከተለው ልማታዊ ፖሊሲ ጋር ተዳምሮ ባለፉ አንድ ተኩል አስርት ዓመታት በአማካይ ባለሁለት አሃዝ የኢኮኖሚ እድገት ማስመዘገብ አስችሏል። የኢኮኖሚ እድገቱ ደግሞ በህዝቡ የኑሮ ሁኔታ መሻሻል የተገለጸ ልማትን አስከትሏል።

የህዝቡ ኑሮ ላይ የታየውን ለውጥ የሚያሳዩ መረጃዎችን እንመለከት። የመጀመሪያው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ትግበራ በተጀመረበት 2003 ዓ/ም 396 ዶላር የነበረው የሃገሪቱ ዜጎች የነብስ ወከፍ ገቢ አሁን በእጥፍ አድጎ 794 ዶላር ደርሷል። ይህ የነብስ ወከፍ ገቢ እድገት በ2017 ዓ/ም ባለመካከለኛ ገቢ ሃገር ለመሆን የተያዘው ራዕይ ሊሳካ የሚችል መሆኑን ያመለክታል። በ1997 ዓ/ም የሃገሪቱ የድህነት ምጣኔ 38 ነጥብ 7 በመቶ ነበር። ከአምስት ዓመታት በኋላ በ2003 ዓ/ም የድህነት ምጣኔው ወደ 29 ነጥብ 6 በመቶ ዝቅ ብሏል።

ከዚህ በኋላ እስከ 2007 ዓ/ም ባሉት አምስት የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ትግበራ ዓመታት የድህነት ምጣኔው ወደ 22 ነጥብ 2 በመቶ ዝቅ ብሏል። ከዚህ ጋር ተያይዞ ባለፉት ዓመታት በተመዘገበው ዕድገት ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር ተችሏል። በተለይም በከተሞች ውስጥ የነበረው ሥራ አጥነት ምጣኔ እየቀነሰ መጥቷል። ሆኖም አሁንም ድህነቱና ሥራ አጥነቱ ያፈጠጠ ችግር ነው።

ከላይ በሰፈሩት መረጃዎች የሚገለጸው እድገትና ልማት፣ ሃገሪቱ በዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ግንኙነት ውስጥ ያላትን ስፍራም ቀይሮታል። አሁን ኢትዮጵያ ከበለጸጉ ሃገራትና ከዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ተቋማት ጋር ያላት ግንኙነት የረጂ ተረጂ ግንኙነት መሆኑ እየተቀየረ መጥቷል። ኢትዮጵያ የበለጸጉ ሃገራት ባለሃብቶች ለኢንቨስትመንት የሚጎመጇት ሃገር እየሆነች መጥታለች። ዓለም አቀፍ ቦንድ መሸጥ የቻለችበት ደረጃ ላይ ደርሳለች። የዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት (ባንኮች) አባል እየሆነች ነው።

ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት ውስጥ ያላትን ስፍራ የሚያሳዩ የተወሰኑ የቅርብ ጊዜ አስረጂዎችን እንመልከት። የአለም ባንክ ሰሞኑን በኢትዮጵያ ሁሉን አሳታፊና ተጠቃሚ የሚያደርግ እድገት ማስመዝገብ ያስችላል የተባለለት የአምስት አመት የትብብር ማዕቀፍ ይፋ አድርጓል።

ይህ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ምክክር በማድረግ የተዘጋጀ የትብብር ማዕቀፍ፣ በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ቅድሚያ በተሰጣቸው ጉዳዮች ላይ ያተኩራል። አዲሱ የትብብር ማዕቀፍ ኢትዮጵያ ሁሉን የሚያሳትፍ እና ተጠቃሚ የሚያደርግ የእድገት ጉዞ እንዲኖራት እንደሚያግዝ የዓለም ባንክ አስታውቋል።

ማዕቀፉ በገጠርና ከተማ የትምህርት ተቋማት እንዲስፋፉ በማደረግ፣ በገበያ ትስስርና ለወጣቶች ሰፊ የስራ እድል እንዲፈጠር በማድረግ የሀገሪቱን መዋቅራዊና ኢኮኖሚያዊ ሽግግር ያግዛል ተብሏል። ከዚህ በተጨማሪ የትብብር ማዕቀፉ የተቋማትን ተጠያቂነት ለማሳደግና ሙስናን ለመከላከል የማህበራዊ ተጠያቂነትን ማጎልበት ላይ የሚከናወኑ ተግባራት ላይ እንደሚያተኩርም ተነግሯል።

የማዕቀፉን ይፋ መሆን አስመልክተው የዓለም ባንክ የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ክሎሪን ተርክ በሰጡት መግለጫ፣ ማዕቀፉ በኢትዮጵያ ድህነትን ለማስወገድና የሀገሪቱን ቁልፍ ችግሮች ለመፍታት ባንኩ የሚያደርገውን ድጋፍ ያጠናክራል፤ ዜጎች በሀገሪቱ ልማት በስፋት እንዲሳተፉ፣ ከሚመዘገበው እድገትም ተጠቃሚ እንዲሆኑ፣ በተለይም ወጣቶች የስራ እድል የሚያገኙበትን ሁኔታም ይደግፋል ብለዋል።

ባንኩ ማዕቀፉን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ የግሉ ዘርፍ የኢትዮጵያ መፃኢ እድገት ዋነኛ አንቀሳቃሽ ይሆናል፤ የትብብር ማዕቀፉ በግሉ ዘርፍ ላይ ትኩረት አድርገው ከሚሰሩ የአለም ባንክ ተቋማት ጋር ልዩ ትስስር እንዲፈጠር ያግዛል ብሏል። የትብብር ማዕቀፉ ኢትዮጵያ እ ኤ አ በ2025 ዓ/ም መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገራት ተርታ ለመሰለፍ የያዘችውን ራዕይ ሊያሰናክሉ የሚችሉ ችግሮችን ለመፍታት ያግዛልም ተብሏል። በሁሉም የሀገሪቱ ክፍል የጤና፣ የትምህርት እና ውሃ አቅርቦት ለማዳረስ የሚደረገውን ጥረት እንደሚያጠናክርም ተገልጿል።

ይህን የልማት ማዕቀፍ ያዘጋጀው የዓለም ባንክ፣ ኢትዮጵያ በፈረንጆቹ 2017 ዓ/ም የ8 ነጥብ 3 በመቶ እድገት እንደምታስመዘግብ ተንብይዋል። ባንኩ በግንቦት ወር  ያወጣው የዓለም ኢኮኖሚ እድገት ትንበያ ሪፖርት፣ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊ እድገት ዓለም ላይ ከሚመዘገቡ ፈጣን ኢኮኖሚያዊ እድገቶች አንዱ መሆኑን ይናገራል።

ዝቅተኛ ገቢ ካላቸው ሃገራት አንጻር ሲታይ ደግሞ የኢትዮጵያ እድገት ፈጣኑ እንደሚሆን የትንበያው ሪፖርት ይገልጻል። ኢትዮጵያ በእድገት ትንበያው መሰረት ከአፍሪካም ቀዳሚ ስትሆን ታንዛኒያ በ7 ነጥብ 2፣ አይቬሪኮስት በ6 ነጥብ 8 እንዲሁም ሴኔጋል በ6 ነጥብ 7 ይከተላሉ። እርግጥ የኢፌዴሪ መንግስት ቢያንስ የ10 በመቶ እድገት ይመዘገባል የሚል ትንበያ ነው ያለው።

የዓለም ባንክ የልማት ማዕቀፉን ይፋ ባደረገበት በዚሁ ሰሞን የአውሮፓ ኢቨስትመንት ባንክ በኢትዮጵያ ልዩ የፋይናንስ ፕሮግራም ጀምሯል። ባንኩ በዚህ የፋይናንስ ፕሮግራሙ መሰረት፣ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር የ1 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር የብድር ስምምነት ተፈራርሟል። ገንዘቡ በግብርና ማቀነባበሪያና በማምረቻ ዘርፎች ለተሰማሩ የጥቃቅን፣ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች የፋይናንስ አገልግሎት የሚውል ነው ተብሏል። በጨርቃጨርቅ፣ በቆዳና በግብርና ምርት ማቀነባበሪያ ዘርፎች ለተሰማሩ ኢንተርፕራይዞች የመሳሪያ አቅርቦት የሊዝ ስርዓቱን ለማጠናከር ዓላማ እንደሚውልም ተገልጿል።

በሌላ በኩል፣ ባለፈው ግንቦት ወር 56 ሃገራትን በአባልነት ያቀፈው የእስያ መሰረተ ልማት ኢንቨስትመንት ባንክ ኢትዮጵያን በአባልነት ተቀበሏል። ኢትዮጵያ የዚህ ባንክ አባል በመሆን ከደቡብ አፍሪካና ግብጽ ቀጥላ ሶስተኛዋ አፍሪካዊት ሃገር ነች። ኢትዮጵያ የባንኩ አባል መሆኗ ሃገሪቱ ለጀመረቻቸው የመሰረተ ልማት ዝርጋታዎች የሚያግዝ በቂ የብድር አቅርቦት የማግኘት እድል እንዲኖራት ያደርጋል። ለመሰረተ ልማት ግንባታ ከሚገኘው ብድር በተጨማሪ፣ ማምረቻና ማዕድን ለመሳሰሉ አዋጪ የልማት ፕሮጀክቶች እንዲሁም ለአቅም ግንባታ ተግባራት ድጋፍ የማግኘት እድልም ይኖራታል። ከባንኩ የሚገኘው ብድር አነስተኛ ወለድ ያለው ነው።

የኢትዮጵያን ዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ግንኙነት ደረጃ ከሚያሳዩ የሰሞኑ በርካታ እውነታዎች መሃከል አንድ ልጨምርና ላብቃ። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በያዝነው የሰኔ ወር የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን በተመለከተ ባወጣው ሪፖርት በፈረንጆቹ 2016 የኢትዮጵያ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት የ46 በመቶ እድገት ማሳየቱን አስታውቋል። አጠቃላይ ወደ አፍሪካ የፈሰሰው የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ግን ቅናሽ ማሳየቱን ነው ሪፖረቱ የሚያመለክተው። ሪፖርቱ ከጥር ወር 2008 እስከ ታህሳስ ወር 2009 ዓ/ም ድረስ ኢትዮጵያ 3 ነጥብ 2 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር ቀጥታ የውጭ ኢንቨስትመንት ማግኘቷን አስታውቋል።

እነዚህ ከብዙ በጥቂቱ መርጬ ያቀረበኳቸው ኢኮኖሚያዊ ሁኔታዎች ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ግንኙነት ውስጥ ያላት ስፍራ ምን ያህል እንደተለወጠ ያሳያሉ። ኢትዮጵያ አሁን ከበለጸጉና መካከለኛ ደረጃ ላይ ከሚገኙ ሃገራት ጋር ያላት ግንኙነት ዋነኛ መላ የረጂና የእርዳታ ተቀባይ መሆኑ ተቀይሯል። ግንኙነቱ በመጠቃቀም ላይ ወደተመሰረተ የትብብር ግንኙነት በመሸጋጋርር ላይ ይገኛል። ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማትም ኢትዮጵያን የሚመለከቱት፣ ልፍጆታ የምታውለው እርዳታ እንደሚለገሳት ሃገር አይደለም። ከዚህ ይልቅ የኢንቨስትመንት ካፒታል ተበድራ እድገቷን ማስቀጠል እንደምትችል ሃገር፣ በዚህም መጪ የዓለም የንግድ ሸሪክ እንደሆነች ሃገር ነው። በአጠቃላይ ኢትዮጵያ ከበለጸጉትተ ሃገራትና ዓለም አቀፍ የገነዘብ ተቋማት ጋር ያላት ግንኙነት ከለጋሽ ተለጋሽ፣ ወደ ትብብር ግንኙነት እያደገ ነው። ይህ የአዲሲቱ ኢትዮጵያ ገጽታ ነው።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy