NEWS

ከትግራይና አማራ ክልሎች በተውጣጡ የሀገር ሽማግሌዎች የተዘጋጀው ህዝባዊ ኮንፈረንስ ተሳታፊዎች መቐለ እየገቡ ነው

By Admin

July 20, 2017

በአማራ እና በትግራይ ክልሎች የሀገር ሽማግሌዎች በተዘጋጀው ህዝባዊ ኮንፈረንስ የሚሳተፉ የሀገር ሽማግሌዎች ወደ መቐለ እየገቡ ነው።

ነገ በመቐለ ከተማ በሚካሄደው ህዝባዊ ኮንፈረንስ ላይ ለመገኘት ትናንት ከ400 በላይ የሀገር ሽማግሌዎች ትግራይ ክልል ሲገቡ ደማቅ አቀባበል ተደርጎላቸዋል።

ከሰሜን ጎንደር ወገራ ወረዳ ተወክለው የመጡት የሀገር ሽማግሌ አቶ ላቀው ታደሰ የሁለቱን ክልሎች ህዝቦች ግንኙነት የሚያበላሽ አንድም ችግር አለመኖሩን ገልጸዋል።

የአማራና የትግራይ ህዝብ የውጭ ወራሪን ለመከላከል በጋራ መስዋዕትነት ከፍለዋል በማለት አሁን በህዝቡ መካከል ምንም የጥላቻ መንፈስ እንደሌለም ተናግረዋል፡፡

የሁለቱ ክልሎች ሕዝቦች ለዓመታት የገነቡትን አብሮነት በቀጣይ አጠናክሮ ለማስቀጠል የበኩላቸውን ጥረት እንደሚያደርጉም አመልክተዋል።

በሁለቱ ህዘቦች መካከል ያለው መተሳሰብና ፍቅር እንደወትሮው ነው ያሉት ደግሞ ከሰሜን ጎንደር ተወክለው የመጡት ወይዘሮ መሰረት ደመቀ ናቸው፡፡

የትግራይ ህዝብ ልብ በሚነካ መልኩ ጥሩ አቀባበል አድርጎልናል፤ ይህም በህዝቦች መካከል ግንኙነትን የሚያደፈርስ ችግር እንደሌለ ይበልጥ ማሳያ ነው ብለዋል።

በሁለቱ ክልሎች ህዝቦች መካከል እርስ በርስ ተሳስቦና ተከባብሮ የመኖር ባህል በበለጠ እንዲጎለብት እንደሀገር ሽማግሌ የሚጠበቅባቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውንም ጠቁመዋል።

የሁለቱንም ህዝቦች ስር የሰደደ ግንኙነት ማጠናከርን ዓላማ ያደረገው ህዝባዊ ኮንፈረንስ ከሐምሌ 14 እስከ 16 ቀን 2009 ዓ.ም በመቀሌ ከተማ ሰማዕታት ሀውልት መሰብሰቢያ አዳራሽ ይካሄዳል።

በህዝባዊ ውይይቱ ላይ ከ1 ሺህ 200 በላይ የሁለቱም ክልል የሀገር ሽማግሌዎች ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል።