Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ከአሜሪካ መጣሹን ተምች ለመከላከል

0 471

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ከአሜሪካ መጣሹን ተምች ለመከላከል

                                                ሰለሞን ሽፈራው

መነሻውን ከልዑለ ሃይሏ ሀገረ አሜሪካ ያደረገና በተለይም የበቆሎ ሰብል ላይ የከፋ ጉዳት የሚያደርስ የተምች ወረርሽኝ አፍሪካን በስተደቡብ ክፍል ጀምሮ እያዳረሳት እንደሆነ የሚያወሳ ዜና ከሰማን ወራት ተቆጥረዋል፡፡ አትላንቲክ ውቅያኖስን ተሻግሮ እንደመጣ የሚነገርለት ይሄው የተምች ወረርሽኝ ወደ ምስራቃዊ አፍሪካ እየተስፋፋ ቀጥሎ ኢትዮጵያ ውስጥ ለመግባት ጊዜ አልፈጀበትም ነበር፡፡ በዚህ መሰረትም የዛሬ 3 ወር ገደማ ከጎረቤት ኬንያ ተነስቶ ወደ የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል አንዳንድ ዞኖች ስለመግባቱ የተደረሰበት ከአሜሪካ መጣሹ ፀረ በቆሎ የሰብል ተምች፤ ቀስ በቀስ ወደሌሎቹ የክልል መስተዳድሮች ተዛምቶ የአብዛኛው ኢትዮጵያዊ አርሶ አደር ሀገር አቀፍ ራስ ምታት ለመሆን ቻለ፡፡

 

ከአሁኑ ወቅታዊ መረጃ መረዳት እንደሚቻለው ከጥቂት የሀገራችን ክፍሎች በስተቀር ከአሜሪካ መጣሹ የተምች ወረርሽኝ ያልተከሰተበት የአርሶአደር ክልል የለም ብንል ከእውነት መራቅ አይሆንም፡፡ በእርግጥ ፀረ በቆሎው አዲስ መጤ የተምች ወረርሽኝ የሚከሰትበት ስፋት ከክልል ክልል ሊለያይ እንደሚችል ይታመናል፡፡ ለአብነት ያህልም የተምች ወረርሽኙ ለመጀመሪያ ጊዜ በታየበት የደበብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ውስጥ የሚገኙ በርካታ በቆሎ አምራች  ዞኖችና ወረዳዎችን ያዳረሰ የስርጭት ስፋት እንዳለው መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡

የበቆሎ ሰብልን የሚያጠቃው የተምች ወረርሽኝ ክልሉን ወደሚያዋስኑት የምዕራብና የደቡብ ምስራቅ ኦሮሚያ ዞኖች ሰፋ ባለ መልኩ ሳይዛመት እንዳልቀረ መረጃዎቹ ያስረዳሉ፡፡ እንዲሁም ደግሞ ከምዕራብ ኦሮሚያ ዞኖች የተነሳው የተምች ወረርሽኙ መንጋ የስርጭት አድማሱን ከቀን ወደቀን እያሰፋ  በጋምቤላ፤ በቤንሻንጉል ጉሙዝ፤ በአማራና በትግራይ ብሔራዊ ክልሎች አንዳንድ ወረዳዎች ውስጥ መታየቱን ከፌደራል የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር የስራ ሃላፊዎች ማብራሪያ ተረድቻለሁ፡፡ ይሁን እንጂ ከአሜሪካ የወጣው ፀረ በቆሎ የተምች ወረርሽኝ ሊያደርስ የሚችለውን ጉዳት ለመቀነስና ከተቻለም ጨርሶ ለመከላከል ሲባል የሚደረገው ፈርጀ ብዙ ጥረት አሁን ላይ አወንታዊ ውጤት እያስገኘ መሆኑን ከተሰጠው መግለጫ መገንዘብ ተችሏል፡፡

የተምች ወረርሽኝ የበቆሎ ሰብል ላይ ሊያደርስ የሚችለውን የውድመት አደጋ የመከላከሉ ጥረት ጎላ ባለ መልኩ ከሚካሄድባቸው የሀገራችን ክፍሎች መካከል አንዱና ምናልባትም ዋነኛው በሆነው የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ውስጥ፤ አርሶ አደሩ ህብረተሰብ ተባዩን ለማጥፋት ሲል እያሳየ ያለውን ፈርጀ ብዙ ርብርብ በሚመለከት፤ ከሰሞኑ መገናኛ ብዙሃን ያስደመጡንን ዜና ማስታወስ ተገቢ ይመስለኛል፡፡ እናም የክልሉ መንግስት የግብርናና ገጠር ልማት ቢሮ ሃላፊ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን በቅርቡ በሰጡት ማብራሪያ ፤ የተምች ወረርሽኙ እስካሁን ድረስ ባደረሰው ጥቃት ምክንያት አንድም የበቆሎ ማሳ ከጥቅም ውጭ የመሆን ዕጣ ይገጥመዋል ተብሎ አይታመንም፡፡

ተምች ወረርሽኝ ለመከላከል ሲባል እየተደረገ ያለው ሀገር አቀፋዊ ጥረት፤ ቢራቢሮ መሳዩን ተባይ በእጅ እየተለቀሙ መግደልን ጨምሮ፤ እንዲሁም ተምቹን የሚያጠፋ ኬሚካል የመርጨትና የማፍሰስን አማራጮች በመጠቀም እንደሆነ የገለፁት የቢሮ ሃላፊው  በተለይም የእጅ ለቀማው ከኬሚካል ርጭቱ  ይልቅ አመርቂ ውጤት ሊያመጣ እንደሚችል ተጠይቆ ሲመልሱ ‹‹ የእስካሁኑ ግብረ መልሳችን የሚያሳየው ኬሚካሉ በተሟላ መልኩ ወረርሽኙ ላይ ስለማያርፍ ነው ማለት ይቻላል›› ካሉ በኋላ ‹‹ ለምሳሌ ኬሚካሉን ከመርጨት ይልቅ አርሶ አደሩ ራሱ በጥንቃቄ ይዞ የበቆሎው አገዳ ሙሽራ ውስጥ እንዲያፈሰው ማድረግ ተምቹን ጨርሶ በመግደል ረገድ አስተማማኝ ውጤት ያለው ሆኖ አግኝተነዋል›› በማለት አክለዋል፡፡

ከዓለማችን ልዕለ ሀያል ሀገር ከዩ.ኤስ አሜሪካ ወደ መላው የአፍሪካ አህጉር እንደተዛመተ የሚነገርለት ይሔው ‹‹ ፎል አርሚ ወር›› የተሰኘ የተምች ወረርሽኝ፤ በተለይም የበቆሎ ሰብልን የሚያጠቃበት አግባብ፤ ቅጠሉ ላይ ሳይወሰን አገዳውን እስከ ሙሽራው ድረስ በመግባት እንክት አድርጎ የሚበላ ሆኖ የመገኘቱ ጉዳይ የመከላከል ጥረቱን እጅግ ፈታኝ እንዲሆን አድርጎታል ለሚለው ጉዳይ እርሳቸው የሰጡት ማብራሪያ ‹‹አሁን አሁን አርሶአደሩ ህብረተሰብ የተባዩን ማጥፊያ ዘዴ እየለመደው መጥቷል›› የሚል እንደነበርም አስታውሳለሁ፡፡ በእርግጥም ደግሞ ከአሜሪካ የመጣው ፀረ የበቆሎ ሰብል ተምች በታየባቸው ሌሎች የሀገራችን አካባቢዎች የሚኖረው አርሶአደር ህዝብ ጭምር የተባይ ወረርሽኙን እንዴት መከላከል እንደሚቻል ከጊዜ ወደ ጊዜ ልምድ እየቀሰመ መጥቷል፡፡

ለአብነት ያህልም የተምች ወረርሽኙ ጎላ ባለ መልኩ ከተከሰተባቸው የኦሮሚያ ክልል አካባቢዎች አንዱ በሆነው የባሌ ዞን የሚገኘው አርሶአደር ህብረተሰብ የበቆሎ ሰብሉን በመከላከል ረገድ እያደረገ ስላለው ፈርጀ ብዙ ጥረት የዞኑ አስተዳዳሪዎች በቅርቡ ለመገናኛ ብዙሃን የሰጡት ማብራሪያ ላይ ተመሳሳይ ይዘት ያለው አስተያየት መስማቴን ማስታወስ ይቻላል፡፡ እንዲሁም ደግሞ በአንዳንድ የትግራይና የአማራ ክልሎች ምዕራባዊ ክፍል የሚገኙ ወረዳዎች ውስጥ አዲስ መጤው ፀረ በቆሎ ተምች ታይቶ ነዋሪው ህዝብ ከግብርና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች የተሰጠውን ምክር እየተከተለ ተባዩን በእጅ ለቀማ ተግባር የመከላከል እርምጃ እንደወሰደ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን በብሔራዊ ሬዲዮ ጣቢያው የዘገበው ዜና  አመልክቷል፡፡ ይህ እንግዲህ ተጠቃሹን ከአሜሪካ መጣሽ የሰብል ተምች ወረርሽኝ በመከላከል ረገድ አርሶ አደሩ ህብረተሰብ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ጋር በተቀናጀ መልኩ ተንቀሳቅሶ እያመጣ ስላለው አመርቂ ውጤት እንደ አብነት የሚጠቀስ እንጂ ተባዩ የከፋ ጉዳት ያደረሰበት የሀገራችን አካባቢ አይኖርም ማለት እንዳልሆነ ግንዛቤ ይወሰድልኝ፡፡

ሌላው ተያያዥ ጉዳይ ደግሞ፤ ሰሞኑን በፀረ የበቆሎ ሰብል ተምች ምክንያት ጉዳት የደረሰባቸውን የደቡብና የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ያካተተ አንድ ችግሩን በዘላቂነት ስለመፍታት አስፈላጊነት የሚመክር አህጉር አቀፍ ስብሰባ እዚሁ አዲስ አበባ ውስጥ መካሔዱን የሚመለከት ነው፡፡ የስብሰባውን ዋነኛ አላማ የኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ሃላፊው ሲያስረዱ ‹‹ከአሜሪካ የመጣው የተምች ወረርሽኝ በተከሰተባቸው የአፍሪካ ሀገራት ውስጥ የሚገኙ በቆሎ አምራች አርሶአደሮች ላይ ተባዩ ስላደረሰውና አሁንም እያደረሰ ስላለው አጠቃላይ ጉዳት፤ ጥናታዊ መረጃ ማሰባሰብን ጨምሮ፤ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የሚያስችል የገንዘብ ድጋፍ ከውጭ መንግስታት የሚገኝበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ያለመ ነው ›› ብለዋል፡፡

ፀረ የበቆሎ ሰብል የተምች ወረርሽኙ የመጣባት ዩ.ኤስ አሜሪካ መጤው ተባይ በመከሰቱ ምክንያት ላልተጠበቀ ኢኮኖሚያዊ ጉዳት እየተዳረጉ ለሚገኙት አፍሪካውያን አርሶአደሮች አንዳች የመቋቋሚያ ድጋፍ  አሜሪካ እንድታደርግላቸው የሚያስገድድ የሞራል ሃላፊነት ሊሰማት እንደሚገባ፤ አንድ የስብሰባው ተሳታፊ ኬንያዊ በአፅንኦት ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡ ስለዚህም ሰሞነኛው አህጉር አቀፍ የምክክር መድረክ ላይ ከአሜሪካ የመጣውን የሰብል ተምች ለመከላከል ሲባል እየተደረገ ያለውን ጥረት ይበልጥ አጠናክሮ ማስቀጠል ስለሚቻልበት የጋራ መፍትሄ የተነሱ አማራጮች ሁሉ፤ ወደ ተግባር ተለውጠው፤ ኢትዮጵያውንን ጨምሮ፤ ሌሎች በቆሎ አምራች የአህጉሪቱ አርሶአደሮች ላይ የተጋረጠው ስጋት የሚቀለበስበት ሁኔታ እንዲፈጠር ነው የኔ ምኞት፡፡ በተረፈ ግን  እኛ አገር ውስጥ የተምች ወረርሽኙን ለመከላከልና እንዲሁም ጨርሶ ለማጥፋት የሚደረገውን ፈርጀ ብዙ ጥረት በተቀናጀ የህዝብ ንቅናቄ ማስቀጠል እስከተቻለ ከአሜሪካ መጣሹ ፀረ በቆሎ ተምች የአርሶአደሩ ህብረተሰባችን ስጋት መሆኑ የማይቀርበት ምክንያት አይታየኝም፡፡ ስለዚህም የጽህፌ ማጠንጠኛ የሆነውን የተመች ወረርሽኝ በመከላከል ረገድ የተደረገ ያለው ሀገር አቀፋዊ ጥረት የሚፈለገውን ያህል አመርቂ ውጤት ያመታ ዘንድ ጉዳዩ ሚመለከታቸው የፌዴራሉና የየክልል መንግስታት ባለድርሻ አካላት ሁሉ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ መወጣት ይጠበቅባቸዋል እላለሁ፡፡

  

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy