Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ክረምትና የእርሻ ሥራ

0 1,336

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ክረምትና የእርሻ ሥራ

ብ. ነጋሽ

ክረምቱ ጥሩ ይዟል። የክረምት ዝናብ የሚያገኙት አብዛኞቹ የሃገሪቱ አካባቢዎች መደበኛና ከመደበኛ መጠን በላይ ዝናብ እያገኙ መሆኑን፣ ይህ ሁኔታም እንደሚቀጥል የብሄራዊ ሜቲዮሮሎጂ ኤጀንሲ የትንበያ መረጃ ያመለከታል። ከ85 በመቶ በላይ ምርት እንደሚገኝበት የሚገመተው የሃገሪቱ የክረምት እርሻም በጥሩ ሁኔታ እየተካሄደ ነው፤ የዝናብ እጥረት ፈተና አልገጠመውም። እርግጥ ዝናብ አጠር በሆኑ የሃገሪቱ አካባቢዎች እንደወትሮው ሁሉ አሁንም አስተማማኝ ሁኔታ ያለ አይመስልም።

በተለይ በኦሮሚያ ምስራቅ ሃረርጌ ዞን ባልተለመደ ሁኔታ የዝናብ እጥረት ማጋጠሙን አርሶ አደሮች እየተናገሩ ነው። በዚህ ዞን በቡቃያ ደረጃ ያለ የበቆሎ ሰብል በዝናብ እጥረት የቀነጨረበትና የደረቀበት ሁኔታ መኖሩን ከመገናኛ ብዙሃን ሰምተናል። በአጠቃላይ ግን የክረምቱ የዝናቡ ሁኔታ መልካም ነው።

የእርሻና የተፈጥሮ ሃብት ሚኒስቴር ሰሞኑን እንዳስታወቀው በመላ ሃገሪቱ በክረምት ይታረሳል ተብሎ ከሚጠበቀው 12 ነጥብ 5 ሚሊየን ሄክታር መሬት ውስጥ ግማሽ ያህሉ ታርሶ በዘር ተሸፍኗል። የተቀረውም እነደየአዝርዕቱ አይነት፣ ክረምቱ እስኪወጣ ደረስ ወቅቱን ጠብቆ እንደሚዘራ ሚኒስቴሩ ጠቁሟል። በዘር ከተሸፈነው መሬት ውስጥ አንድ አራተኛ ያህሉ ምርታማነትን እስከእጥፍ ሊያሳድግ በሚችለው የመስመር እርሻ የተዘራ መሆኑንም መረጃዎች ያመለክታሉ።

ምርታማነትን ማሳደግ ከሚያስችል ግብአት በተለይ ከማዳበሪያ አኳያ ዘንድሮ የተሻለ አቅርቦት መኖሩን የእርሻና ተፈጥሮ ሃብት ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል። እንደ ሚኒስቴሩ መረጃ፣ ዘንድሮ ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጻር በ5 ሚሊየን ኩንታል ብልጫ ያለው ማዳበሪያ ቀርቧል። ይሁን እንጂ የማዳበሪያ እጥረት መኖሩን አርሶ አደሮች ሲገልጹ ተሰምቷል። ይህን አስመልክቶ የእርሻና የተፈጥሮ ሃብት ሚኒስቴር በሰጠው መገልጫ፣ ዘንድሮ የማዳበሪያ ዋጋ በኩንታል ከ4 መቶ እስከ 5 መቶ ብር ቅናሽ በማሳየቱ ፍላጎቱ ባለፈው ዓመትና ከዚያ ቀደም ከነበረው በመብለጡ የተፈጠረ ችግር መሆኑን አስታውቋል።

እንግዲህ የሃገሪቱ እርሻ እጅግ በአመዛኙ በዝናብ ላይ ጥገኛ ነው። እስካሁን ያለው ሁኔታ ግን ተስፋ ሰጪ ነው። በቀጣይ አንድ ተኩል ወር ጊዜ በሚያጋጥመው የዝናብ ሁኔታ የሚፈጠረውን ከወዲሁ አፍ ሞልቶ መናገር ባይቻልም፣ እስካሁን ካለው የዝናብ መጠንና ስርጭት፣ እንዲሁም ምርታማነትን የሚያሳድግ ግብአትና የእርሻ ቴክኖሎጂ አጠቃቀም አኳያ ሲታይ በመኸር እርሻ ይገኛል ተብሎ የታቀደውን 345 ሚሊየን ኩንታል ምርት ማሳካት የሚቻልበት እድል አለ።

ዘንድሮ ከእርሻ ስራ ጋር በተያያዘ ያልተለመደ ስጋት ያስከተለ ችግር ማጋጠሙ ይታወቃል። ይህም ከአሜሪካ መጣሽ ተምች ወረርሽኝ ጋር የተየያዘ ነው። ይህ ፎል በመባል የሚታወቅ ተምች ባለፈው ዓመት ጥር ወር ላይ በምዕራብ አፍሪካ ከተከሰተ በኋላ ባሉት ጊዜያት ወደተቀረው የአፍሪካ አካባቢ ተዛምቶ ሃያ አምስት ሃገራትን አዳርሷል።

ኢትዮጵያ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ የታየው በያዝነው ዓመት መጋቢት ወር ገደማ በደቡብ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል ነበር። ከአምስት ወራት ቀደም ብሎ በመጋቢት ወር በደቡባዊ የሃገሪቱ ክፍል የተከሰተው የተምች ወረርሽኝ በአሁኑ ወቅት የጥቃት አካበቢውን በማስፋፋት ስድስት ክልሎችን አዳርሷል። በደቡብ ክልል ሁሉም ዞኖች፣ በአሮሚያ ክልል ሰባት ዞኖች፣ በአማራ ክልል ምስራቅና ምዕራብ ጎጃም፣ በትግራይ፣ በጋምቤላና ቤንሻጉል ጉሙዝ ክልሎች ላይ ተከስቷል። በአጠቃለይ በእነዚህ ክልሎች ከሚገኝ 2 ሚሊየን ሄክታር የበቆሎ እርሻ ውስጥ 22 በመቶ ወይም በ455 ሺህ ሄክታር የሚደርስ መሬት ላይ የተዘራ የበቆሎ ሰብል ላይ ጥቃት አድርሷል።  

ይህ ተምች ከ100 በላይ የተለያዩ ሰብሎችን ያጠቃል። በተለይ የሚያጠቃው ግን በቆሎና ማሽላን ነው። በቆሎና ማሽላ በኢትዮጵያ በስምጥ ሸለቆ ቆላማና ወይና ደጋ አካባቢዎች፣ በምእራብ እርጥበታማና በምስራቅ ደረቃማ አካባቢዎች የሚኖረው ህዝብ ዋና የምግብ ሰብል በመሆን ያገለግላሉ። ተምቹ በተለይ የጎላ ጥቃት በማደረስ የሚታወቀው በቆሎና ማሽላን ቢሆንም፣ ስንዴ፣ ገብስ፣ ማሽላ፣ ዳጉሳ፣ አኩሪ አተር፣ ድንች፣ ወዘተን ያጠቃል።

የአሜሪካ መጤ ተምች በሰብል ምርታማነት ላይ የሚያደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ በባህላዊ መንገድ የተከናወኑ የመከላከል ተግባራት ውጤታማ መሆናቸውን የእርሻና ተፈጥሮ ሃብት ሚኒስቴር አስታውቋል።

በኢትዮጵያ ተምቹ በተከሰተባቸው አካባቢዎች የመከላከል እርምጃ የተወሰደው ከጅምሩ ነበር። በቀዳሚነት የተመረጠው የመከላከል እርምጃ ተምቹን በእጅ እየለቀሙ በመግደል ከማሳ ውስጥ ማስወገድና እንዳይዛመት መከላከል ነው። ከፌደራል የእርሻና የተፈጥሮ ሃብት ሚኒስቴርና ከክልል ቢሮዎች የተገኘ መረጃ እንደሚያመለክተው እስካሁን በተካሄደ ተምቹን በመልቀም የማስወገድ እርምጃ የተምቹ ወረርሽኝ ከተከሰተባቸው እርሻዎች 70 በመቶ ያህሉን ከጥቃት መከላከል ተችሏል። ህዝባዊ ንቅናቄ በታወጀበት በዚህ ተምች የመከላከል እንቅስቃሴ ላይ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት የሚሰጡ ወጣቶች የተሰማሩበት ሁኔታም አለ፤ በተለይ በኦሮሚያ ክልል። እስካሁን በተምቹ ጥቃት ሙሉ በሙሉ የወደመ እርሻ የለም።

ተምቹን በባህላዊ መንገድና እንደአስፈላጊነቱ በኬሚካል ርጭት ከመከላከል የአስቸኳይ ጊዜ ተግባር በተጨማሪ ዘላቂ መፍትሄ የማፈላለግ ጉዳይም ትኩረት ተሰጥቶታል። የኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት፣ ተምቹ የሚያደርሰውን ጉዳት ለመከላከል ዘለቄታዊ መፍትሄ እያጤነ መሆኑን አስታውቋል። ኢንስቲትዩቱ፣ ተምቹ በኢትዮጵያ በበቆሎ ሰብል ላይ  በስፋት መከሰቱንና ጉዳትም ሊያደርስ የሚችል መሆኑን ከግምት በማስገባት በቀጣይ ሃገራዊ ምርታማነት ላይ ችግር ሳያስከትል ዘለቄታዊ ርምጃዎችን መውሰድ ያስፈልጋል የሚል አቋም ይዟል።  ተምቹን በዘላቂነት ለመከላከል መወሰድ ይገባቸዋል በሚል ከተቀመጡ አማራጭ እርምጃዎች መሃከል አንዱ የተምቹን ጥቃት የመቋቋም አቅም ያላቸው ዝርያዎች ከውጭ ማስገባትን የሚመለከት ነው።

አሜሪካ መጣሹን ተምችም ሆነ ሌሎች የሰብል በሽታዎችን በዘላቂነት ለመከላከል የምርምር ስራ ወሳኝ መሆኑን ያመለከተው የኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢኒስቲቲዩት፣ ለዚህም ሲባል  ከኢንስቲትዩቱ፣ ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት፣ ከክልል የምርምር ተቋማትና ከእርሻና ተፈጥሮ ሃብት ሚኒስቴር የተውጣጣ አማካሪ ምክር ቤት መቋቋሙን አስታውቋል።

ከዚህ በተጨማሪ ሰሞኑን የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ አሜሪካ መጤ ተምቹን መከላከል የሚያስችል የመድሃኒት ግኝት ፍንጭ ላይ መድረሱን አስታውቋል። በዩኒቨርሲቲው የግብርና ኮሌጅ ተመራማሪዎች እንደተገኘ የተገለጸው ይህ መድሃኒት ተምቹን በአምስት ደቂቃ ውስጥ መግደል እንደሚችል ዩኒቨርሲቲው አስታውቋል።

መድሃኒቱ ከተለያዩ እጽዋት በተፈጥሯዊ መንገድ በቅመማ የተገኘ መሆኑንና ኬሚካላዊ ይዘት እንደሌለው ዩኒቨርሲቲው አስታወቋል። ዩኒቨርሲቲው ለሁለት ወራት ያህል ምርምር ሲያካሄድ እንደነበረና በአራት ወረዳዎች ውስጥ በሚገኙ የአርሶ አደር ማሳዎች ላይ በተደረገ ሙከራ፣ ፀረ ተምች መድሃኒቱ ውጤታማ መሆኑን ተመራማሪዎቹ በሙከራ ማረጋገጣቸውን፣ የአሜሪካ መጤ ተምቹን ለመከላከል በጥቅም ላይ ከዋለው ኬሚካል የተሻለ ውጤት በአዲሱ የሙከራ ግኝት ላይ መታየቱንም ዩኒቨርሲቲው ገልጿል። ጸረ ተምች መድሃኒቱ  የሙከራ ግኝት በመሆኑ፣ ወደፊት በሚደረግ ተጨማሪ የምርምር ሂደት ሙሉ በሙሉ ውጤታማ የሆነ መድሃኒት ለማግኘት እየተሰራ መሆኑን ዩኒቨርሲቲው አመልክቷል።

ወደፊትም በመድሃኒቱ አጠቃቀም ዙሪያ ለግብርና ባለሙያዎችና ለሚመለከታቸው አካላት የግንዛቤ ማስጨበጫ በመስጠት፣  በሙከራ ደረጃ ጥቅም ላይ በዋለባቸው ወረዳዎች  የተምቹን ስርጭት ለመከላከል በዩኒቨርሲቲው ምክትል ፕሬዝዳንት የሚመራ አንድ ቡድን መቋቋሙም ታውቋል። በሙከራ ደረጃ የተገኘው የፀረ ተምች መድሃኒቱ በሃገር አቀፍ ደረጃ ለተከሰተው ችግር  ጥቅም ላይ እንዲውል ዩኒቨርሲቲው ከሚመለከታቸው አካት ጋር በቅንጅት  ለመስራት  ተዘጋጅቷል።

እንግዲህ፣ የክረምት እርሻ ያሀገሪቱ የሰብል ምርት 85 በመቶ ገደማ የሚመረትበት ነው። እስካሁን ያለው የዝናብ ሁኔታ፣ እንዲሁም የተሻሻለ የምርት ግብአትና ቴክኖሎጂን በመጠቀም ረገድም የተሻለ እንቅስቃሴ እየተከናወነ ነው። ከዚሀ ባሻገር በግብርና ምርት ላይ ተጽእኖ የማሳደር ስጋት የፈጠረውን አሜሪካ መጤ ተምች ለመከላከል እየተደረገ ያለው ጥረት ተስፋ ሰጪ ነው።

በቅርቡ የዓለም የምግብ ድርጅት (FAO) ይፋ ባደረገው መግለጫ የምስራቅ አፍሪካ ሃገራት በአሜሪካ መጤ ተምች ላይ የተቀናጀ የመከላከል እርምጃ ካልወሰዱ በቀጠናው የምግብ እጥረት ሊያስከትል ይችላል ሲል ማሳሰቡ ይታወቃል። በኢትዮጵያ እስካሁን በዚህ ተምች ጥቃት ምክንያት ሙሉ በሙሉ የወደመ የበቆሎ ወይም የሌላ ሰብል ማሳ የለም። ይህ የሆነው ተምቹን የመከላከል ጉዳይ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት ህዝባዊ ንቅናቄ በመፈጠሩ ነው።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy