Artcles

ኮምቦልቻ እና መቐለ ሐዋሳን ተከትለዋል

By Admin

July 18, 2017

 

ኮምቦልቻ እና መቐለ ሐዋሳን ተከትለዋል

ኢዛና ዘ መንፈስ

ሀገራችን ኢትዮጵያ በ2008 ዓ.ም መጀመሪያ ይፋ ያደረገችውን የሁለተኛው አምስት ዓመት የዕድገትና ትራንስፎርማሽን ዕቅድ ለመተግበር ያለመ ፈርጀ ብዙ ጥረት እያደረገች ትገኛለች፡፡ እናም ከዚህ አኳያ ሲታይ የኢኮኖሚያችንን መሰረት ለዘመናት ከሚታወቅበት፤ የከእጅ ወደ አፍ ዓይነት ኋላ ቀር ግብርና በማላቀቅ፤ ወደ ኢንዱስትሪያዊ ስልት ለማሸጋገር ሲባል የሚደረገው ሀገር አቀፋዊ ጥረት አመርቂ ውጤት እያመጣ ስለመሆኑ ደፍሮ መናገር ይቻላል፡፡ ለዚህ አስተያት የተሻለ ማረጋገጫ ተደርጎ የሚወሰድ ተጨባጭ ውጤት እያስገኘ ያለ የልማት ዘርፍ ደግሞ፤ በተለይም የኢንዱስትሪ መንደሮችን በመላው የሀገራችን ከተሞች የመገንባት ጥረት ነው፡፡

ስለሆነም፤ ዘርፉ የሁለተኛን አምስት ዓመት የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን ትግበራ ስኬታማነት የሚያሳይ የፈጣን ልማት ውጤት እየተመዘገበበት እንደሚገኝ፤ በዚህ አሁን እየተገባደደ ባለው የ2009 ዓ.ም በጀት ዓመት ውስጥ ብቻ ተገንብተው የተጠናቀቁትን የኢንዱስትሪ መንደሮች (ፓርኮች) እንደ አብነት ማንሳት ተገቢ ይመስለኛል፡፡ ይህን ስልም ደግሞ፤ የሐዋሳው መጠነ ግዙፍ የኢንዱስትሪ መንደር የግንባታ ስራው ተጠናቅቆ ወደ የማምረት ተግባር ስለመግባቱ ከተገለጸ ወራት መቆጠራቸው እንደተጠበቀ ሆኖ፤ እነሆ አሁን ደግሞ በመቐለና በኮምቦልቻ ከተሞች ውስጥ ተመሳሳይ ይዘት ያላቸው የኢንዱስትሪ ፓርኮች ተገንብተው ለመመረቅ በቅተዋል ማለቴ ነው፡፡ እንግዲያውስ የዚህ መጣጥፍ ዋነኛ ትኩረትም ሐምሌ 1 እና ሐምሌ 2 ቀን በተካሄደ ሥነ ሥረትዓት ተመርቀው ለምርት ተግባር ዝግጁ ስለሆኑት የኮምቦልቻና የመቐለው ኢንዱስትሪ ፓርኮች አጠቃላይ ገጽታ መጠነኛ ዳሰሳ ለማቅረብ መሞከር እንጂ የሐዋሳውን እምብዛም የሚመለከት አይደለም፡፡

ምክንያቱም ደግሞ፤ የደቡብ ኢትዮጵያ ብሄሮች፤ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልላዊ መንግስት መቀመጫ በሆነችው ሐዋሳ ከተማ ውስጥ የተገነባው የኢንዱስትሪ ልማት መንደር በአስር ሺዎች ለሚቆጠሩ ዜጎቻችን የሥራ እድል ያስገኘበትን የማምረት ተግባር ማከናወን ስለጀመሩ እኔ ራሴም ከዚህ ቀደም አንድ ጽሑፍ ማቅረቤ አይዘነጋምና ነው፡፡ ስለዚህም አሁን በቀጥታ የማልፈው፤ የትግራይ ክልሏ ዋና ከተማ መቐለና እንዲሁም ደግሞ በአማራ ክልል የደቡብ ወሎ ዞኗ ኮምቦልቻ የሐዋሳን ፈለግ እየተከተሉ መሆናቸውን ወደ ማነሳበት ሰሞነኛ ዜና ይሆናል፡፡ በዚህ መሰረትም፤ የኮምቦልቻው ኢንዱስትሪ ፓርክ ቅዳሜ ሐምሌ 1 ቀን 2009 ዓ.ም ሲመረቅ፤ የመቐለው ደግሞ በማግስቱ ዕሁድ ሐምሌ 2 ቀን 2009 ዓ.ም ተመርቆ ተከፍቷል፡፡

በሁለቱ የሀገራችን ከተሞች ውስጥ የግንባታ ሂደታቸው የተጠናቀቀውን የኢንዱስትሪ ልማት መንደሮች፤ መርቀው የከፈቱት የኢፌድሪ ጠቅላይ ሚኒስቴር ክቡር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ሲሆኑ፤ እንዲሁም ሌሎች ከፍተኛ የክልልና የፌደራል መንግስት የስራ ኃላፊዎች በስነስርዓቱ ላይ እንደተገኙ ነው ዜናውን ከዘገቡት የመረጃ ምንጮች የተረዳሁት፡፡ ስለሆነም ክቡር ጠቅላይ ሚኒስቴሩን ጨምሮ፤ ሌሎቹም በኢንዱስትሪ ፓርኮቹ የምረቃ ስነሥርዓት ላይ የተገኙ የመንግስት ባለስልጣናት፤ እንዲሁም ደግሞ የየከተሞቹ ነዋሪ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች በወቅቱ ለመገናኛ ብዙሃን ከሰጡት አስተያት አንዳንድ ነጥቦችን እያነሳን እንመለከት ዘንድ ተገቢነቱ የሚያከራክር ጉዳይ አይሆንምና አሁን በቀጥታ የማልፈው ወደ ኮምቦልቻው የምረቃ መድረክ ድባብ ነው፡፡

ከዚህ አኳያም፤ ሐምሌ 1 ቀን 2009 ዓ.ም የኮምቦልቻውን የኢንዱስትሪ ልማት መንደር መርቀው ለመክፈት በከተማዋ የተገኙት የኢፌድሪ ጠቅላይ ሚኒስቴር አቶ ኃ/ማርያም ደሳለኝና እንዲሁም ደግሞ የአማራክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው፤ በስነ ሥርዓቱ ላይ ካደረጉት ንግግር መረዳት እንደሚቻለው፤ ፓርኩ ስለሚኖረው ፈርጀ ብዙ ጠቀሜታ ለመገንዘብ የኢኮኖሚስት ምሁር መሆን አይጠበቅብንም፡፡ ምክንያቱም ደግሞ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስቴሩ ቅዳሜ ሐምሌ 1 ቀን 2009 ዓ.ም የኮምቦልቻውን ኢንዱስትሪ ልማት መንደር መርቀው በከፈቱበት ንግግራቸው “እንደዚህ ዓይነት ፓርኮችን በአንድ የተወሰነ አካባቢ ተገንብተው ወደ ስራ እንዲገቡ ማድረግ ማለት፤ በርካታ ፋብሪካዎች ተከፍተው የየራሳቸውን የማምረት ተግባር ለማከናወንና እንዲሁም ምርታቸውን በአንድ መስኮት ለገበያ ለማቅረብ እንዲችሉ የሚረዳቸውን ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል” ሲሉ ጀምረው የጉዳዩን ፈርጀ ብዙ ፋይዳ ያብራሩበት አግባብ ጠቃሚ መልዕክት ያዘለ ሆኖ ተሰምቶኛልና ነው፤፤

ለአብነት ያህልም ከዚህ ቀደም ጨረቃጨርቅና መሰል የኢንዱትሪ ምርቶችን እያመረቱ ለውጭ ገበያ በማቅረብ የኢንቨስትመንት መስክ የሚሰማሩ ባለሀብቶች ፈጥነው ወደ ስራ እንዳይገቡ ያደርግ የነበረው፤ ለማምረት ተግባር የሚያስፈልጋቸውን የኤሌክትሪክ ኃይልና ሌላም የመሰረተ ልማት አገልግሎት በወቅቱ ያለመሟላት ችግር እንደነበር ይታወቃል፡፡ እናም ችግሩን ለማቃለል፤ ፓርኮቹ ተመራጭ መፍትሔ ተደርገው እንደሚወሰዱ ነው የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስቴሩ፡፡ በእርግጥም ደግሞ እንደ ኢትዮጵያ ስር ከሰደደ የድህነትና የኋላ ቀርነት አዙሪት ለመውጣት ያለመ ፈርጀ ብዙ ጥረት በማድረግ ላይ ለሚገኝ ታዳጊ ሀገር፤ እያንዳንዱ የኢንዱስትሪ ማምረቻ ተቋም በተናጠል የሚጠይቀውን የመሰረተ ልማት አቅርቦት በወቅቱ ማሟላት ቀላል ፈተና እንደማይሆን መገመት ይቻላል፡፡ ስለዚህም ክቡር ጠቅላይ ሚኑስቴራችን እንዳሉት፤ መሰል የኢንዱስትሪ ልማት መንደሮችን በአንድ አካባቢ መገንባትና ለተቋማቱ የማምረት ተግባር እጅግ አስፈላጊ የሆኑ የመሰረተ ልማት አውታሮችን በጋራ የሚጠቀሙበትን ሁኔታ መፍጠር መቻል በርካታ ማነቆዎችን የሚያስቀር ነው ብሎ ማረቃለል ይቻላል፡፡

በግልጽ አነጋገር ጉዳዩን ለማብራራት፤ ሀገራችን ኢትዮጵያ የጀመረችውን ኢኮኖሚያዊ የመዋቅር ለውጥ የማምጣት ጥረት ለማፋጠን ሲባል የሚደረገውን ርብርብ አጠናክሮ ከማስቀጠል አኳያ፤ ቁጥራቸው እየጨመረ የሚሄድ ልዩ ልዩ የኢንዱስትሪ ምርት ማምረቻ ተቋማትን (ፋብሪካዎችን) በእያንዳንዱ ከተማ ውስጥ ተበታትነው እንዲገነቡ እናድርግ ብንል፤ የዚያኑ ያህል የመሰረተ ልማት አገልግሎትና ሌሎችም ወሳኝ ግብዓቶችን በተናጠል እያሟላን ማቅረብ ይጠበቅብናል፡፡ ያ ደግሞ እንዲህ እንደኛ አገሩ ባለ አጠቃላይ እውነታ ውስጥ ለሚገኝ አፍሪካዊ ህዝብና መንግስት የኢኮኖሚ አቅም በቀላሉ የማይታለፍ ከባድ ፈተናን ማስከተሉ እንደማይቀር ከእስከዛሬው ተሞከሯችን መረዳት አያዳግትም፡፡

ለነገሩ ቀደም ሲል በሐዋሳ፤ አሁን ደግሞ በኮምቦልቻና በመቐለ ተገንብተው የተከፈቱትን የኢንዱትሪ ልማት መንደሮች ተመራጭ የሚያደርጋቸው ምክንያት ይሄ ብቻ አይደለም፡፡ ይልቅስ ሌላ ሌላም እጅግ በጣም ጠቃሚ እንዳላቸው በምጣኔ ሀብት ሊቃውንት ጥናታዊ ግኝት ጭምር ስለተረጋገጠ እንጂ፡፡ ለምሳሌ ያህልም፤ በአንድ ስፍራ ተሰባስበው የሚገነቡት የኢንዱስትሪ ውጤቶችን ማምረቻ ተቋማቱ /ፋብሪካዎቹ/ የሚያመርቱትን ሸቀጣ ሸቀጥ ለሀገር ውስጥም ሆነ ለውጭ ገበያ እያቀረቡ የተወዳዳሪነት አቅማቸውን ለማዳበርና ለማሳደግ በተቀናጀ መልኩ የሚንቀሳቀሱበትን ምቹ ሁኔታ ይፈጥርላቸዋል ሲሉ ነው የምጣኔ ሀብት ምሁራን የሚያስረዱት፡፡ ይልቁንም ደግሞ የኢንዱስትሪ ውጤቶችን በስፋትና በጥራት እያመረቱ ለዓለም አቀፍ ገበያ የማቅረብ ፍላጎት ያላቸው የውጭ ባለሃብቶችን በመሳብ ረገድ፤ እንዲህ ዓይነቶቹ የኢንዱስትሪ ፓርኮች የሚኖራቸው ፋይዳ በቀላሉ የሚገመት እንዳልሆነም አስምረውበታል ጠቅላይ ሚኒስቴሩ፡፡

ለዚህ እንደ ጥሩ ተጫባጭ ማሳያ ሊሆነን ይችላል ሲሉ ጠቅላይ ሚስቴር ኃ/ማርያም ደሳለኝ በኮምቦልቻ የምረቃ ስነሥርዓት ላይ ያወሱትም፤ ግንባታው ከተጠናቀቀ ገና አንድ ዓመት እንኳን ባልሞላው የሐዋሳው ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ የማምረት ተግባር የመጀመሩ በርካታ የውጪ ኢንቨስተሮች መኖራቸውን ነው፡፡ በተመረጡ የሀገራችን ከተሞች እየተገነቡ ያሉት የኢንዱስትሪ ልማት መንደሮች ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያውያን ከሚያስገኙት ፈርጀ ብዙ ጥቅም ቀዳሚ ስፍራ የሚይዘው፤ በተለይም ለዜጎቻችን ሰፊ የሥራ ዕድል እየፈጠሩ መሆናቸው እንደሆነም ነው ጠቅላይ ሚኒስቴሩ አክለው የገለጹት፡፡

በእርግጥም ደግሞ በሐዋሳው የኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ እስከ ዛሬ ድረስ ወደማምረት ተግባር መግባት የጀመሩት ተቋማት ቢያንስ ለሃምሳ ሺህ ያህል ኢትዮጵያውያን ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ ዕድል እንደፈጠሩ ነው መረጃዎች የሚያመለክቱት፡፡ እንዲሁም በአንድ ሌላ የውጭ ኩባንያ ግንባታቸው የተጠናቀቀ ስድስት አዳዲስ ፋብሪካዎች ስራ ሲጀምሩ ተጨማሪ 10 ሺህ ዜጎቻችንን ከስራ አጥነት ችግር ይታደጋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ የኢንዱስትሪ ውጤቶችን ማምረቻ ተቋማቱ ምርቶቻቸውን ወደ ዓለም አቀፍ ገበያ ማቅረብ ሲጀምሩ ለሀገራችን የሚያስገኙት የውጪ ምንዛሬ በኢኮኖሚያዊ እድገታችን ላይ ሊያሳድር ስለሚችለው አዎንታዊ ተጽእኖም ከወዲሁ መገመት አይከብድም፡፡

ስለዚህ፤ ባሳለፍነው ሳምንት መጨረሻ ተመርቀው የተከፈቱት የኮምቦልቻውና የመቐለው የኢንዱስትሪ ፓርኮችም፤ አሁን ላይ ከሀገራችን ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት እየተመረቁ ለሚወጡት ወጣት ምሁራን የስራ እድል በመፍጠር ረገድ የሚኖራቸው ሚና ቀላል እንደማይሆን ነው መገመት የሚቻለው፡፡ የአማራ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስረዳደር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው፤ የኮምቦልቻ ከተማና የደቡብ ወሎ ዞን የአስተዳደር አካላት ለኢንዱስትሪ ልማት መንደሩ የግንባታ ሂደት መሳካት ስላሳዩት ጥረት ባመሰገኑበት ንግግራቸው ላይ፤ ፓርኩ ለአካባቢው ህዝብ ሊኖረው የሚችለውን ማህበረ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ መግለፃቸውም ለዚያ ይመስለኛል፡፡ ፓርኩ በአንድ ሺህ ሄክታር መሬት ላይ እንዲያርፍ ታስቦ ግን ደግሞ ለሰባት መቶ ሃምሳ ሄክታር ብቻ አስራ አምስት የማምረቻ ህንጻዎች ተገንብተዋል ያሉት ርዕሰ መስተዳደሩ ለዚህን ያህል ኢንዱስትሪ ልማት መንደሩ ግንባታ ዘጠና ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ወጪ መደረጉንም ነው የገለጹት፡፡ አስራ አምስት የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ ሸልዶችን አቅፎ የያዘው የኢንዱስትሪ መንደሩ ለሃያ ሺህ ዜጎች የሥራ እድል ያስገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅም ርዕሰ መስተዳደሩ አክለው ተናግረዋል፡፡

በተለይም ደግሞ ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተመርቀው ለሚወጡ የአማራ ክልል ወጣቶች የኮምቦልቻው ኢንዱስትሪ ፓርክ ሰፊ የሥራ ዕድል ይፈጥራል የሚል እምነት እንዳቸው የጠቆሙት አቶ ገዱ፤ ወጣት ምሁራኑ ዕድሉን በአግባቡ ይጠቀሙበት ዘንድ የሚመክር መልዕክት አስተላልፈዋል በንግግራቸው፡፡ የጠቅላይ ሚነስቴሩ የኢኮኖሚ ጉዳዮች ልዩ አማካሪ ዶክተር አርከበ ዕቑባይም እንዲሁ፤ የኢንዱስትሪ ልማት መንደሮቹ ተገንብተው ወደ ተጨባጭ የማምረት ተግባር በገቡ ቁጥር ስለሚፈጠረው ሰፊ የሥራ እድልና አጠቃላይ መነቃቃት፤ የሐዋሳውን እውነታ በመጥቀስ ሙያዊ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ የኮምቦልቻ ከተማና የአካባቢው ነዋሪ የሆኑ አንዳንድ ሰዎች በዕለቱ ለመገናኛ ብዙኃን የሰጡት አስተያትም የኢንዱስትሪ ፓርኩ መመረቅ ለልማት ተግባር የመነሳሳት ተስፋቸውን የሚያጎለብት ሆኖ እንዳገኙት ነው የገለጹት፡፡

ይህ እንግዲህ ቅዳሜ ሐምሌ 1 ቀን 2009 ዓ.ም ስለተመረቀው የኮምቦልቻው የኢንዱስትሪ ልማት መንደር ሥነሥርዓቱ ላይ የተገኙት ከፍተኛ የፌደራሉና እንዲሁም ደግሞ አማራ ክልላዊ መንግስት የሥራ ኃላፊዎች የተናገሩትን ጠቅሶ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን በዕለቱ ከስፍራው የዘገበውን ዜና መነሻ አድርጌ፤ በጉዳዩ ዙሪያ የራሴን ተጨማሪ ሃሳብ ለማከል የሞከርኩበት ሐተታ እንደሆነ ልብ ይባልልኝ፡፡ በማግስቱ ዕሁድ ሐምሌ 2 ቀን 2009 ዓ.ም የኢፌድሪ ጠቅላይ ሚኒስቴር ክቡር አቶ ኃ/ማርያም ደሳለኝና የትግራይ ክልላዊ መንግስት ባለድርሻ አካላት መርቀው ስለከፈቱት የመቐለው ኢንዱስትሪ ፓርክ አጠቃላይ ገጽታ የተዘገበበትን ዜና ያስደመጠን ደግሞ፤ ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ነበር፡፡

እናም የፋናው ጋዜጠኛ በዕለቱ ከስፍራው እንደዘገበው ከሆነ፤ የመቐለውን የኢንዱስትሪ ልማት መንደር ግንባታ ይዘት ከሐዋሳው አሊያም ደግሞ ከኮምቦልቻው እንብዛም የተከለየ የሚያደርገው መሰረታዊ ጉዳይ ያለ ሆኖ አልተሰማኝም፡፡ ምክንያቱም፤ ከትግራይ ክልላዊ ምንገስት ርዐረሰ ከተማዋ መቐለ 5 ኪሎ ሜትር ያህል ወጣ ብሎ በሚገኝ አንድ ሺህ ሔክታር መሬት ላይ እንዳረፈና አሁን የግንባታ ሂደቱ ተጠናቅቆ ለምረቃ የበቃው ግን፤ በሰባት መቶ ሃምሳ ሔክታር ላይ የተገነባው ብቻ እንደሆነ የተነገረለት የኢንዱስትሪ ፓርክ፤ 15 ለጨርቃጨርቅ ማምረቻነት የተዘጋጁ የፋብሪካ ሸልዶችን አቅፎ እንደያዘ በፋናው ዜና ዘጋቢ ሲገለጽ ሰምቻለሁና ነው፡፡ ይህን የግንባታ ሂደት ለማጠናቀቅ 92 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ወጪ ስለመደረጉም ጭምር ነው የመረጃ ምንጮቼ ያመለከቱት፡፡

እናም ከዚህ አኳያ ሲታይ፤ ይልቁንም የኮምቦልቻውና የመቐለው በጣም ተመሳሳይ ሊባል የሚችል አጠቃላይ ቁመና እንዳላቸው ደፍሮ መናገር ይቻላል፡፡ ሁለቱም የኢንዱስትሪ ልማት መንደሮች፤ ያረፉበት የመሬት ስፋት፤ እንዲሁም ደግሞ በእስከ አሁኑ የግንባታ ሂደት የጠየቁት ወጪ መቀራረብና አስራ አምስት – አስራ አምስት የጨርቃ ጨርቅ ማምረቻ የፋብሪካ ቨልዶችን አጠናቀው ማስመረቃቸው የይዞታቸውን ተመሳሳይ ገጽታ የሚያመለክት የመሆኑ ጉዳይ እንደተጠበቀ ሆኖ፤ ስራ ሲጀምሩ እያንዳንዳቸው ለ20 ሺህ ኢትዮጵውያን ዜጎች ቦታ ይኖራቸዋል ተብሎ ይታመናል፡፡ ሁለቱ ተመሳሳይ የኢንዱስትሪ ፓርኮቻችን በቀሪው 250 ሔክታር መሬት ላይ ተጨማሪ የማምረቻ ህንጻዎችን ይገነባሉ ተብሎ እንደሚጠበቅና ያኔም ሌላ የስራ ዕድል በሺዎች ለሚቆጠሩ ዜጎች ሊፈጠርላቸው እንደሚችል ታምኖበታል፡፡

ስለዚህም፤ ክቡር የኢፌድሪ ጠቅላይ ሚኒስቴር አቶ ኃ/ማርያም ደሳለኝ፤ እሁድ ሐምሌ 2 ቀን 2009 ዓ.ም በሰሜናዊቷ ኮከብ ተገኝተው የመረቁት የመቐለው ኢንዱስትሪ ፓርክ ለክልሉ ብቻም ሳይሆን፤ ለመላው የሀገራችን ህዝቦች ስለሚኖረው ፈርጀ ብዙ ጠቀሜታ ጭምር ነው የትግራይ ክልላዊ መንግስት ምክትል ርዕሰ መስተዳደር ዶክተር አዲስዓለም ባሌማ ያስገነዘቡት፡፡ በተለይም ደግሞ፤ ሀገራችን ኢትዮጵያ የነደፈችው የኢንዱስትሪ ልማት ፖሊሲ ከግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ ጋር እየተመጋገበና አርሶ አደሩን ህብረተሰብ የመዋቅራዊ ለውጡ አካል እያደረገ በሚተገበር ስኬታማ የአፈጻጸም ሂደት ታግዞ ይቀጥል ዘንድ፤ የሚያስፈልገውን ግብዓት ከማሟላት አኳያ፤ የመቐለው ኢንዱስትሪ ፓርክ ስለሚኖረው አዎንታዊ አስተዋጽኦ ምክትል ርዕሰ መስተዳደሩ የገለጹበት ማብራሪያ በእርግጥም ተስፋ የሚሰጥ ነገር እንዳለ ያመለክታል፡፡

ለምሳሌ ያህልም፤ የልማትዘርፉን በሰለጠነ የሰው ኃይል አስተማማኝ አቅም ለማንቀሳቀስና ከየወቅቱ የቴክኖሎጂ ግኝት ጋር ለመራመድ የሚያስችል ዓለም አቀፋዊ የዕውቀት ሽግግርን አስፈላጊነት ያገናዘበ ቀጣይ ጥረት ለማድረግ ስለመታሰቡ ዶክተር አዲስዓለም ባሌማ መግለጻቸው አይዘነጋም፡፡ ያም ሆነ ይህ ግን፤ በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን እንደዋነኛ የማስፈጸም ጥረታችን አመርቂ ውጤት መገለጫ ተግባር ተደርጎ ሊወሰድ በሚችለው የኢንዱስትሪ ልማት መንደሮችን የመገንባት ሀገር አቀፋዊ የቤት ስራ፤ እነሆ መቐለና ኮምቦልቻ ሐዋሳን ተከትለው ወደፊት እየተራመዱ ናቸው፡፡ አሁንስ የትኞቹ የሀገራችን ከተሞች የእነርሱን ፈለግ በመከተል የኢንዱስትሪ አብዮቱን ሰልፍ ለመቀላቀል ይበቁ ይሆን? ይሄን እንግዲህ ወደፊት አብረን የምናየው ጉዳይ ይሆናል፡፡ እኔ የዛሬውን ጽሑፌን እዚህ ላይ አብቅቻለሁ፡፡ መዓሰላማት!