Artcles

ወደምድርም እንመልከት

By Admin

July 17, 2017

ወደምድርም እንመልከት

ኢብሳ ነመራ

ወርሃ ጥር አልፎ የካቲት ሲገባ፣ ሰኔ ግም ሲል ኢትዮጵያውያን የዝናብ ነገር ያስጨንቃቸዋል። የበልግና ክረምት ዝናብ ነው የሚያስጨንቃቸው።  ሁሉም ኢትዮጵያዊ ከተሜውም ገጠሬ አርሶ አደሩም ይጨነቃል። ሰማይ ደመና ርቆት መሬት የሚያርሰው ዝናብ አጥቶ ፍሬ አልሰጥ እንዳይል ነው ጭንቀታቸው። አሁን አሁን እንጃንጂ ድሮ ዝናብ ወቅቱን ስቶ ቀናት ሲቆጠሩ ህዝብ ለእግዚዮታ ይወጣል፤ ዱኣ ይቀመጣል፣ . . .፤  ምሉዕ በኩለሄ ፈጣሪ ዝናብ እንዲያዘንብ ለመማለድ። እንዲህም ሆኖ ግን ኢትዮጵያና ድርቅ ቀጠሮ አላቸው። በየአስር፣ በየአምስት ዓመቱ፣ አሁን አሁን ደግሞ በየሶስትና ሁለት ዓመቱ ይገናኛሉ።

ታዲያ ደርቅ ቀጠሮውን ጠብቆ ሲመጣ፣ ምድር አዝርእትና ሳር አላበቅል ብላ ሰው ለምግብ እጥረት ይጋለጣል፤ እንስሳት በውሃና በግጦሽ ሳር እጦት ያልቃሉ። ድሮ ድሮ ቀጠሮውን ጠብቆ የሚመጣው ድርቅ የሰው ህይወት ምሱ ነበር። አሁን ግን ቸነፈር አስከትሎ የሰው ህይወት የማስገበር አቅም አጥሮታል። እንስሳ ማስገበሩ ቅን አሁንም አልቀረም።

እንግዲህ ሁሉም ኢትዮጵያዊ እንደሚያውቀው፣ ከ2007 በልግ ጀምሮ እስካሁን ከድርቅ ተጽእኖ አልወጣንም። የ2007 በልግና ክረምት ለግመው አምና 10 ነጥብ 2 ሚሊየን ኢትዮጵያውያን ለምግብ እጥረት ተጋልጠው ነበር። መንግስት ከዓለም አቀፍ የረድኤት ድርጅቶች ጋር ተረባርቦ ድርቁ ያስከተለው የምግብ እጥረት ወደረሃብነት ሳያድግ መከላከል ችሏል። በዚህ የድርቅ ተጽእኖ የአንድም ሰው ህይወት አልጠፋም። አንድም ሰው ከመኖሪያ ቂዬው አልተፈናቀለም። ተማሪዎች ትምህርታቸው አልተስተጓጎለም።

አሁንም 7 ነጥብ 8 ኢትዮጵያውያን ድርቅ ባስከተለው የምግብ እጥረት ተጽእኖ ስር ወድቀው የአስቸኳይ ጊዜ የምግብ እርዳታ አየተደረገላቸው ይገኛሉ። ከእነዚህ የአስቸኳይ ጊዜ የምግብ እርዳታ ከሚቀርብላቸው ዜጎች ውስጥ ለ4 ነጥብ 7 ሚሊየኑ የኢፌዴሪ መንግስት በራሱ አቅም እርዳታ የሚያቀርብላቸው ናቸው። 1 ነጥብ 7 ሚሊየን ዜጎች ደግሞ በዓለም የምግብ ፕሮግራም አማካኝነት እርዳታ የሚቀርብላቸው ናቸው። ቀሪዎቹ 1 ነጥብ 4 ሚሊየን ዜጎችም የካቶሊክ የእርዳታ ድርጅት በሚያስተባብራቸው የለጋሽ ተቋማት እርዳታ እየቀረበላቸው ይገኛል።

ታዲያ ሰሞኑን በተለይ የውጭ ሃገር መገናኛ ብዙሃን፣ በተለይ በአማርኛ ቋንቋ የሚሰራጨው የአሜሪካ ድምጽ ሬድዮ (ቪኦኤ) የዓለም የምግብ ፕሮግራምን እየጠቀሱ የህዝብ ጨራሽ ቸነፈር ምጽአት መቃረቡን እያወሩ ነው። ባለፈው ዓመት፣ ዘንድሮ የምግብ እርዳታ ከሚያስፈልገው በ2 ነጥብ 5 ሚሊየን የሚበልጥ ህዝብ በድርቅ ተጽእኖ ስር ወድቆ የቸነፈር ስጋት ሳይኖር መከላከል መቻሉን የሚያስታውሱ፣ ዘንድሮ ምን የተለየ ነገር መጣ? የሚል ጥያቄ አድሮባቸዋል። ሟርት እንዳይሆን የተጠራጠሩም አሉ።

ነገሩ እንዲህ ነው። ከላይ እንደተገለጸው በተለይ በምስራቅ ኢትዮጵያ አካባቢ፣ በድርቅ ምክንያት የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ ለሚጠብቁ ዜጎች እርዳታ የሚያቀርበው የዓለም የምግብ ፕሮግራም የእርዳታ ክምችቱ ተሟጥጧል።

የዓለም የምግብ ድርጅት የራሱ የእርዳታ ምንጭ የለውም። ከለጋሾች የሚያገኘውን እርዳታ ነው የሚያቀርበው። በያዘነው ዓመት በየመን፣ በደቡብ ሱዳን፣ በሶማሊያ፣ ናይጄርያ ወደቸነፈርነት የተቀየረ የምግብ እጥረት ስላጋጠመ፣ የዓለም ለጋሾች ትኩረት እነዚህ ሃገራት ላይ ሆኗል። ኢትዮጵያ ከ10 ሚሊየን በላይ ዜጎቿ ለምግብ እጥረት ተጋልጠው መንግስት በእርዳታ አሰጣጡ የአንበሳውን ድርሻ በያዘበት ሁኔታ ተጽእኖውን መቋቋም ስለተቻለ ለጋሾች በኢትዮጵያ የቸነፈር አደጋ ሊያጋጥም ይችላል የሚል ግምት የላቸውም።

በዚህ ምክንያት የዓለም የምግብ ፕሮግራም መናልባት ከመስከረም ወር በኋላ እስካሁን እርዳታ ሲያቀርብላቸው ለቆየው 1 ነጥብ 7 ሚሊየን ኢትዮጵያውያን እርዳታ ማቅረብ አይችልም። ይህ ማለት ግን 1 ነጥብ 7 ሚሊየኑ ኢትዮጵያውያን የዓለም የምግብ ፕሮግራም እንደሚያወራው ለቸነፈር ይጋለጣሉ ማለት አይደለም።

የኢትዮጵያ መንግስት እርዳታ ከሚያቀርብላቸው 4 ነጥብ 7 ኢትዮጵያውያን ጋር ቀላቅሎ አስፈላጊውን እርዳታ ያቀርብላቸዋል። የኢትዮጵያ መንግስት ይህን የማደረግ አቅም አለው። ብሄራዊ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን እንዳስታወቀው በመጠባበቂያ የእህል ክምችት ኤጀንሲ መጋዘን ውስጥ ከ600 ሺህ ሜትሪክ ቶን በላይ የእህል ክምችት ስላለ፣ የዓለም የምግብ ፕሮግራም እርዳታ መስጠት ቢያቋርጥ መንግስት ተረጂዎቹን ተረክቦ እርዳታ ማቅረብ እንደሚችል አስታውቋል።

ከዚህ በተጨማሪ የኢፌዴሪ መንግስት የዓለም የምግብ ፕሮግራም አቅም አንሶት የሚተዋቸውን 1 ነጥብ 7 ሚሊየን ዜጎች መመገብ የሚያስችል ባጀት የመመደብ አቅም ዓለው። ባለፈው ዓመት የድርቁ ተፅእኖ የከፋ ደረጃ ላይ ሲደርስ፣ 16 ቢሊየን ብር መድቦ እርዳታ እንዲቀርብ ማድረጉ ይታወሳል። ይህ ብቻ አይደለም። ከአቅም በላይ የሆነ የምግብ እጥረት ቢያጋጥም እንኳን፣ ይህ ተጽእኖ እስኪያልፍ ድረስ በብዙ ቢሊየን ብር የካፒታል ባጀት የሚያከናውናቸውን ግዙፍ ፕሮጀክቶች ገትቶ እርዳታ በማቅረብ ዜጎቹን መታደግ ይችላል።

በመሆኑም የዓለም የምግብ ድርጅት ለተረጂዎች የሚያቀርበው እርዳታ መሟጠጡ እውነት ቢሆንም፣ 1 ነጥብ 7 ሚሊየን ዜጎች ለረሃብ መጋለጣቸው ግን ወሸት ነው። የዓለም የምግብ ድርጅት ይህን እውነታ ከግምት ከማስገባት ይልቅ አደጋውን አጉልቶ ማሳየት የፈለገው፣ በኢትዮጵያ አስተማማኝ ሁኔታ በመኖሩ ከትኩረታቸው ውጭ ያደረጓት ለጋሾች ትኩረታቸውን ወደኢትዮጵያ እንዲመልሱ ለመኮርኮር ሊሆን ይችላል።

ያም ሆነ ይህ፣ ኢትዮጵያ አሁንም በድርቅ ምክንያት ለምግብ እጥረት የተጋለጡና በአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ ላይ ጥገኛ የሆኑ ዜጎች አሏት። ኢትዮጵያ በቀጣይም ከድርቅ ተጽእኖ ተጋላጭነት ነጻ አልወጣችም። ዘንድሮም ሰማይ ሰማይ ከማየት ያለተላቀቅነው ለዚህ ነው። ብሄራዊ የሚትሪዮሎጂ ኤጀንሲ ይፋ ያደረገው መረጃ፣ የምድር ወገብን አቋርጦ ወደ ኢትዮጵያ እየገባ ያለው እርጥበት አዘል አየር ተጠናክሮ በመቀጠሉ፣ በአብዛኛው የሃገሪቱ አካባቢዎች መደበኛና ከመደበኛ በላይ ዝናብ እንደሚኖር ያመለክታል። በተጨባጭ የሚታየው የእስካሁን  የዝናብ ስርጭትም ተስፋ ሰጪ ነው።

በጥቂት አካባቢዎች አርሶ አደሩ የማዳበሪያ አቅርቦት ችግር እንዳለበት ጭምጭምታ ቢሰማም አጠቃላይ የግብአት አቅርቦትና የክረምት እርሻው ጥሩ ነው። የማዳበሪያ ዋጋም ባለፈው ዓመት ከነበረበት በኩንታል እስከ 500 ብር መቀነሱ የማዳበሪያ ተጠቃሚዎችን ቁጥር ይጨምራል ተብሎ ይገመታል።

የእርሻና የተፈጥሮ ሃብት ሚኒስቴር፣ የተሻሻሉ የሰብል ዝርያዎችና ማዳበሪያ  ለአርሶ አደሩ መሠራጨቱን አስታውቋል። አስፈላጊው የግብርና ግብአት ለአርሶ አደሩ እንዲዳረስ  በግብርና ዘርፍ ከሚሠሩ  አካላት  ጋር  በቅርበት እየሠራ  እንደሚገኝም ተናግሯል። ዘንድሮ 13 ሚሊዮን ኩንታል  ማዳበሪያ ተገዝቶ ወደ አገር ውስጥ  ማስገባቱን ያስታወቀው ሚኒስቴሩ፣ ይህም ከባለፈው ዓመት የ4 ሚሊየን ኩንታል ብልጫ እንዳለው አስታውቋል። 2 ነጥብ 7 ሚሊዮን ኩንታል ምርጥ ዘር  ለአርሶአደሩ  መሠራጨቱን፣ አርሶአደሩ ተገቢውን ዘመናዊ አሠራርና ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ምርታማነቱን እንዲያሳድግ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ሥልጠና መሠጠቱንም አስታውቋል።

እናም በዘንድሮው መኸር ይገኛል ተብሎ የታቀደው  345 ሚሊዮን ኩንታል  ምርት ሊገኝ እንደሚችል ነው ሚኒስቴሩ የገመተው።

ዝናብ ባይኖር ኖሮ ግን ማዳበሪያውም ሆነ ምርጥ ዘሩ፣ ዘመናዊ አሰራሩም ሆነ ቴክኖሎጂው ምንም ዋጋ አልነበራቸውም። ዝናብ ባይጥል ኖሮ፣ ሊመረት ከሚችለው ምርት እቅድ ጎን፣ ማምረት አቅቷቸው ለምግብ እጥረት የሚጋለጡትንም መገመት የግድ ይሆን ነበር። እናም ይህ ችግር ዘለቄታዊ መፍትሄ ይፈለጋል።

አንድ ክረምት ወይም በልግ ሲደርቅ ኢትዮጵያውያን ለምግብ እጥረት የሚጋለጡበት ሁኔታ መቀየር አለበት። ለዚህም ግብርናው በከፊልም ቢሆን ከዝናብ ጥገኝነት መላቀቅ የኖርበታል። አንጋጠን ዳመና ከማየት ወደምድርም እንመልከት። ምድር በገጿና በከርሷ ውሃ ይዛለችና። በቀጣይነት ደግሞ በአጠቃላይ የሃገሪቱ ኢኮኖሚ በግብርና ላይ ያለው ጠገኝነት በሚታይ ደረጃ መቃለል ይኖርበታል።