ወጣቱ የአውዳሚዎች መጠቀሚያ አይሆንም
ታከለ አለሙ
አንዳንድ ጽንፈኛና አክራሪ የሆኑ የተቃዋሚ ፖለቲካ ኃይሎች በተለያዩ አጋጣሚዎች በሕዝቡ ውስጥ የሚነሱ ጥያቄዎችን በመጥለፍ ወደራሳቸው ፍላጎትና ግብ ለማዞር ሲንቀሳቀሱ ቆይተዋል፡፡ ዛሬም እንደተለመደው ከግብር ጋር በተያያዘ የሕብረተሰቡን ስሜት ለመኮርኮር በተለይም ወጣቱን ኢላማ አድርጎ አመጽ እንዲቀሰቀስ ለማድረግ ከፍ ዝቅ ሲሉ ይታያሉ፤ የተዛቡና መሰረታዊ እውነቱን የለቀቁ ፕሮፓጋንዳዎችን በማሰራጨት ሁከትና አመጽ ለመቀስቀስ አመቺ ሁኔታ ተፈጥሮልናል በሚል እየሰሩም ይገኛል፡፡ ካለፉት በርካታ ተሞክሮዎች በመነሳት ሲታይ ወጣቱን ለአመጽና ለሁከት በማነሳሳት ንብረትና ሀብት እንዲያወድም ሲያደርገው የነበረው የጀርባ ግፊት ጽንፈኛው ኃይል በሶሻል ሚዲያና በተለያየ ድረገጾች ሲያሰራጨው በነበረው ሰላምና መረጋጋትን የሚያደፈርስ፣ አመጽን የሚያበረታታ ቅስቀሳና የሀሰት ፕሮፓጋንዳ መሆኑ ይታወቃል፡፡
ይህ አካል ዛሬም ወደዚሁ የቀደመ የጥፋት ስራው ተመልሷል፡፡ በሕረብተሰቡ ውስጥ የሚነሱ የትኛውም አይነት የአሰራር ችግሮችና ቅሬታዎች በግልጽ ለውይይት ቀርበው ሊፈቱ፤ መፍትሄ ሊያገኙም የሚችሉ ናቸው፡፡ በየትኛውም አይነት ጉዳይ ሕዝቡ ቅሬታ ሲኖረው ቅሬታውን የማቅረብ መብት አለቸው፤ የሚመለከታቸውም መንግስታዊ ኃላፊዎች ቅሬታውን በአግባቡና በስርአቱ የመመልከትና የመፍታትም መንግስታዊና ሕዝባዊ ግዴታ አለባቸው፡፡
ቀደም ሲል ከሕዝቡ ጋር በተለያዩ መድረኮች ተገናኝቶ በግልጽ የመወያየት ሕዝባዊ ባሕል እየዳበረ የሚገኝ በመሆኑ ለሁከትና ለአመጽ በር የሚከፍት ሁኔታ አይኖርም፡፡ በእርግጥም ሕዝቡ መብቴ ይከበርልኝ ሲል ለሚያነሳቸው ጥያቄዎች ምላሽ በየደረጃው የሚሰጥበት ሁኔታ በጥልቅ ተሀድሶው ተጀምሮ ብዙ እየተሰራበት፤ ደረጃ በደረጃም ለውጦች እየተመዘገቡ ይገኛሉ፡፡
ለተሀድሶው ለውጥ ገፊ የሆነው መነሻ ምክንያት በሙሰኞችና በኪራይ ሰብሳቢዎች በመልካም አስተዳደርና በፍትህ እጦት የተማረረው ሕዝብ ያነሳው የመብቴ ይከበርልኝ ጥያቄ መሆኑ ይታወቃል፡፡ የሕዝብ ምሬት እንዲከሰት ያደረጉ አካላት ሕዝቡን በከፋ ሁኔታ በማስመረራቸው የተነሳ በሁለም የሀገሪቱ ክልሎች ባሉ መንግስታዊ ተቋማት በቀጥታ ከሕዝቡ ጋር በሚያገናኙ ስራዎች ውስጥ በነበሩ፤ በተለይም መሬትን ከመሳሰሉና በሌሎችም ዘርፎች በነበሩ አካላት ላይ የማያዳግሙ እርምጃዎች ተወስደዋል፡፡ ይህ ማለት እርምጃ የመውሰዱ ጉዳይ በዚህ ይቆማል፤ ተጠያቂዎቹም እነዚህ ብቻ ናቸው ማለት ግን አይደለም፤ ምንጠራው ይቀጥላል።
ጥልቅ ተሀድሶው ተከታታይና ቀጣይ ሂደት በመሆኑ አሁንም በየደረጃው የማጥራቱና እርምጃ የመውሰዱ ሂደት ይቀጥላል፡፡ አሁን ለተፈጠሩት ሁኔታዎች ማሳያው ኪራይ ሰብሳቢውና የጥገኛው ኃይል ተንሰራፍቶና ስር ሰዶ የሚገኝ መሆኑን ያረጋግጣል፡፡ ሁልግዜም የሰራውን ስለሚያውቅ፣ ስራው ስለሚያባንነው፣ ነገ ተጠያቂ እሆናለሁ ብሎ ስለሚያምን አዳኝ እንደሚከታተላት ድኩላ ሲበረግግና ጥላውን ሳያምን ውሎ የሚያድር ከመሆኑ የተነሳ ሕዝብ ቅር የተሰኘበት አጀንዳ ሲያገኝ አስፍቶ ለመጠቀም ሁከትና አመጽ ለመቀስቀስ አይተኛም፡፡
ከዚሁ ሀይል ጋር ተቀናጅቶ የሚንቀሳቀሰው ጽንፈኛና አክራሪ የፖለቲካ ተቃዋሚ ኃይል የራሱን አጀንዳ ለማሳካት ሁከትና ግርግር እንዲፈጠር፣ ስርአተ አልበኛነት እንዲሰፍን፣ ሰላማዊ ኑሮ እንዲናጋ፣ ሕብረተሰቡ የበለጠ እንዲማረር የራሱን ስራዎች እንደሚሰራ ይታወቃል፡፡ ኪራይ ሰብሳቢውንና ጽንፈኛውን ኃይል የሚያገናኛቸው አላማ ሳይሆን በሚፈጠር ግርግርና ሁከት ተጠቃሚ እንሆናለን ብለው ማሰባቸው ነው፡፡
ኪራይ ሰብሳቢው የሀገርና የመንግስትን ሀብት በመዝረፍ የደለበ ጫንቃውን ያደነደነ የዘረፈውን ገንዘብ እየረጨ ቀዳዳ ባገኘ ቁጥር የሕዝብ ሁከትና አመጽ ሲቀሰቀስ እኔ ተጠያቂ ሳልሆን አመልጣለሁ ብሎ የማምለጫ መንገዱን ለማዘጋጀት ከቻለም የዘረፈውን ዘርፎ ከሀገር ለመውጣት አኮብኩቦ የሚገኝ ኃይል ነው፡፡ ምናልባትም የዘረፈውን ሀብትና ንብረት አስቀድሞ ከሀገር አውጥቶ አሽሽቶም ለሆን ይችላል፡፡ ይሄም መንገድ ብዙ አያላውሰውም፡፡ የት ሁኜ እበላዋለሁ ብሎ ለማሰብ ያልቻለ ዳፍንት ነው፡፡
ዛሬ በሰለጠነው አለም ውስጥ ሀገርን ዘርፎና አራቁቶ ሀብትን በማጋዝ ውጭ ባንክ በዝግ አካውንት ቢያስቀምጠውም መንግስት በሕግ ተከታትሎ ሊያስመልስ የሚችልባቸው፤ አለም አቀፍ ሕጉም የሚፈቅዳቸው መንገዶች በርካታ ናቸው። ግለሰቡ በንጹኅ ላቡና ጉልበቱ ሰርቶ ያላገኘውን በዘረፋና በማጭበርበር የተከማቸ ሀብትና ገንዘብ እስከሆነ ድረስ በፍርድ ቤት ውሳኔ ይታገዳል፡፡ ሁኖም እያየን ነው፡፡ ይወረሳል፡፡ ገንዘቡም ሀብቱም ወደመንግስት ካዝና ይገባል፡፡ ይሄ በበርካታ ሀገሮች ተደርጎአል፤ በኛም ሀገር ሆኖ ታይቷል።፡፡
ኪራይ ሰብሳቢው ቁርጥ አቋም ይዞ ሰላም ለማደፍረስ የሚተጋው የእራሱ ሁኔታ ከአጀንዳ ውጪ እንዲሆንና ተጠያቂ እንዳይደረግ፤ ጉዳዩ በትርምስ መሀል ተረስቶ እንዲቀር ስለሚፈልግና እግረ መንገዱንም ለማምለጥ የሚያዘጋጀው ስልት ነው፡፡
ለምን አይጨነቅ ሶስትና አራት ቤት በአዲስ አበባና በተለያዩ ክልሎች፤ ንግድ ቤት፤ ሼር ሆልደር፤ የትራንስፖርት ባለቤት፤ ባለፎቅ፤ ባለኮንዶሚኒየም፤ በልማት ስም መንደር እያስፈረሰ፣ ሕዝብ እያፈናቀለ ፎቅ ሲሰራ የኖረ ኪራይ ሰብሳቢ ሕዝብና መንግስትን ሲያናክስ የኖረ እሱ ያልተጨነቀ ማን ይጨነቃል፡፡ ሕዘብ አገልግል ሲባል ሕዝብን እየዘረፈና እያስመረረ ለራሱ የግል ጥቅም ሲሰራ የኖረ ኪራይ ሰብሳቢ ያልተጨነቀ ሌላ ማን ሊጨነቅ ነው?
በየግዜው በሕዝቡ ውስጥ የሚፈጠሩ ቅሬታዎችን በመጠቀም ሁከትና ትርምስ እንዲፈጠር ትልቁን ሚና የሚጫወተውም ይሄው ሀይል ነው፡፡ ይህ ሀይል ያልተረዳው ነገር ቢኖር የትም ሄደ የት ማምለጥ የማይችል መሆኑን ነው፡፡
ጽንፈኛው ተቃዋሚ ኃይል በበኩሉ በሚፈጠር ሀገራዊ ሁከትና ትርምስ አመጽ ወደፖለቲካ ስልጣን በአጭር መንገድ እመጣለሁ ብሎ ስለሚያስብ ነው ቀዳዳ ያገኘ በመሰለው ቁጥር እድሉን ለመጠቀም የሚሮጠው፡፡ የሁለቱም ኃይሎች ስሌትና አካሄድ አዋጪነት የለውም፡፡ ሁለቱም ለሚያቅዱት ሁከትና ረብሻ ወጣቱን በግንባር በማሰለፍ መጠቀም የአመጹ አቀጣጣይና አራማጅ በግንባር አስፈጻሚ እንዲሆን ይሰራሉ፡፡ ለዚህም ከፍተኛ በጀት መድበው በተለያየ አቅጣጫ ያሰራጫሉ፡፡
ይህ ገንዘብ ከጀርባ በጸረ ኢትዮጵያ ኃይሎች በከፍተኛ ደረጃ በሚሊዮኖች ዶላር የሚረዳና የሚታገዝ ሲሆን አመጽ በሀገር ውስጥ ለማቀጣጠል የፅንፈኛውን ሚዲያ፤ በተለይም ማህበራዊ ሚዲያውን ይጠቀማሉ፡፡ ዛሬ የሀገራችን ወጣት በበርካታ አጋጣሚዎች ለመማር የበቃ በመሆኑ እንዲህ አይነት ሀገር አውድም የሆነ እብደት ውስጥ አይገባም፡፡
የራሱን ሀገር በማጥፋት በማውደም የሀገር እድገትና ለውጥ እንደማይመጣ ከሌሎች ሀገራት ውድመትና ጥፋት፣ ስደትና ሞት፣ የሀገር መፈራረስ፣ መጠጊያ ማጣት፣ ሞትና እልቂት ብዙ ተምሮአል፡፡ የትኛውም አይነት ቅሬታ ቢኖር በሕጋዊና ሰላማዊ መንገድ በቀጥተኛ ውይይት ለችግሮቹ ሁሉ መፍትሄ ማበጀት ምርጫው ነው፡፡
ዛሬ ወጣቱ ሀገር ለማጥፋት ሳይሆን ሀገሩን ለማልማት በብዙ መስኮች ተሰማርቶ እየሰራ ይገኛል፡፡ የራሱን፣ የሀገሩንና የሕዝቡን ሀብትና ንብረት ይጠብቃል፡፡
ወጣቱ የራሱን ስራ ፈጥሮ ለለውጥ እየሰራ ነው፡፡ በሀገሩ መስራትን፤ ሰርቶም መለወጥን ነው የሚናፍቀው፡፡ ረብሻና ሁከትን አይናፍቅም፡፡ ሰርቶ ለማግኘት የሚያስችሉ የተከፈቱለት ሰፊና በርካታ እድሎች አሉት፡፡ ትኩረቱ ስራው ላይ ብቻ ነው፡፡ ለሀገር እድገትና ልማት ትልቁ ሰላምና ሰላም ብቻ መሆኑን ጠንቅቆ ተረድቶታል፡፡
አሁን ጽንፈኛው ኃይል ሁከት ለማስነሳት በማቀድ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ያለው በነጋዴውና በግብር ጉዳይ ላይ ነው፡፡ የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከት አሁንም የበላይነቱን ባስጠበቀበት ሁኔታ ኪራይ ሰብሳቢው ነጋዴ ግብሩን በመቃወም እቃዎችን በመጋዘን በማከማቸት፣ ሕዝባዊ አገልግሎቱን በማቋረጥ፣ የገበያ እጥረትና የዋጋ ንረት በመፍጠር የራሱን ሕገወጥ ትርፍ ለማጋበስ እየተክለፈለፈ ይገኛል፡፡
ሰላምን ለማወክ ለሚንቀሳቀሰው ኃይል መጠቀሚያ በመሆን በሀገራዊ ልማቱ ተጠቃሚ የሆነው ነጋዴም ጭምር የግብር ትመናውን እንዲቃወም በማስተባበር ሕዝቡን ለአመጽ የማነሳሳት ስራ ቢሰሩም ውጤት ሊያገኙበት አልቻሉም፡፡ የምርት አገልግሎት እጥረት በመፍጠር ሕዝቡን በማስመረር ለአመጽ ለማነሳሳት እያደረጉት ያሉት ጥረት በሕዝቡ ትግል በመምከን ላይ ይገኛል፡፡
አብዛኛው ነጋዴ የመንግስት ሰራተኛው ትንሽ የደመወዝ ጭማሪ ሲያገኝ ተስገብግቦ በሸቀጥ ዋጋዎች ላይ የዋጋ ጭማሪ የሚያደርግ ነው፡፡ ገበያ መር ሳይሆን እሱ በፈለገው መጠን ዋጋ የሚጨምር፤ ምርትና ሸቀጦችን በብዛት ገዝቶ እጥረት ለመፍጠር ሲል ሕዝቡን የሚያስመርር፤ ድብቅነትን የስኬት መለኪያ አድርጎ የሚወስድ፣ በራሱ ሕዝብ ላይ ለማትረፍ ሲል በደልና ወንጀል የሚፈጽም ነጋዴ የበዛበት ሀገር ነው፡፡ አብዛኛው የሚያገኘውን ትርፍ ያህል ግብር ክፈል ሲባል የሚያመው፤ የሀገርን ሳይሆን የግል ክብረትንና ብልፅግናን ብቻ የሚናፍቅ፤ ስለሕዝብና ስለሀገር ማሰብ የማይሆንለት ነው።
ባጠቃላይ፣ በግብር ላይ የሚነሳ ቅሬታ የሚፈታበት የሕግ አግባብ ጥንትም ዛሬም አለ፡፡ ሰላም ለማደፍረስ ምክንያት ሊሆን አይገባም፡፡ በሀገር ልማትና ግንባታ ተሰማርቶ ታላቅ ስራ እየሰራ ያለውን ወጣት አውዳሚ ለሆነ ጥፋት መጠቀሚያ ለማድረግ መባጀት ለማንም አይበጅም፡፡ ወጣቱ ለአፍራሽ ኃይሎች አጀንዳ መጠቀሚያ አይሆንም፡፡