ወጣቱ የፀረ ሰላም ኃይሎችን ቅስቀሳ ሊያከሽፍ ይገባል!
ወጣቱ የፀረ ሰላም ኃይሎችን ቅስቀሳ ሊያከሽፍ ይገባል!
ቶሎሳ ኡርጌሳ
አበው “ወጣት የነብር ጣት ነው” ይላሉ—ጥንካሬውንና አፍላነቱን ለመግለፅ። እርግጥም በወጣትነት ዘመን ጉልበት አለ። ወጣትነት ሁሉንም ነገር ለማድረግ ፍላጎት የሚያይልበት አፍላ ነው። በወጣትነት ሁሉንም ነገር ለማድረግ፣ ሁሉንም ነገር ለመከወን ፍላጎት ይበረታል። ወጣት በዚህ የአፍላ ዘመኑ የማይፈፅመው ነገር ያለ አይመስለውም። ይህ እውነታ ተፈጥሮአዊ ነው። በወጣትነት ዘመኑ እንዲህ ዓይነት ፍላጎትና ስሜት ያላደረበት ሰው ያለ አይመስለኝም።
በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት ካሏቸው ሃብቶች መካከል አንዱ የሰው ሃብት ነው። እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ሀገራት ይህን የሰው ሃብታቸውን በአግባቡ ከተጠቀሙ ሃብቱ የዕድገታቸው ምንጭ መሆኑ አያጠያይቅም። ከሀገራችን ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆነው ወጣቱ የህብረተሰብ ክፍል እንደሆነ ይታወቃል። ይህን አፍላና ሁሉንም ነገር የመፈፀም ባህሪያዊ ተፈጥሮ ያለውን ወጣት በልማት ስራ ላይ ማሰማራት ከተቻለ ለውጥ ማምጣት ይቻላል።
ይህን ሃቅ የተገነዘበው የኢፌዴሪ መንግስት ቀደም ባሉት ጊዜያት ወጣቶችን በአነስተኛና ጥቃቅን በማደራጀት ራሳቸውን ጠቅመው የሀገራቸውን ዕድገት እንዲደግፉ ማድረግ ተችሏል። በአሁኑ ወቅትም ወጣቱ በልማት ስራው ላይ እንዲሳተፍ በፌዴራል መንግስት ደረጃ የ10 ቢሊዮን ብር ተዘዋዋሪ ፈንድ ተመድቦ ወጣቱን ወደ ስራ ማስገባት ተችሏል። በዚህም ውጤት እየተገኘበት ነው።
ክልሎችና የከተማ መስተዳድሮችም ከዚህ የፌዴራል መንግስት ፈንድ በተጨማሪ፤ ከራሳቸው በጀት መድበው ወጣቱ በተጠናከረ ሁኔታ ወደ ስራ እንዲገቡ ማድረግ ችለዋል። በተያዘው የ2010 የበጀት ዓመትም በዋነኛነት ለወጣቱ ትኩረት በመስጠት እንደሚሰሩ መግለፃቸው ይታወቃል። ይህም መንግስት እዚህ ሀገር ውስጥ ላሉ ወጣቶች ምቹ የልማት ተግባሮችን እያከናወነ መሆኑን የሚያመላክት ነው። ይህ ለወጣቱ የተፈጠረው ምቹ ሁኔታ ሀገራችን ለወጣቶቿ፣ ወጣቶቹም ለሀገራቸው እንዲጠቅሙ ከማሰብ የመነጨ ነው።
እዚህ ሀገር ውስጥ እየተከናወነ ያለው ፈጣንና ተከታታይ ልማት ተስፋ ሰጪ መሆኑን የተግባሩ ተሳታፊዎች ከሆኑት ከሀገራችን ወጣቶች ውጪ ማንም ሊመሰክር አይችልም። ሆኖም አንዳንድ ፀረ-ሰላም ኃይሎች የኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ መስተዳድር ላይ ስላለው ልዩ ጥቅምን በተመለከተ ወደ ህዝብ ተወካዩች ምክር ቤት የተመራውን ረቂቅ አዋጅ አስመልክቶ በአንደኛው ጽንፍ በኩል “ሌላውን ብሔር ለመጉዳት ታስቦ የተዘጋጀ ነው” የሚል፣ በሌላኛው ጽንፍ በኩል ደግሞ “የኦሮሚያን ተጠቃሚነት አያረጋግጥም” የሚል እጅግ የተሳሳተ መዝሙር አተያያቸውን ሲያሰሙ እያደመጥን ነው።
ከቀን ገቢ ግብር አወሳሰን ጋር ተያይዞም በሚያስገርም ሁኔታ “ጀግናው የእገሌ ከተማ ህዝብ ሱቁን ዘግቶ ዋለ” ከሚል ዲስኩር እስከ “ሱቃችሁን አትክፈቱ” የሚል የሁከት ናፋቂነት መርዛቸውን ሲረጩ ሰንብተዋል። በተለይም በኤርትራ መንግሰት ዳራጎት የተቋቋሙት እንደ “ኢሳት” ያሉ መርዘኛ ሚዲያዎችና ማህበራዊ ድረ ገፆች እንዲሁም በአንዳንድ ፀረ-ኢትዮጵያ ሀገራት እገዛ የሚዘወሩ ባንዳዎች በዚህ ረገድ አመፅን የማቀጣጠል ሚናቸውን ሲወጡ ነበር።
ታዲያ ወጣቱ የእነዚህን ፀረ-ሰላም ሃይሎች ዓላማና ግብ በሚገባ መረዳት ይኖርበታል። ፀረ-ሰላም ኃይሎቹ የትኛውንም የሀገራችንን ህዝብ የሚወክሉ አይደሉም። ሊወክሉም አይችሉም። ምክንያቱም ዓላማቸውና ግባቸው ከበስተኋላቸው የሚደጉማቸውን ፀረ-ኢትዮጵያ ሃይል ፍላጎት ማስፈፀም ብቻ ስለሆነ ነው።
የኤርትራ መንግስት ለረጅም ጊዜ የሚያልመው በሁከት የተዳከመችና የተበታተነች ኢትዮጵያን ማየት ነው። ለዚህም ሲል የሀገራችንን አሸባሪዎችና ፀረ-ሰላም ኃይሎችን በጉያው ውስጥ ወሽቆ ሰላማችንን ለማደፍረስና የጀመርነውን ፈጣን ዕድገት ለማስተጓጎል ያልፈነቀለው ድንጋይ የለም።
ይሁንና ይህ ፍላጎቱ በኢፌዴሪ መንግስት በሳል አመራር እንዲሁም በህዝቡና በፀጥታ ኃይሎች ርብርብ ሊከሽፍ ችሏል። እናም ፀረ-ሰላም ሃይሎቹና አሸባሪዎቹ የአስመራው አስተዳደር የፈለገውን ውጤት ሊያመጡለት አልቻሉም። አይችሉምም።
የአስመራው አስተዳደር በድንበር አካባቢ ፀረ-ሰላም ኃይሎችንና አሸባሪዎችን በማሰማራት ሰላማችንን በማደፍረስ ልማታችንን ለማስተጓጎል ከሚያደርገው ሙከራ በተጨማሪ፤ ሚዲያዎችንና ማህበራዊ ድረ ገፆችን እየከፈለ ጭምር በማሰማራት ሀገራችን ውስጥ አመፅ እንዲቀጣጠል ለማድረግ ይጥራል። ለዚህ ማስረጃ ይሆን ዘንድ በአንድ ወቅት በአስመራው ፕሬዚዳንት ሳንባ የሚተነፍሱትና ራሱን ‘አርበኞች ግንቦት ሰባት’ እያለ የሚጠራው አሸባሪ ቡድን መሪ መሆናቸውን የሚናገሩት ዶክተር ብርሃኑ ነጋ ከኤርትራ መንግስት የስድስት ወር ስራ ማስኬጃ ግማሽ ሚሊዮን ዶላር እንደተቀበሉና ከዚህ ውስጥ 200 ሺህ ዶላሩ ለኢሳት ማጠናከሪያ እንደሚውል ሲናገሩ የስልክ ልውውጣቸውን ማድመጣችንን አስታውሳለሁ። በወቅቱ እኔም ሆንኩ ሌሎች ኢትዮጵያዊያን ይህንን የዶክተሩን ባንዳዊ ቅሌት በግርምታ መፃፋችንን አስታውሳለሁ።
‘ኢሳት’ በዚህ መንገድ ከኤርትራ መንግስት ገንዘብ እየተቀበለ የውሸት ወሬዎችን ያናፍሳል። ዓላማው የአስመራው መንግስት ሀገራችን ውስጥ ሁከት እንዲፈጠር ለማድረግ የሚያደርገውን የሴራ ሙከራ ማገዝ በመሆኑ የፈጠራ ወሬውን ሲያሰራጭ ሌሎች እንደ ፌስ ቡክ ዓይነት ማህበራዊ ድረ ገፆችም እየተቀባበሉ ያራግቡታል። ለሀገራችን በጎ የማይመኙ ኃይሎችም በፌስ ቡክ ላይ ብቅ እያሉ ጉዳዩን ያስተጋቡታል።
በሌላ በኩልም ኢትዮጵያ ውስጥ ሰላም እንዳይኖርና ኢኮኖሚያችን እንዳያንሰራራ የሚፈልጉ አንዳንድ የውጭ ሃይሎች መኖራቸው ይታወቃል። እነዚህ ሃይሎች ካደግን እንደምንለወጥና የተፈጥሮ ሃብታችንንም በዚያው ልክ እንደምንጠቀም ስለሚያውቁ ኢትዮጵያ ውስጥ ሰላምና መረጋጋት እንዳይኖር ተግተው የሚሰሩ ናቸው። እንደ ፌስ ቡክ ዓይነት ማህበራዊ ድረ ገፆችን በመጠቀምና እንደ ጃዋር መሃመድ ዓይነት ግለሰቦችን በመቅጠር ወጣቱን በተሳሳተ መንገድ ሊመሩት ይሞክራሉ።
ታዲያ ወጣቱ በእነ ‘ኢሳት’ና በእነ ጃዋር ውሸት አቀናባሪነት ሳቢያ እየተፈፀመ ያለውን ይህን የአመፃ አቀጣጣይነት ሚናን በሚገባ መረዳት አለበት። እውነታውን ከራሱ እማኝነት በመነሳት መገምገምም አለበት። አንድ ጉዳይ በፌስ ቡክ ዓይነት ማሀበራዊ ድረ ገፅ ብቻ ስለተነገረ እውነት ነው ብሎ መደምደም አይቻልም።
ከላይ ለመጥቀስ እንደሞከርኩት ሆን ተብሎ የሀገራችንን ሰላም ለማወክ በፀረ-ኢትዮጵያ ሃይሎች እንደሚቀነባበር መረዳት ይገባል። እናም ፀረ-ሰላም ኃይሎቹ የኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ ላይ ስላለው ህገ መንግስታዊ ልዩ ተጠቃሚነትም ይሁን በየትኛውም ሀገር መንግስት ስራውን ለማከናወን የሚሰበስበውን ግብር አስመልክተው የሚያራግቡት አሉባልታ ቅስቀሳ መነሻውም ይሁን መድረሻው ይኸው ኢትዮጵያን የማተራመስ ተልዕኮ መሆኑን ወጣቱ ማወቅ ይኖርበታል። ማወቅ ብቻም ሳይሆን፤ የእነርሱን ማንነት በመገንዘብ ሊታገላቸውና ቅስቀሳቸውን ሊያከሽፍ ይገባል።
የሀገራችን ወጣት ባለ ራዕይና ተስፋ ያለው ነው። የዛሬው ትውልድ ወጣት እንደ ትናንቱ ወጣቶች እየታፈነ ለጦርነት አይወሰድም። ይህ ወጣት ዛሬ “ሰርተህ ተለወጥ፤ እኔ የምትሰራበትን ምህዳር አመቻችልሃለው” የሚል መንግስት ባለቤት ነው። ችግሩን በህዝባዊ መንፈስ የሚጋራው መንግስት አለው። መፍትሔም በአፋጣኝ የሚሰጥ መንግስት አለው። በየዕቅዶቹ ሁሉ ወጣቱን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የልማት ትልሞችን የሚይዝ መንግስት ባለቤትም ነው።
እርግጥ በየትኛውም ሀገር ውስጥ ችግሮች ይኖራሉ። እንኳንስ ለልማቱም ይሁን ለዴሞክራሲው ጀማሪ የሆነችው ሀገራችን ቀርቶ ባደጉት ሀገሮችም ውስጥ ቢሆን ችግር መኖሩ አይቀርም። የአልጋ በአልጋ መንገድ በየትኛውም ሀገር ውስጥ የለም። በመንግስት የስራ አስፈፃሚዎች ውስጥ ችግር ሊኖር ይችላል።
ዋናው ጉዳይ ችግሩን መፍታት የሚቻለው በሰላማዊና በህጋዊ መንገድ እንጂ የራሳቸው አጀንዳ ሳይኖራቸው የባዕዳን ተላላኪ በመሆን የፈጠራ ወሬን በሚረጩ ፀረ-ሰላም ሃይሎች አማካኝነት አይደለም። እነርሱ የዚህ የባዕዳን ጉዳይ ፈፃሚዎች እንጂ የዚህ ሀገር መፍትሔ ሰጪዎች አይደሉም። ውክልናቸው ለባዕዳን እንጂ ለዚህ ሀገር አይደለም። እናም ወጣቱ ማናቸውም መፍትሔ ያለው ለተጠቃሚነቱ እየሰራና ወደፊትም ከሚሰራው ህዝባዊ መንግስት እንጂ ከፀረ-ሰላም ኃይሎቹ አለመሆኑን በመረዳት፤ የውሸት ቅስቀሳቸውን ሊያከሽፍ ይገባል እላለሁ።