Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ወጣት ሆይ ንቃ!

0 370

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ወጣት ሆይ ንቃ!

ዳዊት ምትኩ

 

ፀረ ሰላም ኃይሎች ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ የአገራችንን ሰላም ለማደፈረስና ልማታችንን ለማደናቀፍ በርካታ እንቅስቃሴዎችን ያደርጋሉ። በተለይ ወጣቱ ዋነኛ ዒላማቸው ሆኗል። በአሁን ሰዓትም በግብር አወሳሰን ሁኔታ ‘እገሌ የሚባል አገር ሱቁን ዘጋ፣ አጠናክሮ ይቀጥል’ በሚሉ የአመፅ ቅስቀሳ ተግባራት ወጣቱን ወጣቱን ሰለባ ለማድረግ እየሞከሩ ነው።

ሆኖም ወጣቱ ሰላምን አጥብቆ መሻት ይኖርበታል። ፀረ ሰላም ኃይሎቹ የሚፈልጉት በአሁን ወቅት ያገኘውን ተጠቃሚነት እንዳያጣጥም መሆኑን ተገንዝቦ ወጣቱ ሴራቸውን በመንቃት ወደ ልማት ስራው ላይ ማተኮር አለበት። እንደሚታወቀው ሁሉ ወጣቶች የዛሬ አፍላ የልማትና የዴሞክራሲ ኃይሎችና የነገ ሀገር ተረካቢ ዜጎች ናቸው። ይህን የሚገነዘበው መንግስት በትምህርት የታነፀና የተገነባ አቅም እንዲኖራቸው ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ በመስራት ላይ ይገኛል።

የወጣቶችን ሁለንተናዊ ብቃት በማሳደግ በሀገሪቱ የዴሞክራሲያዊ ስርዓትና መልካም ልማታዊ አስተዳደር ግንባታ እንዲሁም በኢኮኖሚ፣ ማህበራዊና ባህላዊ ልማት እንቅስቃሴዎች ውስጥ በተደራጀና በተቀናጀ አኳኋን የነቃና ግንባር ቀደም ተሳትፎ እንዲያደርጉና ከውጤቱም በተገቢው መንገድ ተጠቃሚ እንዲሆኑ መንግስት ያላሰለሰ ጥረት እያደረገ ነው።

ይህን በማድረግም በአገሪቱ ወጣቶች አካበባቢ ከሥራ ስምሪት ጋር ተያይዞ የሚታየውን የተሳታፊነትና ፍትሐዊ ተጠቀቃሚነት ጥያቄ ለመመለስ እየጣረ ነው። እንዲሁም የሴቶችና የወጣቶች ፓኬጆች ትስስርና ተመጋጋቢነት ባለው ሁኔታ ተፈጻሚ እንዲሆን ትኩረት ሰጥቷል።

የተለያዩ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ልማት ዘርፎች የወጣቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ከግምት ውስጥ ያስገቡ እንዲሆኑ፣ ወጣቶች በህብረት ሥራ ማህበራት በመደራጀት የብድርና ቁጣባ አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆኑ እየተደረገም ነው።

በተለይም ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና ከቴክኒክ ሥልጠና ማዕከላት ተመርቀው የሚወጡ ወጣቶች ያገኙትን ዕውቀትና ክህሎት የወደፊት የአገራችን ተስፋ በሆኑ አምራች ዘርፎች ማለትም ግብርና፣ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎችና ዲጂታል ቴክኖሎጂ ላይ ተሰማርተው የወደፊት የአገራችን ልማታዊ ባለሃብቶች መፍለቂያ እንዲሆኑ ሁሉን አቀፍ ድጋፍ እየተደረገላቸው ይገኛል። በዚህም በየክልላቸው የስራ ዕድሎች ተፈጥሮላቸው ራሳቸውን ጠቅመው አገራቸውንም እየጠቀሙ ነው።

በመንግስት በኩል ይህ ሁሉ ጥረት እየተደረገ የኢትዮጵያን ሰላም የማይሹ ወገኖች እንደ ሰሞነኛው የግብር አከፋፈል ዓይነት ሁኔታብ እየተከታተሉ ወጣቱን ለአመፅ ለማነሳሳት እየሞከሩ ነው። እናም ወጣቱ መንቃት አለበት።

እርግጥ አንድ መንግሥት ወይም የፖለቲካ ድርጅት በባህሪው ህዝባዊ ከሆነ፤ የሚያከናውናቸው ማናቸውም ተግባራት የህዝቡን ተጠቃሚነት ያማከሉ መሆናቸው አይቀርም፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥትም በባህሪው ህዝባዊና ልማታዊ በመሆኑ፤ ላለፉት 26 ዓመታት በአብዛኛዎቹ መስኮች ህዝቡን በየደረጃው ተጠቃሚ አድርጓል፡፡

ከ26 ዓመት በፊት በማንነቱም ይሁን በኑሮው አንገቱን ደፍቶ ይሄድ የነበረው ወጣት፤ ዛሬ ቀና ብሎ በሀገሪቱ በመመዝገብ ላይ ከሚገኘው ፈጣንና ተከታታይ ዕድገት በኢኮኖሚው ላይ ባበረከተው አስተዋጽኦ መጠን በየደረጃው ተጠቃሚ ሆኖ ወደ አዲስ ምዕራፍ እየገሰገሰ ነው፡፡ ለአብነትም በእነዚህ ዓመታት ውስጥ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ወጣቶች በተለያዩ የስራ መስኮች ተደራጅተው ተጠቃሚ መሆናቸውን ማንሳት ይቻላል። እናም ወጣቱ በአሁኑ ወቅት የላቀ ተጠቃሚ ለመሆንም ቁርጠኛ አቋም ከመንግስት ጋር መስራት ያለበት ይመስለኛል፡፡

እኔ እስከሚገባኝ ድረስ ከድህነት ጋር ፍልሚያ ገጥሞ ተጠቃሚ እየሆነ ያለው ወጣት፤ በምንም ዓይነት ምክንያት ሁለንተናዊ የጥቅም ተጋሪነቱ የኋሊት ተጎትቶ እንዲሸረሸርበት አይፈልግም፡፡ ነገ ትልቅ የዕድገት ባለቤት ለመሆን ያለመው ወጣት ዜጋ፤ ትኩረቱን ማድረግ ያለበት የትናንት እሱነቱን በስራ ለመቀየር ደፋ ቀና በማለት እንጂ፤ ሁከትን በማዳመጥ አይደለም፡፡ በመሆኑም እነርሱ ባህር ማዶ ሆነው ልጆቻቸውን በሰላም እያስተማሩ እዚህ ሀገር ውስጥ ያለውንና ህይወቱን ለመቀየር እየተጋ ያለውን ወጣት በእሳት ለመማገድ የሚሹ የሁከት ኃይሎችን ጥሪዎች ማምከን ይኖርበታል።

ወጣቱ ከሁከቱ ወዲህ ስለ እነዚህ ኃይሎች ባዶና የአሉባልታ አጀንዳ አራማጅነት እንዲሁም ስለ መንግሥት ትክክለኛነት የልማት አቅጣጫዎች የተገነዘበ ይመስለኛል። አዎ! ቀደም ሲል ለመጥቀስ እንደሞከርኩት መንግስት የወጣቱን ተጠቃሚነት በዳግም ተሃድሶው ይበልጥ ለማረጋገጥ እንደሚሰራ ቃል ገብቷል።

እርግጥ የኢትዮጵያ መንግስት አደርገዋለሁ ብሎ ገቢራዊ ያላደረገው ምንም ዓይነት ነገር የለም—በየጊዜው እያደገ ከመጣው የህዝብ ቁጥር ጋር ዕድገቱ ሁሉንም ዜጎች ተጠቃሚ ካለማድረጉ በስተቀር። ያም ሆኖ አብዛኛውን ህዝብ ተጠቃሚ ማድረግ ችሏል።

ቀደም ባሉት ጊዜያት በሀገሪቱ ውስጥ ድህነትን አቅም በፈቀደ መጠን በመቀነስ ህዝቡን በየደረጃው ተጠቃሚ እንደሚደርግ፤ ትምህርትን፣ ጤናን፣ የመሠረተ-ልማት አውታሮችን እንደሚያስፋፋ እንዲሁም ዴሞክራሲያዊ ስርዓቱ ስር እንዲሰድ አደርጋለሁ በማለት የገባቸውን የተስፋ ቃላት ተፈፃሚ አድርጓቸዋል። አስተማማኝ ሰላም በማረጋገጥ ረገድም የገባውን ቃል አላጠፈም። እነዚህን ዕውነታዎች ወጣቱ አሳምሮ የሚያውቃቸው ይመስለኛል።

ከእነዚህ ተጨባጭና የማይታጠፉ ቃሎቹ በመነሳትም፤ በቅርቡ ሀገራችን ውስጥ  የተፈጠረውን ጊዜያዊ ችግር መንግሥት መስመር እንደሚያሲዘው ማመን ያለበት ይመስለኛል። እርግጥ ባለፉት ጊዜያት ገዥው ፓርቲና መንግሥት የለውጥ አደራጅና ቀያሽ መሆናቸውን ወጣቱ በሚገባ ስለሚያውቅ፤ አሁን የተፈጠረው ችግር በመንግስት እንጂ በሁከት አቀንቃኞች ይፈታል ብሎ ያስባል ማለት አይቻልም።

ምንም እንኳን የሁከት ኃይሎቹ በተቀናጀ ሁኔታ የህዝቡን ብሶቶችና የራሳቸውን አሉባልታዎች በማያያዝ አያ ለማራገብ ቢሞክሩም እንዲሁም ከህገ መንግስቱ ጋር የሚቃረኑና የሚምታቱ ፀረ-ልማት ሃሳቦችን እያቀረቡ ለማሳሳት ቢሞክሩም ወጣቱ ጆሮውን ሊሰጣቸው አይገባም፡፡

የማናቸውም ችግሮች መፍትሐሔ የሚመነጨው በሀገረቱ መንግስት እንጂ የራሳቸውን አጀንዳ ለማራመድ ብሎም የሌሎች ፀረ-ኢትዮጵያ ሃይሎች ተላላኪ በመሆን በህዝቦች ስቃይ ትርፍ ለማጋበስ በሚፈልጉ ፀረ ሰላም ኃይሎች ባለመሆኑ ሃቁን መገንዘብ ይኖርበታል። መንግሥት የአዳዲስ ልማታዊ ሃሳቦችና አሰራሮች አመንጪ ብሎም ለወጣቱ ችግር የሚደርስ ህዝባዊ አካል መሆኑን በመገንዘብ ከእነዚህ ሃይሎች አሉባልታ ራሱን ማራቅ ያለበት ይመስለኛል። ወጣት ሆይ ንቃ! ሲባል መንቃት ያለበት ይህነ ነባራዊ ሃቅ ነው።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy