Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ዛሬም ፅንፈኝነትን መታገል የግድ ይላል!

0 329

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ዛሬም ፅንፈኝነትን መታገል የግድ ይላል!

                                                      ታዬ ከበደ

ፅንፈኞች ሁከት አምላኪዎች ናቸው። ሁከት አምላኪዎች ምናልባትም በፖለቲካው መስክ የከሰሩ፣ አክራሪ ሃይማኖተኞች አሊያም የሀገራችንን ልማት ለማየት የማይሹ የውጭ ሃይሎችና የእነርሱ ተላላኪዎች ሊሆኑ ይችላሉ።

ሁከት አምላኪዎች በስም ቢለያዩም በግብር ግን አንድ ዓይነት ናቸው። ከአንድ ግንድ ላይ የሚዘነጠፉ ቅርንጫፎች። እነዚህ ኃይሎች መነሻቸውና መድረሻቸው አንድ ነው፤ የሀገራችንን ህዝቦች ሰላም በማሳጣት እዚህ ሀገር ውስጥ የሚከናወኑና ፍሬ በማፍራት ላይ የሚገኙ የልማት ትሩፋቶችን የኋሊት በመቀልበስ ስልጣንን በብጥብጥ ለመያዝ መቋመጥ።

ይህን ‘ግባቸውን’ ዕውን ለማድረግ ሲሉም የማይቧጥጡት የተንኮል ቁልቁለት፣ የማይወጡት የሴራ ተራራ የማይፈነቅሉት የጎዳና ድንጋይ የለም። ሲያሻቸው ይጣመራሉ፣ በል ሲላቸው ደግሞ ይለያያሉ። ሴራው ሲያቧድናቸው ደግሞ በአንድ ዕቃ አብረን ካልበላን ይባባላሉ። በስተመጨረሻም ተጣልተው ለመለያየት የመቶ ሜትር ሯጩ ሁሴይን ቦልት እንኳን የሚቀድማቸው አይመስልም። ወትሮም በቅድሚያ ‘ላልከዳህ፣ ላትከዳኝ’ ተብለው ሲማማሉ አንድ እጃቸውን ጎናቸው ላይ በሻጡት ካራ ላይ አስቀምጠው ስለሆነ ለመለያየቱም ወዲያውኑ ‘የመበላላት’ ካራቸውን ሲያወጡ ጊዜ አይወስዱም።

ከእነዚህ ሁከት አምላኪዎች ውስጥ ራሱን ግንቦት ሰባት እያለ የሚጠራው የሽብር ቡድን አንዱ ነው። ይህ የሁከት አምላኪዎች ቡድን ምን ያህል ሀገሩን ከመሸጥ የማይመለስ መሆኑን የትናንት ዳራዎቹን መፈተሽ ተገቢ ይመስለኛል። መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ቡድኑ በሙባረክና በሙስሊም ወንድማማቾች የስልጣን ዘመን ያልቧጠጠው ጉዳይ የለም። የሽብር ቡድኑ መሪ ዶክተር ብርሃኑ ነጋ ከዚህ አኳያ ተጠቃሽ ናቸው። እርግጥ የግለሰቡ የትላንት ዳራ ሲፈተሽ ስብዕናቸውን ጥያቄ ውስጥ የሚያስገቡ ሃቆች ይገኛሉ። በትረ ስልጣን የሚያስገኝልኝ ከሆነ ከዲያቢሎስ ጋርም በሸርክና የመስራት ችግር የለብኝም ብለው ነበር— ያኔ አሜሪካ ቁጭ ብለው ስልጣን እንደ እህል ውሃ የሚርባቸውና የሚጠማቸው አሸባሪው ዶክተር ብርሃኑ ነጋ።

ከትላንት እስከ ዛሬ ድረስ የኤርትራ መንግስት ተላላኪና ተወርዋሪ ድንጋይ በመሆን ተንቀሳቅሰው አንዳችም ፋይዳ ያላስገኙት አሸባሪው ግለሰብ፤ በሙባረክና በሙስሊም ወንድማማቾች የስልጣን ዘመን ሀገራዊ ክህደታቸውን አሳይተውናል—የህዳሴው ግድብ ላይ አሜኬላ እሾህ ለመሆን። እኚህ ግለሰብ በተለያዩ ወቅቶች ከዋህቢያና ከስደተኛው ሲኖዳስ ጋር በመሻረክ ኢትዮጵያዊያንን በሃይማኖት ሰበብ ለማበላላትና ኤኬልዳማ ለማድረግ መውገርገራቸውን እናስታውሳለን። በህዝብና በመንግስት ቅንጅታዊ ተግባር ፍላጎታቸው እየመከነባቸው እንጂ፤ እንደ እርሳቸው የቀን ቅዠት ቢሆንማ ሀገራችን እንዳልነበረች በሆነች ነበር።

እርሳቸው የሚመሩት የግብረ-ሽበራ ድርጅትና ልሳናቸው የሆነው ኢሳትም እዚህ ሀገር ውስጥ “እሳት” ለመለኮስ የነገር አንቴናቸውን ያልቀሰሩበትን ቀን አላስታውስም። በግብረ-ሽበራ ማህፀምን ከተፈጠረበት ዕለት አንስቶ ከአስመራው አስተዳደር ጋር ሆኖ በመዶለት ለመፈፀም ያሰባቸው እይ ሴራዎች ሁሉ ከንቱዎች ነበሩ—ከመኝታ ላይ ቅዥት ያላለፉ። እንኳንስ የሁከት ፈጣሪነት ህልሙ ሊሳካለት ቀርቶ መፈረካከሱን ራሱ እያሳየን ነው። ከእገሌ ጋር ተሰነጠቀ የሚል ማንነቱን እየሰማን ነውና። ይህም ድርጅቱ ከወሬ በስተቀር አንዳችም ጥንካሬ እንደሌለው የሚያሳይ ነው።

ይሁንና ከአንዳንድ ፀረ-ኢትዮጵያ ኃይሎች ገንዘብ በገፍ እየተቀበለ ጥቂት ፅንፈኞችን በማሰማራት በየማህበራዊ ሚዲያው እንዲሁም ኢሳት በተሰኘው የሁከት ማቀነባበሪያ ጣቢያው አማካኝነት አሉባልታን ከመንዛት አልተቆጠበም። አንዳንድ ወገኖችም ሳያውቁ የዚሁ አሉባልታ ሰለባ መሆናቸው አልቀረም። በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ የተለያዩ ፎቶዎችን በማቀናጀት በሩቅ ምስራቅ ሀገራት ውስጥ የተከናወኑ ድርጊቶችን እዚህ ሀገር የተፈጠሩ በማስመሰል አንዳንድ ወገኖችን ሲያደናግሩ ይታያሉ። እዚህ ላይ በምሳሌነት ባንግላዴሽ ውስጥ ተጥሎ የተገኘ ቦምብ ሲጫወት የነበረና ቦንቡ ፈንድቶ የተጎዳ የአንድ ህፃን ልጅን አካል በፌስ ቡክ ላይ በማሳየት ‘ኢትዮጵያ ውስጥ ህፃናት በአውሮፕላን እየተደበደቡ ነው’ የሚል አስገራሚ የፈጠራ ድርሰትን ማንሳት ይቻላል። እናም የሽብር ቡድኑ አባላት ሌሎች ፎቶዎችንም ‘በፎቶ ሾፕ’ ቴክኖሎጂ ጥበብ በማቀናጀት ያልተደረገን ጉዳይ ተከናወነ በማለት አንዳንድ ወገኖችን ለማሳሳት እየሰሩ መሆኑ ሊታወቅ የሚገባ ይመስለኛል።

እርግጥ የሽብር ቡድኑ በተለያዩ ወቅቶች ህዝብን ከማደናገር የተቆጠበት ጊዜ የለም። በተለይም እዚህ ሀገር ውስጥ ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ የማያውቀውን የዋህ ዲያስፖራ በተለያዩ መንገዶች ያጭበረብሩታል። መሪውን ጨምሮ የቡድኑ አባላት ፍላጎታቸው በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ በልማታዊ ዕድገቱ ድል ምክንያት የሚፈጠሩ ነባራዊና ጊዜያዊ እንቅፋቶቸን ተመርኩዘው በውጭ የሚገኙ ጥቂት ደጋፊ ዲያስፖራቸውን እያደናገሩ የጥቂት አመራሮቻቸውን ኪስ ማደለብ ነው። ይህን ለማስፈፀምም አይናቸውን በጨው ታጥበው የአሉባልታ እምቢልታቸውን ከመንፋት ወደ ኋላ አይሉም። እናም ሃሳባቸው በሙሉ የራሳቸው አጀንዳ ሳይኖራቸው በሌሎች አጀንዳዎች ላይ በመንጠላጠል የሽብር ቡድኑን “በገቢ ማሰባሰቢያ ዘዴ” ማጎልበት ነው—ሁከት መፍጠር አንድ የስራ መስክ ነውና።

እርግጥ ይህ “ዘዴ” እስከ የት ድረስ እንደሚሰራ ለእነርሱ ትርጉም አልባ ይመስለኛል። ብቻ አጀንዳ ከተገኘ እንደ አንድ የገቢ ማግኛ መንገድ ጉዳዩን በማጦዝ “አካኪ ዘራፍ” ይላሉ። ኢትዮጵያ ውስጥ አንድ የሚያነጋግር ነባራዊ ጉዳይ ከተገኘ፤ ባህር ማዶ ቁጭ ብለው አይስክሬም እየላሱ ተራ ቃላት ጨዋታን በመምረጥ እዚህ ሀገር ውስጥ ሁከት ለመፍጠር የሚሯሯጡት እነ አሸባሪው ዶክተር ብርሃኑ ነጋ ሎተሪ የደረሳቸው ያህል መጨፈራቸው የተለመደ ነው— የተጨማደደ የልመና ኮሮጆአቸው በዶላር ሲሞላ ይታያቸዋልና። እናም አጀንዳውን የግል ጉዳያቸው በማድረግ በኢሳትና በፌስ ቡክ ላይ እንደ አቡነ ዘ- ሰማያት ሲደጋግሙት ይከርማሉ። ግባቸው አጋጣሚውን በመጠቀም ሊገኝ ከሚችል “ሁሉንም የማግኘት” የዜሮ ድምር ፖለቲካን ማራገብ እንጂ፤ ከህዝብ ተጠቃሚነት ጋር የሚገናኝ ባለመሆኑ የሰው ልጅ ሰቆቃ ለእነርሱ ምናቸውም አይደለም።

የሽብር ቡድኑና አባላቶቹ በተለያዩ ወቅቶች ከሚጠቀሙባቸው የሁከት ማቀጣጠያ ጉዳዩች ውስጥ አንዱ የሃይማኖት ጉዳይ ነው። በተለይም በሙስሊሞች ጉዳይ ጣልቃ በመግባት በአጀንዳ ቅብብሎሽ በሽብር ቡድኑና በልሳኑ ኢሳት የስበት ማዕከል አማካኝነት  ለመፍጠር የሞከሩት “የአየር ላይ አመፅ” ጠብ  የሚል ፍሬ ባያስገኝላቸውም ጉዳዩን በማጎን ከፍተኛ ድርሻ ነበራቸው። ከዚህ በተጨማሪም በክርስትና ሃይማኖት ውስጥም ስደተኛውን ሲኖዶስ በመደገፍ ቤተ-ክርስቲያኗን በሪሞት ኮንትሮል ለመምራት ሞክረዋል። እርግጥ ሁሉም ጥረታቸው መና ቀርቷል። ለዚህ ደግሞ ሁለት ምክንያቶችን በዋነኛነት  መጥቀስ የሚቻል ይመስለኛል። የመጀመሪያውና ግንባር ቀደሙ ሙስሊሙም ሆነ ክርስቲያኑ ማህበረሰብ ሰላም ወዳድ ከመሆኑም በላይ፣ መንግስት በጉዳዩ ላይ የሚከተለውን አካሄድ ሙሉ በሙሉ በመገንዘቡ ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ መንግስት በሃይማኖትና በአሰራሩ መካከል ያለውን ድንበር በማይጥስ መልኩ የሁሉንም ምዕመናን ጥያቄዎችን በህገ መንግስቱ አግባብ በማያሻማ ሁኔታ መመለስ በመቻሉ ነው።

ፅንፈኞች በሁከት አምላኪነት የማይቧጥጡት ዳገት የለም። በእነዚህ የሽብር ቡድኖች ትስስርም እንደ ፌስ ቡክ ባሉ ማህበራዊ ሚዲያዎች በአሉባልታ ሁከትን ይጋግራሉ። ገቢ እስከሚያስገኝላቸው ድረስ ያለመታከት ይሰራሉ። እዚህ ሀገር ውስጥ የሚፈጠር ነገር ለእነርሱ የገቢ ማስገኛ በመሆኑ፤ አንዱን ብሔር ከሌላው በማባለት የሁከት ሴራን ይጠነስሳሉ። ይህ ዋነኛ ስራቸው ነው። እናም እነዚህን ፅንፈኞች ዛሬም ቢሆን ልንታገላቸው ይገባል።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy