Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ዜጎቹን የመታደግ ኃላፊነትና ብቃት ያለው መንግስት

0 372

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ዜጎቹን የመታደግ ኃላፊነትና ብቃት ያለው መንግስት

                                                                 ዘአማን በላይ

የኢትዮጵያ ህዝብ ባለፉት ስርዓቶች በድህነት የመጨረሻው ጠርዝ ላይ ተቀምጦ ለመኖር መገደዱ የታሪካችን አንድ እውነታ ነው። ይህን በቀደምት ሥርዓቶች ሳቢያ ከዘመን ወደ ዘመን ሲንከባለል የመጣን የድህነት ችግር ከነ ስንክሳሩ የዛሬ 26 ዓመት ገደማ የተረከበው የኢፌዴሪ መንግስት፤ ባለፉት 15 ዓመታት ባስመዘገባቸው ፈጣንና ተከታታይ የዕድገት ውጤቶች ብቻ የህዝቦችን ነባራዊ ሁኔታ በአንዴ አሽንቀንጥሮ ይጥላል ብሎ ማሰብ አይቻልም።

ልማታዊውና ዴሞክራሲያዊው መንግስት ሀገራችንን የበለጸገች ለማድረግ ብቻ ሳይሆን፤  ከድህነት ተላቃ መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገሮች ተርታ ለማሰለፍ ጥረት እያደረገ ነው። ለዚህ ጉዞው መደላድሎችንም እየፈጠረ ነው። ሆኖም መንግስት በቀየሰው የልማት ስትራቴጂ ምክንያት የተመዘገበው ዕድገት ድህነትን ከመቅረፍ አኳያ በአጭር ጊዜ ውስጥ አበረታች ውጤት ማምጣት ቢችልም፤ ልማታዊ እመርታው ገና ጨቅላ በመሆኑ፣ ሁሉንም የሀገሪቱን ህዝቦች ሙሉ ለሙሉ እኩል ተጠቃሚ አድርጓል ብሎ ለመናገር የሚያስደፍር አይደለም። ያም ሆኖ ግን በምስራቅ አፍሪካ ውስጥ በአየር ለውጥ መዛባት ሳቢያ የሚከሰተውን የድርቅ በእነዚህ ጥቂት ዓመታት ውስጥ መቋቋም ተችሏል።

እንደሚታወቀው የበለፀጉት ሀገራት ለመልማት ባደረጉት እንቅስቃሴ በዓለማችን ሥነ- ምህዳር ላይ በፈጠሩት ቀውስ ሳቢያ በሚፈጠረው የአየር ንብረት መዛባት የተለያዩ አህጉሮች በድርቅ አደጋ ይጠቃሉ። ከእነዚህም ውስጥ እንደ አፍሪካ ያሉ ያላደጉ አህጉሮች ባልፈጠሩት ችግር ግንባር ቀደም ሰለባ ይሆናሉ።

በተለይም የምስራቅ አፍሪካ ሀገሮች የችግሩ ሰለባ ከሆኑ ዓመታት ተቆጥረዋል። በዚህም ሳቢያ መንግስት እዚህ ሀገር ውስጥ የሚከሰተው የድርቅ አደጋ ወደ ረሃብነት እንዳይሸጋገር ብርቱ ጥረት አድርጓል።

በተለይም በአሁኑ ወቅት በሀገራችን በአንዳንድ ዝናብ አጠር አካባቢዎች የተከሰተውን ድርቅ ባለፉት 15 ዓመታት እዚህ ሀገር ውስጥ በተገኘው የልማት አቅም መቋቋም ተችሏል። ለጋሾች ለድርቅ ተጠቂው ወገን ርዳታ እያደረጉ ቢሆንም ቅሉ፤ መንግስት አሁንም ቢሆን ችግሩን ለመወጣት በህዝባዊ የሃላፊነት መንፈስ እየተንቀሳቀሰ ነው። ይህም መንግስት ምን ያህል ዜጎቹን የመታደግ ህዝባዊ ሃላፊነትና አቅም እንዳለው የሚያረጋግጥ ነው።

መንግስት ከአጭር ጊዜ አኳያ በተፈጥሮ ችግር ምክንያት የሚከሰተውን የድርቅ አደጋ ለመከላከል በፍጥነት በመድረስና ዕርዳታ ማድረግ እንዲሁም ድጋፉ ልማታዊ በሆነ አኳሃን ጥቅም ላይ እንዲውል ማድረጉ ለዜጎቹ ያለውን የኃላፊነትና የተጠያቂነት መንፈስ እንዲሁም የገነባውን አቅም የሚያሳይ ነው።

ባለፉት 26 ዓመታት መንግስት የአርሶና የአርብቶ አደሩ ኑሮ እንዲሻሻል ተገቢውን ትኩረት ሰጥቷል። በዚህም አርሶ አደሩ ከራሱ ተርፎ ለገበያ በማምረት ተጠቃሚ የሚሆንበት ደረጃ ላይ እንዲደርስ፣ ሀገሪቱም ከግብርናው ዘርፍ ማግኘት የሚገባትን ጥቅም እንድታገኝ ለማድረግ የሚያስችል የለውጥ ጎዳና እንዲፈጠር አድርጓል። ለዚህ ስኬት በመንግስት በኩል የተወሰዱት እርምጃዎች በቂ ማሳያዎች ናቸው ማለት ይቻላል።

እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ ለእርሻ የሚውል ሰፊ መሬት አላት። ሆኖም በተለያዩ ምክንያቶች በአርሶ አደሩ እጅ እንዳለ የሚታሰበው መሬት አነስተኛ ነው። ከዚህም በተጨማሪ ካለችውም መሬት ቢሆን የሚያገኘው ምርት ዝቅተኛ ነው። አመራረቱም እጅግ ኋላ ቀር ሆኖ ቆይቷል።

ይህን ዕውነታ የተገነዘበው መንግስት ዘርፈ ብዙ የማሻሻል ጥረቶች አድርጓል። በውጤቱም አነስተኛ ይዞታ ባላቸው አነስተኛ የአርሶ አደሮችን ማሳ ላይ ለውጥ ማምጣት አይቻልም የሚለውን አስተሳሰብ ሰብሯል። አነስተኛ ይዞታ ያላቸው አርሶ አደሮች ትኩረት ከመስጠት ይልቅ ለሰፋፊ እርሻዎች ትኩረት መስጠትና ለውጥ ማምጣትን የሚሰብኩ ወገኖችን አፍ ማስያዝ የቻለ ትክክለኛ መስመርን በመከተል ውጤት ማምጣት ችሏል።

በአርብቶ አደሩም አካባቢ ተመሳሳይ የፖሊሲ ማሻሻያዎችን በመቅረፅና ቀደ ተግባር እንዲገባ በማድረግ ድርቅ ሊፈጥር የሚችለውን አደጋ በአያሌው መቀነስ ተችሏል። ከእነዚህ መንግስታዊ ጥረቶች ውስጥ የአርብቶ አደር የልማት ፓኬጆችን በመቅረፅ፤ አርብቶ አደሩ ከልማዳዊ የአኗኗር ባህል ወጥቶ ወደ ዘመናዊ ህይወት እንዲቀየር፣ ከአርብቶ አደሩ ጋር በመነጋገር ድርቅን በዘላቂነት ለመቅረፍ የሚያስችሉ የመስኖ ልማት ስራዎችን በማስፋፋት ወደ ከፊል አርሶ አደርነት እንዲሸጋገር ብሎም ምርጥ ዝርያዎችን አግኝቶ ተጠቃሚነቱን እንዲያሳድግ፣ የከርሰ ምድርና የገፀ ምድር ውሃዎችን በአግባቡ የማሰባሰብ ስራዎችን እንዲያጠናክር፣ የመሰረተ ልማትና የሌሎች የልማት ዘርፎች ተቃሚ ይሆን ዘንድ በፍፁም ፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ የሰፈራ ፕሮግራምን እንዲቀበል፣ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱ እንዲጠናከርና በዚህም ብሔራዊ መግባባት እንዲፈጠር የማድረግ ስራዎችን ማከናወኑና በማከናወን ላይ መሆኑ ጥቂት ተጠቃሽ ምሳሌዎች ናቸው።

እንደ እውነቱ ከሆነ ባለፉት ዓመታት የመንግስት ትኩረት ምንም ዓይነት  የአየር ንብረት  መዛባትና ድርቅ ቢያጋጥምም፤ ህዝባችን የማይራብበት ሁኔታን በመፍጠር ላይ ሲረባረብ ቆይቷል።

በመሆኑም መንግስት ከአጭር ጊዜ አኳያ በተፈጥሮ ችግር ምክንያት የሚከሰተውን ድርቅ ለመከላከል በፍጥነት በመድረስና ዕርዳታ ማድረጉ እንዲሁም ድጋፉ ልማታዊ በሆነ አኳኋን ጥቅም ላይ እንዲውል የክትትል አሰራርን መከተሉ አሁን ላለበት አቅም ያበቁት ይመስለኛል።

እንደሚታወቀው በልማታዊውና ዴሞክራሲያዊው መንግስት የምትመራው ሀገራችን ላለፉት 15 ተከታታይ ዓመታት ባስመዘገበችው ዕድገት ችግሮችን እየተቋቋመች መጥታለች። በእነዚህ ዓመታቶች ውስጥ መንግስት ልማታዊ የግል ኢንቨስትመንቶችን በማበረታታትና የኪራይ ሰብሳቢነት አማራጮችን በማጥናት ለማስወገድ በመሞከርና በግሉ ዘርፍ የማይሰሩ የልማት ክንዋኔዎችን በመስራት፣ ያሉትን ውስን ሃብቶች መሠረታዊ ችግሮችን በሚፈቱበት የልማት ስራዎች ላይ በማዋል፣ የልማት ኃይሎችን በማቀናጀትና በመምራት፣ የህዝብ ተሳትፎን በማጎልበት እና የግል ኢንቨስትመንት በማበረታታት ፈጣን ቀጣይነትና ፍትሃዊ የኢኮኖሚ ዕድገትና ማህበራዊ ልማት ለማምጣት ተችሏል።

ይህ ኢኮኖሚያዊ ዕድገትና ማህበራዊ ልማት በአሁኑ ወቅትም ገቢራዊ እየሆነ ላለው ሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ መንደርደሪያ ነው። ዕድገቱም የሚያጋጥሙ ችግሮችን እየፈታ ህዳሴያችንን አረጋጋጭ መሆኑ አይቀሬ ነው።

በአሁኑ ወቅት የተፈጠረውን የድርቅ አደጋ ለመከላከል ከለጋሽ ሀገራት እገዛና ድጋፍ ከተገኘ እሰየው ነው። ካልተገኘ አሊያም እገዛው የሚፈለገውን ያህል ካልሆነ ደግሞ መንግስት ህዝባዊ ኃላፊነት ያለበት በመሆኑ እንደተለመደው ችግሩን ከህዝቡ ጋር በመሆን ይወጣዋል። ይህን ለማድረግም ቀደም ሲል የጠቀስኩት የመንግስት አቅም ምላሽ ይሰጣል፤ እየሰጠም ነው።

የኢፌዴሪ መንግስት የተከተለው ልማታዊ መስመር ድርቅን በተገቢው ሁኔታ እየተቋቋመ ነው። በአሁኑ ወቅትም በዝናብ እጥረት ሳቢያ በደቡብና በምስራቁ የሀገራችን ክፍል የተከሰተው የድርቅ አደጋን ለመከላከል፣ ያለፉትን ተሞክሮዎች በመቀመርና ሊከሰቱ የሚችሉ ተግዳሮቶችን ከወዲሁ በመለየት ህዝባዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ ነው። ላለፉት 15 የልማት ዓመታት በገነባው አቅምም ይህን እያደረገ ነው። ነገም ቢሆን ልክ እንደ ዛሬው ህዝቡ በተፈጥሮም ይሁን በሰው ሰራሽ አደጋ ሲጠቃ ብቃቱን እያጎለበተ ስለሚሄድ ህዝባዊ ኃላፊነቱን በብቃት እንደሚወጣ መገንዘብ ተገቢ ይመስለኛል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy