Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የህብረቱ ጉባኤና የኢትዮጵያ ሚና

0 696

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የህብረቱ ጉባኤና የኢትዮጵያ ሚና

                                                       ቶሎሳ ኡርጌሳ

29ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ የአህጉሪቱ መዲና በሆነችው አዲስ አበባ ተካሂዷል። የህብረቱ የመሪዎች ጉባኤ ከመካሄዱ በፊት በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ደረጃ የስራ አስፈጻሚዎች ምክር ቤት ስብሰባ ተካሂዶ ነበር። ታዲያ በወቅቱ ስብሰባውን በንግግር የከፈቱት የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፈቂ ማህመት፤ የህብረቱ ተቋማዊ ለውጥና የአፍሪካ የመደመጥ ጉዳይ ላይ መሰራት እንዳለበት ማውሳታቸው ይታወቃል። ሊቀመንበሩ አጀንዳ 2063ን ለማስፈጸም ሃገራት ከራሳቸው አንፃር መስራት እንዳለባቸውም አሳስበዋል።

በአህጉሪቱ ውስጥ ሰላምንና መረጋጋትን ማስፈንና እንዲመጣ የታሰበው ኢኮኖሚያዊ ትስስር ሊፋጠን እንደሚገባ ያመለከቱት ሊቀመንበሩ፤ አህጉሪቱ በአንድ ድምፅ መናገር እንዳለባትና ለወጣቶችዋ ትኩረት መስጠት እንደሚገባትም ተናግረዋል። ለአፍሪካ እድገትም አፍሪካዊ መፈትሄ እንደሚያስፈልግም በጉባኤው ላይ ተጠቁሟል።

ታዲያ ይህ የህብረቱ ኮሚሽን ሊቀመንበር ንግግር የሚያመላክተው ጉዳይ የህብረቱ አቋም ከሀገራችን ጋር ተመሳሳይ መሆኑን ነው። እርሳቸው እንዳሉትም አፍሪካ በመላው ዓለም ተደማጭ እንድትሆን ሀገራችን በርካታ ስራዎችን አከናውናለች። በአየር ንብረት ለውጥ አማካኝነት አፍሪካዊያን እየተጎዱ መሆናቸውን በማስታወቅ የአፍሪካ ድምፅ እንዲሰማ፣ አፍሪካ በፀጥታው ምክር ቤት ተደማጭ እንድትሆን በሰላምና በሰብዓዊ ምብት ኮሚሽኖች ውስጥ ግንባር ቀደም ተዋናይ እንድትሆን እንዲሁም በቡድን ስምንትና 20 ላይ በመሳተፍ የአፍሪካዊያንን ፍላጎት በማንፀባረቅ ላይ ትገኛለች። ይህም ኢትዮጵያ ምን ያህል ለአፍሪካና ለአፍሪካዊያን እየታገለች መሆኗን የሚያሳይ ይመስለኛል።

ርግጥ ኢትዮጵያ ለአፍሪካዊያን ነፃነትና ትግል ድጋፍ መስጠት የጀመረችው ዛሬ አይደለም። ትናንትም በዘመነ ቅኝ አገዛዝ ዘመን ኢትዮጵያ ለአፍሪካዊያን ነፃነት ታግላለች። እንደሚታወቀው የአፍሪካዊያን በዘመነ ቅኝ ግዛት ወቅት የእኔ የሚሉት አህጉር ሁሉንም እሴታቸውንና ገፅታቸውን ለዘመናት አጥተው ኖረዋል። የአፍሪካ በዚያን ወቅት ማራኪ መልክዓ ምድሯንና የተፈጥሮ ሀብቷን ጥቅም ላይ አላዋለችውም። የበይ ተመልካች ሆና ኖራለች። የህዝቦቿን ህልውና ሳይረጋግጥም የብጥብጥና ጦርነት እንዲሁም የባርነትና የስደት ተምሳሌት ሆና ቆይታለች።

ይህቺን ድንቅ ምድር በቀኝ ግዛት የተቀራመቷት ምዕራባውያን የቻሉትን ያህል መዝብረዋታል። ዜጎቿን ገዝተዋል፤ ሸጠዋል። በኋላም ሀገሮቹ ባደረጉት የነፃነት ቆራጥ ተጋድሎ ህዝቦቿ ነፃነታቸውን ቢቀዳጁም ሌላ መርዝ ረጭተውባት በመሄዳቸው አለመግባባት እንዲነግስ፣ ጦርነት ያውም የርስ በርስ ጭምር እንዲስፋፋ፣ ወንድም በወንድሙ ላይ እንዲነሳ፣ ሰላም፣ ልማትና መልካም አስተዳደር ህልም ሆኖ ገፅታዋ ጥላሸት የተቀባ፣ እሴቷም ሰላም ያጣ እንዲሆን ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል።

ርግጥም የአፍሪካ ብጥብጥና ጦርነት ለእነሱ ኢንቨስትመንት ነበር። እንቁዎቿ እየተሸጡ በምዕራባውያን የተፈበረኩ ገዳይ የጦር መሣሪያዎች ተገዝተውበታል። መሣሪያዎቹ ሚሊዮን አፍሪካውያንን በልተዋል። ሀገራችን እንደ ሌሎቹ የአፍሪካ ሀገራት የቅኝ ግዛት ሰለባ ባትሆንም፤ አህጉሪቱ ላይ ያነጣጠሩትን ሴራዎች ገፈት ያልቀመሰችበት ወቅት አለ ማለት አይቻልም።

ወታደራዊ ጥቃቱን በወታደራዊ መንገድ መክታ ነፃነቷን አስጠብቃ የኖረችው ኢትዮጵያና ህዝቦቿ ለሌሎች አፍሪካውያን ነፃነትም በፅኑ ታግለዋል። በንጉስ ኃይለ ስላሴ ዘመን የአፍሪካ አንድነት ድርጅት እንዲመሰረትም ከፍተኛውን ሚና ተጫውታለች።

ርግጥ ኢትዮጵያ ነፃነቷን ጠብቃ የኖረች ብቸኛዋ አፍሪካዊት ሀገር መሆኗ ባይካድም በውስጥ አስተዳደሯ የታደለች አልነበረችም። የታሪኳን ያህል የገዘፈ ስምና ዝና ሳታገኝ የረሃብና ስደት ተምሳሌት ሆና ቆይታለች። አንዴ ከምዕራቡ ሌላ ጊዜ ደግሞ ከምሥራቁ ርዕዮተዓለም ጋር ስትላተም በፊውዳልና አምባገነን አገዛዝ ስትወዘወዝ እዚህ ግባ የሚባል ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገትን ሳታስመዘግብ ኖራለች።

የያኔዋ ኢትዮጵያ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች የማይከበሩባት፣ ወጣት አምራች ኃይሏ በጅምላ የተጨፈጨፈባት፣ ዜጎቿ የቁም ስቅል ያዩባት ሀገር ናት። ኢትዮጵያ ያኔ ይህን መሰል የውስጥ ችግሮች ቢኖርባትም በአፍሪካ ላይ ያላት አቋም ግን ለአፍታም ቢሆን ላልቶና ተለውጦ አያውቅም።

የኢትዮጵያ ቀደምት መሪዎች ለአህጉሪቱ ነፃነት በፅኑ ታግለዋል። አፍሪካዊያን ከኮሎኒያሊዝምና ከአፓርታይድ የግፍ አገዛዝ ነፃ እንዲወጡ፣ ጉዳያቸውን በጋራ እንዲያዩ፣ የሚወስኑበትና የሚታገሉበት መድረክ እንዲፈጠር እንዲሁም እንዲጠናከርና ለህብረት መደላድል እንዲፈጠር ለፍተዋል፤ ደክመዋልም። ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ፖለቲካዊ አንድነት መፈጠር፣ ሰላምና ፀጥታ መከበር እንዲሁም ልማትና ብልፅግና ብሎም ለሌሎች ማህበራዊ ጉዳዮች ሚናዋ የላቀ ነበር።

በቅኝ ግዛት ስር የነበሩ አብዛኞቹ የአፍሪካ ሀገራት ይህ ነው የሚሉት ሀገራዊ የሰላም፣ የልማትና መልካም አስተዳደር ግንባታ ፖሊሲና እስትራቴጂ አልነበራቸውም። ከገዥዎቻቸው የወረሱት የኒዮ ሊበራሊዝም የፖለቲካ -ኢኮኖሚ አስተሳሰብ ህዝቦቻቸውን ከበይ ተመልካችነት አላዳናቸውም። ፖለቲካዊ ነፃነቱ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ማምጣት ባለመቻሉ ሙሉዕ ህልውና ሊኖራቸውም አልቻለም።

ያም ሆኖ የኢትዮጵያ የነፃነት ተምሳሌትነት በአፍሪካዊያን ዘንድ በተለየ መንገድ መታየት ከጀመረ ቆይቷል። ከ15 ዓመታት በላይም አስቆጥሯል። ከውስጣዊ ሁኔታዋ የሚመነጭ፣ ሰፊውን ህዝብ በማሳተፍ በእጁ ያዘለውን መሬት ተጠቅሞ ዕድገት ማምጣት የሚችል ፖሊሲና ስትራቴጂ ቀይሶ ዓለም የመሰከረለት እንዲሁም መላው አፍሪካውያን የኮሩበት ዕድገት በማስመዝገብ ላይ ትገኛለች።

አዲሲቷ ኢትዮጵያ ያለ ማንም ጣልቃ ገብነትም የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት ካልተከበረ፣ በመከባበር ላይ የተመሰረተ የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ አብሮነት አይታሰብም የሚል ጽኑ አቋም በማራመድ ውጤታማ ሆናለች።  ይህም ለአፍሪካዊያን መልካም ተሞክሮ መሆኑን በተጨባጭ አሳይታለች።

ይህች ጦርነት፣ ረሃብና ስደት ተደራርቦባት የሰው ዘር መገኛ የቀደምት ስልጣኔ አምባ፣ የነፃነት ተምሳሌት፣ የራስ ፊደልና ቋንቋ ባለቤት የአፍሪካ ውሃ ማማነቷን ያደበዘዙባት ሀገር በበሳልዋ መሪዋና ድርጅታቸው ፖሊሲና ስትራቴጂ አዲስ የህዳሴ ተምሳሌት መሆን ጀምራለች። አፍሪካ በራሷ አህጉር በቀል ፍልስፍና፣ በህዝቦቿ ጥረትና ባላት ሃብት ተጠቅማ ማደግ እንደምትችል ኢትዮጵያ አብነት ሆናለች።

ያለ ብድርና እርዳታ እንደ ሀገር የመቀጠል ህልውናዋ ጥያቄ ምልክት ውስጥ ገብቶ የነበረችው ሀገር፤ ለአህጉሩ ችግር መፍትሔ አፍላቂ፣ ምዕራባውያንን ጭምር የሚያሳምን ተከራካሪ የቁርጥ ቀን ልጅ ሆናለች። መላው የአፍሪካ ጥቁር ህዝቦች ለነፃነታቸው እንዲነሳሱ ምክንያት የሆነች፣ ሊግ ኦፍ ኔሽንና የተባበሩት መንግሥታትን የመሰረተች፣ በእነዚህ መድረኮች ለእህት ሀገራት የተሟገተችው ሀገራችን ዛሬም በልማቱ፣ በመልካም አስተዳደር ግንባታው ፊት አውራሪነቱን ቀጥላበታለች።

አሁን የአፍሪካ ገጽታ በእጅጉ በመቀየር ላይ ነው። የኒዮ- ሊበራል አስተሳሰብ አራጋቢዎች የነበሩ የምዕራብ ሚዲያዎችና የዚሁ ሥርዓት ጉዳይ አስፈጻሚ ይመስሉ የነበሩት የዓለም ባንክን የመሳሰሉ ተቋማት ጭምር አፍሪካን ብሎም እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ሀገራትን ተጨባጭ ለውጥ መመስከር ከጀመሩ ቆይተዋል።

አፍሪካ ከጨለማ አህጉርነት ወደ አማላይ የኢንቨስትመንት ዞን በመቀየር ላይ ትገኛለች ብለው እስከ መመስከር ደርሰዋል። ኢኮኖሚያቸው በፍጥነት በማደግ ላይ ከሚገኙ የዓለማችን ሀገራት ብዙዎቹ በዚሁ አህጉር መገኘታቸውንም ጥሩ ማሳያ አድርገው እያቀረቡት ነው። እነዚህ ጥቂት እውነታዎች ኢትዮጵያ ለአፍሪካና ለአፍሪካዊያን ያደረገችውን አስተዋፅኦ የሚያመላክቱ ይመስለኛል።    

ያም ሆኖ ኢትዮጵያ እንደ አፍሪካ ህብረት መቀመጫነቷ 29ኛውን የመሪዎች ጉባኤ ባመዘጋጀቷ ብቻ ሳይሆን፤ እንደ ሀገር የአህጉሪቱ የልማትና የአስተማማኝ ሰላም ተምሳሌትነት ሚናዋ ጭምር አብሮ መታወስ ያለበት ይመስለኛል።  

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy