Artcles

የህዳሴያችን ፋና ወጊ ፕሮጀክት

By Admin

July 27, 2017

       የህዳሴያችን ፋና ወጊ ፕሮጀክት

                                                               ደስታ ኃይሉ

የታላቁ የህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ገና ሲጀመር የኢትዮጵያ ህዝቦች በገንዘባቸው፣ በጉልበታቸውና በእውቀታቸው እንደሚፈፅሙት ገልጸው ነበር። አሁንም ቃላቸውን ጠብቀው እያገባደዱት ነው። ይህ ተግባራቸውም ግድቡ የህዳሴያቸው ፋና ወጊ እንደሆነ ተገንዝበው የሚያከናውኑት ነው። ይህን ሲያደርጉም ህዳሴያቸውን ባልዘገዬ ጊዜ ውስጥ እንደሚያረጋገጡ እርግጠኛ ስለሆኑ ነው።

እንደሚታወቀው ሁሉ የዘመናት የድህነት ታሪካችንን ለመቀየርና ከተጫነን ድህነት ለመውጣት በምናደርገው ትግል ልማታዊውና ዴሞክራሲያዊው የኢፌዴሪ መንግስት በግድቡ ግንባታ ስፍራ ላይ የመሰረት ድንጋይ ካኖረበት ሰዓት ጀምሮ፤ መላው የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ያለ አንዳች ልዩነት ስኬታማነቱን ዕውን ለማድረግና በራሳችን ተነሳሽነት ማናቸውንም ጉዳዮች ለመከወን ቃል ገብተናል፡፡ በዚህም ሁሉም የሀገራችን ህዝብ የዘመናት ቁጭትና ብሔራዊ ሀብቱ የሆነውን የዓባይ ወንዝን የመጠቀም ምኞትና ፍላጎት በአዲስ ምዕራፍ እንዲከፈት ተደርጓል፡፡

በህዝቦች የማይነጥፈና ሙሉ ተሳትፎ የሚገነባው እንዲሁም የዜጎች ሀብት የሆነው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በራሳችን ገንዘብና ተሳትፎ የሚገነባ ብቸኛው የዓለማችን ፕሮጀክት ለመሆን በቅቷል፡፡

ዜጎች ከዕለት ምግባቸው ቀንሰው የሚገነቡትና እንደ አይናቸው ብሌን የሚንከባከቡት ግድብ መሆኑም ታሪካዊነቱ የትየሌለ ነው፡፡ እርግጥ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በብሔራዊ መግባባት መንፈስ ግድቡን ካለአንዳች ልዩነት በገንዘባቸውና በጉልበታቸው ለመገንባት ሲነሱ ተርፏቸው አይደለም።

በድህነት አለንጋ መገረፉ ማብቃት እንዳለበት በማመናቸው እንጂ፡፡

ለስኬታማነቱ ህዝባዊ ተሳትፏቸውን ለማረጋገጥ ሲነሱም የማንንም ጉትጎታ ያለመሻታቸው ለድህነት ካላቸው ከፍተኛ ጥላቻ የመነጨ መሆኑም ከማንም የሚሰወር አይመስለኝም፡፡ ህዝቡ ግድቡን ዕውን የማድረግ ህዝባዊ ስሜት ዛሬ ላይ ባለበት የግለት መንፈስ ውስጥ ይገኛል። በመሆኑም በእኔ እምነት ህዝቡ ዛሬም ተግባሩን በብቃት እንዲወጣ ቀስቃሽ የሚያስፈልገው አይመስለኝም። ስለ ግድቡ ያለውን ዕውነታ በሚገባ ይገነዘባል።

ስለሆነም የህዳሴው ግድብ የሚገነባው በህዝቦች ተሳትፎ እንደ መሆኑ መጠን የሚያወዛግቡ ጉዳዩችን ወደ ጎን በማለት ለግድቡ ዕውን መሆን አሁን ካለው በበለጠ ሁኔታ መረባረብ ይኖርበታል።

እንደ ህዝብ ስራችንን መስራት ይኖርብናል። እኛ ኢትዮጵያዊያን በታሪካችን የየትኛውንም ሀገር መብት የማንጋፋ ከህዝቦች ጋር ተባብረን የምንኖር ነን። ይህ ህዝባዊ እምነታችን በመንግስታችን ፍትሐዊነትን ዕውን በሚያደርጉ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች የታጀበ ነው። ዋነኛው ጠላታችን ድህነት ነው።

ግድቡን የምንገነባው ይህን ጠላታችንን ድል ለመንሳት እንጂ የትኛውንም ወገን ለመጉዳት እያሰብን አይደለም። ህዳሴያችንን የምናረጋግጥበት ፋና ወጊ ፕሮጀክታችን ስለሆነ እንጂ በየትኛውም ወገን ላይ ችግር ለመፍጠር አይደለም።

እርግጥ የኢትዮጵያ መንግስትና ህዝብ ለአፍሪካ ቀንድም ሆነ ለመላው አፍሪካ ህዝቦች ሰላም፣ መረጋጋትና ብልፅግና የሚጨነቁና ለዚህም ተግባራዊነት የህይወት መስዕዋትነት ጭምር እየሰጡ የሚተጉ እንዲሁም የዓባይን ወንዝ በተመለከተ የተፋሰሱ ሀገራት ፍትሃዊነትና እኩል ተጠቃሚነት በፅናት የሚቆሙና ሃላፊነት የሚሰማቸው ነው።

ከዚህ ውጪ የትኛውንም የተፋሰሱን ሀገር የመጉዳት አንዳችም ዓይነት ፍላጎት የላቸውም። ማንኛውንም አለመግባባቶች ዴሞክራሲያዊና ስልጡን በሆነ መንገድ በጠረጴዛ ዙሪያ ድርድር ለመፍታት የሚጥሩ የክፍለ ዘመኑ የአፍሪካ ተምሳሌቶች ናቸው።

በዚህ ክፍለ ዘመን ለብቻ ማደግ ብሎ ነገር የለም። የአንዱ ማደግ የሌላውም አብሮ መመንደግ ነው። የአንዱ መውደቅም የሌላው አብሮ የቁልቁለት ጉዞ መያያዝ መሆኑም እንዲሁ። እናም እንኳንስ ከጎረቤቶቻችን ጋር ቀርቶ በሩቅ ሆነው ከእኛ ጋር አብረው ለማደግ ለሚሹ ሀገራትም ቢሆኑ የእኛ ብልፅግና ለእነርሱ ጉዳያቸው መሆኑ አያጠያይቅም። ይህን ሃቅ የሚገነዘቡት የኢፌዴሪ መንግስትና ህዝቡም የሀገራቸው መፃዒ ዕድል ከሌሎች ጋር የተቆራኘ መሆኑን ያምናሉ። እናም በሀገር ውስጥ ለማደግ የሚያደርጉት ጥረት ምን ያህል ፍትሃዊ፣ ምን ያህል ሌሎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ በማጤን ተግባራቸውን ያከናውናሉ።

ይህን ሲከውኑም እንደ ታላቁ የህዳሴ ድግብ ዓይነት የህዝብ ፕሮጀክቶች ለአፍታም ሳይስተጓጎሉ ያለሙትን ሀገራዊና ቀጣናዊ ጥቅም ለመፍጠር ይጥራሉ። እርግጥ የሀገራችን ህዝቦች ከስድስት ዓመታት በላይ በሁለንተናዊ አቅማቸው ሲገነቡት የመጡትና ዛሬ ላይ የኤሌክትሪክ ሃይል የማመንጨት አቅሙ ከፍ እንዲል የተደረገው ግድብ የህዝቡ መታሰቢያ ሃውልት መሆኑ የህዳሴያቸው ፋና ወጊ ፕሮጀክት መሆኑን አመላካች ነው።

እንደሚታወቀው የሀገራችን ህዝብ በብሔራዊ አንድነቱና ጥቅሙ ላይ የመደራደርና የራሱን ጥቅም ለባዕዳን አሳልፎ የመስጠት ባህል የለውም። ይህ በመሆኑም ለሁለንተናዊ ዕድገቱ ቀናዒ የሆነው የአዲሲቷ ኢትዮጵያ ህዝብ የህዳሴውን ግድብ ለመገንባት ከልሂቅ እስከ ደቂቅ ከጫፍ እሰከ ጫፍ በገንዘቡ፣ በዕውቀቱና በጉልበቱ ያለ አንዳች እረፍት ለሃያ አራት ሰዓት ተረባርቦ ዛሬ ላይ ከስድሰተኛ ዓመት በላይ ተጉዟል።

ይህ ዕውነታም ህዝቦች ከተባበሩና ለአንድ ዓላማ በቁርጠኝነት መስራት ከቻሉ የማያስመዘግቡት ሀገራዊ ዕድገት ሊኖር እንደማይችል የሚያረጋግጥ ነው። ከዚህ አኳያ የሀገራችን ህዝቦች የሀገራቸውን ህዳሴ ቅርብ ለማድረግ ሁለት ጊዜ የአምስት ዓመት የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድን ተግብረዋል፤ እየተገበሩም ነው።

ግድቡ የሀገራችን ህዝቦች በጋራ ሆነው በድህነት ላይ የከፈቱት ዘመቻ ሁነኛ ማሳያ ነው። ለዘመናት በህዝባችን ውስጥ ሰፍኖ የነበረውን የ“አይቻልም”ን መንፈስ በ“ይቻላልነት” የቀየረ ማሳያ ፕሮጀክት ነው። በድህነት ላይ ያለንን ቁጭት የምናሳይበት የተግባር መድረካችንም ነው።

የኢትዮጵያ በመጀሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ወቅት ህዳሴያቸውን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ መደላድሎችን ዕውን አድርገዋል። ከተጀመረ ከአንድ ዓመት በላይ ዕድሜ ያስቆጠረውን ሁለተኛውን የልማት ዕቅድንም እያሳለጡ ነው።

የዚህ ፕሮጀክት ከፍፃሜ መድረስ የህዳሴያቸው ፋና ወጊነት ማመላከቻ ነው። እናም ከስድስት ዓመት በላይ በሁለንተናዊ ሁኔታ እንዲያድግ ያደረጉት የህዳሴው ግድብ የህዳሴያቸው ፋና ወጊ መሆኑን እስከሚያረጋግጡ ድረስ ፈፅሞ አይተውትም። እናም ግድቡ የህዳሴያቸው አሳላጭ አድርገው ስለሚወስዱት ይህ ተግባራቸው እስከ ግድቡ መጠናቀቂያ ድረስ ይቀጥላል።