Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የመልካም አስተዳደር ተግባሮች በሁሉም ዘርፎች ይጠናከሩ!

0 476

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የመልካም አስተዳደር ተግባሮች በሁሉም ዘርፎች ይጠናከሩ!

                                                      ቶሎሳ ኡርጌሳ

መልካም አስተዳደርን በአንድ ጀንበር ለማስፈፀም መሞከር፤ “ሲሮጡ የታጠቁት ሲሮጡ ይፈታል” እንደሚባለው የአንድ ጊዜ ‘ሆይ…ሆይታ’ ከመሆን ሊያልፍ የሚችል አይመስለኝም። እናም በሂደትና በሰከነ መንገድ ተግባሩን ማከናወን የግድ ይላል። በሌላ በኩልም ‘መልካም አስተዳደር ጊዜን የሚወስድ ተግባር ነው’ በሚል እሳቤ እጅና እግርን አጣጥፎ መቀመጥ አገባም። ትግበራውን እውን ለማድረግ ቀደም ሲል የተከናወኑ ጉዳዩችን ማጠናከርና የህዝቡን እርካታ ሊፈጥር የሚችል ተደማሪ ስራዎችን ማከናወን ያስፈልጋል።

እርግጥ የመልካም አስተዳደር ትግበራ የሀገራችንን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ዕለታዊ ህይወት በቀጥታ የሚነካ ነው። ምንም እንኳን በአተገባበሩ ዙሪያ ከሀገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ አኳያ መጠነ ሰፊ ተግባራዊ ክንዋኔዎች ቢደረጉም፤ የሚፈለገውን ዓይነት ለውጥ አምጥተዋል ማለት ግን የሚቻል አይመስለኝም። ታዲያ እዚህ ላይ ባለፉት ጊዜያት ምንም ነገር ስላልተከናወነ ሁሉም ነገር ዛሬ ርብርብ ይደረግ እያልኩ አለመሆኑ ሊታወቅልኝ ይገባል። ምክንያቱም ላለፉት 26 ዓመታት ተግባሩን እውን ለማድረግ ጥሩ ጅማሮዎች ያሉት ድርጊቶች ተፈፃሚ ሆነው ውጤት ስለተገኘባቸው ነው።

መንግስት ባለፉት 26 የሰላም፣ የልማትና የዴሞክራሲ ዓመታት ውስጥ መልካም አስተዳደር አስተዳደር የዴሞክራሲ አካልና መሠረት መሆኑን በመገንዘብ የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ባህል ግንባታን በግብነት አስቀምጦ የተለያዩ ተግባራትን አከናውኗል። በዚህም ግልፅነትንና ተጠያቂነትን ሊያሰፍኑ የሚችሉ ተቋማትን ከመመስረት ጀምሮ በየደረጃው የሚገኙ አስፈፃሚዎችን አቅም በማጎልበት በርካታ ስራዎችን ሰርቷል።

ያም ሆኖ እነዚህ ተግባራት የህዝቡን እርካታና አመኔታ ሊያተርፉ ባለመቻላቸው መንግስት በየደረጃው በአስፈፃሚዎቹ ላይ የተለያዩ ርምጃዎችን ከመውሰድ አልቦዘነም። በጥናት ላይ ከተመሰረተና የችግሩ ምንጭ ምንና የት መሆናቸውን ከማወቅ ባሻገር፣ በጥልቅ ተሃድሶው በፌዴራልም ይሁን በክልል ደረጃ ህዝቡን ባሳተፈ መልኩ አስተማሪ ርምጃዎችን ወስዷል።

ለምሳሌ ያህል ሰሞኑን እንደተገለፀው በትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በተገባደደው የበጀት ዓመት ለመልካም አስተዳደር ችግሮች መንስኤ በሆኑ ከሰባት ሺህ 700 በላይ የመንግስት አመራሮችና ሰራተኞች ላይ ህጋዊ ርምጃ የመውሰድና ማስጠንቀቂያ የመስጠት ተግባር መውሰዱ ተነግሯል። ይህም መንግስት የመልካም አስተዳደር ችግርን ለመቅረፍ ያለውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው።

ለመልካም አስተዳደር ተፈፃሚነት ማነቆዎች ናቸው የሚባሉትን ችግሮች ሊቀይሩ የሚችሉ አሰራሮችን በመዘርጋት ረገድም ብዙ ርቀት መጓዝ ተችሏል። እናም ከትናንት ዛሬ የተሻለ ሁኔታን መፍጠር ተችሏል። ከትናንት ዛሬ የተሻለ ሁኔታ እየተፈጠረ መምጣቱን ህዝቡ በጥልቅ ተሃድሶው መሳተፉና ችግሮቹን ያለ አንዳች በማቅረብ ጠያቂ እየሆነ መሄዱን ብቻ በማሳያነት ማንሳት ይቻላል። ህዝቡ በመንግስት ፐብሊክ ሰርቪስ ስራዎች ውስጥ መብትና ግዴታውን ጠንቅቆ ከማየት ባሻገር፤ በየደረጃው የሚገኙ አመራሮችን በማንሳት ንቁ ተሳታፊ ሆኗል። በመልካም አስተዳደር ተግዳሮቶች አኳያ በቂ ግንዛቤ ይዟል።

ሆኖም አሁንም ድረስ ቢሆን የህዝቡን እርካታ መፍጠር አልተቻለም። ለዚህ ደግሞ በመንግስት በኩል ሲገለፅ እንደነበረው፣ የመንግስትን ስልጣን ለግል ጥቅም የማዋል ፍላጎት ገዥውን ድርሻ እየወሰደ ነው። በዚህም ሳቢያ ተሿሚዎችና በየደረጃው የሚገኙ አስፈፃሚዎች ህዝቡን ከማገልገል ይልቅ ራሳቸው በህዝቡ የመገልገል ስሜትን አዳብረው በመልካም አስተዳደር አፈፃፀም ጉዞ ላይ አሜኬላ ሆነው መቆማቸውን ህዝቡ በሚገባ አውቋል።

ያም ሆኖ ይህ የተለየ ችግር የመልካም አስተዳደር ተግዳሮት ቢሆንም፤ አሁንም ህዝብ በመንግስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ላይ አመኔታ ይዞ የተገልጋይነት ስሜቱ ከፍ እንዲልና ፈፃሚው አካልም የህዝቡ ተቀጣሪና አገልጋይ መሆኑን እንዲያውቅ ማድረግ የሚያስፈልግ ይመስለኛል።

እርግጥ በማንኛውም ሀገር ውስጥ መልካም አስተዳደር የሚታሰበው ስርዓቱ ተግባሩን ለማከናወን ካለው በጎ ምልከታ አኳያ መሆኑ ግልፅ ነው። ምንም እንኳን የሀገራችን ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ ስርዓትም መልካም አስተዳደርን በሂደት ለመፈፀም ቁርጠኝነት ቢኖረውም፤ ይህ የመንግስት ቁርጠኝነት ወደ አስፈፃሚው አካል በተለይም ወደ ታችኛው የስልጣን እርከን እየወረደ በሄደ ቁጥር የመሸርሸር ሁኔታ እንዳያጋጥመው መጠንቀቅ ያስፈልጋል። በተለይም በአንዳንድ የታችኛው የስልጣን እርከን የህዝብ መሆኑ ተዘንግቶ ፈፃሚዎች እንዳሻቸው ህዝቡን ያንገላቱታል። ከአቅም ማነስ በመነጨም ለህዝቡ ጥያቄዎች ተገቢውን ምላሽ የማይሰጡበት ሁኔታ ሊኖር የሚችል መሆኑ ወደ ታች ወርዶ ሁሉንም ጉዳዩች በተገቢው መንገድ ከህዝቡ ጋር በመሆን መፈተሽ ይገባል።

እንደሚታወቀው መንግስት ተጠሪነታቸው ለህዝብ ተወካዩች ምክር ቤት ለሆኑት የህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋምና የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ዓይነት ገለልተኛ ተቋማት ከህብረተሰቡ የሚቀርቡ ቅሬታዎች በርካታ ናቸው። ከተቋማቱ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት በመመስረትና ራሱን ለመከላከል ሳይሆን ችግሮችን ለመፍታት በማዘጋጀት ችግሮችን ለመፍታት ቁርጠኛ መሆን የሚጠበቅበት ይመስለኛል።

ይህ ሁኔታም ቅሬታዎች በህዝቡ ውስጥ እንዳይጠራቀምና አመኔታን የሚያጎለብት በመሆኑ፣ ችግሮችን በቅንነት ተቀብሎ ከስር ከስር ለመፍታት ያግዛል። እናም ገለልተኛ ተቋማትን በችግር ፈቺነታቸው በመመልከት የሚከሰቱ ችግሮችን ፈጥኖ ማረም ያስፈልጋል። ምክንያቱም ገለልተኛ አካላቱ ዋነኛ ስራቸው ህዝቡ በህገ-መንግስቱ ላይ የተቀመጡለት መሰረታዊ መብቶቹ ተግባራዊ መሆናቸውን ማረጋገጥ ስለሆነ ነው።

እነዚህ ገለልተኛ አካላት እስካሁን ድረስ በነበራቸው የስራ አፈፃፀም አቅም በፈቀደ መጠን በርካታ ህዝባዊ ጉዳዮችን በመመልከት ህዝብ የተጣለባቸውን ኃላፊነት በብቃት እየተወጡ የመጡ ቢሆንም፤ ይሁንና ለየተቋማቱ የሚሰጧቸውን አስተያየቶች የማይተገብሩ የምንግስት አስፈፃሚ አካላት መኖራቸው እየተነገረ ነው።

ለዚህ አባባሌ ከመሰንበቻው የኢፌዴሪ የህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም በ12 የመንግስት ተቋማት ላይ ክስ መመስረቱንና ምክረ-ሃሳቡን ላልተቀበሉ ተቋማት ደግሞ ተግባራቸውን በአግባቡ እንዲወጡ ማሳሰቢያ መስጠቱን መጥቀስ የሚቻል ይመስለኛል። ይህ ሁኔታ ቢያንስ ክስ በተመሰረተባቸው ተቋማት ውስጥ አሁንም የመልካም አስተዳደር ችግሮች አለመቀረፉን የሚያሳይ በመሆኑ፤ በዚህ ረገድም በቁርጠኝነት መስራት የሚገባ ይመስለኛል።

በመሆኑም በየተቋማቱ ችግሮች እንዳይከማቹና በህዝቡ ውስጥ የቅሬታ መነሻ እንዳይሆኑም ጠንክሮ መስራት ያስፈልጋል። እዚህ ሀገር ውስጥ ህዝብን ማዕከል ያደረጉ፣ የተሟሉና ሊያስሩ የሚችሉ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች አሉ። ችግሩ እነዚህን የህዝብ ተጠቃሚነት ማዕቀፎች መተግበሩ ላይ ነው። አንዳንዱ ችግር ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎችን ባለማስፈፀም ጭምር የሚገለፅ ነው። ቀላል የማይባሉ ተሿሚዎችና አስፈፃሚዎች ሙሉ ጊዜያቸውን ለህዝቡ በመስጠት ከመስራት ይልቅ፣ መንግሰትም ጭምር ቀደም ሲል እንደገለፀው በራሳቸው ተጠቃሚነት ዙሪያ ሲሯሯጡ እንደነበር ይታወቃል። እናም አሁንም ‘ይህ ሁኔታ ምን ደረጃ ላይ ነው ያለው?’ ብሎ መጠየቅ የሚያስፈልግ ይመስለኛል። በጥቅሉ በቀጣዩ የበጀት ዓመት የመልካም አስተዳደር ተግባሮችን በሁሉም መስኮች ማጠናከር ያስፈልጋል። ለዚህ ደግሞ መንግስትና ህዝብ እጅ ለእጅ ተያይዘው መስራት ይኖርባቸዋል እላለሁ።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy