የመታደሳችን ምልክት
ታዬ ከበደ
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በሀገራችን ህዝቦች ትብብር ተጀምሮ እየተገባደደ ያለ የቁርጠኝነታችን ሃውልት ነው፡፡ ግድቡ የአዲሲቷ ኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቁርጠኝነት መገለጫ ነው፡፡ ነገን አሻግረው የሚመለከቱበት መነፅራቸውም ጭምር ነው ማለት ይቻላል—የህዳሴያቸው ማሳያና ፈር ቀዳጅ የውሃ ላይ ሃውልት፡፡
የግድቡ ግንበታ ለዘመናት አብሮን የዘለቀው ዓባይን የመገደብ አይሞከሬነት አስተሳሰብ ያከተመበትና የይቻላል አስተሳሰብ ለውጥ የተፈጠረበት፣ በየትኛውም የዓለማችን ክፍል የሚገኝ ኢትዮጵያዊ የዜግነት ድርሻውን ለመወጣት ቃል የገባበት እንዲሁም ምላሹን የሰጠበት ፕሮጀክት መሆኑ በዓለማችን በዜጎች ገንዘብና ባለቤትነት የሚገነባ ብቸኛው ፕሮጀክት ነው፡፡
ግንባታው በዘርፉ ከፍተኛ ልምድ ባካበተው የሳሊኒ ኮንስትራክሽን ኩባንያና በሀገር በቀሉ የብረታብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፓሬሽን አማካኝነት እየተከናወነ ሲሆን፤ የመጀመሪያው ምዕራፍ ተጠናቆ ዋነኛ የግንባታ ሥራው በመፋጠን ላይ ነው፡፡
የግንባታ ሥራው ሲጠናቀቅ አንድ ሺህ 780 ሜትር ርዝመትና 145 ሜትር ከፍታ እንደሚኖረው የሚነገርለት የህዳሴው ግድብ ግንባታ፤ የሲቪል ሥራ የሚከናወነው በሳሊኒ ኮንስትራክሽን፣ የኤሌክትሮ እና የሃይድሮ ሜካኒካል ሥራው በብረታብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፓሬሽን፣ የማማከሩ ተግባር ደግሞ የጣልያንና የፈረንሳይ መሃንዲሶች ጥምር ኩባንያ አማካኝነት እየተካሄደ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡
ታዲያ “ነገርን ነገር ያነሳዋል” እንዲሉ የግድብ ግንባታን ስናነሳ የዓላማችን ሃያሏ ሀገር አሜሪካ በ1930ዎቹ ያስገነባቸው የሁቨር ግድብ ይጠቀሳል፡፡ በኮሎራዶ ወንዝ ላይ የተገነባው የሁቨር ግድብ አሜሪካውያኑ ግሬት ዲፕረሽን ብለው በሚጠሩት አስቸጋሪ ወቅት ከተገነቡት ግድቦች መካከል አንዱ ነው፡፡ በወቅቱ የግድቡ ግንባታ የዕድገታቸው ዋነኛ መሰረት እንደሆነ በማሰብ በዜጎች ከፍተኛ መነሳሳትን የፈጠረ እንደነበርም አይዘነጋም፡፡
የግድቡ ግንባታ ሥራ ለዜጎች ከፍተኛ የስራ ዕድል መፍጠር መቻሉም እንዲሁ፡፡ በዚህም ለግድቡ የአርማታ ሥራ ብቻ 5000 ሺህ የሀገሪቱ ዜጎች ተሰማርተው ኑሯቸውን ለመግፋት አስችሏቸዋል፡፡ የሁቨር ግድብ ግንባታ ሥራ የከሎራዶ ወንዝን ተፈጥሯዊ የፍሰት አቅጣጫ ለማስቀየር ከአንድ ዓመት በላይ መፍጀቱንም ማስረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
ታዲያ በዚህ እውነታ የምንረዳው ነገር ቢኖር የሁቨር ግድብ በበርካታ ጉዳዮች ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ጋር የሚያመሳስለው ቢሆንም የሚለይበት ሁኔታ መኖሩንም ጭምር ነው፡፡ ከዚህ አኳያ የወንዙን የፍሰት አቅጣጫ ለመቀየር የፈጀው ጊዜና ፍጥነት ከወንዙ መጠን ጋር ተዳምሮ ግድቡ በተፋጠነ መልክ እንዲከናወን ማድረጉ ተጠቃሽ ሲሆን፤ ይህም የስኬታማነቱን ደረጃ ፈጣንነት የሚያመላክት ነው፡፡
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብም ሃያ አራት ሰዓታት ያለማቋረጥ እየተገነባ ነው። ከ10 ሺህ የሚበልጡ ሰራተኞችም በሥራው ላይ ተሰማርተው በከፍተኛ ሀገራዊ ስሜትና ኃላፊነት ተግባራቸውን በሀገራዊ ፍቅር ስሜት በማከናወን ላይ ናቸው፡፡ በዚህም የግንባታ ሥራው በመለዋወጫና ግብዓት ረገድ አንዳች ችግር ሳይገጥመው በተፈለገው ፍጥነት እንዲጓዝ አስችሎታል፡፡
ሀገር በቀሉ የብረታብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፓሬሽን በበኩሉ የኤሌክትሮ ሚካኒካልና የሃይድሮ ሜካኒካል እንዲሁም ተዛማጅ የመቆጣጠሪያ መሣሪያዎች ዲዛይን የማድረግ፣ የመፈብረክ፣ የማምረት፣ የመትከልና ፈትሾ የማስረከብ ስራውን በተገቢው ሁኔታ በመፈጸም አመርቂ ውጤት በማስመዝገብ ላይ ይገኛል፡፡ ይህም ሀገራዊ አቅምን በማጠናከር ረገድ ትልቅ አቅም እየፈጠረ በመምጣቱ፤ በዘርፉ ለሚካሄድ የግንባታ ሥራ ራስን በመቻል ረገድ ከፍተኛ ዕድል እየፈጠረ መሆኑ በገሃድ ያሳያል፡፡
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የተለያዩ ሁነቶችን ተሻግሮ ዛሬ ላይ ደርሷል፡፡ በዚህም የግንባታ ሥራውን ከጋራ ተጠቃሚነት አኳያ በመመዘን ድጋፋቸውን ያንጸባረቁ ሀገሮች የተስተዋሉበት እንዲሁም ፍትሃዊ የውኃ አጠቃቀም ከምንጊዜውም በላይ ትኩረት እንዲስብ አስችሏል።
በተቃራኒው ደግሞ ሥራውን ከመቃወም እስከ የማደናቀፍ ሴራ ጥንስስም ታይቶበታል፡፡ ነገር ግን መንግስትና ህዝብ በሰጡት ትኩረት የግንባታ ሥራው ላፍታም ሳይደናቀፍ በታለመለት መንገድ እየተፈጸመ አሁን በሚገኝበት ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ ለዚህም በመላው ኢትዮጵያዊ የተፈጠረው መነሳሳትና የመንግስት የፀረ- ድህነት ትግል ቁርጠኝነት ለግንባታ ሥራው የእሰካሁኑ ጉዞ ስኬታማነት በምክንያት የሚጠቀሱ ዋነኛ ጉዳዮች ናቸው ማለት ይቻላል፡፡
አገራዊው ቀደሚ አጀንዳ የሆነው የግድቡ ሥራ በአሁኑ ጊዜም የቅርብ ክትትል አልተለየውም፡፡ መላው የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች እንደ “ዓይን ብሌናቸው” የሚንከባከቡት ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በየዕለቱ በርካታ ዜጎች ይጎበኙታል፡፡ ይህም በሥራው ለተሰማሩ ኢትዮጵያውያንና የውጭ ዜጎች ትልቅ የሞራል ስንቅ በመሆኑ ለሥራው መፋጠን ሚናው የላቀ ሆኗል፡፡
ግድቡ ለተለያዩ ዜጎችና ሀገር በቀል ተቋራጮች የዕውቀት መቅሰሚያ መንገድ በመሆኑ የነገን ብሩህነት ማመላከት ያስችላል፡፡ በተለይም የዓለማችን ከተፈጥሮ ጋር የሚሰማማ የኃይል ፍላጎትን የሚያሟላው የሃይድሮ ኃይል ማመንጫ ግንባታ ሥራ መስፋፋት ጋር ተያይዞ በዘርፉ ተሰማርቶ ተጠቃሚ ለመሆን የሚያስችል በመሆኑ ጠቀሜታው ከፍተኛ ነው፡፡
በሌላም በኩል በሀገራችን በከፍተኛ ፍጥነት እያደገ ለሚገኘው የመሠረተ ልማት ግንባታ ምላሽ የሚሰጥ የሰው ኃይል መፈጠሩ ሀገራዊ ፋይዳው የላቀ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ለማመን በሚያዳግት ሁኔታ እያስገመገመ ለመጣው የኢንቨስትመንት ፍሰት በቂ ምላሽ መስጠት የሚችል የኃይል አቅርቦት የሚያጎናጽፍ በመሆኑ፤ ለሀገራዊው ዕድገት ቀጣይነት ታላቅ ዋስትና እንደሚሆን አያጠራጥርም፡፡
የግድቡ ጠቀሜታ በዚህ ብቻ የተወሰነ አይደለም። ከጎረቤት ሀገሮች ጋርም ኢኮኖሚያዊ ትስስራችንን ወደ ላቀ ደረጃ ያሸጋግራል፡፡ ይህም ለአካባቢው ሀገራት የጋራ ዕድገትና አስተማማኝ ሠላም መስፈን አስተዋጽኦው የጎላ ነው፡፡
በመሆኑም በጀርባችን ላይ የተፈናጠጠው ድህነትን አሽቀንጥረን ለመጣል ለጀመርነው የፀረ-ድህነት ትግል ከግብ መድረስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል። እርግጥም የግድቡ ግንባታ ሥራ ፅናትና ቁርጠኝነት በተሞላበት ሁኔታ በመካሄድ ላይ መሆኑን ለሚመለከተው ሰው የሚያጎናፅፈው ሀገራዊ ኩራት ምን ያህል ሊሆን እንደሚችል ከማንም የሚሰወር አይመስልኝም፡፡
የነገዋን የታደሰች ኢትዮጵያን የሚያመላክተው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ሥራ መሠረተ ድንጋይ ከማኖር ጀምሮ መላው ኢትዮጵያዊ የሰጠው ምላሽ ለስኬታማነቱ በር መከፈት ከፍተኛ ድርሻ እንደነበረው የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡ በህዝቦች ትብብር የግድቡ ግንባታ ስድተኛ ዓመቱን ተሻግሯል፡፡ ግንባታውም እየተገባደደ መሆኑ እየተነገረ ነው፤ ወሳኝ የሚባሉት ስራዎችም ፈራቸውን ይዘዋል፡፡ ታዲያ ይህን የመታደስ ምልክታቸን የሆነውን ግድብ እስከመጨረሻዋ ፍፃሜ ድረስ ለመጨረስ ዛሬም እንዳለፉት ጊዜያት ሁሉም ዜጋ በነቂስ ሊረባረብ ይገባል፡፡