የሚያስመሰግን ተግባር
ብ. ነጋሽ
የሳኡዲ አረቢያ መንግስት በሃገሩ በህገወጥነት የሚኖሩ የውጭ ሃገር ዜጎች ሃገሩን ለቀው እንዲወጡ ከሶስት ወር በፊት አዋጅ ማውጣቱ ይታወቃል። ይህ አዋጅ በዚያ በህገወጥነት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንንም የሚመለከት ነው። በሳኡዲ አረቢያ በህገወጥነት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ቁጥር 400 ሺህ ይደርሳል ተብሎ የገመታል።
ይህ የሳኡዲ አረቢያ መንግስት ያወጣው አዋጅ የኢትዮጵያ መንግስትንም የሚመለከትና ያሳሰበ ጉዳይ ሆኗል። አሳሳቢ የሚያደርገው የሳኡዲ አረቢያ መንግስት ኢትዮጵያውያኑ ሃገሩን ለቀው እንዲወጡ ያስቀመጠው የጊዜ ገደብ ከተጠናቀቀ በኋላ፣ በኢትዮጵያውያኑ ላይ ክብረ ነክ እንግልትና ስቃይ መድረሱ እንዲሁም የሰብአዊ መብት ጥሰት መፈጸሙ አይቀሬ መሆኑ ነው። የሳኡዲ አረቢያ መንግስት የውጭ ሃገር ዜጎች ሃገሩን ለቀው እንዲወጡ ያስቀመጠው የጊዜ ገደብ ካበቃ በኋላ በሚወስደው ህግ የማስከበር እርምጃ ህገወጦቹን የሚያጉርባቸው እስር ቤቶች በተለያዩ የሃገሪቱ አካባቢዎች ማዘጋጀቱ ተሰምቷል።
የሳኡዲ አረቢያ መንግስት በመላ ሃገሪቱ ተሸሽገው የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን አድኖ ይዞ የህግ ቅጣት ወደሚያገኙበት ማጎሪያ ሲወስድና በማጎሪያ ቤቶቹ ውስጥ ለከፍተኛ ስቃይና እንግልት የሚዳረጉ መሆኑ ግልጽ ነው። በዚህ በጅምላ በሚካሄድ ህገወጦችን ይዞ ወደማጎሪያ የማጓጓዝ እርምጃ፣ በተለመደ የዘውትር ህግ የማስከበር እርምጃ ታይተው የማያውቁ እንግልትና ስቃዮች ሊያጋጥሙ መቻላቸው ሳይታለም የተፈታ ነው።
ከዚህ በተጨማሪ በግዜ ገደቡ ውስጥ ወደሃገራቸው ሳይመለሱ የቀሩ ኢትዮጵያውያን፣ ከህግ ለማምለጥ በተሸሸጉበት ቦታ በግለሰቦችና በቡድኖች ለሚፈጸሙ የሰብአዊ ጥቃት ይጋለጣሉ። በህገወጥነት ተሸሽገው የሚኖሩት ኢትዮጵያውያን ሰብአዊ ጥቃት ተፈጸመብኝ ብለው አቤት የማለት የህግም የሞራልም አቅም አይኖራቸውም።
በመሆኑም የሚፈጸምባቸውን ጥቃት ማስቀረት ወይም መከላከል የሚያስችላቸው እድል የላቸውም። በተለይ በሴቶች ላይ ክብረ ነክ የሆነና በህግ ሊከላከሉት የማይችሉት የአስገድዶ መደፈርና ሌሎች ክብረ ነክ ወንጀሎች ሊፈጸምባቸው ይችላል። በአንድ ቤት ውስጥ ወይም ጊቢ ውስጥ ታግተው በባርነት እንዲኖሩ ለሚያደርግ አደጋ ሊጋለጡ መቻላቸውም እርግጥ ነው። ከአራት ዓመት በፊት የሳኡዲ አረቢያ መንግስት ተመሳሳይ እርምጃ ወስዶ በነበረበት ወቅት የዚህ አይነት ዘግናኝ ድርጊት በኢትዮጵያውያን ላይ መፈጸሙ ይታወሳል። በወቅቱ ህይወታቸውን ያጡ ኢትዮጵያውያንም እንደነበሩ እናስታውሳለን።
የሳኡዲ አረቢያ መንግስት ያወጣው በህገወጥነት የሚኖሩ የውጭ ሃገር ዜጎች እንዲወጡ የሚጠይቅ አዋጅ፣ የኢትዮጵያ መንግስትን ያሳሰበው ከላይ የተገለጸው ስቃይ፣ እንግልት፣ የሰብአዊ መብት በዜጎቹ ላይ ሊፈጸሙ አይቀሬ በመሆኑ ነው። በዚህ ምክንያት በአወጁ የተቀመጠው የ90 ቀናት የጊዜ ገደብ ተግባራዊ መደረግ በጀመረበት ዕለት ነበር ዜጎቹን በሰላም ወደሃገራቸው የመመለስ እንቅስቃሴ የጀመረው።
የኢትዮጵያ መንግስት በህገ ወጥነት በሳኡዲ አረቢያ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ለስቃይና ለሰብአዊ መብት ጥሰት ሳይጋለጡ ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ለማድረግ መጋቢት 21፣ 2009 ዓ/ም ከሳዑዲ አረቢያ ባለስልጣናት ጋር በመመካከር ኢትዮጵያውያኑን ወደሀገራቸው መመለስ የሚቻልበትን መንገድ የሚያመቻች የልኡካን ቡድን ወደሳኡዲ አራቢያ ልኮ ስምምነት ላይ ደርሷል።
በዚህ መሰረት የኢትዮጵያ መንግስት ኢትዮጵያውያኑ ሳይንገላቱ ወደ ሃገራቸው እንዲመለሱ ለማድረግ የሚያስችሉ ተግባሮች አከናውኗል። በቅድሚያ በኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አማካኝነት ኢትዮጵያውያኑን ወደሃገራቸው የሚመልስ አስተባባሪ ግብረ ሃይል የማደራጀት ተግባር ነበር የተከናወነው።
ከዚህ በተጨማሪ ኢትዮጵያ ውስጥ በሃገር አቀፍ ደረጃ ስራውን የሚመራ ግብረ ሃይል እንዲዋቀር ተደርጓል። የፌዴራልና የክልል መንግስታትን ጨምሮ፣ በቅርብም ይሁን በሩቅ ጉዳዩ የሚመለከታቸውን አካላት ያካተተ በከፍተኛ የመንግስት ኃላፊዎች የሚመራ ብሔራዊ ግብረ ኃይል እንዲሁም በሳኡዲ አረቢያ ዘጠኝ ማዕከላት በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የሚመራ አስመላሽ ግብረ ሃይል አዋቅሮ ኢትዮጵያውያኑን ወደሃገራቸው ለመመለስ ከፍተኛ ጥረት ሲያደግ ቆይቷል።
የኢትዮጵያ መንግስት በህገወጥነት በሳኡዲ አረቢያ የሚኖሩ ዜጎቹን በየአካባቢው ባዘጋጀው ጣቢያ ቀርበው ወደሃገራቸው ለመመለስ የሚያስፈልጋቸውን የጉዞ ሰነድ ወስደው እንዲመዘገቡ ባደረገው ከፍተኛ ጥረት የ90 ቀናት ገደቡ እስከተጠናቀቀበት ጊዜ ደረስ ከ110 ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን እንዲመዘገቡ ማድረግ ችሏል።
እርግጥ በሳኡዲ አረቢያ በህገወጥነት ይኖራሉ ተብሎ ከሚገመተው እስከ 4 መቶ ሺህ የሚደርስ የኢትዮጵያውያን ቁጥር አንጻር ሲታይ ወደሃገራቸው ለመመለስ የተመዘገቡት እጅግ በጣም ጥቂት ናቸው። መንግስት ግን ሁሉም ኢትዮጵያውያን ተመዝግበው ወደሃገራቸው እንዲመለሱ በተለያዩ ብሄረሰቦች ቋንቋዎች ማህበራዊ ሚዲያዎችን በመጠቀም ጭምር መልዕክት በማስተላለፍ ከፍተኛ ጥረት ማደረጉ መታወቅ አለበት።
ከእነዚህ ወደሃገራቸው ለመመለስ ከተመዘገቡት 110 ሺህ ኢትዮጵያውያን መሃከል እስከአሁን ወደሃገራቸው የተመለሱት 52 ሺህ ገደማ ናቸው። ለመመለስ ፍቀደኛ ሆነው ከተመዘገቡት መሃከል እስካሁን ግማሽ ያህሉ ብቻ ናቸው የተመለሱት። ይህ የሆነው አብዛኞቹ ለመመለስ የቀረቡት ዘግይተው በመሆኑ በተፈጠረ የጉዞ መጨናነቅ ነው።
በትራንስፖርት ክፍያ እጥረት ለመቅረት የሚገደዱ ኢትዮጵያውያን የሚኑሩበትን እድል ለማጥበብ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የበረራ ክፍያ ላይ የ50 በመቶ ቅናሽ አድርጓል። ከዚህ በተጨማሪ አየር መንገዱ ተደራሽነቱን ለማሰፋት የየእለት በረራውንና አገልግሎት የሚሰጥባቸውን ስፍራዎች ጨምሯል። ወደሃገራቸው ለመመለስ ከተመዘገቡት ውስጥ ግማሽ ያህሉ ብቻ የተመለሱት ይህ ሁሉ ርብርብ እየተደረገ ነው። በዚህ ሁኔታ ነበር የሳኡዲ አረቢያ መንግስት ያስቀመጠው የ90 ቀናት የጊዜ ገደብ የተጠናቀቀው።
በርካታ ዜጎቹ፣ ወደሃገራቸው የመመለስ ፍላጎት ያላቸው ጭምር አለመመለሳቸው ያሳሰበው የኢትዮጰያ መንግስት በጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም አማካኝነት ለሳኡዲ አረቢያው ንጉስ ሳልማን ቢን አብዱልአዚዝ የምህረት ቀኑ እንዲራዘም ጥያቄ አቅርቧል።
ይህ የኢትዮጵያ መንግስት ጥያቄ በሳኡዲ አረቢያው ንጉስ ተቀባይነት አግኝቶ የምህረት ጊዜው ከሰኔ 18፣ 2009 ዓ/ም ጀምሮ በ30 ቀናት ተራዝሟል። ይህ የተራዘመ የጊዜ ገደብ ሊጠናቀቅ አሁን ከ10 ቀናት ያነሰ ጊዜ ነው የቀረው። ይህም ሆኖ የኢትዮጵያ መንግስት በቀሩት ጥቂት ቀናት ውስጥ ቢያንስ ወደሃገራቸው ለመመለስ የተመዘገቡትን በሙሉ ለማጓጓዝ ርብርብ በማድረግ ላይ ይገኛል።
ኢትዮጵያውያኑ ላለመመለሳቸው የተለያዩ ምክንያቶች መኖራቸውን በሳኡዲ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ይገልጻሉ። ከእነዚህ ውስጥ ዋነኛው ቀጣሪዎቻቸው የጊዜ ገደቡ ቢያበቃም ምንም አትሆኑም እያሉ የሚያቀርቡላቸው ማባበያ መሆኑን ነው ኢትዮጵያውያኑ የጠቆሙት። የሰሩበትን ክፍያ አለማግኘትና መሰል ችግሮችም በምክንያትነት ይጠቀሳል።
በአጠቃላይ የኢፌዴሪ መንግስት በሳኡዲ አረቢያ በህገወጥነት የሚኖሩ ዜጎቹ ላይ ስቃይና እንግልት፣ የሰብአዊ መብት ጥሰት እንዳይፈጸም፣ ማድረግ የሚችለውን ሁሉ አከናውኗል። ይህ የህዝብ ውክልና ካለው መንግስት የሚጠበቅ ተግባር ነው።
ዜጎቻቸው በሳኡዲ አረቢያ በህገወጥነት የሚኖሩ በርካታ ዜጎች ያላቸው የባንግላዴሽ፣ የፊሊፒንስ፣ የህንድ፣ ፓኪስታንና ሌሎችም መንግስታት ዜጎቻቸውን ከእንግልትና ከሰብአዊ መብት ጥሰት ለመታደግ አንዳችም እንቅስቃሴ አላደረጉም። ከዚህ አኳያ የኢትዮጵያ መንግስት ያከናወናቸው ተግባራት የሚያስመሰግኑ ናቸው። ህዝባዊ መንግስት መሆኑንም ያሳያል።