Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የሥራ እንጂ የሙያ አጥነት ችግር ተቃሏል

0 378

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የሥራ እንጂ የሙያ አጥነት ችግር ተቃሏል

ኢብሳ ነመራ

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት (ዩኒቨርሲቲዎች)  ትምህርታቸውን  በብቃት አጠናቀዋል ያሏቸውን ተማሪዎቻቸውን እያስመረቁ ነው። ዘንድሮ በአጠቃላይ 150 ሺህ ተማሪዎች በመጀመሪያ፣ በሁለተኛና በሶስተኛ ዲግሪ ይምረቃሉ ተብሎ ይጠበቃል። ከእነዚህ ተመራቂዎች መሃከል 25 ሺህ ገደማ የሚሆኑት በግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚመረቁ ናቸው። ከሁለት አስርት ዓመታት በፊት ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚመረቁ ተማሪዎች ቁጥር በተጋነነ ግምት ከሶስት ሺህ አይበልጥም ነበር፤ የዲፕሎማ ተመራቂዎችን ጨምሮ።

ታዲያ ያኔ የነበሩት ሁለት ዩኒቨርሲቲና ጥቂት መካከለኛ ባለሞያ የሚያሰለጥኑ ኮሌጆች ብቻ ነበሩ። አሁን 36 የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች አሉ። የሞያና የቴክኒክ ስልጠና የሚሰጡ ኮሌጆች ቁጥር ከ1 ሺህ 300 በላይ ነው። በየዓመቱ በተለያየ ደረጃ ከእነዚህ ኮሌጆች በዲፕሎማ ተመርቀው የሚወጡ ወጣቶች እስከ አንድ ሚሊየን ይደርሳሉ።

ይህ ሃገሪቱ ባለፉ ሁለት አስርት ዓመታት በከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ ያመጣችውን እመርታዊ ለውጥ ያሳያል።

አሁን  በሃገሪቱ ከአንደኛ ደረጃ ጀምሮ ባሉ የትምህርት እርከኖች ወደ28 ሚሊየን ወጣቶች በትምህርት ገበታ ላይ ይገኛሉ። እነዚህ በአንደኛና በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሚገኙ ተማሪዎች፣ በቀጣይ የሞያና ቴክኒክ ኮሌጆች እንዲሁም ዩኒቨርሲቲዎች የመማር እድላቸው እጅግ ሰፊ ነው። ከሁለት አስርት ዓመታት በፊት  በሃገሪቱ የነበሩት የሞያ ማሰልጠኛ ኮሌጆችና ዩኒቨርሲቲዎች ጥቂት በመሆናቸው፣ የከፍተኛና የሞያ ትምህርት የማግኘት እድል የነበራቸው ወጣቶች ቁጥር እጅግ ውስን ነበር።

የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ከሚያጠናቅቁ ተማሪዎች መሃከል ከ90 በመቶ በላይ የሚሆኑት ሞያ አልባ ሆነው ነበር የሚቀሩት። በዚህ ምክንያት ስራ የማግኘት እድላቸው ጠባብ ነበር። ከአስር ዓመት በላይ ምንም ስራ ሳያገኙ የሚኖሩ፣ ስራ በመፈለግ የወጣትነት እድሜያቸውን ጨርሰው ወደጎልማሳነት የሚሸጋገሩ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ያጠናቀቁ ዜጎች ቁጥር ቀላል አልነበረም። በወቅቱ የነበረው የስራ አጥነት ችግር ብቻ አልነበረም። የሞያና የስራ አጥነት ድርብ ችግር ነበር።

አሁን እጅግ አብዛኞቹ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት የሚያጠናቅቁ ተማሪዎች ባለሞያ የመሆን እድል ይጠብቃቸዋል። ሃገሪቱ አሁንም ከፍተኛ የወጣት ስራአጥነት ችግር ቢኖርባትም የሞያ አጥነት ችግርን ግን አቃላለች። ይህ በራሱ አንድ ትልቅ ስኬት ነው። የስራ አጥነትን ችግር በግማሽ እንደማቃለል ሊቆጠርም ይችላል። ሞያ የታጠቁ ዜጎች በስራ ፈጠራ፣ ስራ ላይ የመሰማራት አቅም አላቸውና። አሁን በሃገሪቱ በስራ ፈጠራ ላይ መሰማራት የሚችል ሞያ የታጠቀ በቂ የሰው ሃይል አለ።

አሁንም ግን በተለይ ከዩኒቨርሲቲዎች ተመርቀው የሚወጡ ተማሪዎች ዘንድ  በተለይ በማመረት ዘርፍ የስራ ፈጠራ ላይ የመሰማራት ስልጠና የወሰዱ ተማሪዎች ውስን መሆናቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ። እርግጥ መንግስት የሚከተለው የ70 በ30 የሳይንስና ቴክኖሎጂ የማህበራዊ ሳይንስ ጥመርታ አንዱ ዓላማ በማምረት ዘርፍ የስራ ፈጣሪ ወጣቶችን ማፍራት ነው።

ይህ በሃገሪቱ ትምህርትና ስልጠና ላይ የታየ እመርታዊ ለውጥ በዋዛ የመጣ አይደለም። ከፍተኛ የመንግስት ካፒታል ኢንቨስትመንትን ጠይቋል። ልብ በሉ የኢትዮጵያ የከፍተኛ ትምህርት የተጀመረው በ1940 ዎቹ ነበር። ታዲያ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ባለው የግማሽ ከፍለ ዘመን ጊዜ ውስጥ የሃገሪቱ ዩኒቨርሲቲዎችና ከፍተኛ ኮሌጆች ቁጥር አስር እንኳን መሙላት አልቻለም ነበር።

በወቅቱ የነበሩት ሁለት ዩኒቨርሲቲዎችና ከአምስትና ስድስት የማይበልጡ ከፍተኛ ኮሌጆችም ቢሆኑ የተማሪ ቅበላ አቅማቸው ከመቶዎች የሚዘል አልነበረም። ከአንድ ሺህ በላይ ተማሪዎች የመቀበል አቅም የነበረው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ብቻ ነበር። በሃገሪቱ የነበሩ መለስተኛ ሞያ የሚያሰለጥኑ የተግባረ ዕድ (የሞያና ቴክኒክ) ማሰልጠኛዎች ቁጥር ደግሞ 14 ገደማ ብቻ ነበር።

አሁን በስራ ላይ ያሉትን 36 ዩኒቨርሲቲዎች እንዲሁም በክልላዊ መንግስታት ስር የሚተዳደሩትን ከ1 ሺህ 3 መቶ በላት የቴክኖክና ሞያ ተቋማት ለመገንባት በብዙ ቢሊየን የሚቀጠር የካፒታል በጀት ተመድቧል። ይህ መንግስት ለትምህርት ዘርፉ የሰጠውን ትኩረት ያሳያል። እንዲሁም ባለፉ ሁለት አስርት ዓመታት የመንግስት የካፒታል በጀት አቅም ምን ያህል እንደጎለበተ ያሳያል። በቀጣይ ዓመት 11 አዳዲስ ዩኒቨርሲቲዎች ተማሪዎችን ለመቀበል በዝግጅት ላይ የሚገኙ መሆኑም ታውቋል።

በትምህርት ልማት ዘርፍ ይህን ያህል እመርታዊ ለውጥ ማምጣት ቢቻልም፣ አሁንም ከትምህርት ልማቱ ጋር የተያያዙ ፈተናዎች አሉ። ቀዳሚው ፈተኛ በየአመቱ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚመረቁ በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ዜጎችን በሚፈለገው ልክ ተቀጥረው የሚሰሩበት እድል የማያገኙ መሆኑ ነው።

ሃገሪቱ አሁን ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የምታወጣቸውን ተማሪዎችን በሙሉ መቅጠር የሚያስችል የስራ እድል እየፈጠረች አይደለም። በዚህ ምክንያት በየዓመቱ የተከማቹ በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ከዩኒቨርሲቲ የተመረቁ ስራ አጥ ወጣቶችን መመለከት የተለመደ ነው። ይህ የከፍተኛ ትምህርት ተመራቂዎች የስራ አጥ ጎራ በሁለተኛ ዲግሪ የተመረቁትንም ያጠቃልላል። ይህ ሁኔታ በወጣቶቹና በወላጆቻቸው ዘንድ ምቾት የሚነሳ ሰሜት ፈጥሯል።

እርግጥ የኢፌዴሪ መንግስትና የክልል መንግስታት ይህን ችግር ተገንዝበው ማቃለል የሚያስችሉ ፕሮግራሞችን ቀርጸው ተግባራዊ ሲያደርጉ መቆየታቸው ይታወቃል። ይህም ስራ አጥ ወጣቶች በስራ ፈጠራ የስራ እድል እንዲያገኙ ማድረግ የሚያስችል ፕሮግራም ነው።

የፌደራልና የክልል መንግስታት ስራ አጥ ዜጎች ተደራጅተውም ይሁን በግል በሚያቀረቡት የስራ ፈጠራ ፕሮጀክት መሰረት ገንዘብ በብድር የሚያገኙበት፣ መስሪያ (ማምረቻና አገልግሎት መስጫ) እና ምርት መሸጫ ቦታ የሚያገኙበት ስርአት ዘርግተው ተግባራዊ ሲያደርጉ መቆየታቸው ይታወቃል። ይህ የአነስተኛና ጥቃቅን ተቋማት የስራ እድል ፈጠራ በተለይ ከ1998 ዓ/ም በኋላ ባለው ጊዜ ውስጥ ተግባራዊ ሲደረግ የቆየ ነው።

በዚህ የስራ ፈጠራ ፕሮግራም፣ በሚሊየን የሚቆጠሩ ሰራ አጥ ዜጎች (ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማትና ከሞያና ቴክኒክ ኮሌጆች የተመረቁ ወጣቶችን ጨምሮ) የስራ እድል አግኝተዋል። በዚህ ፕሮግራም ወደስራ ከገቡት መሃከል  ሳይሳካላቸው ቀርቶ የተበተኑ መሆናቸው ባይካድም፣ ተሳክቶላቸው በሚሊየን የሚቆጠር ሃብት አፍርተው ወደመካከለኛ ኢንደስትሪና የአገልግሎት ተቋም የተሸጋገሩ መኖራቸው እውነት ነው።

ይህ በ1998 ዓ/ም የጀመረ በወጣቶች የልማትና ተጠቃሚነት ፓኬጅ መሰረት ተግባራዊ የተደረገ የስራ ዕድል ፈጠራ፣ ከላይ እንደተነሳው ተጠቃሽ ወጤት ማሰመዝገብ ቢችልም፣ በየጊዜው ትምህራተችውን እያጠናቀቁ የስራ ፈላጊውን ጎራ ከሚቀላቀሉ ወጣቶች ቁጥር አኳያ ሲታይ የሚፈለገውን ውጤት ማምጣት አልቻለም። በዚህ መሰረት መንግስት ከ2009 የበጀት ዓመት ጀምሮ አዲስ የስራ ፈጠራ ፕሮግራም ነድፋል።

ይህ ፕሮግራም የወጣቶች የልማት ተሳትፎና ተጠቃሚነት ፓኬጅን በመከለስ ነው የጀመረው። ከዚሀ ባሻገር፣ የስራ ፈጠራ ፕሮጀክት ቀርጸው ወይም በመንግስት ከተቀረጹት ፕሮጀከቶች መሃከል ውጤታማ እንሆንበታለን ብለው የመረጡትን ይዘው ለሚቀርቡ ስራ አጥ ወጣቶች በብድር የሚሰጥ የ10 ቢሊየን ብር ተዘዋዋሪ ባጀት ተመድቧል። በ2009 በጀት ዓመት አጋማሽ ላይ ተጨማሪ የፌደራል መንግስት ባጀት ሲጸድቅ ከ10 ቢሊየን ብር ተዘዋዋሪ በጀት ውስጥ 5 ቢሊየኑ ተመድቦ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ተጀምሯል።

እርግጥ ይህን ተዛዋወሪ ፈንድ በመጠቀም ወጣቶችን በስራ ላይ እንዲሰማሩ የማድረጉ ተግባር አፈጻጻም አርኪ አይደለም። በዚህ ረገድ የሚጠቀስ ስራ የተከናወነው በኦሮሚያ ክልል መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ።  አፈጻጸም ላይ የታየው ችግር ምንጭ፣ ፈንዱን ስራ ላይ የማዋሉ እንቅስቃሴ የወጣቶች ተሳትፎና ተጠቃሚነት ፓኬጁን ከማሻሻል፣ የፈንድ አጠቃቀም መመሪያ ከማውጣትና ሌሎች ተያያዥ የዝግጅት ስራዎችን ከማከናወን የጀመረ መሆኑ የፈጠረው መጓተት ሊሆን እንደሚችል ይገመታል። አሁን የዝግጅት ስራዎቹ በሙሉ በመጠናቀቃቸው ከቀጣይ አመት ጀምሮ በሁሉም ክልሎች የወጣቶችን የስራ አጥነት ችግር በጉልህ መቀነስ የሚያስችል ስራ ይከናወናል ተብሎ ይጠበቃል።

በጽሁፉ መግቢያ ላይ እንደተጠቀሰው እጅግ አብላጫ ቁጥር ያላቸው ስራ አጥ ወጣቶች ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት እንዲሁም ከሞያና የቴክኒክ ማሰልጠኛ ተቋማት በተለያየ ሞያ ሰልጥነው የወጡ ናቸው። በመሆኑም የስራ ፈጠራ አቅም አላቸው።

ይህ ከባለሙያነት የመነጨ የስራ ፈጠራ አቅም፣ መንግስት ከመደበው ስራ የማስጀመሪያ በብድር የሚገኝ ካፒታልና ሌሎች ድጋፎች ጋር ተዳምሮ በተለይ የተመራቂ ተማሪዎችን የስራ አጥነት ችግር በጉልህ ያቃልላል የሚል ተስፋ አለ። ባለሞያ ስራ አጥ በስራ ፈጠራ የስራ አድል እንዲያገኝ ማድረግ፣ ሞያም ስራም የሌለውን ስራ ላይ ከማሰማራት እንደሚቀል ልብ ይሏል።     

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy