Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የሰላም ቀንዲል

0 341

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የሰላም ቀንዲል

                                                  ዘአማን በላይ

ኢትዮጵያ ሀገረ ሰላም ናት—የሰላም ሀገር። ግጭቶች በማይለዩት የምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ውስጥ በሰላም ቀንዲልነቷ ትታወቃለች። ሰሞኑን የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ በአሜሪካ ተዘጋጅቶ በነበረውና በደህንነት ጉዳዩች ላይ በሚመክረው ጉባኤ ላይ ተገኝተው ከአሜሪካ ሴኔት የውጭ ግንኙነት ሊቀመንበር ሴናተር ቦብ ኮርከር ጋር ሲገናኙ ሴናተሩ የተናገሩትን በእማኝነት መጥቀስ የሚቻል ይመስለኛል።

ሴናተር ኮርነር “ኢትዮጵያ የሰላም መድረክ ናት፤ ስጋት ባንዣበበት የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ የምትገኝ ሰላማዊ ሀገር ናት” በማለት ተናግረዋል። ይህ የሴናተሩ አባባል ኢትዮጵያ የሰላም ቀንዲል ከመሆኗም በላይ፤ ከራሷ አልፋ ቀጣናውን ሰላምና መረጋጋት የሰፈነበት ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት የምታደርግ ሀገር መሆኗን የሚያረጋግጥ ነው።  

ርግጥ የኢትዮጵያ ሰላም ዝም ብሎ የተገኘ አይደለም—በመላው የኢትዮጵያ ውድ የህዝብ ልጆች ደም የተገኘ ነው። ይህ ሰላም በምንም መልኩ የሚቀለበስ አይደለም። የኢትዮጵያ ህዝቦች እስካሉ ድረስ ለዘመናት ይመኙት የነበረውን ሰላም ለየትኛውም ሃይል አሳልፈው ሊሰጡ አይችሉም። በደም የዋጁት መስዋዕትነት እንዲህ በቀላሉ የሚሸረሸር አይደለም።

ርግጥ የኢትዮጵያ ህዝቦች ሰላም ላለፉት 26 ዓመታት በርካታ ትሩፋቶችን አስገኝቶላቸዋል። ኢትዮጵያዊያን በሀገራቸው መገንባት በቻሉት አስተማማኝ ሰላም ልማታቸውን ፈጣን ማድረግ ችለዋል። ከልማቱም በየደረጃው ተጠቃሚ እየሆነ ነው። ይህ ተጠቃሚነታቸውም የኑሮ ደረጃቸውን እያሻሻለ ነው። ከዚህ በተጨማሪ የሀገራቸውን ዴሞክራሲ በማስፋትና በማጥለቅ ምቹ ምህዳርን ፈጥሮላቸዋል።

ሰላም፣ ልማትና ዴሞክራሲ የሚነጣጠሉ ጉዳዩች አይደሉም። አንዱ ከሌለ ስለ ሌላኛው ማውራት አይቻልም። ሁሉም የማይነጣጠሉ ናቸው። የኢትዮጵያ ህዝቦች ይህን እውነታ በመገንዘባቸው ሁሉንም መሳ ለመሳ እያስኬዱ ነው። በዚህም ሳቢያ ዛሬ በምስራቅ አፍሪካ ጠንካራ ሀገርና ህዝብ መሆን ችለዋል።

የምስራቅ አፍሪካ ቀጣና አውራ፣ የአፍሪካ ቃል አቀባይና መብት ተከራካሪም ሆነዋል። ቀደም ሲል በመግቢያዬ ላይ እንደገለፅኩትና አሜሪካዊው ሴናተር እንዳሉት ለወትሮው የግጭት በማይለየው የምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ሰላማዊ ደሴት ባለቤቶች ሆነዋል። ይህም ኢትዮጵያዊያን በመጀመሪያ በሀገራቸው አስተማማኝ ሰላም ፈጥረዋል፤ ለጥቆም የከባቢውንና የአፍሪካን ብሎም የዓለምን ሰላም ለማስጠበቅና የመፍትሔ ሃሳብ ለመስጠት የፀጥታው ምክር ቤት ተለዋጭ አባል እስከ መሆን የደረሱ ነው። ተሰሚነታቸውም የዲፕሎማሲው ማማ ላይ ደርሷል።

ዓለም አቀፉ ማህበረሰብም ይህን እውነታ በመገንዘብ እውቅና ሰጥቷቸዋል። የዶክተር ቴዎድሮስ ኣድሃኖም የዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት ዋና ዳሬክተር ሆነው መመረጣቸው የዚህ ሃቅ ማሳያ ይመስለኛል። ታዲያ ኢትዮጵያ የዚህ ሁሉ ስኬት ባለቤት መሆን የቻለችው ሀገር ውስጥ ባከናወነችው ጠንካራ የሰላም፣ የልማትና የዴሞክራሲ ስራዎች መሆኑን መገንዘብ ይገባል።   

ርግጥ ኢትዮጵያ የራሷን ሰላም ከማስከበር አልፋ የቀጣናውን ሀገራት ሰላም ለማስጠበቅ ከፍተኛ ጥረት እያደረገች ነው። ይህ ዓለም የሚያውቀው ነጭና ጥቁር እውነታ ነው። ከኤርትራ በስተቀር የቀጣናው ሀገራት፣ የአፍሪካ ህብረትና ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የሚመሰክሩት ነው። ለዚህ ደግሞ እጅግ በሰከነ አመራር የሚመራው መንግስት፣ የፀጥታ ሃይሎችና ህዝቡ የማይተካ ሚና ተጫውተዋል።

የቀጣናውን አመዛኙን የሰላም ማስጠበቅ ስራ እያከናወነ የሚገኘው መከላከያ ሰራዊታችን የሀገራችንን ሰላምና መረጋጋት እንዲሁም ህገ መንግስታዊ ስርዓታችን በአስተማማኝ እንዲጠብቅ ከተሰጠው ተልዕኮ ባሻገር፤ የጎረቤቶቻችንና የአካባቢያችንን ሰላምና መረጋጋት በማስጠበቅ ረገድ የበኩሉን ድርሻ እንዲጫወት ከተባበሩት መንግስታትና ከአፍሪካ ህብረት ተደጋጋሚ ጥሪዎች ይቀርቡለታል።

ይህን ተልዕኮውን በዓለምና በአህጉር አቀፍ የሰላም ማስከበር ጥበቃዎችን በንቃት በመሳተፍ እየተወጣ ነው። በዳርፉር፣ በአብዬና በሶማሊያ እያከናወነ ያለው የሰላም ማስጠበቅ ተልዕኮ በዋነኛነት ሊጠቀሱ የሚችሉ ናቸው።

በአሁኑ ወቅት የደቡብ ሱዳንን ሰላም ለማረጋገጥም ከኢጋድ በመሆን ሀገራችን እያከናወነች ያለችው ተግባርም ዓለም አቀፉን ማህበረሰብ ያኮራ ነው። ይህም ኢትዮጵያ የራሷን ሰላም አስተማማኝ አድርጋ ለምስራቅ አፍሪካን ቀጣና ሰላም መሆን ምን ያህል እየሰራች መሆኑን የሚያሳይ ይመስለኛል።

የምስራቅ አፍሪካን ቀውስ ለማርገብ የቀጣናው ሀገራት በሚያደርጉት ርብርብ እንደ ኤርትራ አይነቱ ፀብ ጫሪ ሀገር ጉዳዩን ይበልጥ በማወሳሰብ እንዲሁም ለአሸባሪዎችና ለፀረ-ሰላም ኃይሎች የገንዘብና የሎጀስቲክስ ድጋፍ በማድረግ ቀውሱን ለማቀጣጠል እየሰራ ይገኛል።

ያም ሆኖ በጎረቤት ሀገራት ለሚፈጠሩ ችግሮች ኢትዮጵያ በግንባር ቀደምትነት በመሰለፍ አኩሪ ተግባራትን እያከናወነች ነው። ይህ ቁርጠኛ አቋሟም የኤርትራን እኩይ ሴራ ውሃ ቸልሶበታል። እንዲያውም እንደ ኤርትራ ዓይነት መንግስታት ቀጣናውን ለማወክ የሚያደርጉትን እኩይ ተግባር አጋልጧል። በሌላ ዘውጉም የሀገራችንን ሰላም ወዳድነት ማረጋገጥ ችሏል።

ርግጥ እዚህ ላይ ሴናተር ኮርነር ኢትዮጵያን “ስጋት ባንዣበበት የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ የምትገኝ ሰላማዊ ሀገር ናት” በማለት የተናገሩትን እውነታ አፍታትቶ ማየት የሚገባ ይመስለኛል። አዎ! የምስራቅ አፍሪካ ቀጣና በአለም አቀፍ ደረጃ ውስብስብና ለረጅም ዘመናት የዘለቀ የፀጥታ ስጋት ያንዣበበት አካባቢ ነው። ይህን የፀጥታ ስጋት ለማስወገድም ሀገራቱ እንደ አቅማቸው የጋራ ርብርብ አድርገዋል።

ይሁንና እንቅስቃሴው በተደራጀ መልኩ ያልተከናወነ ስለነበር ፍሬ ማፍራት አልቻለም። ታዲያ የቀጣናው ሀገራት በአሁኑ ወቅት ችግሩን በመረዳታቸው በልማት፣ በፀጥታ፣ በንግድ ዙሪያ በጋራ እየሰሩ ይገኛሉ። የፀጥታ ችግሩን ለመፍታትም ኢትዮጵያን ጨምሮ አስር ሀገራት የጋራ የተጠንቀቅ ኃይል መስርተዋል—“የምስራቅ አፍሪካ ተጠባባቂ ኃይል ብርጌድ” የተሰኘ።

እንደ እውነቱ ከሆነ ይህን አካል በማቋቋምና ዋና ቢሮው አዲስ አበባ ላይ እንዲሆን በማድረግ ሀገራችን የተጫወተችውን ከፍተኛ ዲፕሎማሲያዊ ሚና በዚህ አጭር ፅሑፍ ለመግለፅ እጅግ አስቸጋሪ ነው። እንዲያው በጥቅሉ ‘የመሪነት ሚናዋን በመወጣት የሰላም ቀንዲልነቷን አስመስክራለች’ ቢባል ተገቢ ይመስለኛል።

ታዲያ ይህ ሃቅ ለሀገራችን ሰላም ወዳድነት ገፅታ የራሱን አስተዋፅኦ ማበርከቱ አይታበይም። ይህ ሰላም ወዳድነታችን ከምንም የመነጨ አይደለም—የጎረቤቶቻችን ሰላም የእኛም ጭምር መሆኑን ሀገራችን ስለምትገነዘብ እንጂ። እናም የሀገራችን ዘላቂ ሰላማዊነትና የሰላም ፍላጎት እስካለ ድረስ፤ የምስራቅ አፍሪካ፣ የአፍሪካ ብሎም የዓለም ሰላም አረጋጋጭነታችንና የሰላም መቅረዝ ቀንዲልነታችን መቀጠሉ አይቀሬ ይሆናል።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy