የስደት ለምን?
መልካሙ ተክሌ
ከጥቂት ዓመታት በፊት ነው፡፡ አንዲት በሕጋዊ መንገድ ወደ ተባበሩት ዓረብ ኢምሬት ለሥራ ፍለጋ የሄደች ጎረቤቴ ነበረች፡፡ ሁለት ዓመት ያህል እንደሰራች የተወሰነ ጊዜ ያህል እረፍት ሰጥተዋት ወደ ኢትዮጵያ መጣች፡፡ እንደመጣች ግን ቤተሰቦቿ ወደሚገኙባት ዝዋይ ከተማ አላመራችም፡፡ እረፍቷን ጨርሳ እስክትሄድ ድረስም ከአዲስ አበባ ውልፍት አላለችም፡፡ ከውጭ ሀገር የተላከ በማስመሰል ግን ዕቃ ለቤተሰቦቿ ልካለች፡፡ ይህን ያደረገችበትን ምክንያት ስታብራራም ቤተሰቦቿ እና ዘመዶቿ ከሷ ብዙ ስለሚጠብቁ ሀገር ቤት ብትሔድ እያንዳንዱን በስጦታ ዕቃ እና በዶላር ማንበሽበሽ ባለመቻሏ ነበር፡፡ እናም እረፍቷን እስክትጨርስ ቤት ተከራይታ ወደ ተባበሩት አረብ ኢምሬትስ ተመለሰች፡፡
እንደሷ አይነት መጠነኛ ጥሪት ቋጥረው በሀገር ላይ ለመሥራት ቢያልሙም የዘመዶቻቸውን ፍላጎት ባለማሟታቸው ለዳግም ስደት የሚዳረጉ ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን በርካታ ናቸው፡፡ ከነዚህ አብዛኞቹ ሕጋዊ የጉዞ እና የሥራ ፈቃድ ሰነዶች ሳይኖሯቸው በሕገ ወጥነት በሰው ሀገር የሚኖሩ እና በብዙ የስደተኝነት ቀውስ ውስጥ እያለፉ ያሉ ናቸው – ልክ ሰሞኑን በሳዑዲ አረቢያ ያሉ ኢትዮጵያውያን እና የውጪ ሀገር ሰዎች እንደገጠማቸው፡፡
ሳዑዲ አረቢያ ሕገወጥ ናቸው ያለቻቸውን የውጪ ሀገር ዜጎች “ወደ የመጣችሁበት ሂዱልኝ” ማለት የጀመረችው ዛሬ አይደለም፡፡ ከአራት ዓመት በፊት በተደረገ ተመሳሳይ ዘመቻ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የሕንድ፣ የፊሊፒንስ፣ የኢትዮጵያ እና ሌሎች የውጪ ዜጎች ከሀገሪቱ ተባረዋል፡፡ በወቅቱ የውጭ ሀገር ስደተኞችን ሀገሪቱን የመልቀቂያ ሰባት ወራት የእፎይታ ጊዜም ሰጥታ ነበር፡፡ በወቅቱም 140 ሺህ ዜጎቻችን ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰዋል፡፡
በአሁኑ ግን መጀመሪያ ከሰጠችው ጋር አተጨማሪ ሁለት ወራት ታክሎ አምስት ወራት ሰጥታለች፡፡ ኢትዮጵያን በመሰሉ ሀገራት የዲፕሎማሲ ጫና ለተጨማሪ ሁለት ወር አራዘመችው እንጂ የተሰጠው ጊዜ ሶስት ወር ብቻ ነበር ፡፡ከዚሁ ጊዜም አንድ ወሩ አብቅቷል፡፡ ያም ሆኖ በሳዑዲ ይኖሩ የነበሩ አምስት ሚሊየን የውጪ ሀገራት ዜጎች “ወደ የመጣችሁበት ካልተመለሳችሁ አስሬና ንብረታችሁን ወርሼ በግዳጅ እመልሳችኋለሁ” ብላለች፡፡ ለዚህ ደግም ዋነኛ ምክንያቶቿ የወንጀል መበራከት እና የራሷ ዜጎች የሥራ እድል መጥበብ እንደሆነ ይነገራል፡፡
ከዓለም ህዝብ ሦስት በመቶው ስደተኛ መሆኑ በሚነገርባት አለማችን የስደተኞች ቁጥር እ.አ.አ በ1990 ከነበረበት 155 ሚሊየን ከ15 ዓመት በኋላ ወደ 191 ሚሊየን አድጓል፡፡ የዓረቡ ዓለም በርካታ ስደተኞችን ከሚያስተናግዱ አካባቢዎች አንዱ ነው፡፡ በተመሳሳይ ጊዜ ማለትም በ15 ዓመታት ውስጥ በዚያ የሚገኙ ስደተኞች ከ13 ሚሊየን ወደ 20 ሚሊየን ደርሰዋል፡፡ ከዚህ ውስጥ ትልቁን ቁጥር ያስተናገደችው ደግሞ ሳዑዲ ዓረቢያ ነች፡፡ ለዚህም ይመስላል ሰሞኑን ባበቃው እና ዳግም ለአንድ ወር በተራዘመው የእፎይታ ጊዜ ተጠቅመው ካልተመለሱ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሕገወጥ ያለቻቸውን የውጪ ሀገር ዜጎች አባርራለሁ አስራለሁ ያለችው፡፡
400 ሺህ ያህል በህገወጥ መልኩ የሚኖሩ አትዮጵያውያን ይገኙባታል የምትባለው ሳዑዲ አረቢያ የዓለማችን ዜጎች በብዛት ከሚሰደዱባቸው አሜሪካ፣ ሩስያ፣ ጀርመን፣ ካናዳ እና እንግሊዝ ተርታ ተሰልፋለች፡፡
ሀገሪቱ ለስደተኞች አያያዝ የከፋች ብትሆን እንኳን ኢትዮጵያውያን ወጣቶች በተለይም ሴቶች አሁንም ቢሆን ለመሰደድ ይመርጧታል፡፡ ምርጫቸው ግን ከድህነት ለመላቀቅ እንጂ እንደምኞታቸው ለነሱ አጓጊ ሆና ስለተገኘች አይደለም፡፡ ስደታቸው በበቂ መረጃ ላይ የተመሠረተም አይመስልም፡፡ በሀገሪቱ እንኳን በሕገ ወጥነት የሄዱ ቀርቶ ሕጋዊ ሰነድ የላቸውም በመሆኑም የወሲብ ጥቃትና የአካል ጉዳት ይደርስባቸዋል፡፡ ለዚህም ነው “በአሰሪዋ ከምናምነኛ ፎቅ ተወርውራ ሞተች፣ አሰሪዋ አስገድዶ ደፍሯት ነፍሰጡር ስትሆን ተባረረች፣ ሙቅ ውሃ ተደፋባት፣ በአልሞት ባይ ተጋዳይነት አሰሪዋን ገድላ በስቅላት ተቀጣች…” ሲባል የሚሰማው፡፡ ድህነትን ለማምለጥ፣ ለቤተሰብ ለማሳለፍ ተብሎም እንዲህ በቀላሉ ሕይወት አልፎ እንደወጡ መቅረትም አለ፡፡
በአስከፊ ድህነት ውስጥ ያሉትም ሆኑ የተሻለ ኑሮ ፍለጋ ከሚሰደዱት ዜጎቻችን ውስጥ የሚሳካላቸው ጥቂቶቹ እንደሆኑ ጉዳዩን ያጠኑ ተቋማትና ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡ ወደ ሳዑዲ አረቢያ ብቻ ሳይሆን ወደ አውሮፓ ለመሻገር የሚሰደዱትንም መጥቀስ ይቻላል፡፡ የቦታ ለውጥ እና የአደጋ አይነት ልዩነት እንጂ የስደት ኑሮውን አስከፊነት ወደ አስደሳችነት የሚቀይር አንዳችም ነገር የለም፡፡ እንደውም በጣሊያኗ ላምፓዱሳ ይህን ያህል ስደተኞች ሰጠሙ፣ የእገሌ አገር መርከቦኞች እየሰጠመች ያለች ሕገወጥ ጀልባ ላይ ከተሳፈሩ ስደተኞች ማትረፍ የቻሉት ጥቂቱን ብቻ ነው ሲባል በተደጋጋሚ ይደመጣል፡፡ እንግዲህ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ነው በርካታ ዜጎቻችን እና የሌላ ሀገር ሰዎች ተሰድጄ ያልፍልኛል ብለው ካሰቡበት ሳይደርሱ እንደወጡ የቀሩት፡፡
ወላጆች ከብትና ሌላም ንብረት ሸጠው ገንዘቡን ለደላላ በመክፈል ልጆቻቸውን ይሰዳሉ፡፡ አንዳንዴም መኪናውን፣ ቤቱን ሸጦ የተሻለ ለማግኘት በሚል የሚሰደድም አለ፡፡ እዚህ ላይ ምን ያህሉ ስደተኞች ተሳካላቸው ብሎ መጠየቅ ብልህነት ነው፡፡ በሀገር ውስጥ ሠርቶ መለወጥን ቢያስቡ ደግሞ የላቀ ብልህነት ይሆናል፡፡ ለሥራ ምቹ ሁኔታ እስካለ ድረስ በሀገር ውስጥ ሠርቶ መለወጥ ይሻላል፡፡ የስደትን ኑሮ ያልቀመሱት ይህ የተሳሳተ ነው ሊሉ ይችላሉ፡፡ ያዩት ግን እንደዚያ አይሉም፡፡
የስደትን አስከፊነት ከቀመሱት ወጣቶች አንዷ ሶፊያ መኩሪያ ናት፡፡ ሶፊያ የዛሬ አራት ዓመት ለኢሪን በሰጠችው አስተያየት እርም ስደት አልመለስም ብላለች፡፡ ምክንያቷን ተጠይቃም “እዚሁ ነው መስራት የምፈልገው፡፡ በሳዑዲ ማጎርያ ሲያስገቡን እንደ ሰው እንኳን አልቆጠሩንም” ነው ያለችው፡፡ለዚህ መፍትሔው ሕጋዊ ሆኖ መሄድ ሊመስል ይችላል፡፡ ይሁንና ሕጋዊ ሆነው ሄደውም መከራና እንግልት የሚደርስባቸው የትዬለሌ ናቸው፡፡
ሀብታቸውን ተቀምተው፣ ሕገወጥ ናችሁ ተብለው ከታሰሩ አሊያም ከተባረሩ የውጭ ሀገር ዜጎች መካከል በተደጋጋሚ እንደተጠቀሰው በ100 ሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንም ይገኙበታል፡፡
ለኢንድራ ጋንዲ ኦፕን ዩኒቨርሲቲ በሜሮን መንገሻ በቀረበ አንድ የማስተርስ ዲግሪ ማሟያ ጽሑፍ እና በሌሎችም ጥናቶች እንደተመለከተው 97 በመቶ ዜጎቻችን ወደ ሳዑዲ የተሰደዱት ሕጋዊ የጉዞ ሰነድ ሳይኖራቸው እንደሆነ አመላክቷል፡፡ በብዛት መመለሳቸውም የባለድርሻ አካላትን ትኩረት ስለሚስብ በፖሊሲ የታገዘ ማቋቋሚያ ከመንግሥት እንደሚጠበቅ የመፍትሔ አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡ ከዚህም ሌላ መንግሥት ለዜጎቹ በገቢ አመንጪ ሥራዎች ላይ የቴክኒክ ድጋፍ ማድረግ እንደሚጠበቅበት እና ግማሽ ያህል ከስደት ተመላሾች ሴቶች በመሆናቸው የሴቶችን አቅም መገንባት እንዳለበት ከአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ናሙና በመውሰድ የተደረገው ጥናት ያመለክታል፡፡
ዜጎች ዳግም ወደ ስደት አይናቸውን እንዳያዞሩ የገንዘብ ብቻ ሳይሆን የማኅበራዊ እና የሥነልቦና ድጋፎችን ማድረግ ግድ ይላል፡፡ ይህ ሲሆን ዜጎቻችን የስደት ኑሮ ለምኔ ማለት ይጀምራሉ፤ በሀገር ላይ ሠርተው መክበርና መከበርንም ይላመዱታል፡፡