Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የባለስልጣናቱ በህግ ጥላ ስር መዋል ምንን ያሳያል?

0 285

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የባለስልጣናቱ በህግ ጥላ ስር መዋል ምንን ያሳያል?

                                                        ዘአማን በላይ

ከመሰንበቻው የኢፌዴሪ መንግስት በፌዴራል ደረጃ 37 ግለሰቦችን በአንድ ነጥብ 15 ቢሊዮን ብር የሙስና ወንጀል በመጠርጠር በህግ ጥላ ስር እንዲውሉ አድርጓል። ከእነዚህ ተጠርጣሪዎች ውስጥ እጅግ የሚበዙት ከፍተኛ ባለስልጣናት ሲሆኑ፤ የሀገር ውስጥና የውጭ ባለሃብቶች እንዲሁም ደላሎች ይገኙባቸዋል። ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር የዋሉት ግለሰቦች ከኢትዮጵያና ከአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን እንዲሁም ከስኳር ኮርፖሬሽንና ከገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር ብሎም ከሌሎች አካላት ናቸው።

የኢፌዴሪ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዩች ፅህፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር ዶክተር ነገሪ ሌንጮ የግለሰቦቹን በህግ ጥላ ስር መዋል አስመልክተው ለጋዜጠኞች እንደገለፁት፤ መንግስት ጥልቅ ተሃድሶውን ሲጀምር ለህዝቡ በገባው ቃል መሰረት ከተሰጣቸው ኃላፊነት ውጪ ለልማት መዋል የነበረበትን የህዝብና የመንግስት ሃብትን በማጉደል የሙስና ወንጀል የተጠረጠሩ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ላይ ክትትል ተደርጎ መረጃ የተገኘባቸው በህግ እንዲጠየቁ ተደርጓል። ኃላፊ ሚኒስትሩ መረጃ የተገኘባቸው የመንግስት የስራ ኃላፊዎችና ባለሃብቶችን በቁጥጥር ስር የማዋሉ ተግባር ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑንም አስታውቀዋል።

ታዲያ እዚህ ላይ ከሚኒስትሩ አባባል በመነሳት ‘የባለስልጣናቱ በህግ ጥላ ስር መዋል ምንን ያሳያል?’ የሚል ጥያቄ ማንሳት ተገቢ ይመስለኛል። እንደሚታወቀው መንግስት ጥልቅ ተሃድሶውን በሚያካሂድበት ወቅት በሀገሪቱ ህዝብን ያስመረሩ ጉዳዩችንና ዘርፎችን በማስጠናት ችግሩን ለመፍታት ቃል ገብቶ እንደነበር እናስታውሳለን።

በተለይም ከመልካም አስተዳደርና ከኪራይ ሰብሳቢነት ጋር በተያያዘ በመረጃና በማስረጃ ላይ ተመስርቶ የህዝብንና የመንግስትን ሃብት የዘረፉ ከፍተኛ ባለስልጣናቱ ላይ ርምጃ እንደሚወስድ ደጋግሞ መግለፁ ይታወቃል። ሰሞኑን በ37ቱ የመንግስት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎችና ግለሰቦች ላይ የተወሰደው ርምጃ የጥልቅ ተሃድሶው ውጤት ነው ማለት ይቻላል። ይህ የመንግስት ተግባር ወደፊትም ቢሆን መረጃና ማስረጃ እስከቀረበለት ድረስ በህዝብ ሃብት ላይ የሚቀልዱና የተሰጣቸውን ህዝባዊ ሃላፊነት ወደ ጎን በማለት በኪራይ ሰብሳቢነትና በሙስና የተዘፈቁ አመራሮቹ ላይ ርምጃ የመውሰድ ቁርጠኝነት አቋም ያለው መሆኑን የሚያሳይ ነው።

እንደሚታወቀው መንግስት ራሱን በጥልቅ ተሃድሶ ለመፈተሽና ችግሮችን ለማጥራት እያደረገ ያለው ጥረት ቀጣይነት ያለው ነው። ጥልቅ ተሃድሶ በባህሪው የአንድ ጀምበር ስራ አይደለም። የጊዜ ዑደትን ይጠይቃል። የሚፈለገው ደረጃ ላይ ለመድረስ ጊዜን የሙጥኝ የሚል ተግባር ነው።

ጥልቅ ተሃድሶን በሂደት እውን ለማድረግ በቅድሚያ በማህበረሰቡ ውስጥ የአስተሳሰብ ለውጥን ማምጣት ያስፈልጋል። ችግሮችና ጠቀሜታዎች በሚባሉ ሀገራዊ ጉዳዩች ላይ በሂደት መናበብን ይጠይቃል። መንግስት ለብቻው፣ ህብረተሰቡም ለብቻው ሊታደሱ አይችሉም። የሁሉንም የሀገሪቱን ፖለቲካል- ኢኮኖሚ ተዋናዮች መግባባትንና የጋራ ቁርጠኝነትን የሚጠይቅ ከጊዜ ጋር የተሳሰረ ተግባር ነው—ጥልቅ ተሃድሶ። ለዚህም ይመስለኛል— የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዩች ፅህፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር ዶክተር ነገሪ ሌንጮ “መረጃ የተገኘባቸው የመንግስት የስራ ኃላፊዎችና ባለሃብቶችን በቁጥጥር ስር የማዋሉ ተግባር ተጠናክሮ ይቀጥላል” በማለት የገለፁት።

ርግጥ እዚህ ላይ የህዝብን ሃብት በመዘበሩ አካላት ላይ እየተወሰደ ያለው ርምጃ ቀጣይነት ያለውና ተጠያቂነትን ከማስፈን አኳያም በመንግስት በኩል ቁርጠኝነት መኖሩን መገንዘብ የሚገባ ይመስለኛል። መንግስት ጥልቅ ተሃድሶው ሲጀመር በመዋቅሩ ውስጥ የነበሩትንና ያሉትን የኪራይ ሰብሳቢነትንና የሙሰኝነትን ተግባሮችን ለመቅረፍ ያደረጋቸው ጥረቶችና የወሰዳቸው ርምጃዎች በርካታ ናቸው። በዚህ አጭር ፅሑፍ ውስጥ ተዘርዝረው የሚያልቁ አይደሉም።

ያም ሆኖ የቅርብ ጊዜውን ለማስታወስ ያህል፤ ሰሞኑን በደቡብ ብሔሮች፣ ብሐረሰቦችና ህዝቦች ክልል በፍትህ ዘርፍ ዙሪያ በተካሄደ የጥልቅ ተሃድሶ ግምገማ 26 የዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንቶች፣ በርካታ ዳኞችና ኦፊሰሮች ከስራ እንዲሰናበቱ መደረጉንና  የሌሎችም በርካታ ዳኞች ጉዳይም በመታየት ላይ መሆኑን በጠቋሚ አስረጅነት ማንሳት የሚቻል ይመስለኛል። ይህም ጥልቅ ተሃድሶው በፌዴራል ብቻ ሳይሆን በክልሎች ውስጥም በቁርጠኝነት እየተሰራበት እንደሆነ የሚያረጋግጥ ይመስለኛል። እናም የ37ቱ ተጠርጣሪ ባለስልጣናትና ግለሰቦች ምዝበራ ጉዳይ ገዝፎ ስለወጣ እንጂ፣ ሂደታዊ ተግባሩ በየቦታውና በየዘርፉ እየተከናወነ መሆኑን መገንዘብ የሚገባ ይመስለኛል—ምንም እንኳን ኪራይ ሰብሳቢነትን አሁን ባለበት ደረጃ መድፈቅ ባይቻልም።

ማንኛውም የዚህ ፅሑፍ አንባቢ እንደሚገነዘበው፤ በየትኛውም ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ውስጥ የኪራይ ሰብሳቢነት አስተሳሰብና ተግባር ነባራዊ ክስተት ነው። አዲስ አይደለም። እንደ ሌሎቹ ልማታዊ መንግስታት ኢትዮጵያም ውስጥ የኪራይ ሰብሳቢነት አስተሳሰብና ተግባር ከባድ ፈተና መሆኑ አይቀርም። የሀገራችን ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መንግስት የህዝቡን ተጠቃሚነት በየደረጃው ለማረጋገጥ ልማትን በስፋት እያከናወነ ነው። ስራውን የሚመሩት የመንግስት አስፈፃሚ አካላት በሚሊዮንና በቢሊዮን የሚቆጠሩ የህዝብ ገንዘብን ያንቀሳቅሳሉ። በዚህም ሳቢያ የኪራይ ሰብሳቢነት አስተሳሰብና ተግባር ሰለባ ሊሆኑ የመቻል እድላቸው ከፍተኛ ነው።

ከሁሉም በላይ ግን ለኪራይ ሰብሳቢነት አስተሳሰብና ተግባር መገንገን እንዲሁም ጥልቅ ተሃድሶው ጊዜ እንዲጠይቅ ካደረጉት ጉዳዩች ውስጥ አንዱ ሀገራችንና ህዝቦቿ ባለፉት ስርዓቶች ሲንከባለሉ የመጡ ፀረ-ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰቦች ይመስሉኛል። ምንም እንኳን መንግስት በየጊዜው በወሰዳቸው በርካታ ርምጃዎች የኪራይ ሰብሳቢነት አስተሳሰቦች ደረጃ በደረጃ ለውጥ እየታየባቸው ቢሆንም ቅሉ፤ እንደ “ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል፣ ብላና አብላኝ” የመሳሰሉና ካለፉት ስርዓቶች ይዘናቸው የመጣናቸው ፀረ-ዴሞክራሲያዊ ቅሪት እሳቤዎችን ሙሉ ለሙሉ መቅረፍ አይቻልም።

እነዚህ አስተሳሰቦች በጊዜ ሂደት የሚቀየሩ እንጂ በአንድ ጀምበር የሚጠፉ ስላልሆኑም በህብረተሰባችን ውስጥ መንፀባረቃቸውና ገቢራዊ መሆናቸው ባህሪያዊ ነው። እናም በመንግስት መዋቅሮች ውስጥ የአስፈፃሚነት ስራን የሚከውኑ ግለሰቦችም ከዚሁ ህብረተሰብ አብራክ የተገኙ በመሆናቸው ከዚህ አስተሳሰብ ውጪ ሊሆኑ አይችሉም።

ታዲያ እዚህ ላይ የመንግስት ስራ ፈፃሚዎቹ በዚህ ነባራዊ ሁኔታ ውስጥ ስላሉ ምንም አይደረጉም እያልኩ አለመሆኑ ግንዛቤ ይያዝልኝ። ምክንያቱም የዚህ ሀገር ልማት ይበልጥ እየጎለበተ እንዲሄድ በተቻለ መጠን ስህተቶቹ ጥቂትና መሰረታዊ እንዳይሆኑ መሰራት ስለሚኖርበት ነው። ለዚህም ነው— መንግስት የሚወስዳቸውን ርምጃዎች በቁርጠኛ የጥልቅ ተሃድሶ የተጠያቂት መንፈስ እየከወነ ያለው። ለዚህም ነው—ስህተቶች መፈፀማቸው ስለማይቀር ችግሩን ለመፍታት በሁሉም ዘርፎች ፈጥኖ በማስተካከል ላይ የሚገኘው። ለዚህም ነው—መንግስት ሰሞኑን በህግ ጥላ ስር የዋሉትን 37 ከፍተኛ ባለስልጣናቱን፣ የሀገር ውስጥና የውጭ ባላሃብቶችን እንዲሁም ደላላዎችን ብሎም በሁሉም ክልሎች ውስጥ መዝባሪዎችን በቁርጠኝነት ተጠያቂ እንዲሆኑ በማድረግ ላይ የሚገኘው።

ታዲያ መንግስት በጥልቅ ተሃድሶው አማካኝነት በተጠያቂነት መንፈስ እያከናውናቸው ያሉት ኪራይ ሰብሳቢነትንና ሙስናን የመዋጋት ተግባሮች በህዝቡ ለደገፉ ይገባል። ከህዝብ ዓይን የሚሰወር ምንም ዓይነት ተግባር ባለመኖሩ፤ ወደፊት መዝባሪዎችን በህግ እንዲጠየቁ ለሚደረገው ጥረት ህዝቡ ጥቆማ በመስጠት የዜግነት ግዴታውን መወጣት ይኖርበታል።    

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy