Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የታላቁ ህዳሴ ግድባችን ፋይዳ ሲፈተሽ

0 473

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የታላቁ ህዳሴ ግድባችን ፋይዳ ሲፈተሽ

 

ስሜነህ

 

ቻይና የዓለም አገራት ከሚጠቀሙት የውሀ ኃይል 26 በመቶ፤ ብራዚል ስምንት ነጥብ ስድስት በመቶ ድርሻን ይወስዳሉ:: የተባበሩት የአሜሪካ ገዛቶች (USA) ሰባት ነጥብ ስምንት የውሀ ኃይል የተጠቃሚነት ድርሻ አላቸው:: እንዲሁም፣ ካናዳ ሰባት ነጥብ ስድስት በመቶ ያህሉን ድርሻ እንደምትይዝ የ21ኛው ክፍለ ዘመን የታዳሽ ኃይል ፖሊሲ መረብ የተባለ ድርጅት በ2014 የታዳሽ ኃይል ዓለማቀፍ አመላካች ሪፖርት (Renewable Energy Policy Network for 21st Century) ሲል ባወጣው ጽሁፍ አስነብቧል::

 

የዓለም የኃይል ም/ቤት (World Energy Council) በበኩሉ “የዓለም የ2013 የኃይል ምንጮች ጥናት” በሚል ርዕስ ይፋ ባደረገው መረጃ ከውሃ የሚገኘው የኃይል አቅርቦት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል:: ለአብነት ይሆን ዘንድም ም/ቤት  እ.ኤ.አ ከ1993 እስከ 2011 ዓ.ም የታየውን እድገት አስፍሯል:: በጥናቱ መሠረት በተጠቀሱት ዓመታት ከውሃ የሚገኝ የኤሌክትሪክ ኃይል ከነበረበት 609ሺ 264 ወደ 946ሺ 182 ሜጋ ዋት አድጓል:: አጠቃላይ የሃይል አቅርቦቱም ያለውን ፍላጎት የሚያሟላ ባለመሆኑ አምራች ፋብሪካዎች ትልቅ ችግር ውስጥ እንዳሉ በድረ-ገፁ ሰፍሯል።

 

ዳዊት ሀይሉ ማዘንጊያ ስዊድን ለሚገኘው ሀኘሳላ ዩኒቨርስቲ የሁለተኛ ዲግሪ ማሟያ “የኢትዮጵያ የኃይል ስርዓት᎓ አቅም፣ አጋጣሚዎችና ዘላቂ አጠቃቀም” በሚል የጥናት ርእስ ባቀረቡት ጽሁፍ ስንመለከት ኢትዮጵያ ነዳጅ ዘይት ከውጭ የምታስገባ በመሆኗ የኃይል አቅርቦቷ ላይ ጫና ፈጥሮበታል፡፡ ይህ ብቻ አይደለም፤ በጥናቱ እንደተመለከተው በምጣኔ ኃብት ዕድገቷ በኩልም ግዙፍ ገንዘብ እየወሰደባት ይገኛል። አገሪቱ ወደ ውጭ ከምትልካቸው ምርቶች ከሚገኘው ገቢ ከ50 በመቶ በላይ የሚሆነውን ነዳጅ ዘይት ለመግዛት የምታውል መሆኑ በምጣኔ ኃብቱ ላይ ትልቅ ጫና እንደሚኖረው ይሄው ዳዊት ሀይሉ ጥናት ይገልፃል፡፡ እናም ይላል ጥናቱ፤ የሀይል (Waterpower) አቅርቦቱን ማሻሻልና ከውሀ በሚገኝ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ልማት ላይ ማተኮሯ ለአጠቃላይ ምጣኔ ሀብቷ እድገት ወሳኝ መሆኑ አጠያያቂ አይደለም ብቻ ሳይሆን የህልውናዋ ጉዳይ ነው፡፡

 

ኢትዮጵያ ሁሉንም ዓይነት የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት የሚያስችላት ምቹ መልከአምድርና የተፈጥሮ ሀብት/ፀጋ ያላት ሀገር መሆኗ ሲታሰብ  የወደፊት ተስፋዋን ቁልጭ አድርጎ የሚያመላክት ነው፡፡ በእርግጥ የመብራት መቆራረጥ ብቻ ሳይሆን ከነጭራሹም መብራት የሌላቸው አካባቢዎቻችንን ስናስብ፤ ግድቡ በአጠቃላይ ምጣኔ ኃብታችን ላይ የሚኖረውን አሉታዊ ተጽእኖ ለመገመት አይከብድም፡፡ ፋብሪካ ከፍቶ መብራት “ይመጣ/ይቀር ይሆን?” እያለ ቀኑን ሙሉ ስጋት ውስጥ ወድቆ የሚውል ባለሀብት ቁጥሩ ብዙ ነው፡፡ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦታችን ደካማና ጥራቱም አስተማማኝ ባለመሆኑ የህዝቡ የአኗኗር ዘይቤ ላይም ያለው ለውጥ እዚህ ግባ የማይባል ነው፤ እስካሁን፡፡

አንዳንዱ ፋብሪካ ሞቆ እንኳ ሳይጨርስ፤ አንዳንዱም ጥሬ ዕቃውን እንደጐረሰ መብራቱ ይጠፋበታል፤ ድርግም:: በዚህ አይነቱ አሰራር ደግሞ ምርታማ፤ በአለም አቀፍ ደረጃም  ተፎካካሪ መሆን አይቻልም:: 300፣ 200 እና 100 የሰው ሀይል የቀጠሩ ኢንዱስትሪዎቻችን በመብራት ብልጭ/ድርግም ምክንያት በግማሽ እየንቀነሱ ለመሄድ የተገደዱባቸው አጋጣሚዎች መኖራቸውም ይታወቃል። (ይህን ስንል መንግስት ችግሩን በመገንዘብ ለተቋማቱ ያደረገላቸውን ልዩ ልዩ ድጎማዎች ሳንረሳ ነው።)

 

ለምጣኔ ሀብቱ ፈጣን እድገት መሠረት የሆነውን የመሰረተ ልማት አቅርት በመጠንና በጥራት ማሟላት የሚገባ መሆኑ እሙን ነው:: የሀይል አቅርቦቱ የምጣኔ ሀብት ዕድገት ላይም ፈተና በመሆኑ ችግሩን ከመሰረቱ ማስወገድ ይገባል:: በመሆኑም የሀይል ማመንጫ ግድቦችን በፍጥነት እየገነቡ ለምጣኔ ሀብቱ ዕድገት አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱ ማድረግ ለነገ የማይባል መሰረታዊ ጉዳይ ይሆናል ማለት ነው።

የ2014 የተዳሽ ኃይል ዓለማቀፍ አመላካች ሪፖርት እንደሚያሳየው ደግሞ ከውሃ የሚገኝ

ኤሌክትሪክ ኃይል ተፈላጊነቱ እየጨመረ በመምጣቱ በዓለም ሁሉም አካባቢዎች በየጊዜው እየተገነቡ ያሉ የኃይል ማመንጫ ግድቦች እየተበራከቱ መምጣቸውን ያረጋግጣል:: በተለይ ለአፍሪካ የወደፊት ዕድገት ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ስለታመነበት በአህጉሪቱ የተለያዩ ሃገራት ግንባታዎች እየተከናወኑ እንደሆነም አመላክቷል:: ከእነዚህ ውስጥም ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ አንድ ማሳያ ተጠቅሷል:: ግድቡ ወደ ከባቢ የሚለቀው ቆሻሻም ሆነ የተቃጠለ አየር (ካርቦንዳይኦክሳይድ) ስለሌለው ከሌሎች አገሮች ይበልጥ ተመራጭ እያደረገው እንደሚገኝ የገለፀ ሲሆን፤ ከዚህ ባሻገር ከውሃ የሚገኝ የኤሌክትሪክ ኃይል ከሌሎች በተሻለ ደረጃ በርካሽ ዋጋ ሊገኝ የሚችል እና አስተማማኝ እንዲሁም ውጤታማ የኃይል ምንጭ በመሆኑ ተመራጭ እየሆነ መምጣቱን በሪፖርቱ አመልክቷል:: የኢትዮጵያ መንግስትም ጥናቱ እያደረገ ያለው ይህንኑ ነሲሆን፤ ለአረንጓዴው ምጣኔ ኃብት እድገት እና ለአካባቢ ተስማሚ የሆነ የኃይል አጠቃቀም ይከተላል:: ለዚህም ማሳያ ሊሆኑ የሚችሉት ተገንብተው ያለቁ እና በግንባታ ላይ የሚገኙ የውኃ ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድቦች አሉን::  

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ዋና ጠላቷ ድህነት ነው:: ከዚህ ድህነት ለመውጣት ደግሞ ወንዞቿን መጠቀም ግድ እንደሚላት ግንዛቤ ከተያዘ ሰንበትበት ብሏል:: ባለፉት 10 ዓመታት ብቻ

ኮይሻን ጨምሮ ወደ 7 ግድቦችን በመገንባት ላይ መሆኗም ከድህነት ለመውጣት እያደረገች ላለችው ትግል አንዱ ማሳያ ነው:: ከስድስት ሺህ ሜጋ ዋት በላይ የሚያመነጨው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ደግሞ የህዝቡን ኑሮ በማሻሻል አገሪቱን መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገራት ተርታ ያሰልፋል ተብሎ ትልቅ ተስፋ የተጣለበት እንደሆነም ብዙዎች እየመሰከሩለት ነው::

ግብጻውያን ድህነት አመጣሽ ከሆኑ በርካታ ችግሮቻቸው ማምለጥ የቻሉት የአስዋንን ግድብ ገንብተው በመስኖ ማምረት ስለቻሉ ነው:: በመሆኑም ኢትዮጵያውያንም የህዳሴውን ግድብ ነሲያጠናቅቁ በተመሳሳይ ከችግር እና ከድህነት የሚወጡበት ይሆናል ማለት ነው:: ግብፃውያን የአስዋን ግድብ በፈጠረላቸው እድል አማካኝነት ዓለማቀፍ ጥራት ያለው ጥጥ ማምረት ጀምረዋል:: ከተሞቻቸውን እና የገጠር መንደሮቻቸውን የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ አድርገዋል፤ የንፁህ መጠጥ ውሃ እንዲያገኙ አስችሏቸዋል:: በአጭር ጊዜ ውስጥም መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገራት ተርታ መሰለፍ ችለዋል፤ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ሲጠናቀቅም ለኢትዮጵያ የምጣኔ ኃብት እድገት ትርጉም ያለው ለውጥ ይዞ እንደሚመጣ የሚያሣይ  ነው።  

ይህ ብቻም አይደለም፤ ግድቡ ሲጠናቀቅ ሃገራችን ኢንዱስትሪዎቿን ለማስፋፋት ትችል ዘንድ ትልቅ አቅም እንደሚፈጥርላት ይጠበቃል። አሜሪካ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት 60ሺ አውሮፕላኖችን ለመስራት የገጠማትን የኃይል አቅርቦት ችግር የተወጣችው ወንዝ በመገደብ ከውኃ የኤሌክትሪክ ኃይል በማመንጨት ነው:: እናም ኢትዮጵያም ወደ ኢንዱስትሪው ለመሸጋገር በቂ የኃይል አቅርቦት ያስፈልጋታል፤ ለዚህም የህዳሴውን ግድብ እየገነባች መሆኗ ትልቅ ትርጉም ይኖረዋል:: የህዳሴው ግድብ ኢንዱስትሪዎች ያለምንም የኃይል መቆራረጥ ስራቸውን ማከናወን እንዲችሉ በማድረግ በኩል ትልቅ ተስፋ ይዞ እየመጣ ነው። ከዚህ ባለፈ የህዳሴው ግድብ ሲጠናቀቅ የሠለጠነ የሰው ኃይል በማፍራት በኩልም የሚጫወተው ሚና ቀላል አይደለም።

የመብራት ኃይል ካለ ገጠሮች ድረስ ወርዶ የገጠር ልጆችን የኮምፒዩተር ተጠቃሚ ማድረግ ይቻላል:: ይህ ማለት ደግሞ በየፋብሪካው በተለያዩ ቦታዎች የሚፈለገውን የሠለጠነ እና ክሂሎት ያለው ሠራተኛ ማፍራት ያስችላል ማለት ነው። ለአብነት አሁን ተገንብተው የተጠናቀቁትና በግንባታ ላይ የሚገኙት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ከ100ሺህ በላይ ሠራተኞች ይፈልጋሉ።  

ስለዚህ በሁሉም ቦታ መብራት ቢኖር እና የአገሪቱ ወጣቶች የቴክኖሎጂ ተጠቃሚ ቢሆኑ በቀላሉ የሠለጠነ ባለሙያ ማግኘት ይቻላል፤ ለዚህ ደግሞ ግድቡ  ትልቅ ሚና ይኖረዋል ማለት ነው። ግድቡ ተጠናቆ ኃይል ማመንጨት ሲጀምር በገጠር በሚገኘው ማህበረሠብ ዘንድ ትልቅ የአኗኗር ለውጥ ይፈጠራል:: ምግብ ለማብሠል ከአመድ እና ጭስ ጋር ሲታገሉ የሚውሉ እናቶች በቀላሉ በኤሌክትሪክ የሚሠራ ምድጃ በመጠቀም ወደዘመናዊ የአኗኗር ዘዴ መለወጥ ያስችላል:: ቀሪ ጊዜያቸውንም ምርታማ ሊሆኑ በሚችሉበት ዘርፍ እንዲያውሉት ያደርጋል:: በየገጠሩ የኤሌክትሪክ ኃይል ሲገባ ለማገዶ ተብሎ የሚጨፈጨፍ ደን አይኖርም፤ በዚህም ለተፈጥሮ ኃብቱ መጠበቅ የራሱ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ማለት ነው።

በገጠሩ አካባቢ የመድሀኒት አቅርቦቱን ለማሻሻል፤ ትምህርት ቤቶችን በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ለመደገፍ የህዳሴው ግድብ ተጠናቆ ኃይል ማመንጨት መጀመሩ ትልቅ ትርጉም ይኖረዋል። ከዚሁ ጐን ለጐን ከውሃ የሚገኘው ኃይል ለአካባቢ ንፁህ ነው:: የሚተወው ቆሻሻ ወይም ደግሞ ለአካባቢው የሚለቀው የተቃጠለ አየር ስለሌለ ከማንኛውም የኃይል ምንጭ ተስማሚ መሆኑ የህዳሴው ግድብ ጥቅም እጅግ ከፍተኛ እንደሚሆን አያጠያይቅም። የህዳሴው ግድብ ግንባታ ሲጠናቀቅ የኢትዮጵያን ህዝብ የኑሮ ሁኔታ ወደ ትልቅ ደረጃ የሚያሸጋግረው በመሆኑ በእልህ እና በወኔ ግድቡን ለመጨረስ ከፍተኛ ጥረት ማድረግ ይገባል።

“The Grand Ethiopian Renaissance Dam᎓ Significance and Consequences” በሚል ርዕስ አፍሮ ሚድል ኢስት ሴንተር በተባለ ተቋም የቀረበ ፅሁፍ እንዳሰፈረው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሲጠናቀቅ የአገሪቱን የሀይል ፍላጎት 50 በመቶ መሸፈን ይችላል። በቀን 27 ሚሊዮን ዶላር ገቢም እንደሚያስገኝ ፅሁፉ አመላክቷል። የአገሪቱን የኃይል አቅርቦት ከማሟላቱም ባለፈ ለጐረቤት አገራት ኃይል በመሸጥ በቀን እስከ ሁለት ሚሊዮን ዩሮ የሚሆን የውጭ ምንዛሬ ማግኘት እንደሚቻል በዚሁ ጥናት ላይ ተመልክቷል። በዚህም በከፍተኛ ደረጃ የውጭ ምንዛሬ እጥረትን ማቃለል ያስችላል።

በአንድ አገር ውስጥ አንድ ዩኒት ኤሌክትሪክ ኃይል በተጨመረ ቁጥር በዓመት አጠቃላይ የአገር ውስጥ ምርት እድገቱን ቢያንስ አንድ በመቶ እንደሚያሳድገው ይታሰባል:: በዚህ ስሌት መሠረትም የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ተጠናቆ ኃይል ማመንጨት ሲጀምር ባሉት ዩኒቶች በዓመት የኢትዮጵያን ጠቅላላ ብሄራዊ የምርት መጠን ቢያንስ በአራት በመቶ ተጨማሪ እድገት እንዲያስመዘግብ ያግዘዋል ማለት ነው። የህዳሴው ግድብ መጠናቀቅ የአገሪቱን የኃይል አቅርቦት ያሣድገዋል፤ ተጨማሪ የውጭ ምንዛሬ ያመጣል፤ ውሃ የማጠራቀም አቅምን ያሣድጋል፤ ከጐረቤት አገራት ጋር ያለውን ግንኙነት ያጠናክራል:: እንዲሁም የምጣኔ ኃብት መዋቅሩን ወደ ኢንዱስትሪ ለማሸጋገር ትልቅ መንገድ ይከፍታል። በመሆኑም፣ የህዳሴ ግድባችንን ማጠናቀቅና ወደ ስራ ማስገባት ምንም አይነት ጊዜ የማየሰጠው የሁላችንም ተግባር ሊሆን ይገባል።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy