Artcles

የትኛው ይቀድማል? ፈረሱ፤ ወይስ ጋሪው?

By Admin

July 27, 2017

የትኛው ይቀድማል? ፈረሱ፤ ወይስ ጋሪው?

ስሜነህ

የገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን በ2009 ዓ/ም የነጋዴዎች የቀን  ገቢ ትመና አካሂዷል። የገቢ ትመናው የተደረገው ከስድስት ዓመት ቆይታ በኋላ ነው። ከዚህ ቀደም ለመጨረሻ ጊዜ የገቢ ትመና የተደረገው በ2003 ዓ/ም ነበር። የቀን ገቢ ትመናው ዓላማ ግብር ከፋይ ነጋዴዎች አሁን በሚያገኙት ገቢ ልክ የገቢ ግብር መክፈል የሚችሉበትን መረጃ ማሰባሰብ እንደሆነ ባለስልጣኑ አስታውቋል። ከዚህ በተጨማሪም በግብር መረብ ውስጥ ያልተካተቱና ተሸሽገው የሚሰሩ ነጋዴዎችን በመለየት በግብር መረብ ውስጥ እንዲካተቱ ማድረግ ነውም ብሏል። ስለሆነም ከላይ በተመለከተው ተጠየቅ መሰረት ነጋዴና ንግድ የሚባሉ መሰረታዊ ጉዳዮች ይኖራሉ ማለት ነው። እንዲያ ከሆነ ዘንድ የተሸሸገውን ለማውጣትና የተደበቀውም እንዲጋለጥ የባለስልጣኑ የትኩረት አቅጣጫ በገቢ ላይ ብቻ ሊሆን ይገባዋል? የሚል ጥያቄ ማንሳት ተገቢ ይሆናል፤ ምክንያቱም ከፈረሱ ጋሪውን ካሰቀደመ ክፉ ደዌ መፈወስ ባለመቻላችን ሁሉ ነገር አድሮ ቃሪያ እየሆነብን ስላስቸገረን።

የንግድ ስርአቱ ባልተሳለጠበት፤ የገቢ ሰብሳቢው መስሪያ ቤት ሙያተኞችና ሃላፊዎች ከሙስና ባልጸዱበት፤ አቅማቸው ባልጎለበተበት አሁን የተተመነውስ ወደመንግስት ገቢ ለመሆኑ ምን ዋስትና ይኖረናል?። አለም ላይ የሌለ ህገወጥ የንግድ አይነት በተንሰራፋበት ሃገር መንግስት ከላይ የተመለከቱ አለማዎች ባሉት የቀን ገቢ ትመና ነገሩን መቆጣጠር ይቻለዋል?። እንደማይቻለውም ሆነ ይቻለው እንደሆን ለማጠየቅ እና ወደመፍትሄው ለመንደርደር  ያግዘን  ዘንድ የህገወጥ የንግድ አይነቶችን ስፋትና ጥልቀት መመልከት ጠቃሚ ይሆናል።

በአዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን በክልል ከተሞችም ሳይቀር  አምናም ዘንድሮም፤ ትናንትም ዛሬም ከእጅ ሰዓት አንስቶ እስከ ተለያዩ አልባሳት፣ ጌጣጌጦችና መሰል ቁሳቁሶች ከጭልፋ እስከ ማንኪያና ሹካ፤ ከመዋቢያ እቃዎች እስከአይጥ መድሃኒቶች፤ ከሶፋ ጨርቅ እስከመጋረጃ፤ ከሙሉ ልብስ እስከ ውስጥ ሱሪ ያለከልካይ በአደባባይ በህገወጥ መንገድ እየተቸበቸበ ነው። ገቢዎች የማያውቃቸው ዳቦ ቤቶችና መዝሙር ቤቶች በየመንደሩ እና በዋና ጎዳና ላይ ሲብስም በየዳቦ ቤቱና በየመዝሙር ቤቱ ደጃፍ ዳቧቸውን እና ካሴታቸውን በመኪና ጭነው ህጋዊ ነኝ የሚለው ዳቦም ሆነ መዝሙር ቤት እየጮኸ ባለበት ሰዓትም ላይ ያለአንዳች ከልካይ እየቸበቸቡ መሆኑ ይታወቃል። በአሪቲ እና ቄጤማ፤ በጧፍና ሻማ ከለላ ስር በየአብያተ ክርስቲያናቱ ደጃፍ ላይ ኮንቴይነር በትነው ጭልፋው አይቀራቸው ድስቱ፤ ኦሞው አይቀራቸው ሳሙናው፣ ጋቢና ኩታውን ጨምሮ የሃገር ልብሱ ሁሉ እየተቸበቸበ ነው። ገቢዎች ሊተምን የሄደው ሽሮ ሜዳ። እነርሱ የሚገኙት ንግስና ክብረ በአል ሜዳ። ዛሬ ከጉሙሩክ የወጣ ጫማ በ40 ብር ብቻ ….. በ40 ብር …….. እየተባለ በአደባባይ ሲቸበቸብ እያየን ከየትና በምን አግባብ ብሎ የማይጠይቅ መንግስት በቀን ገቢ ትመና ነገሩን ወደ ህጋዊ መስመር አመጣለሁ ቢል የነጋዴው መስሚያ ጥጥ እንደሚሆን አያከራክርም።

ጉዳዩን በተመለከተ በአንድ የሬዲዮ ጣቢያ የቀጥታ ስልክ ውይይት ላይ ሳለሁ ከውጭ የመጣ መሆኑን የነገረኝ አንድ አድማጭ አውሮፓ 50 ዶላር አውጥቶ ለባለቤቱ የገዛውን ተመሳሳይ ብራንድ ያለው ጫማ በ4ኪሎ አደባባይ በ40 ብር ሲቸበቸብ እንዳገኘው አጫወተኝ፤ ይህ የሚያረጋግጥልን እንግዲህ የባለስልጣኑ ሰራተኞች በኤግዚቢት የተያዙ እቃዎችን ማስፈንጠሩን የተያያዙት መሆኑን ነው።

ወደ ብሄራዊ ዙሪያ ብንሄድም የምናገኘው ተመሳሳይ ሁኔታና ግብይትን ነው፤ “ከ10 ያልበለጡ የውሃ እሽጎችን ለደረደርንበት ሱቅ የቀን ገቢ 10 ሺህ ብር መጣብን” ብለው ሲጮሁ ታገኟቸኋላችሁ። ዳሩ 10 ውሃ ልትሸጡ 20ሺህ ብር ሱቁን ምን አከራያችሁ? ስትሉ ጥያቄ ብታነሱ መልሱ የንግድ ስርአቱን መንበዛበዝ የሚያመለክት ይሆናል። በ10 የውሃ እሽጎች ከለላ የህገወጥ የውጭ ምንዛሬ ሱቆች መሆናቸው እየታወቀ ነው እንግዲህ የቀን ገቢ ግምቱ የተጣለባቸው። በዚህ አግባብ ገቢዎች 20ሺህ ሲተምንባቸው ህገ ወጥ ንግዳቸውን ታሳቢ አድርጎ ይሆናል ማለት ነው። ይህ ከሆነ ደግሞ ትልቁ ጥያቄ እዚህ ጋር ይመጣል። የመንግስት የሆነው ገቢዎች ህገወጥነትን የሚከላከለው ለህገወጥ ንግዶች ሲከፋም ለወንጀለኞች ሳይቀር እውቅና በመስጠትም ጭምር መሆኑን የተመለከተ ጥያቄ።

ሌላ እንጨምር። በጋራ መኖሪያ መንደሮች ነዋሪው ሊገለገልባቸው የሚገቡ ኮሚዩናሎች፣ ሆቴል እና ክሊኒክ፤ ትምህርት ቤትና ባንክ ሆነዋል። ህግ ያወጣው መንግስት፤ ንግድ ፈቃድ ሰጪው መንግስት፤ ተከራዩ የመንግስትን ባንክም ይጨምራል። የሁለቱ ህገወጥ መሆን ሳያንስ የመንግስት የሆነው ገቢዎች ለህገወጦቹ እውቅና በመስጠት የቀን ገቢ ትመና አውጥቶ ሲሰጣቸው ቢጮሁ ላስጮኸው እንፍረድ ወይንስ ለጮኸው ያስብላል። ለነገሩ ይህ ባንክ ህግ ባለበት ሃገር ላይ ህገወጥ የውጭ ምንዛሬ ሱቆችን ማስያዝና ተጠያቂ እንዲሆኑ ከመስራት ይልቅ፤ የመረጠው አብሮ በእነርሱው መንደር የውጭ ምንዛሬ ሱቁን ከኢትዮጵያ ሆቴል በስተጀርባ ከፍቶ መመንዘርን ነው። ይህ ደግሞ የውርደታችንን እና የስርአተ አልበኝነት ልካችንን የሚያመላክት ሲሆን የህገወጦቹን ጡንቻና አድራሻም የሚጠቁም ይሆናል።

ከምናየው ሕገወጥ ንግድ በተጨማሪ በየጉራንጉሩና በየጓዳ ጎድጓዳው የሚሸጠው ምርትና አገልግሎት የትየለሌ ነው። ከአንደኛው ቤት ማኪያቶ ጠጥተን ደረሰኝ ሲሰጠን እዚያው ከጎኑ ያለው ለተመሳሳይ አገልግሎት እኩል መጠን ያለው ገንዘብ ተቀብሎን በባዶ እጅ ይሸኘናል። ቁጥራቸው ቀላል የማይባሉ ምግብ ቤቶችና ሬስቶራንቶችም ከላይ ካነሳናቸው አንጻር የሚቃኙ ናቸው። አይነ ውሃው ላላማረው ተገልጋይ ወይም ሸማች የሚሰጥ ህገወጥ እና ከባለስልጣኑ ጋር ግንኙነት የሌለው ፎርጅድ ካሽ ሬጅስተሮችና እና ደረሰኞችም የከተሞቻችን ጉድ ሆነዋል። በሁለት ካሽ ሬጅስተር የሚነገድባት ብቸኛዋ ሃገር ሳትሆንም አትቀር። ጎን ለጎን ያሉ ነጋዴዎች አንዱ አጭበርባሪ አንደኛው ህጋዊ የሚሆኑበትም አግባብ ሰፊ ነው። ግን ደግሞ ህጋዊነት እራስን ህጋዊ አድርጎ ማቅረብና ህጋዊ ሆኖ መገኘት ብቻ ነው? ወይስ ህገወጦችንም ማጋለጥን ይጨምራል? ነው ጥያቄው። የንግዱ ማህበረሰብም ለዚህ ጥያቄ መልስ ሳይሰጥ ቢጮህ ዋጋ ቢስ መሆኑ ዛሬ በተጣለበት የቀን ገቢ ግምት ሳያበቃ ተከታታይነት ያለው ባለእዳ መሆኑን ማሰብ ይጠበቅበታል።

የደንብ ማስከበሩ ደግሞ ጉድ ነው። በወር በወር ለህገወጦቹ ከለላ በመስጠት ደሞዝ ከአንድ የንግድ ድርጅት ብቻ ሳይሆን ከአንድ አራቱ የሚቆረጥለት መኖሩንም በዚሁ ውይይት ሰምተናል። ስለምን ይህ ሆነ? ተብለው ጥያቄ የቀረበላቸው የደንብ ማስከበር ጽ/ቤት ምክትል ሃላፊ ደግሞ ጽ/ቤቱ ለብቻው የሚሰራውና ሊወስን የሚችልባቸው ስልጣኖች እንደሌሉት ገልጸው፤ ለዚህም ኮሙዩናል ንግድ ቤት መሆን እንደማይችል ህገ ወጥነቱን ጠቅሶ ሊከለክል ሲሄድ ሌላኛው የመንግስት መዋቅር ንግድ ፈቃድ ሰጥቶ እና አድሶ እንደሚያገኘውና ለእርምጃ አስቸጋሪ እንደሆነበት ጠቅሰዋል ።

በከተማችን ላይ በሚገኙ ዋና ዋና ጎዳናዎች የተሰቀሉና አድራሻቸው ጭምር የሰፈረባቸው ህገወጥ ማስታወቂያዎችም ከልካይ ያላቸው አይመስልም። ቢያንስ ማስታወቂያቸው ላይ በተጠቀሰው አድራሻቸው ሄዶ የመንግስትን ገቢ የሚጠይቅ አካል የለም። ይህም ሳያንስ የዛሬ 5 እና ከዚያ በላይ የተለጠፉ እና ምናልባትም የተዘጉ ድርጅቶችንም ማስታወቂያ እያየን መሆኑ የንግድ ስርአቱን መዝረክረክ የሚያጠይቅ ነው። በየገቢዎቹ ጽ/ቤቶች ደጃፍ የሚገኙት  ፎቶ ኮፒ  ቤቶች የባለስልጣኑ ሙያተኞችና የህገወጦቹ አገናኝ ደላሎች መሆናቸውንም ሄዶ ማረጋገጥ በሚቻልበት አግባብ ላይ የቀን ገቢ ግምቱ ህገወጡን ወደ ህጋዊ መስመሩ ለማምጣት ነው ማለት የሚሆነው ከፈረሱ ጋሪውን ማስቀደም ነው። ኪሎ ለመጨመር በቆሻሻ እና ባእድ ነገር በርበሬ ዘፍዝፈው፤ ኪሎውን በጨው አብዝተው እና ቅላቱን በጎመን ዘር አስተካክለው የሚሸጡ የበርበሬ ነጋዴዎች ባሉበት ሃገር ላይ ከህጋዊው እኩል የቀን ገቢ ከመገመት ሊቀድም የሚገባው የንግድ ስርአቱን መፈተሽ መሆኑም አያከራክርም። ከጋሪው ፈረሱ መቅደም ያለበት የመሆኑን አመክንዮ በመሳት የሚመጣ ለውጥ ስለማይኖር።

ከፍ ከፍ ወዳሉቱ ደግሞ እንሂድ። ጎማ ላለቀበት መኪና ጎማ አስመጪዎችና ሱቆች እዚህ አፋቸውን ከፍተው በተጣለባቸው የቀን ገቢ ግምት ሲያንጎላጁ፤ ህገወጡን ሃይ የሚለው  የለም። ከህጋዊዎቹ የተወሰነውን ቅናሽ ማግኘቱን ያስበለጠ የከባድ መኪና ባለቤት በሊሾ ጎማ ከጅቡቲ ይገባና አዲስ ጎማ ገጥሞ ይመለሳል። ይህን የሚቆጣጠርበት አሰራርና ስርአት እንዲሁም ምግባር ያለው ሰራተኛ የሌለው ገቢዎች አፉን ከፍቶ የዋለውን ህጋዊ ነጋዴ በቀን ገቢ ግምት ያስጮኸዋል። ወዲህ ደግሞ ለሃገር እድገት ጠንቅ ከሚሆነው ህገወጥ ንግድ ጋር ከላይ በተመለከተው መልኩ የተመሳጠረው የመኪና ባለቤት መልሶ በራሱ ላይ ሲደርስ የተጋነነ የቀን  ገቢ ትመና መጣብኝ ሲል ሲያለቅሰ ማየት ግራ ገብ ይሆናል። የመኪና ጎማው ጉዳይ በዚህ አያበቃም። ሊሾ የነበረው ጎማ ስለማያስነቃ ከመነዳሪው ይወጣና መድሃኒቱ የለ፤ ሜሞሪና ፍላሹ ይጠቀጠቅበትና (ስኮርት ጎማ መስሎ) በህገወጥ መንገድ ይገባና በየአደባባዩ ይቸበቸባል። አሳላፊው የባለስልጣኑ አጋርም በወፍራሙ ይጎርሳል። ይህን እንዳላየ የሚያልፈው ባለስልጣን መልሶ መየከተሞቹ የሚገኙ የኤሌክትሮኒክስ ቤቶችን የቀን ገቢ ግምት ሲያሰላ ማየት ከፈረሱ ጋሪውን የማስቀደም ውጤት አልባ ግርግር መሆኑን ለመገንዘብ አይከብድም።

ደረቅ ወደብ ብትሄዱ፤ ሞጆ ሚዛንና ሚሌ በየኬላው ያለው ጉዳይ ገቢዎች የግለሰብ ተቋም እስኪመስል ከሁለትና ሶስት ያልበለጡ ሰዎች ነግሰውበትና አብጠውበት እያየን ለሃገር ጥቅም ሲባል ህገወጡን ህጋዊ ለማድረግ ወዘተ የሚሉት የባለስልጣኑ የቀን ገቢው ግምት ምክንያቶች ግራ ገብ ቢሆኑብን ሊገርም አይገባም።

ለንግዱ ስርአት መበሻቀጥና በተበሻቀጠው ልክ ለመጣው የቀን ገቢ ግምት ምክንያቱ መንግስት ብቻ ሳይሆን ነጋዴውም ጭምር ነው።  

በኡራኤል አካባቢ ሄደን ሴራሚክ ስንገዛ እኮ ገንዘቡን እዛች ሱቅ ላይ እንከፍለው እንደሆነ እንጂ የሚጫንልን ከሱሉልታ ወይም ለገጣፎ ከሚገኙ ድብቅ መጋዘኖች መሆኑንም እናውቃለን። በአዲስ አበባ ከእስጢፋኖስ በስተጀርባ የሚገኙት መጋዘኖች እኮ የቀን ገቢ ግምቱ የማያውቃቸው የህገወጥ ነጋዴዎች ዋሻ ናቸው። 20 እና ከዚያ በላይ ኩንታሎችን በሱቆቹ ደርድሮ የተቀረውንም በየቆጣ ቆጡ መወተፉን የምናውቅ ጎረቤቶች ቢያንስ እንዳለን ከመጤፍ ሳይቆጥረን “በቀን አንድ ኪሎ ነው ስሸጥ የምውለው” የሚል ነጋዴ ባለበት ሃገር ላይ መንግስት ላይ ብቻ ማነጣጠር መፍትሄ ይሆናል ወይ? የሚል ጥያቄ ያስነሳል። ለአሽከርካሪዎቹ በፔሮል የማይከፍል የከባድ መኪና ባለቤት፤ ተሳፋሪን በየምክንያቱ የሚያጨናንቅ እና መሸት ባለ ቁጥር ያሻውን የሚጨምር አሽከርካሪ፤ ሃገር አቋራጭ ለሆኑ የህዝብ ማመላለሻ አውቶብሶች የጭነት ክፍያው ቅዲሚያ እየተከፈለ፤ በአንጻሩ ደግሞ ድንበር ተሻጋሪ ለሆኑ የደረቅና ፈሳሽ ጭነት የጭነት ክፍያ ከሁለት ወርና ከዚያም በላይ ሲከፋም በጩኸት እየተከፈለ በሚገኝበት ሃገር ላይ፤ የቀን ገቢ ግምት ለማውጣት እንዴትስ ያስችላል። ከትንሽ እስከ ትልቅ፤ በ100 ኩንታል ሲሚንቶ መጠናቀቅ ከሚገባው ግንባታ ላይ ቢያንስ ሰላሳውን የሚያጭድ የስራ ተቋራጭ የቀን ገቢ ግምት ምናምን እያለን ሲጮህ ቢውልና ቢያድር መጨናነቅ አለብን ወይ?። ከፈረሱ ጋሪው ቀድሟልና መፍትሄው አስቸጋሪ ይሆናል።

የንግድ ስርአቱ  በጥቅሉ የተንዛዛ ብቻ ሳይሆን የተንዘባዘበም ነው። ዛሬ ደግሞ የቀን ገቢ ግምቱም እንኳ ቢያንስ የማያውቃቸው የሞባይል የጽሁፍ መልእክት ህገወጦች ደግሞ በመላው ሃገሪቱ እንዳሻቸው እየፈነጩብን ነው። እኒህንም ገራም የሚያደርጋቸው የባለስልጣኑ ተጠሪ የሆነው የመንግስቱ ብሄራዊ ሎቶሪ ባለበት ሃገር ላይ ነው።

ህገወጥ ንግድን ለመከላከል ብሎም ለማስቀረት መንግሥት ህግ ቢያወጣም አፈፃፀሙ ላይ ቁርጠኝነት ባለመኖሩ የተፈለገውን መሰረታዊ ለውጥ ሲያመጣ አይስተዋልም። የጎዳና ህግ አስከባሪዎች በድንገተኛ ደርሰው ከአንድ አካባቢ በዱላ አስፈራርተው የሚያሯሩጡት ህገወጥ ነጋዴ ሮጦ ያመልጥና ከሌላኛው ጫፍ ይደርሳል። ግን ብዙም ሳይቆይ ፖሊሶች ዞር ሲሉ ተመልሶ በቦታው ይሰየማል። አንዳንድ የዋሆች ደግሞ ሰርተው ቢበሉበት ምን አለበት? ሲል መንግስትን ያማርራል። ደንብ አስከባሪዎቹ ህገ ወጡ ከእጃቸው ቢገባም “ወይ አንሳ ወይ ሃምሳ” በመሰረቱ የሚለብሰው እራፊ በላዩ ላይ ያለቀበት የጎዳና ላይ ነጋዴ፤ ለሱሪው መጣፊያ ማስለጠፍ ያቃተው የጎዳና ነጋዴ የሚይዛቸውን ጂንሶች እና ሸሚዞች ልብ ብለው ይሆን?። የኤርገንዶው ጫማ በላዩ ላይ ያለቀበት ጎረምሳ ነጋዴ የሚይዘውንስ የጫማ አይነት ተመልክተውታል?። ልብ ብለው ከነበረ በጎዳና ንግድ ለመሄጃ መንገድ አሳጥቶ የተሰጣው ሁሉ ከሱቆቹ በስተጀርባ ተበትኖ የሚሸጥ የህገወጥ ሃብታሞች ንብረት ነው። በየአትክልት ቤቱ ደጃፍ ላይ በጋሪ የሚቸበቸበው ሽንኩርት የለ ቲማቲም፤ እንዲሁም ብርቱካኑና ሙዙ ሳይቀር ከህገወጥ አትክልት ቤቶች ተበትኖ የሚሸጥ ነው። እንዲህ በሆነበት አግባብ የቀን ገቢ ግምት ማውጣት ፍትሃዊ አይሆንም። መጽዳት ያለበትን ማጽዳት መጀመሪያ ያስፈልጋል።

ይህ እንዳለ ሆኖ ግን፤ ማለትም የቀን ገቢ ግምቱ አመክንዮአዊ አለመሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ በርካታ ኢፍትሃዊ በሆኑ አሰራሮች የተተበተበ መሆኑም በዚሁ የሬዲዮ ፕሮግራም ላይ የተወሳ ሲሆን ገዥ የሚመስሉ መፍትሄዎችም ከአድማጮች ቀርበዋል። የቀን ገቢ ግምቱ አላማ ነጋዴው በሚያገኘው ገቢ ልክ የመንግስትን ገቢ እንዲያስገባና ህገ ወጡን ወደ ህጋዊ መረቡ ለማስገባት ሆኖ ሳለ የንግዱን ማህበረሰብና በየደረጃው የሚገኙ የንግድ መዋቅሮችን ያላሰተፈ መሆኑ የመጀመሪያው ችግር ሲሆን፤ ዘፈቀዳዊና ለኪራይ ሰብሳቢነት የተመቻመቹ ግምቶች መኖራቸውም ሌላኛው ነው።

የቀን ገቢያቸው  ቢበዛ በመቶ እና አምስት መቶ ብር ሊበላለጡ በማይችሉ ሱቆች መሃል የ18 ሺህ ብር የቀን ገቢ ግምት ልዩነት መታየቱ አንደኛውን ለኪራይ ሰብሳቢነት አጀንዳ ማመቻመች እና እንኳንስ ባለሙያ ለሆነ ለማንኛውም ተራ ሰው የማይከብድ ሆን ብሎ የተሰራ ሴራ መሆኑ ተገልጿል። የቀን ገቢ ገማቾቹ እራሳቸው ሸማች እንዳልሆኑ ሁሉ የግምቱን አላማ ከማብራራት ይልቅ “አምጡ ተብለናል፤ አምጡ” የሚል ምላሽ የሚሰጡ መሆኑም ሌላኛው ችግር የነበረ መሆኑና በመንግስትና በህዝብ መካከል መቃቃርን የፈጠረ፤ በሸማቹም ላይ ጭማሬ በማምጣት ጫናን የሚፈጥር መሆኑ ተወስቷል። ይልቁንም ለቀን ገቢ ገማቾቹ በሱቅና በንግድ ተቋማት ቁጥር ኮታ መስጠት ሲገባ በብር መጠን ኮታ የተሰጠ መሆኑ ችግሮቹን ያገዘፈ እና አምጡ ስለተባሉት የብር መጠን እንጂ ለግምቱ ከግምት ውስጥ መግባት የሚገባቸውን ጉዳዮች እንዳያስተውሉ ማድረጉን የመሳሰሉ በርካታ እና በተለይ በዝቅተኛው ነጋዴና በሸማቹ ላይ ከፍተኛ ተጽእኖን የሚፈጥሩና የመንግስት የሆኑ ችግሮች ተወስተዋል።

ከንግዱ ማህበረሰብ ጋር ተከታታይነት ያላቸው ውይይቶች ማድረግና ባለድርሻዎችን ከማሳተፍ ባሻገር በየደረጃው የሚገኙ የገቢዎች መዋቅርን ከኪራይ ሰብሳቢ ነጋዴዎች እና ከደላሎች ከማጽዳት የመፍትሄ አቅጣጫዎች ባሻገር፤ በመቶ ሺህ እና አምስት መቶ ሺህ መካከል ያለውን ሰፊ ልዩነት በማጤን እስከ መቶ ሺህ አመታዊ ገቢ ለሆኑቱ ሌላና ደረጃ “መ”፣ “ሠ” እያሉ ደረጃውን ማብዛት ነጋዴውም ሳይጎዳ መንግስትም ሳይቀርበት ትክክለኛውን ገቢ መሰብሰብ ያስችለዋል በሚል የቀረቡት የመፍትሄ አቅጣጫዎች ገዥ ይመስላሉ እና መንግስት ሊያያቸው  ይገባል።

ባጠቃላይ፣ መንግስት የግብር ስርአቱን ለማጠናከርና ልማትን ለማፋጠን እያደረገ ያለው እንቅስቃሴ የሚበረታታ ነው፤ ይሁን እንጂ የዚያኑ ያህልዕ ህዝብን ከመንግስት ለማጋጨት ሌት ተቀን የሚሰሩ ሀይሎች አሉ። እነዚህ ሀይሎች ወደባሰና ከፋ ደረጃ ሳይሸጋገሩ ሀይ ሊባሉ ይገባል። በመሆኑም መንግስት የጀመረውን ፀረ-ምስና ዘመቻ አጠናክሮ ሊቀጥልበት፤ ህዝቡም ከመንግስት ጎን በመቆም አስፈላጊውን ትብብር ሊያደርግ ይገባል።