Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የትውልድ ምልክት

0 723

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

 

የትውልድ ምልክት

በሀብቶም ገብረእግዚያብሄር (16/11/09) nahat143love@gmail.com

ጠንካራ ሀገር የሚመሰረተው በትውልዶች ጠንካራ ስራ ነው። አንድ ትውልድ ጠንካራ ሀገር ለመመስረት መሰረቱን ይጥላል እንጂ በራሱ ጠንካራ ሀገር ሊመሰርት አይችልም። ለምን ቢባል ሀገርን በሁሉም መስክ ጠንካራ ለማድረግ የትውልድ ቅብብሎሽ እና ተደራራቢ ስራ የሚፈልግ በመሆኑ ነው። እዚህ ጋር ሮም በአንድ ለሊት አልተገነባችም የሚለውን ቢሂል ማስታወስ መከራከሪያውን ያጠናክርልናል። ስለዚህ በአንድ ሀገር ውስጥ የሚፈጠሩ ትውልዶች አንዱ የገነባው ላይ ሌላኛው በመጨመር ሀገራቸው ጠንካራ ለማድረግ መስራት አሁን ልዕለ ሀያል እያልን የምንጠራቸው ሀገሮች የመጡበት መንገድ ነው። የነዚህ ሀገራት የሀያልነት ሚስጥር ይሄ እንጂ ሌላ የተለየ ሚስጥር የለውም። እኛም ስንጓዘው የነበረው የማሽቆልቆል ጉዞ ምንጭ ከዚህ እውነታ በተቃራኒው በመጓዛችን እንጂ እንደህዝብ የተረገምነው እርግማን ስለነበረ አይደለም።

የታሪክ ማህደራት እንደሚያስረዱን ከሁለት ሺ አመታት በፊት ሀገራችን በአለም ላይ ከነበሩት ሀያላን ሀገራት አንዷ ነበረች። እነዚህም ሀገራት ቻይና፣ ህንድና ፐርዢያ ነበሩ። ይህም የሀገራችን ሀያልነት በጊዜ ሂደት እንደተገነባው ሁሉ በሂደት ሊከስም እና ብሎም ሊጠፋ ሆኗል።

የሀገራችን እንደዚህ መሆን የተለያዩ ምክንያቶችን መደርደር ብንችልም ዋነኛው ነገር ግን በትውልዶች መሀከል በተፈጠረ ክፍተት ነው። ሂደቱ በዚህም ተባለ በዚያ የሚያሳየን ነገር ቢኖር አንድ ትውልድ ያስረከበውን ቀጣዩ ትውልድ ጠብቆ ያለማቆየቱ ብሎም በተሰራው ላይ ያለመጨመሩን ያመላክተናል። ዞሮ ዞሮ ይሄ የተውልድ ክፍተት ለብዙ ሺህ አመታት ሄዶ ሄዶ የት ጋር እንደደረስን ማብራሪያ አያስፈልገውም። ነገር ግን በጥንታዊቷ ኢትዮጲያ ላይ የተነሱ ብርቱ ትውልዶች የራሳቸውን ምልክት እና አሻራ አሳርፈው ሄደዋል። በአክሱም ዘመን የተሰሩት ሐውልቶች በዋነኝነት የሚያሳዩን ያንን የሰራውን ትውልድ ጥንካሬ ነው። በዛግዌ ስርወ መንግስት የተሰሩትን አስደናቂ ስነ ህንፃዎች የሚነግሩን በዘመኑ የተፈጠረውን ትውልድ ጥንካሬ ነው። ያለመቀጠሉ እና ያለመስፋቱ ደግሞ ቀጥሎ የተፈጠረው ትውልድ የሚወስደው ክፍተት ነው። በጥንታዊቷ የሀረር ከተማ ያለውን ስነ ህንፃ እና ዙሪያዋን የከበባት አጥር በወቅቱ የነበሩትን ትውልዶች ጥንካሬ የሚያሳይ ነው። በርግጥ እነዚህ ከላይ የተዘረዘሩት የሰሪዎቻቸውን ጥንካሬ ቢያመላክትም ቀጥሎ ለመጣውም ትውልድ ሆነ ዛሬ ላይ ላለነው የሚያኮራ ታሪክ ነው። ነገር ግን አንድ ትውልድ ያለበት ሀላፊነት ከሱ ቀደምት በነበሩት ዜጎች በተሰሩ ስራዎች እየኮራና እየተኮፈሰ መኖር አይደለም። እነዚህ የቀድሞ ስኬቶች አሁን ላለው ትውልድ መንደርደሪያና ሀይል ሊሆኑ ይገባል እንጂ ለዛሬው ውድቀት መደበቂያ ሊሆኑ አይገባም። ስለዚህ እያንዳንዱ ትውልድ የራሱን ድንቅ ምልክት እና አሻራ ትቶ ለመሄድ ማሰብ እና መንቀሳቀስ ይገባዋል።

ይሄን ፅሁፍ እንድፅፍ ያነሳሳኝ በቅርቡ በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል በጉባ ወረዳ የሚገኘውን የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታን በጎበኘሁበት ወቅት የተሰማኝ ስሜት ነበረ። ይህ ግድብ ለመላው ኢትዮጲያውያን የዛሬው ትውልዶች ያለው ትርጉም ከግድቡ ከሚመነጨው 6450 ሜጋ ዋት ጋር ብቻ የተያያዘ አይደለም። ወይም ደግሞ ግድቡ ሀይል ማመንጨት ሲጀምር የሚገኘውን ትሩፋት በማሰብ የተቀኘ አይደለም። በርግጥ እነዚህ ጥቅሞች ለሀገራችን ከፍተኛ ለውጥ የሚያስገኙ መሆናቸውን ባንዘነጋም።

በኔ እምነት በዋናነት የዚህ ግድብ ግንባታ የሚያመላክተው ያለንበትን ትውልድ ጥንካሬ እና የራሱን የሆነ ምልክት እና አሻራ አሳርፎ ለማለፍ የተነሳ መሆኑን ነው። የትኛውም ጎራ እና የፖለቲካ አመለካከት ሳያግደው በህዝባዊ ማዕበል እየተገነባ ያለው የህዳሴ ግድብ ወደድንም ጠላንም አሁን በሀገራችን ያለው ትውልድ ምልክት እና ማስታወሻ ነው። ከማስታወሻነትም ባለፍ በትውልድ ሰንሰለት ልንገነባት ለምናልማት ሀያል ኢትዮጲያ ለቀጣዩ ትውልድ ጥሩ መሰረት የሚሆን ነው። እኛ ስንኮራበት ከኖርነው የሀገራችን የሩቅ ታሪክ ለቀጣዩ ትውልድ የቀረበ እና የበለጠ መነሳሻ የሚሆን አስደናቂ ጅማሮ ነው። ከዚህ በሗላ የህዋ ሳይንስን ጨምሮ የተለያዩ ስኬቶችን ለሀገራችን ብናስመዘግብ አስደናቂነታቸው ከዚህ የበለጠ አይሆንም። እኔም በግሌ የዚህ ትውልድ አካል ሆኜ ለዚህ ተግባር ምስክር በመሆኔ እና የተቻለኝን አስተዋፅኦ በማድረጌ እድለኛ ነኝ። የህዳሴው ግድብ ለኔ ያለው ትርጉም ከፖለቲካ ሪዕዮተ አለም ፣ ከአስተሳሰብ ልዩነትም ሆነ ከጊዜያዊ የፖለቲካ ትኩሳት በላይ ነው።ለምን ቢባል ምልክቴ ስለሆነ! ትውልዴ የሚወሳበት አኩሪ ገድል ስለሆነ ነው! ይህንን እውነታ ደግሞ የኔ አስተሳሰብ ብቻ ሳይሆን የመላው የሀገራችን ህዝቦች እንደሆነ አምናለሁ። እኔም ይህን ግድብ ከአይኔ ብሌን በላይ የምሳሳለት የምመኘውን የሀገሬን ሀያልነት መሰረት ይጥላል ብዬ የምኖርለት ግድብ ተፈፅሞ ማየት የዕለት ተዕለት ህልሜ ነው። ከግድቡ ስር ቆሜም ለራሴ ቃል የገባሁት ነገር ቢኖር ይህንን ግድብ በማንኛውም መስዕዋትነት ከፍፃሜ እንዲደርስ ለማድረግ አስተዋፅኦ ማድረግ እንዳለብኝ ነው። አክሱሞች ሀውልቱን ጨርሰው ከስሩ በቆሙበት ወቅት ያጣጣሙትን ስሜት ማጣጣም እፈልጋለሁ። የላሊበላ ህንፃዎችን ባለቁ ጊዜ ያ ትውልድ ያጣጣመውን ሀሴት መረዳት እፈልጋለሁ። የሚሰጠው ደስታ ተራ አይደለማ።

ለማንኛውም በጉብኝቴ ወቅት ያጋጠመኝን አንድ ጉዳይ እዚህ ጋር ላንሳ። አስጎብኛችን ስለግድቡ ማብራሪያ እየሰጠን ነበር። ራቅ ብሎ አንድ የቴክኒክ ስራ የሚሰሩ በእድሜያቸው ጠና ያሉ አባት ተመለከትኩ። እኔም ነጠል ብዬ ቀጥታ ወደሳቸው አመራሁ። ከሚሰሩት ስራ ላይ ላፍታ ሳይስተጓጎሉ ቀና ብለው ተመለከቱኝና ˝እንኳን ደህና መጣችሁ˝ አሉኝ። እኔም እንኳን ደህና ቆያችሁን ካልኩ በሗላ አየሩ በጣም እንደሚሞቅ ነገርኳቸው። እሳቸውም ለአፍታ ከሚሰሩት ስራ ቀና ብለው የምፀት ፈገግታ ካሳዩኝ በሗላ ˝በክረምት መጥተህ እንዲህ የሞቀህ በበጋ ብትመጣማ ምን ልትል ነው˝ ብለው የሚያገላብጧትን ሞተር ነገር ማገላበጣቸውን ቀጠሉ።

እርግጥ ነው አካባቢው በጣም ሞቃታማ እና የበረሀ ገነት የምንለው አይነት ስነ ምህዳር እንዳለው ቀድሞ መረጃው ነበረኝ። ነገር ግን በዚህ በክረምት እንደዚህ የሞቀ በበጋው ምን ሊሆን እንደሚችል ሳስበው ገረመኝ። እነዚህ የትውልዱን ምልክት ለማቆም ሌት ተቀን የሚለፉት ፊትውራሪዎች ፅናት ደነቀኝ። የፊትውራሪ ከፊት ስለሆኑ እንጂ ከራስም በላይ ንጉሶች ናቸው።

ከኝህ ድንቅ ኢትዮጲያዊ ጋር ብዙ ነገሮች ተጫወትን እኔም ለህይወቴ ስንቅ የሚሆነኝን ብዙ ትምህርት አገኘሁኝ። ከዛ ማሀከል ግን ስለ ሀገር ፍቅር የነገሩኝን ሳላነሳ ማለፍ አልፈልግም። ለሀገራቸው ያገለገሉበትን ቦታ እና ዘመን በመጥቀስ ነበር ይጀመሩት።

˝እኔ˝ አሉ ለአፍታ እንኳ ስራ ሳይፈቱ ˝ እኔ በደርግ ዘመነ መንግስት ወታደር ነበርኩ። በዚህም በሚገባ ሀገሬን አገልግያለሁ። በቀይ ኮኮብ ዘመቻ ወቅት ከሻዕቢያ ጋር ስንዋጋ ለብዙ ጊዜ ምሽግ ውስጥ እየራበን እና እየጠማን ስንዋጋ ለማን ብለን ነው እንደዚህ የምንሆነው የሚል ጥያቄ ይነሳ ነበር። መልሱ ግን አጭር እና ግልፅ ነበር። ለሀገር! በኢህአዴግ ጊዜም በኤርትራ ወረራ ወቅት ሰራዊቱን ተቀላቅዬ ሀገሬን አገልግያለሁ።˝

ለአፍታ ዝም ካሉ በሗላ ቀጠሉ ˝ዛሬ ደግሞ እንደምታየኝ በቴክኒክ እውቀቴ እዚህ እያገለገልኩ ነው። ዛሬስ እዚህ ምን ትሰራለህ ብትለኝ ልክ እንደ ቀይ ኮከብ ዘመቻው ለሀገር ብዬ ነው የምመልስልህ። ለምን ብትለኝ ሀገር ማለት በረቂቅ ፍቅር እንጂ በወሬ የማትገለፅ በተግባር እንጂ በመቀመጥ የማትለወጥ መሆኑን እወቅ። አንተም ልጄ˝ አሉኝ እኔም ጆሮዬን አቆምኩ ˝ለሀገር ያለህን ፍቅር በልብህ ይዘህ በእጅህ ግለጠው። ያኔ ሀገርህን መውደድህን ከበዛ ንግግር ባለፈ በተግባር ትገልፀዋለህ።˝

እኔም ተገረምኩ! ለሀገር ያለህን ፍቅር በልብህ ይዘህ በእጅህ ግለጠው የሚለው ንግግር እጅግ የሚናገር እና የሚገልፅ ነው። በልቤም አኖርኩት!

˝መቼ ይጠናቀቃል?˝ አልኳቸው

˝እሱን እግዚያብሄር ያውቃል። ነግር ግን እኔ ይህቺን መብራት ሳላበራ ጡረታ እንደማልል አረጋግጥልሐለሁ።˝ አሉኝ

እኔም ሀሴት አደረኩኝ። የጥንት አባቶቼ ላይ በምናቤ የሳልኩትን ሀሴት እንዲሰማኝ አደረጉኝ! ነገን እዛችው አሳዩኝ!

ቸር እንሰንብት   

   

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy