የትግራይ ክልል ምክር ቤት ለ2010 ዓመት የቀረበውን 12 ነጥብ 33 ቢሊየን ብር በጀት በአብላጫ ድምጽ አጸደቀ።
ከጸደቀው በጀት 56 ነጥብ 6 በመቶ ለድህነት ቅነሳና ዘላቂ ልማት ማስፈጸሚያ እንደሚውል ተነግሯል።
ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ያናገራቸው የምክር ቤቱ አባላት የጸደቀው በጀት ለታለመለት ዓላማ እንዲውል ጥብቅ ቁጥጥር እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።
ምክር ቤቱ የ51 አዳዲስ ዳኞች ሹመትን ጨምሮ 81 የከፍተኛና የወረዳ ፍርድ ቤቶች ዳኞችን ሹመትም አጽድቋል።
በአንድ የምክር ቤቱ አባል ላይ የቀረበውን የህግ ከለላ እንዲነሳም ምክር ቤቱ ተቀብሎታል።
ምክር ቤቱ የመቐለ ማየት የተሳናቸው የአዳሪ ትምህርት ቤት ማቋቋሚያን ጨምሮ ሶስት ረቂቅ አዋጆችንም አጽድቋል።
በሌላ ዜና የአፋር ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት የ2010 በጀት 4 ነጥብ 49 ቢሊየን ብር ሆኖ ፀድቋል።
ምክር ቤቱ ያጸደቀው በጀት ለካፒታል በጀትና የልማት ግቦችን ለማሳካት የሚውል ነው ተብሏል።
በጸደቀው በጀትም ድርቅን የመከላከል ስራ፣ በመንደር የማሰባሰብ ፕሬጀክት፣ ጤና፣ ትምህርት እና የወጣቶች ስር እድል ፈጠራ ትኩረት ይሰጣቸዋል ብለዋል የክልሉ የፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ሃላፊ አቶ ኡስማን ማጥቡል።
የመልካም አስተዳደር ችግሮችን መፍታት፣ የእናቶችና ህጻናት ሞት ቅነሳ፣ የትምህርት ተደራሽነት፣ የእንስሳት ሃብት ልማት፣ ግብርናና የተፋሰስ ልማት የመጪው አመት የክልሉ የትኩረት አቅጣጫ መሆናቸው በምክር ቤቱ ተጠቁሟል።
ምክር ቤቱ ለአራት ቀናት ባካሄደው ጉባኤ የ2009 በጀት አመትን ሪፖርት የገመገመ ሲሆን የ2010ን በጀት በሙሉ ድምጽ አጽድቋል።
በአብዱ ካህሳይ እና አሊ ሹባህሪ