Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የአርብቶ እና ከፊል አርብቶ አደር ህይወት እንዲለወጥ ዛሬም

0 1,511

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የአርብቶ እና ከፊል አርብቶ አደር ህይወት እንዲለወጥ ዛሬም…

አባ መላኩ

 

ኢትዮጵያ ልማትን ማረጋገጥ የህልውና ጉዳይ ነው በሚል ርብርብ ከጀመረች 26 ዓመታት ተቆጥሯል። ይህንን እውን ለማድረግ ደግሞ በመላ አገሪቱ ዘርፈ ብዙ የልማት ግንባታ እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ ይገኛል።

 

በአገሪቱ ፍትሃዊ ልማትን እውን ለማድረግና በተለይ ደግሞ ባለፉት ሥርዓታት ትኩረት ተነፍገው የነበሩ አርሶና አርብቶ አደሮች ከዚህ ልማት ተጠቃሚ ይሆኑ ዘንድ የግብርና ልማትን ማዕከል ያደረገ የልማት ስትራቴጂ ተነድፎ እየተሰራበት ይገኛል። አርብቶና አርሶ አደሩ ከሚኖሩበት የከፋ ድህነት ተላቅቀው የተሻለ ህይወት እንዲኖሩ ለማስቻል በመላ አገሪቱ ቀላል የማይባል ለውጥ ተካሂዷል።

ኢትዮጵያ የበርካታ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች አገር ነች። በአገሪቱ በፌዴሬሽን ምክር ቤት ሕጋዊ እውቅና አግኝተው የተወከሉ የብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቁጥር 75 ደርሷል። የኢትዮጵያ ህዝቦች በተለያየ የሥራ መስክ የተሰማሩ ቢሆኑም አብዛኛው ህዝብ የሚተዳደረው በግብርና ነው። ከ85 በመቶ የሚሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ በገጠሪቱ ኢትዮጵያ የሚኖርና በግብርና ሥራ የሚተዳደር በመሆኑ በግብርናው ዘርፍ እየተካሄደ ያለው ልማት የህዝቡን ጥያቄ በመመለስ ላይ ይገኛል።

በዚህ ማዕቀፍ ውስጥ ከሚገኙት ህዝቦች መካከል የአርብቶና ከፊል አርብቶ አደር ህዝቦች ይገኙበታል። እነዚህ ህዝቦች በተለይም በአገሪቱ ሰሜን ምሥራቅ፣ ደቡብ ምሥራቅ፣ ደቡብ፣ ደቡብ ምዕራብና ምዕራብ አካባቢዎች የሰፈሩ ናቸው።

 

እነዚህ አርብቶና ከፊል አርብቶ አደር የሚኖርባቸው አካባቢዎች ጠረፋማ አካባቢዎች ናቸው። በእነዚህ አካባቢዎች ከ15 ሚሊዮን በላይ አርብቶና ከፊል አርብቶ አደር ህዝብ እንደሚኖር ይገመታል።

የአርብቶና ከፊል አርብቶ አደር ህዝቦች ከሌሎች የአገሪቱ ህዝቦች ጋር በንጽጽር ሲታዩ በሁሉም መልክ ተጠቃሚነታቸው ይቀንሳል። በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ የመሠረተ ልማት ግንባታ በፈጣን የዕድገት ምህዋር ላይ ይገኛል። በመላ አገሪቱ የመንገድ፣ የስልክ፣ የመብራትና የመሳሰሉ መሠረተ ልማቶች እየተስፋፉ መጥተዋል።

በእነዚህ አካባቢዎች ያለው የመሠረተ ልማት ዝርጋት ግን ከቀደሙት ሥርዓታት የተወሰነ መሻሻል ቢያሳይም ከሌላ የአገሪቱ ክፍሎች ጋር ሲነጻፀር እምብዛም የሚያስመካ አይደለም። በአርብቶና ከፊል አርብቶ አደሮች አካባቢዎች ያለው የልማት ለውጥ ከሌላው የአገሪቱ ክፍል እኩል መሄድ አልቻለም። አካባቢዎቹ መሠረተ ልማት በተፈለገው መልክ ካልተስፋፋባቸው የአገሪቱ ክፍሎች ተጠቃሽ ናቸው።

  

በአካባቢዎቹ የመሠረተ ልማት አለመስፋፋት ደግሞ የአገልግሎት ተቋማት እንዳይስፋፋ ከፍተኛ መሰናክል ሆኖ ለዘመናት ዘልቋል። የትምህርት፣ የጤና፣ የንጹህ መጠጥ ውኃ አገልግሎቶች በሚፈለገው ደረጃ ይገኛል ብሎ ለመናገር አያስደፍርም። ለመሠረተ ልማትም ሆነ ለአገልግሎት ተቋማት በተፈለገው መልክ አለመስፋፋት ዋናው ምክንያት አካባቢዎቹ በቀደሙት ሥርዓታት ትኩረት ተነፍጓቸው የነበሩ በመሆናቸው ነው።

በአገራችን በህዝብ ድምጽ ልማታዊ መንግሥት ከተመሠረተ በኋላ ግን ለአካባቢዎቹ የተለየ ትኩረት በመስጠት የአገልግሎት ተቋማትን ለማስፋፋት ጥረት እየተደረገ ነው። ይሁንና አሁንም በተፈለገው መልክ ከሌሎች የአገሪቱ ክልሎች ጋር ሲነጻፀር ተጣጥሞ መሄድ ስላልቻለ ከፍተኛ ጥረትን ይጠይቃል። ለዚህ መሰናክል ከሆኑት ዐበይት ችግሮች መካከል የሕዝቡ ተረጋግቶ አለመኖር ተጠቃሽ ምክንያት ነው።

 

አርብቶና ከፊል አርብቶ አደሩ ህዝብ አንድ የተወሰነ የሚኖርበት ሠፈርም ሆነ መኖሪያ የለውም። የሚተዳደረው በእንስሳት ዕርባታ ነው። የእንስሳት ግጦሽና ውኃን ፍለጋ ሲባል ወቅትን ተከትሎ ከአንድ አካባቢ ወደ ሌላ አካባቢ በመዘዋወር መኖር ግድ ሆኖበት ዘመናት ተቆጥረዋል።

 

መንግሥት የየአካባቢው ማኅበረሰብ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተጠቃሚነቱን ለማረጋገጥ የሚያስችል የአጭርና የረዥም ጊዜ ዕቅድ ነድፎ በመሥራት ላይ ይገኛል። የዚህን ህዝብ ችግር በጊዚያዊነት ለመፍታት መንግሥት የተጠቀመው ነገር ቢኖር ከአኗኗሩ ጋር የሚጣጣም ማህበራዊ አገልግሎት ማቅረብን ነው።

 

በዚህ መልክ በአርብቶ አደሩ አካባቢ የሚገኙ ትምህርት ቤቶችና የጤና ተቋማት ተንቀሳቃሽ እንዲሆኑ ተደርጓል። አርብቶ አደሩ አንድን ሠፈር ለቆ ወደ ሌላ ሰፈር በሚጓዝበት ወቅት የአገልግሎት ሰጭ ተቋማትም የሰው ኃይላቸውንና ቁሳቁሳቸውን ይዘው ከአርብቶ አደሩ ጋር እንዲጓጓዙና  በሚያርፉበት አካባቢም ሆነው አገልግሎቱን ያለማቋረጥ እንዲሰጡ የማድረግ አቅጣጫ ተይዞ እየተሰራበት ነው።

 

በዚህ መልክ የተወሰነ ርቀት መሄድ ተችሏል። ይህ የመፍትሄ አካል ግን የአርብቶ አደሩን ችግር በዘላቂነት መፍታት የሚችልና የልማት ተጠቃሚነቱን ሙሉ በሙሉ ሊያረጋግጥ የሚችል አይደለም። መፍትሄው በጊዚያዊነት አርብቶ አደሩን ለማገዝ የተወሰደ ነውና።  ከዚህ አንድ እርምጃ ወደፊት በመሄድ ሌላ መፍትሄ ማፈላለግ የግድ ይላል። በመሆኑም መንግሥት ይህንን ጊዘያዊ መፍትሄ እየተጠቀመ ጎን ለጎን ደግሞ ዘላቂ መፍትሄ ይሆናል ያለውን በመሥራት ላይ ይገኛል።

 

የአርብቶ አደሩና አርሶ አደሩ ችግሮች ተመሳሳይነት ያላቸው ናቸው። የሁለቱም መሠረታዊ ችግር ድህነት ነው። ይኸውም የዕለት ጉርስና የዓመት ልብስ በተሟላ መልኩ አለማግኘት ነው። የአርሶ አደሩና የአርብቶ አደሩ አኗኗር የተለያየ በመሆኑ ችግሩን ለመፍታት የተለያየ ዘዴ መጠቀም የግድ ነው።

 

የአርሶ አደሩን፣ የአርብቶ አደሩንና ሌሎች የአገራችን የኅብረተሰብ ክፍሎች ዋነኛ ጠላት ድህነት መሆኑ ይታወቃል። ታላቁ መሪ መለስ ዜናዊ በህይወት ዘመናቸው እያሉ “ኢትዮጵያዊያን ጠላታቸውን መውጋት ከቻሉ ከድህነት የከፋ ጠላት የላቸውም።” ነበር ያሉት። እርግጥ ነው።   

የአርብቶ አደሩ አካባቢ የዝናብ እጥረት የሚያጋጥመው፣ ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ የሚያስተናግድ እና ተደጋጋሚ ድርቅ የሚያጠቃው በመሆኑ ህዝቡ የበለጠ ተጎጂ ሆኖ ለዘመናት ዘልቋል።

 

ይሁንና አርብቶ አደሩን ከአርሶ አደሩ የሚለየው ነገር አለ። አርሶ አደሩ ቢያንስ በአንድ አካባቢ የሠፈረ የራሴ የሚለው መንደርና የመኖሪያ ቤት ያለው ነው። አርብቶ አደሩ ግን ኑሮው ያልተረጋጋና ከአንድ ሥፍራ ወደ ሌላ ቦታ በመዘዋወር ላይ መመሥረቱ ነው። ከድህነት ለመላቀቅ በሚደረገው ትግል በአርሶ አደሩ አካባቢ የሚተገበረው በአርብቶ አደሩ ከሚተገበረው በተለየ መልክ ሊቀርብ የግድ ይላል።

በአንድ አካባቢ ሰፍሮ የሚገኘውን አርሶ አደሩ በቀላሉ የመሠረተ ልማትና የአገልግሎት ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል። ዘመናዊ የእርሻና ልማትና የእንስሳት እርባታ ዘዴዎችን በማስፋፋት ምርቱን በቀላሉ ማሳደግ እንዲችል ማድረግ ተችሏል።

 

በአብዛኛው የአገራችን ክፍሎች የሚገኘው አርሶ አደር በአሁኑ ወቅት ራሱን በምግብ የሚችልበት ሁኔታ ተፈጥሮለታል። ከዚህም አልፎ በሚሊዮን የሚቆጠሩ አርሶ አደሮች በሞዴልነት ብቅ ብለዋል። ከአርሶ አደርነት ወደ ኢንቬስተርነት መሸጋገር የቻሉም በርካቶች ናቸው።

 

በአርብቶ አደሩ አካባቢ በተመሳሳይ መልክ ለመሥራት ግን በአንድ አካባቢ ባለመሰባሰቡና የተወሰነ ሥፍራ ላይ ስለማይኖር ለየት ያለ መፍትሄ ያስፈልገዋል። አርብቶና ከፊል አርብቶ አደሩን በአንድ ጊዜ ወደ አርሶ አደርነት ለመቀየር ስለሚያስቸግር ደረጃ በደረጃ የአርብቶ አደሩን ህይወትና አኗኗር ለማሻሻል የሚያስችል ዘላቂ መፍትሄ ጎን ለጎን እየተገበሩ በጊዚያዊነት ደግሞ ከአኗኗሩ ጋር የተጣጣመ ተንቀሳቃሽ አገልግሎት መስጠት አስፈላጊነቱ ታምኖበታል።

የአርብቶ አደሩ ህይወት የሚቀየረው አኗኗሩን መቀየር ሲቻል ብቻ ነው። ተበታትኖ የሚኖረውን ህዝብ በአንድ መንደር በማስፈር፣ አስፈላጊውን መሠረተ ልማትና ማህበራዊ አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን በማስፋፋት ነው።

 

ይህ አንደኛው በዘላቂነት የአርብቶ አደሩን ህይወት ለመቀየር ልንጠቀም የሚገባን አንዱ መንገድ ነው። ይህ በመንደር የማስፈሩ ጉዳይ የሚመለከተው አርብቶ አደሩን ብቻ ሳይሆን አርሶ አደሩንም ጭምር ነው። በርካታ አርሶ አደሮችም ተበታትነው የሚኖርባቸው አካባቢዎች ስላሉ የሠፈራና በመንደር የማስፈር ተግባራት ሁሉንም የሚያካትት ይሆናል።

 

በአንዳንድ አካባቢዎች ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ የማስፈር ተግባር የሚከናወን ሲሆን በሌሎች አካባቢዎች ደግሞ የተበታተነውን የማሰባሰብ ሥራ ይተገበራል። ቋሚ መኖሪያ መንደር የሌላቸው አርብቶ አደሮች ቋሚ ሠፈር እንዲኖራቸው የማድረግ እንቅስቃሴም እየተደረገ ነው። ይህ የአርብቶና ከፊል አርብቶ አደሩን ህይወት ለመቀየር የሚያስችልና ከአገሪቱ ሁለንተናዊ ለውጥ ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያግዝ እንደሆነ አያጠራጥርም።

በመንደር ማሰባሰብ የመሠረተ ልማትና ሌሎች የልማት አውታሮችን ለማስፋፋት ጠቀሜታው የጎላ ነው። የልማቱ መስፋፋት ደግሞ ለአርብቶ አደሩም ሆነ ለሌላው የአገራችን ህዝብ ኑሮ መለወጥ መሠረታዊ ጉዳይ ነውና ይበልጥ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባዋል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy