Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የኢትዮጵያ ሚና፤ ከአ.አ.ድ እስከ አፍሪካ ህብረት

0 3,033

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የኢትዮጵያ ሚና፤ ከአ.አ.ድ እስከ አፍሪካ ህብረት

ብ. ነጋሽ

የአፍሪካ ህብረት 29ኛ መደበኛ የመሪዎች ስብሰባ በቅርቡ በአዲስ አበባ ተካሂዷል። 29ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ስብሰባ አጀንዳዎች፤ የህብረቱን መዋቅር ማሻሻልን፣ የአፍሪካ ሰላምና መረጋጋትን፣ እንዲሁም የአፍሪካ ወጣቶች ተጠቃሚነትን የሚመለከቱ ጉዳዮች ነበሩ። የ24 የአፍሪካ ሃገራት ፕሬዝዳንቶች፣ እንዲሁም በርካታ ጠቅላይ ሚኒስትሮችና ምክትል ፕሬዝዳንቶች የተሳተፉበት ስብሰባ፣ በአጀንዳዎቹ ላይ ውይይት አካሂዶ ውሳኔዎችን አሳልፏል። በአጀንዳዎቹ ላይ የተደረጉት ውይይቶችና የተላለፉ ውሳኔዎች  በስብሰባው ወቅትና ማግስት በመገናኛ ብዙሃን ሰፊ ሽፋን ተሰጥቷቸው ስለነበረ ደግሜ ማሰልቸት አልፈልግም።

ይሁን እንጂ ኢትዮጵያን በተመለከተ በጉባኤው ተሳታፊዎች የተሰጡ አንዳንድ አስተያየቶችን ማንሳት እፈልጋለሁ። በዋናነት ህብረቱ በጉባኤው መዝጊያ ላይ ለአፍሪካ አንድነት ድርጅትና ለአፍሪካ ህብረት ምስረታና ውጤታማ አፈጻጸም አስተዋጽኦ ላበረከቱ ሁለት የኢትዮጵያ መሪዎች – ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃ/ሥላሴና ታለቁ መሪ መለስ ዜናዊ እውቅና ሰጥቶ በህብረቱ ቅጥር መታሰቢያ ሃውልት እንዲቆምላቸው ያሳለፈውን ውሳኔ መነሻ በማደረግ ስለኢትዮጵያና ህብረቱ አንዳንድ ጉዳዮችን ለማንሳት ወድጃለሁ።

የአፍሪካ ህብረት የ50 ዓመት የአንድነት፣ የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ የተገለጸበት አጀንዳ 2063 ዋነኛ ግብ አፍሪካን በመሰረተ ልማት በማሰተሳሰር የኢኮኖሚና የፖለቲካ ውህደት መመስረት ነው። ኢትዮጵያ በዚህ ረገድ ከአሁኑ የሚታይ ተግባር ማከናወን ጀምራለች። በተለይ የምስራቅ አፍሪካን ቀጠና በቀጣይነትም እስከሰሜን አፍሪካ ያሉትን ሃገራት በሃይል ለማስተሳሳር የያዘችው እቅድ፣ እስካሁን ያከናወነችውና በማከናወን ላይ የምትገኘው ተግባራት ለዚህ አስረጂነት ሊጠቀሱ ይችላሉ።

የአፍሪካ ህብረት ሰሞኑን ባካሄደው 29ኛ መደበኛ የመሪዎች ስብሰባው ኢትዮጵያ በታዳሽ ሀይል ልማት አማካኝነት ለአህጉሪቱ ምጣኔ ሀብት ውህደት እየሰራች መሆኗን አስታውቋል። በህብረቱ የመሰረተ ልማትና ኢነርጂ ዘርፍ የኢነርጂ ዲቪዥን ኃላፊ  ራሽድ አሊ አብዱላሂ፣ ኢትዮጵያ  እንደ ሱዳንና ጂቡቲ  ለመሳሰሉ  ጎረቤት ሃገራት የኤሌክትሪክ ሃይል በማቅረብ ለአህጉሪቱ ምጣኔ ሀብታዊ ውህደት በማበርከት ላይ የምትገኘው አስተዋጽኦ በአብነት የሚጠቀስ መሆኑን ለጋዜጠኞች በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቀዋል። ኢትዮጵያ በታደሽ ሃይል ልማት ከምታከናውናቸው ተግባራት ባሻገር፣ በማሰመዝገብ ላይ የምትገኘው የኢኮኖሚ እድገት ሌሎች የአፍሪካ ሃገራትም የሚያነቃቃ  መሆኑን ሃላፊው ገልጸዋል።

በጉባኤው ላይ የተሳተፉ የሃገራት ከፍተኛ የመንግስት ሃላፊዎችና አህጉራዊ ተቋማት ሃላፊዎችም ለመገናኛ ብዙሃን በሰጡት አስተያያት፣ የአፍሪካ ህብረት ላቀደው የኢኮኖሚ ውህደት ኢትዮጵያ አርአያ የሚሆን ተግባር እያከናወነች መሆኑን ገልጸዋል። ለአብነት ያህል፣ የኬንያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አሚና መሃመድ ለመገናኛ ብዙሃን በሰጡት አስተያየት፣ ኢትዮጵያ የዘመነች አፍሪካን መፍጠር የሚቻለው ሃገራት በራቸውን ለእርስ በርስ ንግድ ልውውጥ ዝግጁ ሲያደርጉና ከተጽዕኖ የሚያላቅቁ ስራዎችን መስራት ሲችሉ ነው የሚል ሃሳብ ስታራምድ መቆየቷን አስታውሰዋል። ኢትዮጵያ የተባበረችና አንድ አፍሪካን መፍጠር የሚቻለው በተለይ አመቺ መሰረተ ልማቶች ሲዘረጉ ነው የሚል አቋም እንዳላትም አስታውሰው፣ በዚህ ረገድ  የኤሌትሪክ ኃይል ልማትና የትራንስፖርት መሰረተ ልማቶችን  እያስፋፋች እንደምትገኝ ገልጸዋል። ኢትዮጵያ ከኬንያ ጋር በመንገድና በአየር ትራንስፖርት አገልግሎት ጠንካራ ትስስር ለመፍጠር መስራቷንም ጠቅሰዋል።

የምስራቅና ደቡብ አፍሪካ አገሮች የጋራ ገበያ (ኮሜሳ) ቢዝነስ ምክር ቤት ሊቀመንበር ዶክተር አማኒ አስፎር በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ህብረት ለያዘው የኢኮኖሚ ውህደት ከጎረቤት አገሮች ጋር ማስተሳሰር የሚያስችላትን የንግድ መሰረተ ልማቶችን በማስፋፋት ላይ መሆኗ በአርአያነት የሚጠቀስ መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ አህጉራዊ ኢኮኖሚያዊ ትስስር ለመፍጠር ከምታደርገው ጥረት በተጨማሪ በአፍሪካ ህብረትና በኢጋድ አማካኝነት ለአህጉሩና ለምስራቅ አፍሪካ ቀጠና ሰላምና መረጋጋት ጉልህ አስተዋጽኦ አያበረከተኝ መሆኑ ይታወቃል። የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በተባበሩት መንግስታትና በአፍሪካ ህብረት ሰላም አስከባሪ ሃይል አማካኝነት ባለፉ ሁለት አስርት ዓመታት በሩዋንዳ፣ ቡሩንዲ፣ ላይቤርያ፣ ሱዳን ዳርፉር፣ ሶማሊያ፣ ደቡብ ሱዳንና ሱዳን አዋሳኝ በሆነችው አቢዬ ግዛት የሰላም ማሰከበር ተልዕኮዋን በአግባቡ የተወጣች ሃገር ነች። በተለይ በሶማሊያ በ1998 ዓ/ም በወቅቱ ከነበረው የሶማሊያ የሽግግር መንግስት በኋላም ከሶማሊያ መንግስት በቀረበ ጥሪ መሰረት የመከላከያ ሰራዊቷን አሰልፋ ለሶማሊያ መንግስት መመስረትና አሁን በሶማሊያ ለሰፈነው አንጻራዊ ሰላም ጉልህ አስዋጽኦ አበርክታለች።

ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ያበረከተችው አስተዋጽኦ ግን ከላይ ከተገለጸውም በላይ የጎላና ታሪካዊ ነው። ኢትዮጵያ በራስዋ ልጆች ነጻነቷን ጠብቃ የኖረች ብቸኛዋ የአፍሪካ ሃገር ነች። ኢትዮጵያ ያለምንም የውጭ ሃይል ጥበቃ፣ በራስዋ ልጆች ነጻነቷን አስከብራ መኖሯ፣ ነጻነቷን ለማስከበር ልጆች የከፈሉት መስዋጽትነት፣ በምእራብ አውሮፓ ሃገራት ቅኝ ግዛት ስር ወድቀው የነበሩ የአፍሪካ ሃገራት ህዝቦች በራሳቸው አቅም ነጻነታቸውን ለማስመለስ እንዲነሳሱ አድርጓል። ብዙ የተነገረለት ጥቁር ህዝቦች የነጭ ወራሪ ሃይልን ያንበረከኩበት የአድዋ ድል ለዚህ ማሳያነት ይጠቀሳል። የአድዋ ድል በቅኝ ግዛት ስር ወድቀው የነበሩ የአፍሪካ፣ የኢሲያና የደቡብ አሜሪካ ህዝቦች የነጻነት ትግል እንዲያቀጣጥሉ አነሰስቷል።

ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ያበረከተችው አስተዋጽኦ በነጻነት ተምሳሌትነት ተነሳሽነትን በመፍጠር የተገደበ አይደለም። በቅኝ ግዛት ስር የነበሩ የአፍሪካ ሃገራት ነጻነታቸውን እንዲቀዳጁ የማድረግ ዓላማ የነበረውን የአፍሪካ አንድነት ድርጅት (አ.አ.ድ) እንዲመሰረት የመሪነት ሚና ተጫውታለች። ኢትዮጵያ የተባበረች አፍሪካን ለመመሰረት እንቅስቃሴ ማድረግ የጀመረችው ከ1950ዎቹ መጀመሪያ አንስቶ ነበር። በወቅቱ የነበሩትን 30  ገደማ የሚሆኑ ነጻ ሃገራትን በማነሳሳትና የመሪነት ሚና በመጫወት በ1955 ዓ/ም ግንቦት ወር ላይ በአዲስ አበባ አ.አ.ድ ተመስርቷል። አ.አ.ድን የመሰረቱት 32 ነጻ የአፍሪካ ሃገራት ነበሩ።

ይህ ከሃያ በላይ በአውሮፓውያን ቅኝ ግዛት ስር የነበሩ የአፍሪካ ሃገራትን ነጻ ማውጣትና የጥቂት ነጮች የበላይነት ስርአት ያለባቸውን ሃገራትም ከዚህ የዘር መድልዎ ስርአት ማላቀቅ ዋነኛ ዓላማው ነበር። የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ይህን ዓላማውን አሳከቷል። በመጨረሻ የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን የተቀላቀለችው ሃገር ደቡብ አፍሪካ ነች። ደቡብ አፍሪካ  የጥቂት ነጮች የዘረኝነት ስርአትን አስወግዳ አ.አ.ድን የተቀላቀለችው በ1986 ዓ/ም ነበር።

ታዲያ ይህን የአፍሪካ ሃገራትን ነጻነት ማረጋገጥ ቀዳሚ ዓላማው አድርጎ የተመሰረተና ዓላማውን ያሳካው አ.አ.ድ እንዲመሰረትና ተልዕኮውን እንዲወጣ በማደረግ ረገድ የኢትዮጵያ መሪ የነበሩት ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃ/ሥላሴ ትልቅ ድርሻ ነበራቸው። ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃ/ሥላሴ በአ.አ.ድ መስረታ የመሪነት ሚና እንዲጫወቱ እንዲሁም ድርጅቱ ዓላማውን በመወጣት ሂደት የጎላ ድርሻ እንዲኖራቸው ያደረጋቸው በቅድሚያ የነጻ ሃገር መሪ በመሆናቸው ነው መታወስ አለበት። የኢትዮጵያ ህዝብ ነጻነት ደግሞ በህዝቧ መስዋዕትነት ነው የተረጋገጠው።

በ1990ዎቹ ከግማሽ ክፍለ ዘመን ቆይታ በኋላ አ.አ.ድ ተልዕኮውን አድሶ በአዲስ መልክ መዋቀር ነበረበት።  የአ.አ.ድ ምዕራፍ ተዘግቶ፣ በ1993 ዓ/ም ግንቦት ላይ በአዲሰ አበባ የአፍሪካ ህብረት ተመሰረተ። የህብረቱ ምስረታ ይፋ የተደረገው በ1994 ዓ/ም ደቡብ አፍሪካ ላይ ነበር።

ታዲያ፤ የአፍሪካ ህብረት በአዲስ የአፍሪካ መጻኢ ራዕይ እንዲፈጠርና ወደስራ እንዲገባ በማድረግ ረገድ ኢትዮጵያ ከአራት አስርት ዓመታት በፊት እንዳደረገችው ሁሉ የጎላ ድርሻ ነበራት። በወቅቱ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት ታላቁ መሪ መለስ ዜናዊ በዚህ ረገድ ትልቅ ድርሻ ነበራቸው። እኛ ኢትዮጵያውያን ደግሞ ታላቁ መሪ መለስ ዜናዊ፣ ኢትዮጵያውያንና ቀደምት የሃገሪቱ መሪዎች ለአፍሪካ ነጻነት ያበረከቱትን ታላቅ አስተዋጽኦ አስታውሰው አዲስ የተመሰረተው የአፍሪካ ህብረት ጽህፈት ቤት አዲስ አበባ እንዲሆን ማድረጋቸውን ስናስታውሰው የምንኖር ተግባር ነው። የአፍሪካ ህብረት ጽህፈት ቤት፣ ኢትዮጵያ አዲስ አበባ ላይ እንዲሆን መደረጉ ኢትዮጵያውያንና ቀደምት መሪዎቿ ለአፍሪካ ሃገራት ነጻነት ላበረከቱት አስተዋጽኦ የሚመጥን ተገቢ ዋጋ ነው።

የታላቁ መሪ መለስ ዜናዊ አስተዋጽኦ የአፍሪካ ህብረት በአዲስ ራዕይ እንዲመሰረት የጎላ ሚና በመጫወት የተገደበ አልነበረም። አፍሪካውያን በዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ ተሰሚ እንዲሆኑና በውሳኔ ላይ ተጽዕኖ ማሳደር እንዲያስችሉ አድርገዋል። መለስ ዜናዊ አፍሪካውያን የሚጋሩት ታሪክ፣ የልማት ፍላጎትና ራዕይ ያላቸው መሆኑን መነሻ በማድረግ ለጋራ ጥቅማቸውና ግባቸው በህብረት ድምጻቸውን እንዲያሰሙ አድርገዋል። በአየር ንብረት ለውጥ ተጽእኖ ላይ አፍሪካውያን አንድ አቋም እንዲይዙ በማድረግ በዓለም አቀፍ መድረክ ላይ የአፍሪካ ተወካይ ሆነው ቆመው ያስገኙት ውጤት ለዚህ አስረጂነት ሊጠቀስ ይችላል። ይህ አፍሪካውያን በህብረት መቆማቸው በዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ ተጽእኖ ማሳደር የሚችሉ መሆኑን አስተምሮ ያለፈ ታሪካዊ ተግባር ነው።

እናም የአፍሪካ ህብረት ሰሞኑን ባካሄደው 29ኛ የመሪዎች ስብሰባው፣  ኢትዮጵያ ከአ.አ.ድ ጀምሮ እስከ አፍሪካ ህብረትም ላበረከተችው አስተዋፅኦ እውቅና ሰጥቷል። ይህን እውቅና መነሻ በማድረግ የኢትዮጵያ አስተዋጽኦ መሪ ለነበሩት ነጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃ/ሥላሴና ለታላቁ መሪ መለስ ዜናዊ በህብረቱ ጽህፈት ቤት ቅጥር ጊቢ መታሰቢያ ሃውልት እንዲቆምላቸው ወስኗል። ይህ ለኢትዮጵያውያን ሁሉ የተሰጠ እውቅናና ሽልማት ተደርጎ የሚወሰድ ነው። ኢትዮጵያውያን በመሪዎቻቸው አማካኝነት ከአ.አ.ድ ጀምሮ እስካሁን ለአፍሪካ ላበረከቱት አስተዋጽኦ የተሰጠ እውቅና ነው።           

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy