Artcles

የኢትዮጵያ ፅኑ አቋም

By Admin

July 21, 2017

የኢትዮጵያ ፅኑ አቋም

                                                      ታዬ ከበደ

ኢትዮጵያ በሰላም ፈላጊነት አቋሟ የምትታወቅ ሀገር ናት። በባህረ ሰላጤው ሀገራትና በኳታር መካከል በተፈጠረው ፖለቲካዊ ውዝግብ የኤርትራ መንግስት በወሰደው አቋም ከጂቡቲ ጋር እየተወዛገበ ቢሆንም አገራችም ሁለቱ አገራት ችግራቸውን በውይይት እንዲፈቱ ሃሳብ አቅርባለች። ይህም ኢትዮጵያ ሁሌም ለሰላምና ለድርድር ያላትን ፅኑ አቋም የሚያረጋግጥ ነው።

እንደሚታወቀው የኢትዮጵያ መንግስት በማናቸውም ዲፕሎማሲያዊ ጉዳዩች የሚከተለው የገለልተኝነት መርህን ነው። ይህ መርህ መቼም የሚቀየር አይደለም። ለሁሉም ሀገራት የሚሰራ ነው። መንግስት ከጎረቤቶቹም ይሁን የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ካለውም ይሁን ከሌለው ሀገራት ጋር የሚያደርገው ግንኙነት መርህን የተከተለ ነው። በህዝቦች መካከል ሰላም እንዲሰፍን በመደጋገፍና በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የሚያጠነጥን ነው። ይህ መርህ ላለፉት 26 ዓመታት ሲሰራበት የመጣ ነው።

ምንም እንኳን ከኤርትራ መንግስት ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ባይኖረንም ዋናው ጉዳይ የኤርትራ ህዝብ ነው። የኤርትራ ህዝብ  በምንም መንገድ ሰላሙ መታወክ የለበትም። እናም ያ ወንድም ህዝብ ሰላሙ እንዲጠበቅ መስራት ከአንድ ለሰላም ከቆመ መንግስት ተሚጠበቅ ነው። ከጂቡቲም ጋር እንዲሁ ጉዳዩ ከህዝብ ጋር የተያያዘ ነው።

ታዲያ መንግስት ይህን የሚያደርገው የጎረቤቶቹን ሉዓላዊነት ከማክበርና የጋራ ተጠቃሚነትን መሰረት በማድረግ መሆኑ ከማንም የሚሰወር ዕውነታ አይመስለኝም። የጂቡቲም ሆነ የኤርትራ ሰላምና መረጋጋት ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና ልማት ሚናው የጎላ ሀገራችን በፅኑ ታምናለች።

እርግጥ ጂቡቲ ሰላም ለሀገራችን ሰላምና ልማት የሚኖረው አስተዋጽኦ በቀላሉ ሊታይ የሚችል አይደለም። ምክንያቱም ቢያንስ በጎረቤት ሀገራት አካባቢ ያለው የሰላም እጦት ቢያንስ የድንበሮቻችን አካባቢዎችን የስጋት ቀጣና ሊያደርጋቸው ስለሚችል ነው።

ይህ ደግሞ ፍልሰት እንዲኖርና ስደተኞች እንዲበራከቱ ማድረጉ አይቀሬ ነው። እናም ጂቡቲም ሆነ ኤርትራ ሰላም ሆኑ ማለት ሀገራቱ ከስጋት ነፃ የሚሆኑበት ዕድል እንዲፈጠር ያደርጋል። ይህ ሁኔታም የልማት ስራዎችን ያለ አንዳች እክል እንድንፈፅም ዕድል ይሰጠናል። ከዚህ ጎን ለጎንም የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱም ፍጹም ሰላማዊ ሆኖ እንዲቀጥል ያግዛል።

በተለይም ከሀገሪቱ ጋር በሰላም ጉዳይ በጋራ ለመስራት የሚያስችለን አስተማማኝ ደረጃ ላይ እንድንደርስ ትልቅ ድጋፍ ማድረጉ አይቀሬ ነው። ኢትዮጵያ ከዚህ አኳያ የምትከተለው ጎረቤት ሀገርን የሚያከብርና በሉዓላዊነታቸው ጣልቃ ባለመግባት የጋራ ጥቅምን መርህ የተከተለ የገለልተኝነት ፅኑ አቋም አካሄድ የሚመነጨውም ከዚህ ዕውነታ ይመስለኛል።

በአንፃሩ ደግሞ የኤርትራ መንግስት የሰላም ፀር ነው። ጦርነት እንጂ ሰላም ባለበት ቦታ አይገኝም። በዚህም ሳቢያ የኤርትራ መንግስት ለአሸባሪዎች የሚያደርገውን ድጋፍ ተከትሎ ዓለም አቀፉ ማህረሰብ በማውገዝ ማዕቀብ ጥሎበታል። ካንዴም ሁለቴ። ሻዕቢያ ከአስመራ አንስቶ እስከ ሶማሊያ ድረስ የሽብር መረብ ዘርግቶ እንደነበር ከማንም የሚሰወር አይመስለኝም።

ይህ  የትርምስ መረብ በጀግናው መከላከያ ሠራዊታችንና በሀገራችን ህዝቦች ንቁ ተጋድሎና ተሳትፎ ሲበጣጠስበት፣ ፊቱን ወደ ሶማሊያ ግንባር በማዞር በዓለም መንግሥታት ዕውቅና የተሰጠውን የሀገሪቱን ፌዴራላዊ የሽግግር መንግስት ለመጣል በይፋ አውጆ መንቀሳቀሱ የትናንት ትውስታችነ ነው።

ሰላማዊ ኑሮና የልማት እንቅስቃሴ ምንጊዜም የሚያስደነግጠው የኤርትራ መንግስት መንግሥት፤ “ጭር ሲል አልወድም” የሚለው ፖሊሲውን ገቢራዊ ለማድረግ ከፅንፈኛው እስላማዊ ፍርድ ቤቶች ህብረትና አል ሸባብ እያለ ራሱን በሚጠራው የአሸባሪዎች ስብስብ መጠለያ በመስጠትና በመደገፍ በሶማሊያ ልሳነ ምድር ያላስተኮሰው ጥይትና ሮኬት፣ ያላስወረወረው ቦምብና ያላስቀበረው የፈንጂ ዓይነት ያለ አይመስለኝም። የመንን፣ ኢትዮጵያንና ጂቡቲን መውረሩ ተረጋግጦበታል።

ምንም እንኳን የኤርትራ መንግስት ወረራን እንደ አንድ የስራ መስክ ቢቆጥረውም፤ የኢትዮጵያ መንግስት ግን መንግስታት በየትኛውም አገር ውስጥ እንደሚቀያየሩ ያውቃል። ቀሪው ህዝብ በመሆኑ የዚያች ሀገር ህዝብ የሰላም እጦት ሰለባ እንዲሆን አይሻም። ይህ ተግባሩም ለሰላም ካለው ቁርጠኛ አቋም የሚመነዘር ነው።

ይህ ሰላም ወዳድነቷም ኢትዮጵያ ከምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ጋር የተያያዘ ነው። እርግጥ የምስራቅ አፍሪካን ቀውስ ለማርገብ የቀጣናው ሀገራት በሚያደርጉት ርብርብ እንደ ኤርትራ አይነቱ ፀብ ጫሪ ሀገር ጉዳዩን ይበልጥ በማወሳሰብ፣ የሃይልና የሎጀስቲክስ ድጋፍ በማድረግ ቀውሱን ለማብረድ የሚደረገውን ርብርብ አድካሚ እንዲሆን ማድረጉ አይካድም።

ያም ሆኖ ሀገራት በጎረቤት ሀገራትም ሆነ በተለያዩ ሀገራት ለሚፈጠሩ ችግሮች ኢትዮጵያ በግንባር ቀደምትነት በመሰለፍ አኩሪ ተግባራትን እየከወነች ትገኛለች። ይህም በአንድ ወገን እንደ ኤርትራ ዓይነት መንግስታት ቀጠናውን ለማወክ የሚያደርጉትን እኩይ ተግባር የሚያጋልጥ ይሆናል። በሌላ በኩል ደግሞ የሀገራችንን ሰላም ወዳድነትን ያረጋግጣል።

እንደሚታወቀው የምስራቅ አፍሪካ ቀጠና በአለም አቀፍ ደረጃ ውስብስብና ለረጅም ዘመናት የዘለቀ የፀጥታ ስጋት አካባቢ ነው። ይህን ለማስወገድም አገራቱ እንደ አቅማቸው የጋራ ርብርብ ማድረግ ይኖርባቸዋል።

ይህን እንቅስቃሴ በተደራጀ መልኩ ማከናወን ይገባል። በአሁኑ ወቅት ሀገራቱ ይህን ችግር በመረዳታቸው በልማት፣ በፀጥታ፣ በንግድ ዙሪያ በጋራ እየሰሩ ነው። ኤርትራ ግን ዛሬም ድረስ የጦር አዝማች ሆና ቀጣናውን ከማወክ አልተመለሰችም። ሆኖም ኢትዮጵያ የቀጣናውን ሰላም ለማስጠበቅ በምታደርገው ጥረት ማንነቷን ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ማሳየት ችላለች። ተወዳሽና ተመስጋኝም ሆናለች።

ይህም ለሀገራችን ሰላም ወዳድነት ገፅታ የራሱን አስተዋፅኦ አበርክቷል። ይህ ሰላም ወዳድነታችን ከምንም የመነጨ አይደለም፤ የጎረቤቶቻችን ሰላም የእኛም ጭምር መሆኑን ሀገራችን ስለምትገነዘብ ይመስለኛል። እናም የሀገራችን ዘላቂ የሰላም ፍላጎት እስካለ ድረስ የቀጣናው፣ የአፍሪካ ብሎም የዓለም ሰላም አረጋጋጭነታችን ሚና ሁሌም መጉላቱ የሚቀር አይመስለኝም። በጂቡቲና በኤርትራ ላይ ያራመደችው ፅኑ አቋም መነሻውም ሆነ መድረሻው ይኸው ነው ማለት ይቻላል።

የኢትዮጵያ መንግስት ለሰላም የቆመ እንደመሆኑ መጠን፤ ኤርትራና ጂቡቲ ችግራቸውን በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ ማሳሰቡ ተገቢም ትክክልም ነው። ከኤርትራ ጋር ምንም ዓይነት የዲፕሎማሲ ግንኙነት የሌለው ቢሆንም እንኳን ለአንድ ወገን አልወገነም። ሚዛናዊ በመሆን በሁለቱም ወገኖች መካከል ሰላም እንዲሰፍንና ችግራቸውን በሰለጠነ መንገድ እንዲፈቱ ነው የጠየቀው። ይህ መርሁ ለሌሎች ሀገራት ምሳሌያዊ የሚሆን ይመስለኛል።