Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የኢንዱስትሪዎቻችን ደጀን የሚሆን የግብርና አቅም ለመገንባት

0 289

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የኢንዱስትሪዎቻችን ደጀን የሚሆን የግብርና አቅም ለመገንባት

 

ስሜነህ

ሃገራችን  በዚህ መኸር ወቅት ከዋና ዋና ሰብሎች ብቻ  ከ345  ሚሊዮን ኩንታል በላይ  ምርት ለመሰብሰብ ዕቅድ ስለመያዟ ተነግሯል። በአገር ደረጃ  ማረጋገጥ የተቻለውን  የምግብ ሰብልን ፍላጎት በቤተሰብ ደረጃ ለመድገም መንግስት በርካታ ጥረቶች እያደረገ ነው። የምግብ ሰብልን በቤተሰብ ደረጃ ለማረጋገጥ ደግሞ  የመኽር ስራዎች ወሳኝ ሚና ያላቸው መሆኑ ይታወቃል።  ለዚህም አርሶ አደሩ ለይስሙላ ሳይሆን በእርግጥ የመሬቱና የምርቱ ተጠቃሚ መሆን መቻሉ ምርታማነቱ ላይ የሚታይ ለውጥ ለማምጣት አስችሎታል፡፡ የአየር ሁኔታ መዛባት በየመሃሉ  በተለይ ባለፉት ሁለት ተከታታይ አመታት ያስከተለው ጉዳት እንደተጠበቀ ሆኖ አርሶ አደሩ በሙሉ ተነሳሽነት የመስራቱን ያህል ምርታማነቱ ላይ ውጤት በማስመዝገብ አረጋግጧል፡፡  

ሰፊ የህዝብ ቁጥር ያላት አገራችን ለልማት ግብአት ሊሆን የሚችል የሰው ሃይል ወይም ጉልበት ያለ መሆኑና ውሱን ካፒታል በላቀ ደረጃ በመጠቀም ፈጣን ልማት ለማረጋገጥ የሚያስችል ፖሊሲ ባለቤት መሆኗ የሚሊኒየሙን የልማት ግቦች ማሳካት እንደሚቻል ካለፉት ዓመታት ልምዶቻችን መገንዘብ የተቻለ መሆኑም በዚህ ሰዓት ለተቀጣጠለው ልማት አቅም ሆኗል።

በገጠር ልማት ስራዎች ህዝቡን በማንቀሳቀስ የተፈጥሮ ጸጋዎቻችንን በማልማት የመሬት ለምነትንና የውሃና የደን ሃብታችን ከፍተኛ መሻሻል ያሳየ ቢሆንም ባለን አቅም ልክ ግን አሁንም ያልተሰራ ለመሆኑ በተደጋጋሚ እየጎበኘን ከሚገኘው ድርቅ በላይ አስረጅ መጥቀስ አያስፈልግም። ሃገራችን የረጅም ጊዜ ታሪክና ገናና ሥልጣኔ ባለቤት የነበረች መሆኗ የሚታወቅ ሲሆን የግብርና ስራም ለብዙ ሺህ ዓመታት ሲካሄድ የኖረባት ሀገር ነች፡፡ እጅግ ሠፊ የስነ-ምህዳር ተለያይነት ያላት ሀገር በመሆኗም በኢትዮጵያውያን የተላመዱና የኢትዮጵያ ብቻ የሆኑትን ጤፍ፣ ገብስ፣ እንሰት፣ ጫት እና ሌሎችም ሀገር በቀል ሰብሎች መኖራቸው ሲታይ መልማት የሚችል እምቅ ሀብት እንዳለን ያሳያል፡፡ ይሁን እንጂ የግብርና ሥራው ኋላ-ቀር በመሆኑ የአርሶ አደሩ ተጠቃሚነት በነዚህ እምቅ ሃብቶቻችን እና ጸጋዎቻችን ልክ አለመሆኑ ሊጤንና ይህንኑ ቀርነት ታሳቢ ያደረገ ትጋት የሚያስፈልግ መሆኑ ሊዘነጋ አይገባም።

ቀደም ብሎ ስለዚህ ቀርነት  ከሚጠቀሱት ምክንያቶች መካከል አንዱና ዋናው ጉዳይ የህዝቡ የመሬት ባለቤትነት መብት በተሟላ መልኩ አለመረጋገጥና ይህንንም ለመለወጥ የሚያስችል የፖለቲካና ኢኮኖሚ ፖሊሲ ያልተቀረጸበት ይልቁንም ድህነትና ኋላቀርነትን የሚያባብሱ ፀረ ልማት መንግስታት እየተፈራረቁ ሲገዙት የኖሩ መሆኑ ይታወቃል። ካለፉት 26 ዓመታት ወዲህ ግን መላውን ህዝብ ከድህነት የሚያላቅቅ በሂደትም የበለፀገ ሃገር ለመገንባት የሚያስችልና የግብርና ልማትን የሚያፋጥን ፖሊሲና ስትራቴጂ ወጥቶ በሁሉም አካላት የጋራ ርብርብ ተግባራዊ ማድረግ የተጀመረ ሲሆን መንግስትም ለግብርናና ገጠር ልማት ሥራዎች እና ለገጠሩ ህብረተሰብ ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡

በዚህ ሂደት በተለይ በ1994 ዓ.ም የተነደፈው የግብርናና ገጠር ልማት ፖሊሲና ስትራቴጂ ያለንን የልማት አቅም ማለትም ሰፊ ጉልበት፣ መሬት፣ ውሃ እና ውስን ካፒታል በቁጠባ ለመጠቀም የሚያስችል መሆኑ፤ በሂደትም ግብርናው የኢንዱስትሪ ግብዓት፣ የካፒታል ክምችት፣ የገበያ ዕድልና የጉልበት አቅርቦትን በማረጋገጥ ለከተማውና ለኢንዱስትሪ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከት የሚችል መሆኑ ለበርካታ ውጤቶች ያበቃን ቢሆንም በፖሊሲው አቅጣጫ፣ በመንግስት ጥረትና ፍላጎት ልክ ውጤት ሊመዘገብ አልቻለም፡፡

በመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ከተቀመጡ ግቦች አንጻር አፈጻጸሙ ሲታይ በመሠረታዊ የዕድገት አማራጭ በመነሻው ዓመት የነበረውን 191ሚሊዮን ኩንታል ምርት በዕቅድ ዘመኑ መጨረሻ 267 ሚሊዮን ኩንታል ለማድረስ ታቅዶ 27ዐ ሚሊዮን ኩንታል በማምረት የዕቅዱን 101 በመቶ ማሳካት መቻሉ አንዱ የፖሊሲው እና የመንግስት ጥረት ማሳያ ነው፡፡ ከዚህ ውስጥ ከ95 በመቶ በላይ የሚሆነው የተመረተው በአነስተኛ አርሶአደሩ ማሳ ላይ መሆኑ ሲታይ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችንና አዳዲስ አሰራሮችን በአነስተኛ ማሳ ላይ በመተግበር የግብርና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የተከተልነው አቅጣጫ ትክክለኛነት በተግባር የተረጋገጠበት ነው፡፡ የዋና ዋና ሰብሎች ምርታማነት ከ13 ኩንታል በሄክታር በዕቅድ ዘመኑ መጨረሻ ወደ 22 ኩንታል ማድረስ ተችሎ የነበረ መሆኑም የሚታወስና በእርሻና የተፈጥሮ ሃብት ሚንስቴር የመረጃ ቋት ላይ ተመዝግቦ የሚገኝ ሃቅ ነው።

ሆኖም በአነስተኛ አርሶ አደር ማሳ ቢያንስ በሄክታር ከ50-60 ኩንታል ለማምረት ካለው ዕድል አኳያ ሲታይ ግን አሁንም በሚፈለገው የምርታማነት ደረጃ ላይ ያልደረስን መሆኑ ነው ይህን የመኸር ወቅት ታሳቢ በማድረግ አጀንዳውን ማንሳታችን።  

በተፈጥሮ ሀብት ልማት ረገድም  በመጀመሪያው ዙር ዕቅድ ዘመን የነበረው አፈጻጸም አመርቂ የሚባል ቢሆንም ልክ እንደሰብል ምርቱ በተመሳሳይ ባለን እምቅ አቅም ልክ ያልነበረ መሆኑንም ታሳቢ ያደረገ ስራ አሁንም የሚጠይቀን ይሆናል። እንደእርሻና የተፈጥሮ ሃብት ልማት ሚንስቴር በእቅድ ዘመኑ መነሻ የነበረውን 3.7 ሚሊዮን ሄክታር በተለያዩ የተፋሰስ ልማት ሥራዎች የተሸፈነ ማሳ ከ8 ሚሊዮን ሄክታር በላይ ማድረስ ተችሏል።  ከዚህ ስኬት በስተጀርባ ያለው ምስጢር ደግሞ የህብረተሰቡ ሰፊና የተደራጀ  ተሳትፎ ነው፡፡ የተፋሰስ ልማት ሥራው በእንስሳት ማድለብ፣ በግና ፍየል በማሞከት፣ ንብ በማነብና በመሳሰሉት ዘርፎች በሚሊዮን ለሚቀጠሩ የገጠር ወጣቶችና ሴቶች የሥራ ዕድል ፈጥሯል፡፡ ይህ ሥራ በስፋቱም ሆነ ህብረተሰቡን በማሳተፍና ተጠቃሚነተቻውን በማረጋገጥ ረገድ በአህጉራችንም ሆነ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ በምርጥ ተሞክሮነት የሚጠቀስ ሆኗል፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ በአነስተኛ መስኖ ልማት በዕቅድ ዘመኑ መጀመሪያ የነበረውን በመስኖ የለማ መሬት ሽፋን ከ853 ሺህ ሄክታር ወደ 2.6 ሚሊዮን ሄክታር በማድረስ ከዕቅድ በላይ መፈጸም ቢቻልም እንደሃገር ሊለማ ከሚችለው ፖቴንሽያል ወይም እምቅ አቅም አኳያ ሲታይ ግን በቀጣይ በመስኖ ልማቱ ሥራ ረጅም ርቀት መጓዝ የሚገባን መሆኑ በእቅድ ዘመኑ መጨረሻ ይፋ የተደረገ ቢሆንም አሁንም ትኩረት የተሰጠው ስለማይመስል ቆም ብሎ ማሰብ የሚያስፈልገን ይሆናል፡፡

ይህን የመኸር ወቅት ጨምሮ በተከታታይም በግብርናው ሴክተር የሚታዩትን ውስንነቶች ከመፍታት አኳያ በግብርናው ሴክተር ያለውን የሰው ኃይል በአመለካከትና በክሂሎት የማብቃት ተከታታይ ሥራዎችን በመስራት የሰው ኃይሉን ምርታማነት የማሳደግ፣ እነዚህን የልማት አቅሞች ከተግባር ጋር በማስተሳሰር የማብቃት፣ አደረጃጀቶቹን የማጠናከርና የልማት አቅሞቹን የማነቃነቅ እና ውጤታማ ተሞክሮዎችን እየቀመሩ የማስፋት ሥራ ላይ ትኩረት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

በመጀመሪያው ዙር ዕቅድ ዘመን በግብርናው ዘርፍ የሴቶችንና ወጣቶችን ተጠቃሚነትና ተሳታፊነት ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ተግባራት በመከናወናቸው የገጠር ሴቶችና ወጣቶች ተሳትፎና ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ ያስቻለውን ምርጥ ተሞክሮ አሁንም ማስፋትና ማጠናከር ያስፈልጋል።

ከዚሁ ጎን ለጎን ተፋሰስን መሠረት ያደረገ የግብርና ልማት ሥራ በመሰራቱ፣ ሰፋፊና አነስተኛ የመስኖ አውታሮች ተገንብተው ለህብረተሰቡ አገልግሎት መስጠት በመጀመራቸው፣ የግብርና ኤክስቴንሽን አገልግሎት፣ የግብዓትና ሌሎች የግብርና ቴክኖሎጂዎች አቅርቦት እየተሻሻለ እና ለእንስሳትና ለሰው የመጠጥ ውሃ አቅርቦት ሽፋንና ተደራሽነት እየጨመረ በመምጣቱ የህብረተሰቡ ገቢና ኑሮ እየተሻሻለ የመጣበት ሁኔታ ከመኖሩ ጋር ተያይዞ የአኗኗር፣ የአመራረትና የአረባብ ዘይቤያቸውንም ጭምር መቀየር ያስፈልጋልና እዚህም ላይ በተለየ በዚህ የመኸር ወቅት የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ሁሉ ሊሰሩ ይገባል፡፡

እንደቀድሞው ጊዜ አደጋ ባጋጠመን ቁጥር ወደኋላ የምንመለስበት ምእራፍ መዘጋቱን እንደ ጥሩ እድል ልንጠቀምበት ይገባል። ይኸውም ከላይ በተመለከተው አግባብ ግብርናችን በቀጣይነት ያለማቋረጥ እያደገ በመምጣቱ ለአደጋ ተጋላጭነታችንና ድርቅን የመቋቋም አቅማችን እንደ ሃገር እየተገነባ የመጣበት ሁኔታ መፈጠሩ የመጀመሪያው ነው፡፡ ከአካባቢ አካባቢ የተለያየ አፈፃፀም ያለና አሁንም ለአየር ንብረት መዛባት ተጋላጭነት ያላቸው አካባቢዎች ያሉን መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ጠንከር ያለ ድርቅ ቢከሰት አንኳን ችግሩን ተቋቁሞ የማለፍ አቅማችን እያደገ መምጣቱም ሌላኛው ምቹ ሁኔታ ነው፡፡ ይህም ሆኖ ታዲያ በዚህ እድል መቆዘም ሳይገባን የተሟላ አቅም መገንባት ገና የሚቀረን መሆኑም ግንዛቤ ተይዞ ፈጣንና ቀጣይነት ያለው የግብርና ዕድገት እየተመዘገበ ባለበት ልክ የድርቅ መቋቋምና የአደጋ መከላከል አቅማችንን ማሳደግ የሚገባን መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል፡፡

ከውቅያኖሶች ሙቀት መጨመር ጋር ተያይዞ የተከሰተው የኤሊኖ አየር መዛባት አሉታዊ ተጽዕኖ ቀላል ግምት የሚሰጠው ባለመሆኑ እንደዚህ አይነት ክስተትም ሆነ ተያያዥ ችግሮችን መቋቋም የምንችለው ለአየር ለውጥ የሚይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ መገንባት ስንችል ብቻ ነው፡፡ ስለሆነም በእንደዚህ አይነት የመኸር ወቅት የተጀመረውን የተፈጥሮ ሀብትና የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ሥራ ከመስኖ ልማቱ ጋር አስተሳስሮ በላቀ ቁርጠኝነት በመፈጸም የግብርናን ምርትና ምርታማነት ዕድገት ማስቀጠል የሚገባ መሆኑን ለአፍታም እንኳ ቢሆን መዘንጋት አይገባም።  

በዚህ  የመኸር ወቅት  ህዝብና መንግስት እንደተለመደው በሰብል ምርት ስራዎች ላይ ብቻ ሳይሆን  ድርቅን በዘላቂነት ለመከላከል የሚያስችሉ ተግባራት ታሳቢ ያደረጉ ስራዎችን ማከናወን ቀዳሚ ስራቸው ሊያደርጉ ይገባል። አርሶና አርብቶ አደሩ የጎርፍ  ውሃን በማቆር  ለቀጣይ የመስኖና የእንሰሳት መጠጥ የመጠቀም ባህላቸውን ማዳበር እንደሚገባቸው ከማሳ ላይ ስራ ባሻገር የግንዛቤ ስራዎችንም መስራት ያስፈልጋል።

ከዚህም ባሻገር በዚህ መኸር ሊሰሩ የሚገባቸው ወቅታዊና የዘመቻ ስራዎች መኖራቸውን መዘንጋት አይገባም። ይኸውም  አርሶና አርብቶ አደሩ የጀመረውን  ተምችን በባህላዊ መንገድ የመከላከል  ዘዴ አጠናክሮ መቀጠል የሚገባው መሆኑ የመጀመሪያው እና መሰረታዊው የዘመቻ እና ወቅታዊ ስራ ነው። ከዚህ ጎን ለጎን የመደሃኒት ርጭትም በማካሄድ ተምችን መከላካልና ምርትና ምርታማነትን የማሳደግ ስራ ደግሞ በየደረጃው የሚገኙ የግብርና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች ወቅታዊ ስራ ሊሆን ይገባል።   

የሜትሪዮሊጂ ትንበያዎች እንደሚያሳዩት የዘንድሮው ክረምት በአብዛኛው የአገራችን አካባቢዎች መደበኛውና ከመደበኛ በላይ ዝናብ እንደሚኖር ነው። በመሆኑም በጎርፍ የሚጠቁ ረባዳ አካባቢዎች የሚኖሩ ዜጎች ተገቢው መረጃ እንዲኖራቸውና ከደራሽ ውሃ ራሳቸውንና ንብረታቸውን እንዲከላከሉ ግንዛቤ መፍጠር የነዚሁ ባለሙያዎች ስራ ሊሆን ይገባል። በጥቅሉ በዚህ መኸርና በዘላቂነትም ምርትና ምርታማነታችንን በመጨመር የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥም አልፈን የኢንዱስትሪዎቻችን ደጀን የሚሆን የግብርና አቅም ለመገንባት የሚመለከታቸው ባለድርሻ  አከላት  በሙሉ ለአርሶ አደሩ እና አርብቶ አደሩ  በወቅቱ  ግብዓት ማቅረብ፣  ተገቢውን ድጋፍና ክትትል  ማድረግ ይኖርባቸዋል።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy